| ቻይና ለኢትዮጵያ ባለ ሦስት... |
|
| Wednesday, 12 November 2008 | |
ቻይና ለኢትዮጵያ ባለ ሦስት ነጥብ ኘሮፖዛል አቀረበች- የግብርና ቴክኖሎጂ ማሳያ ማዕከል ግንባታ - የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ - የቻይና የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ በጋዜጣው ሪፖርተር በቻይና ኮንግረስ ሊቀመንበር ሚስተር ው ባንጉኦ የሚመራው የቻይና ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለው ባለ ሦስት ነጥብ ኘሮፖዛል አቀረበ፡፡ ሚስተር ዉ በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ የቻይናንና የኢትዮጵያን ግንኙነት ማጠናከር እንዲቻል ባለ ሦስት ነጥብ ኘሮፖዛል ለኢትዮጵያ መንግሥት አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ያደነቁትና ኢትዮጵያ የልማት ግቡን እንደምታሳካ የተናገሩት ሚስተር ዉ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ባቀረቡት ባለ 3 ነጥብ ኘሮፖዛሎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የመጀመሪያው ኘሮፖዛል የኢትዮጵያን የግብርና ልማት ለማሳደግ የሚያስችል ዋን ቻይና ፖሊሲ (One China Policy) መከተልና የግብርና ቴክኖሎጂ ማሳያ ማዕከል ማቋቋም ነው፡፡ ሁለተኛው ኘሮፖዛል የኢትዮጵያና የቻይናን የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነት የሚያዳብር ሁለገብ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም የተለያዩ ታላላቅ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን በቻይና ኩባንያዎች ማስገንባትና ኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማሳደግ የሚል ይገኝበታል፡፡ ሦስተኛው ኘሮፖዛል የቻይናዊያን የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ሲሆን እንደልዑካን ቡድኑ እምነት ይህ ብዛት ያላቸው ቻይናዊያን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያበረታታል፡፡ ሚስተር ዉ ይህንን አስመልክተው እንደተናገሩት "በኢሕአዴግ እና በቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነትና የልምድ ልውውጥ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጐታል"፡፡ ሚስተር ዉ አያይዘውም የቻይና መንግሥት የአገሪቱ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ እንደሚያበረታታና ነፃ የቴክኖሎጂ ፍሰት እንዲኖር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ደግፌ ቡላ ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሚስተር ዉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ጨምሮ፣ ኘሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ አቶ ተሾመ ቶጋንና አቶ ደግፌ ቡላን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማነጋገራቸውን ሽንዋ ዘግቧል፡፡ |
|
| Last Updated ( Wednesday, 12 November 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |