| "ረቂቅ አዋጁ ከፀደቀ ኃላፊነቴን ለመልቀቅ... |
|
|
| Wednesday, 23 January 2008 | |
|
"ረቂቅ አዋጁ ከፀደቀ ኃላፊነቴን ለመልቀቅ የመጀመሪያው ሰው እኔ ነኝ" አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ የህብረት ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን ለማቋቋምና ለመቆጣጠር ባወጣው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያና ከሁለት ሳምንት በፊት በፍርድ ቤት ብሔራዊ ባንክን በመክሰስ ስለረቱበት ጭብጥ አነጋግረናቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ ከመጠን ያለፈ የሚል አስተያየት እየሰጣችሁ ነው፡፡ መጠን ያለፈው ምኑ ነው? አቶ እየሱስወርቅ፡- ነገሩ ከመጠን ሲያልፍ ነው፤ በዛ የሚባለው ማስፈራሪያ ሲሆን ነው፡፡ ባንክ ውስጥ የምንሰራ ሰዎች እንደማናውቅ ተደርጐ ብዙ ጊዜ መልሶ መላልሶ ይነገረናል፡፡ ችግሩን እናስረዳ በሚሉት ሰዎች ዘንድ ነው፡፡ እነሱ ራሳቸው አንዳንድ ጊዜ ያላቸው ግንዛቤ በቂ አይሆን ይሆን ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ምክንያቱም ባንኮች የሚሠሩት በሕዝብ ገንዘብ ነው የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ባንክ ሥራ ማለት ምን ማለት ነው? የትኛው ዓለም ነው የባንክ ሥራ በሼር ሆልደሮች ገንዘብ ብቻ የሚሠራው? የባንክ ሥራ የግልም ሆነ የመንግሥት በህዝብ ገንዘብ ነው የሚሠራው የሚለው አገላለፅ ስለባንክ አሠራር ግንዛቤ የሌለውንና የማያውቀውን ሰው እንደ ማስፈራሪያ አድርጐ መናገር ይመስላል እንጂ ጥፋት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አስቀምጠህ በማናቸውም ጊዜ የመቆጣጠር ሙሉ መብት ይዘህ ከተቀመጥክ በኋላ አሁን እንደገና መለስ ብሎ እነዚህን ባንኮች እምነት የሌላቸው የሰው ገንዘብ ይዘው እንደሚጠፉ አድርጐ መናገር ልክ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎችን ስታይና ስታዳምጥ ለአገሪቱ ሕዝብና ኢንቬስተር ሳይሆን ለሌላ ለውጭ ዜጋ የምታወራ ይመስላል፡፡ ችግሩ ምንድነው ሱፐርቫይዝ የሚያደርገው አካል እራሱ እውቀት ያስፈልገዋል፡፡ ልምድ ያስፈልገዋል፡፡ የባንክ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተጀመረም፡፡ ሪፖርተር፡- አልተጀመረም ሲባል እንዴት? አቶ እየሱስወርቅ፡- አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የባንክ ሥራ በዓለም ላይ ያለ ነው፡፡ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የተፈፀሙ ስህተቶችን በመመልከት የቁጥጥር ዘዴዎችን በማሻሻል በተቻለ መጠን ስህተቶች እንዳይፈፀሙ ማድረግ ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- በሌሎች አገሮች የግል ባንኮችን በመቆጣጠሩ ረገድ ያለው አሠራር ምንድነው? ማዕከላዊ ባንኮች (በአገራችን ብሔራዊ ባንክ እንደምንለው) ቁጥጥር የሚያደርጉት እንዴት ነው? አቶ እየሱስወርቅ፡- ኮንትሮል ወይም ሱፐር ቪዥን እንበለው፡፡ ሱፐር ቪዥን የሌለበት አገር የለም፡፡ ሁሉም ዓለም ውስጥ ባንኮች ሱፐርቫይዝድ ናቸው፡፡ እንደፈለጉ ሊፈነጩ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ባንኮች የብዙ አስቀማጮችን ገንዘብ ይጠቀማሉ የሚለውን ማንም አይክድም፡፡ እውነት ነው፡፡ እሱ እንደ አዲስ ነገር መነገር አይገባውም፡፡ የባንክ ሥራ ይሄ ነውና፡፡ የአስቀማጮች ገንዘብ ብቻም አይደለም፡፡ ኢንቨስት ያደረጉት የሼር ሆልደሮችንም የሠራተኞችንም የተበዳሪዎችንም ወዘተ. የእነዚህንም ወለድ ጭምር ነው የሚጠቀሙት፡፡ ሱፐርቫይዝ የምታደርገው እንጂ የአስቀማጮች ገንዘብ ላይ ብቻ አይደለም የምታተኩረው፡፡ እኔ አብዛኛውን ከግንዛቤ ማነስ እንጂ በተንኮል አይመስለኝም፡፡ ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ረቂቅና የሌሎች አገሮች አሠራር ወይም መቆጣጠሪያ ስልት ልዩነቱ ምንድነው? አቶ እየሱስወርቅ፡- በእኛ አንደኛ ብሔራዊ ባንክም ቢሆን ከህግ በላይ መሆን የለበትም፡፡ የአገራችን የንግድ ሕግ (ኮሜርሻል ኮድ) አለ፡፡ ህገ መንግሥቱ አለ፡፡ በህገመንግሥቱ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም አካባቢ ኢንቨስት የማድረግ መብት አለው ይላል፡፡ ይሄ ዋናው መርሆ ሆኖ ከዚያ እንደገና በተዋረድ ስትሄድ በኮሜርሻል ኮዱ ኢንቨስት አድርገህ አንድ ድርጅት ወይም ኩባንያ ስታቋቁም ያንን ኩባንያ የሚያስተዳድሩት ባለቤቶቹ ናቸው ነው የሚለው፡፡ የአሁኑ የብሔራዊ ባንክ አዲሱ ረቂቅ ይህንን ሁሉ ጥሶ ይሄዳል፡፡ ዳይሬክተሮቹን እኔ ነኝ የማፀድቅላችሁ ይላል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የቀረቡለትን ተመራጮች ወዲያው ከማፅደቅ ውጪ በአንድ ግለሰብ እይታ መወሰን የለበትም፡፡ የአሁኑ ረቂቅ ለብዙ መጥፎ ነገር ያጋልጣል፡፡ ሪፖርተር፡- ቁጥጥሩ በምን መልክ ይሁን? አቶ እየሱስወርቅ፡- የሚመረጡት ሰዎች ምን ምን መስፈርት ማሟላት አለባቸው የሚለውን ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ በዚያ መስፈርት መሠረት ሊቆጣጠርና ሊሠራ ይችላል እንጂ ዳይሬክተሮችን እኔ ነኝ የምሾመው ብሎ መነሳት የለበትም፡፡ ሪፖርተር፡- በቀድሞው ህግ ላይ ይሄ ያለ ይመስለኛል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ ላይ ይህ በተለየ መልኩ ተቀምጧል? አቶ እየሱስወርቅ፡- ቀደም ብሎ በነበረው ህግ ውስጥ አለ፡፡ እኛ አገር እስከአሁን ድረስ የፈለግከውን ብትል የከሰረ ባንክ የለም፡፡ የተወሰኑ ተበዳሪዎች አጭበርብረዋል፡፡ ይሄ አዲስ ነገር ነው አይደለም፡፡ በተቻለ መጠን መጭበርበሩ እንዳይበዛ ማድረግ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ነው እያለ ብረት ሲገዛ ከርሞ የለም ወይ፡፡ መሳሳት ሃጢያት ነው? አውቆ ማጥፋት ነው ሃጢያት ወይም ደግሞ ተሳስቶ ከስህተት አለመማር ነው ሃጢያት እንጂ መሳሳት በማንኛችንም ላይ ይመጣል፤ ይደርሣል፡፡ ስለዚህ ድርጅት በህጉ መሠረት አቋቁሞ ህጉ በሚለው መሠረት የድርጅቱን አስተዳደር ሌላ ሰው አይሾምም፡፡ ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክን ወደ ፍርድ ቤት ሄዳችሁ ረታችኋል፡፡ በኩባንያው እራሱ በባለአክሲዮን ነው መታዘዝ ያለበት ትላላችሁ፡፡ አሁን ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ከቀድሞው የባሰ ነው ያላችሁትን አዲስ ረቂቅ አውጥቷል፡፡ ከዚህስ በኋላ ምንድነው የምታደርጉት? በአዲሱ ረቂቅ ወደ ፍርድ ቤት የመሄዱ ጉዳይም ጠባብ እንደሆነ ያሳያል፤ አቶ እየሱስወርቅ፡- በአዲሱ ረቂቅ ህግ ዙሪያ የባንኮች ማኀበር ሃሳቡን ሰጥቷል፡፡ ተቆጣጣሪው አካል (ብሔራዊ ባንክ) በደንብ መመልከት አለበት፡፡ ተጨማሪ ሃሳብ ለመስጠት ቁጭ ብሎ መወያየትና መተማመን ያስፈልጋል፡፡ እንደ አለቃና ምንዝር ሳይሆን እንደ ባለሙያ ቁጭ ብሎ መወያየትና የሚበጀውን ማድረግ ይገባል፡፡ ቀደም ብሎ በወጣው ፍርድ ቤት ስንሔድ ሁለት አንቀፆችን ብቻ ነው የተቃወምነው፡፡ አንዱ የዳይሬክተሮችን ምርጫ የሚመለከት ነው፡፡ ዳይሬክተሮችን በሚመለከት ብሔራዊ ባንክ እራሱ ባንክ ስለመፍቀድና ስለመቆጣጠር ብሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 84/1986 የሚለው ነገር አለ፡፡ የባንክ ዳይሬክተር ማለት ምን ማለት ነው ብሎ ይተነትነዋል፡፡ የባንክ እውቀት ቢኖረው እንደሚመረጥ ከዚህ ውጭ ግን ዳይሬክተር ማለት በንግድ ህጉ እንደተደነገገው ይሆናል ብሎ ነው ያስቀመጠው፡፡ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ትክክል አለመሆኑን አስረዳን፡፡ የራሳችሁን ሥልጣን ያገኛችሁበትን አዋጅ እየጣሳችሁት ነው አልን፡፡ አንድ ዳይሬክተር የሚመረጠው በባለአክሲዮን ነው፡፡ ከፍተኛው ለአንድ ጊዜ ምርጫ ሦስት ዓመት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌላ የሚቃወምና የሚያፈርስ ከሌለበት እንደገና ለምርጫ መቅረብ ይችላል ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ ሼር ሆልደሩ እንደገና መልሶ ከመረጠው መረጠው፣ ጥፋት ካለበት ለዚያ ቦታ ብቁ አይደለም ከተባለ ሼር ሆልደሩ ሊጥለው ይችላል፡፡፡ የወንጀል ጉዳይ ከሆነ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን እንዲህ እንዲህ ዓይነት ወንጀል ሰርተናልና አንተ ለዚህ ቦታ ብቁ አይደለህም ሊለው ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- ወደ ፍርድ ቤት ይዛችሁ የሄዳችሁት ሁለተኛው ጭብጥ ምንድነው? አቶ እየሱስወርቅ፡- በአንድ ባንክ ውስጥ ዳይሬክተር የሆነ በሌላ የፋይናንስ ሴክተር ውስጥ ዳይሬክተር መሆን አይችልም የሚለው መመሪያ ነው፡፡ የንግድ ህግ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የለም፡፡ የባንክ ሥራን ስለመፍቀድና ስለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ 84/1986 ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ከየት አመጣህ አልነው፡፡ ሁለት ጊዜ ብቻ ለሦስት ለሦስት ዓመት ተመርጦ ከዚያ በኋላ ግን ለስድስት ዓመት ውጪ መቆየት አለበት፡፡ ዳይሬክተር መሆን የለበትም የሚል ነው፡፡ ይሄ ከሥልጣንህ ውጭ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ሥልጣን የለህም ብሔራዊ ባንክ ይህንን ማድረግ ከፈለግህ ወደኋላ ተመልሰህ የተቋቋምክበትን ህግ ማሻሻል ነው ብለን ነው ያልነው፡፡ ይህንን ሱፐርቪዥን የተቋቋመበተን 84/1986 ሙሉ ለሙሉ አውጥቶ ጥሎ አሁን ደግሞ የባሰ አዲስ ረቂቅ አዘጋጅቷል፡፡ ከአሁን በኋላም እኛ ፍርድ ቤት የወሰድነው ዓይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር ብሔራዊ ባንክ ከመሰለው ወይም ካመነበት የፈለገውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ህግ እንዴት አድርገህ ነው የምትከራከረው? መስሎኛል አምኜበታለሁ ይልሃል፡፡ ሌላ ዳኛ የለም፡፡ ከሳሹም ዳኛው እሱ ሊሆን ነው፡፡ ስለዚህ ረቂቁ ችግር አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- በአዲሱ ረቂቅ ወደ ፍርድ ቤት ሔዳችሁ እንደረታችሁበት ዓይነት እድል የለም? አቶ እየሱስወርቅ፡- አዎ፡፡ እኔ የብሔራዊ ባንኩም ቦርድ ቢሆን ይህንን ረቂቅ ያሳልፋል ብዬ አላምንም፡፡ ፓርላማም ቢሆን ይህንን ያሳልፋል ብዬ አላምንም፡፡ እኔ ይህንን እንደረቂቅ ነው የምመለከተው፡፡ ሪፖርተር፡- ቢፀድቅ ምን ታደርጋላችሁ? አቶ እየሱስወርቅ፡- ረቂቁ ፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቢደረግ ብሔራዊ ባንክ ካመነበትና ከመሰለው ከ50 እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት፣ ከ5 እስከ 15 ዓመት እስራት በሚል ይህንን ማስፈራሪያ ካስቀመጠ ማነው የባንክ ኘሬዚዳንት የሚሆነው፡፡ ማነው የባንክ ምክትል ኘሬዚዳንት ሆኖ የሚሠራው፡፡ በእኔ እይታ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ዳይሬክተሮች ይለቃሉ፡፡ ኘሬዚዳንቶች ይለቃሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮችን ተረክቦ ማስተዳደር ሊያስፈልገው ነው ማለት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በእርግጠኝነት ወደዚያ ያመራል? አቶ እየሱስወርቅ፡- አዎ፡፡ እኔን በአሁኑ እድሜዬ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ እስር ቤት መግባት እፈልጋለሁ? ይህ ረቂቅ ከፀደቀ ኃላፊነቴን ለመልቀቅ የመጀመሪያው ሰው እኔ ነኝ፡፡ የባንክና የፋይናንስ ሥራ ዓይኑን ለማጥፋት ታልሞ የተረቀቀ ነው ብዬ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አንድ ባለአክሲዮን በባንክ ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ከቀድሞ እንዲያንስ መደረጉ ምን ችግር አለው? አቶ እየሱስወርቅ፡- ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ኢንፊሊዌንሻል ሼር ሆልደር አንድ ፐርሰንት የባንኩን ሼር ያለው ነው፡፡ ማኪሲመሙ አምስት በመቶ ብቻ እንዲያዝ አድርጓል፡፡ ድሮ ሃያ በመቶ የነበረውን ማለት ነው፡፡ ብዙ አስተሳሰብ እኮ አለ፡፡ 2ዐ በመቶ የሚፈቅደውን ምናልባት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ወደ አሥር በመቶ አወረዱት ተብሎ መሥራት ይቻላል፡፡ አሁን ባለበት ይሂድ ቢባል የእኛ ህብረት ኢንሹራንስ፣ ህብረት ባንክ ውስጥ አሥር በመቶ የለውም፡፡ ህብረት ባንክ ህብረት ኢንሹራንስ ውስጥ አንድ ፐርሰንት ሊኖረው ይችላል፡፡ እኛ ጋ ችግር አይደለም፡፡ ሌሎች ባንኮች ጋ ግን አለ፡፡ እስከ አሥራ አምስት፣ ሃያ በመቶ ድረስ የያዙ አሉ፡፡ በአዲሱ ረቂቅ ሼሮቻቸውን መሸጥ አለባቸው፡፡ እዚህ አገር ስቶክ ማርኬት የለም፡፡ ስለዚህ እባካችሁ ብሔራዊ ባንክ አስገድዶኛልና ሼሬን ግዙኝ ቢባል ሊገዛ የሚመጣው ዋጋውን አሳንሶ ነው፡፡ ይሄ ትክክለኛ ሥራ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከአሁን በኋላ የውጭ ኢንቨስተሮች በፍፁም በፋይናሺያል ሴክተሩ (አሁንም ክልክል ነው ለወደፊትም ቢሆን እንዳታልሙ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ህግ ኢንቨስት የሚያደርግ የለም፡፡ በፋይናሺያል ሴክተር በኩል ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የሚያግድ ነው፡፡ ይህም ራሱ ሌላ ጉዳት ነው፡፡ አገር ውስጥ ያለን ሰው ዳይሬክተር መሆን የሚፈራ ከሆነ ባንክ ለምን ታቋቁማለህ? ማኔጅመንትህ እንዲፈራና እንዲሸሽ ካደረገብህ እኮ ባንክ ማቋቋም አይሞከርም፡፡ ረቂቁ ትክክል አይደለም፡፡ ቁጥጥር አይኑር አይደለም የምንለው፡፡ ቁጥጥር አይኑር እያሉ ነው ተብሎ ብዙ ጊዜ ይወራል፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ቁጥጥር መኖር አለበት፡፡ ነገር ግን ቁጥጥሩ በህግ ይሁን ነው፤ በግለሰቦች እይታ ወይም አመኔታ ብቻ ዳይሬክተሮችና የባንክ አመራር አባላት ይፈቱ ይታሠሩ ማለት ራሱ ትክክል አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- ረቂቁን ያዘጋጀው ብሐሪዊ ባንክ ነው፡፡ አፅዳቂው አካል ሌላ ነውና መንግሥትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምን ማድረግ አለባቸው? አቶ እየሱስወርቅ፡- የማላምንበትን ቆሜ መከራከር አልችልም፡፡ የማምንበት ሲሆን ደግሞ ከሁለም በላይ ሀገሬ ነችና ጥፋት ሲሰራ ወይም ጥፋት መስሎ ሲታየኝ የምችለውን ያህል መናገር አለብኝ፡፡ እኔ ከእንግዲህ በኋላ እግዚአብሔር ይመስገን ጦሜን አላድርም፡፡ እውነት ነው ብዬ ያመንኩበትን ያለምንም ፍርሃት በቀጥታ እናገራለሁ፡፡ ተናግሬ ቤቴ ገብቼ እተኛለሁ፡፡ እስከአሁንም በመጠራጠርም ባይሆን እንደአሁኑ ፍርድ ቤት ሄጄ አላየሁትም ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ሄጄ አየሁት፡፡ ፍርድ ቤትም ትክክለኛ ፍርድ ማግኘት ይቻላል፡፡ የምናምንበትንና ትክክል የሆነውን ነገር በሰላምና በሕግ በፍርድ ቤት መሞከር አለብን፡፡ ፍርዱ በተቃራኒው ቢመጣ ኖሮ ይግባኝ ከማለት አልመለስም፡፡ በዚህ የፍርድ ሂደት በጣም ስለረካሁ ፍርድ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- አዲሱ ረቂቅ ህግ ማስጠንቀቂያ ነው የሚልም አስተያየት አላችሁ? በተለይ በፍርድ ቤት በመርታታችሁ በአዲሱ ረቂቅ ወደ ፍርድ እንድንሔድ ያደርገናል የሚል አስተያየትም አለ፡፡ አቶ እየሱስወርቅ፡- እኛ ማስፈራሪያ ነው ያልነው፡፡ ማስጠንቀቂያም አይደለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ አምኖበት ለሠራው ነገር ሁሉ፡፡ በማንም የግል ባንክ ጥፋት፣ ጉዳት ወይም ክስረት ቢደርስ አይጠየቅም ይላላ፡፡ ሁሉንም ሥልጣን ለራሱ ሠጥቷል፡፡ ሪፖርተር፡- የግል ባንኮች አሁን ያላቸው የገበያ ድርሻ ምንያህል ነው? ቀደም ብለው ሲጠቅሱልኝ ደግሞ ደካሞች ናቸው ብለዋል፡፡ ድክመቱ እንደዚህ ዓይነት ህጐች ስለሚወጡ ነው? አቶ እየሱስወርቅ፡- እንዲህ ዓይነት ህጐች ስላሉ የባንኮቹ ድክመት ምንም ናቸው ብሎ ማመካኘት አይችልም፡፡ ትክክልም አይደለም፡፡ ብዙ ነገሮችን ማየት ትችላለህ፡፡ አንደኛ አጠቃላይ የባንክ ሥራ ገና በመለመድ ላይ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በአካባቢያቸው የባንክ አገልግሎት ስለሌለ ወይም በሌላ እምነት ገንዘባቸው ትራስ አድርገው የሚተኙ አሉ፡፡ ሁለተኛ በአገራችን ንቃተ ኀሊናው ገና ነው፡፡ መንግሥት ትክክል ነው የሚለው አመለካከት ገና አልተለወጠም፡፡ የኢትዮጵያ አብዛኛው ኢኮኖሚ የተያዘው በመንግሥት ነው፡፡ በማንኛውም መልኩ ቢወሰድ ትልቁ ቀጣሪ መንግሥት ነው፡፡ ትልቁ ኢንቨስተር፣ ኮንሱመር መንግሥት ነው፡፡ በዚህ ላይ አብዛኛውን መንግሥት ትክክል ነው የሚለውን ነገር የሚያስተጋባ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ትልቁን ቦታ ይወስዳል የሚል ባንኮች የገበያ ድርሻ 2ዐ በመቶ ነወ፡፡ 8ዐ በመቶው የመንግሥት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ባንኮች ብዙ ትርፍ ካተረፉ ይህ የእድገት መለኪያ አይሆንም? አቶ እየሱስወርቅ፡- ከዚህ የተሻለ የሚያበረታታ ነገር ቢፈጠር ትርፋቸው የበለጠ ወይም ያነሰ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ባንኮቹ የበለጠ ጡንቻ ሊያመጡ እንደሚችሉ ነው የሚታየኝ፡፡ የሚያስፈልገው እሱ ነው፡፡ አስተሳሰቡ የባንክና የኢንሹራንስ ሥራ ለውጭ ሰዎች ዝግ የሆነበት አንዱና ዋናው ምክንያት አገር ውስጥ ያሉት ባንኮች እንዲፋፉና አዳዲስ እንዲፈጥሩ ለማድረግ ነው፡፡ ለውጭ ባንኮች ሲከፈት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲሰሩ ጊዜ ለመስጠት ታስቦ ነው፡፡ አሁን ግን ይህ እንዲሆን የተፈለገ አይመስለኝም፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |