| ኢትዮጵያ በአፍሪካ |
|
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
|
ታፍራና ተከብራ የኖረችው አገራችን እያልን በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቅን መሆናችንንና ለየት ያለ አፍሪካዊ ታሪክ ያለን መሆናችንን እንተርካለን፡፡ ሰማንያ ብሔር ብሔረሰቦች ያላት አገር መሆንዋን በመግለፅ ደግሞ የውበትና የቅንብር አገርና ሕዝብ መሆናችንን በመዘርዘር በአፍሪካ ልዩ ቦታ እንዳለን እንናገራለን፡፡ የአፍሪካ ሕብረት (የአፍሪካ ህብረት ድርጅት) በመመስረትም መሪና ግንባር ቀደም ሚና መጫወታችንን እንገልፃለን፡፡ ማስረጃው የአፍሪካ ዋና ፅህፈት ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ነው እንላለን፡፡ ትክክል ነውም፡፡ ሁሉ እውነት ነው፡፡ ልንኮራበትም ይገባል፡፡ ታሪክም ሊመዘገብ ይገባል፡፡ ዋናው ቁም ነገርና ዋናው ጥያቄ ግን ድሮስ እንደዚያ ነበር፣ አሁንስ? የሚለው ነው፡፡ በድሮው መመዘኛ አንደኛ ነን እያልን ከምንኩራራ በአሁኑና ዘመኑ በሚጠይቀው መመዘኛ አንደኛ መሆንን መመዘንና መኩራትን እንምረጥ፡፡ አዲሱ መመዘኛ ምን ሊሆን ይችላል? ዋነኛውና ግንባር ቀደሙ መመዘኛ የኢኮኖሚ ልማትና ከድህነት መለወጥ ነው፡፡ ምንም እንኳ በረሃብ ብንሰቃይም ብንጎዳም፣ ምንም እንኳ በምግብ ራሳችንን ባንችልም፣ ምንም እንኳ በምግብ እጥረት ሕፃናቶቻችን እየተጐዱ ቢሆንም፣ ምንም እንኳ ድርቅ በመጣ ቁጥር ህብረተሰባችንና ቤተሰባችን ቢበታተንም በቀኝ ግዛት ግን አልተገዛንም፣ እያልን መኩራራት ለትዝብት የሚዳርገን ነው፡፡ ስለዚህ አዲሱና ዋነኛው መመዘኛ በልማት ያደግንና በኢኮኖሚ የጠነከርን ነን ብለን ስንኮራ ነው፡፡ ይህን ለማለት የምችልበት ሁኔታ እንዳለ የሚያሳየው የኢኮኖሚ ማደግንና መሻሻል መታየቱ ነው፡፡ በአፍሪካ መሪ የኢኮኖሚ ቦታ አለን ለማለት ግን ገና ነን፡፡ ዓላማችንና ግባችን አዲስ የምንሰራበት መመዘኛችን ግን ይህ መሆን አለበት፡፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ አገር ነን ብለን መኩራትም ሌላው አዲሱ መመዘኛ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ራስን የማስተዳደር መብትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ደህና ሥፍራ ትይዛለች፤ ብለን እናምናለን፡፡ በእኛ እምነት የፌደራል አወቃቀሩ ለዚህ ጥሩ መንገድ የሚከፍት እንጂ እንቅፋት የሚሆን አይደለም፡፡ የፍርድ ቤት አወቃቀርና ጥንካሬ፣ የፕሬስ ነፃነትና ጥንካሬ፣ የአስተዳደሩን የፍትሕ አካላት መዋቅራዊ ተቋም ልምድና ጥንካሬ በሚመለከት ግን እኛ ገና ነን፡፡ በብዛትም በአወቃቀሩም በልምድም በባለሙያም ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ምርጫ 97ትን ራሳችን አበላሸነው እንጂ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ከሚታየው ምርጫ የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የተቋም ድጋፍ ስላልነበረው ትንሽ ችግርን ለመቋቋም ሳይችል ቀረ፡፡ በአፍሪካ፣ በአዲስ መመዘኛ፣ ኢትየጵያ መሪ ቦታ ይዛለች፤ ትጫወታለች ለማለት ከፈለግን በአስተዳደርና በፍትህ መመዘኛዎችም መሪ ቦታ ይዛለች ማስባል ይገባናል፡፡ "የታፍራና ተከብራ መመዘኛ" ሩቅ ሊያስኬደን አይችልም፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲመሰረትና አፍሪካ በዓለም ቦታ እንዲኖራት በማድረግ ኢትዮጵያ አብይ ሚና ተጫውታች፡፡ የአፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር እንድንወዳደር በማድረግም አኩሪ ሚና ተጫውታች፡፡ ሱዳን ግብፅና ኢትዮጵያ ሶስቱ ባደረጉት ውድድርም "ድሮ ድሮ ድሮ" ዋንጫ መውሰዳችን ይታወሳል፡፡ ይህ ግን ድሮ ነው፡፡ አሁን ግን የሚሰራበት አጀንዳ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ እናሰተናግዳለን፤ በሚል ሌላ ሊግ እንጂ በአፍሪካ የእግር ኳስ ሊግ የለንበትም፡፡ በአዲስ መመዘኛ እንኩራ ከተባለ ስፖርትም አንድ መስክ መሆን አለበት፡፡ በባህልም በስነ ጥበብም በሌላም በሌላም ሁሉ አዲስ ስፍራ፣ መሪ ሚና ልንይዝ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን በዚህ ጉዳይ ቆም ብለን ልናስብ ይገባል፡፡ አጉል መኩራራትን አቁመን ሃቁን መቀበልና መዋጥ አለብን፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የሚደነቁ እንስሳትና የዱር አራዊቶች አሉዋት፡፡ በብዛትም በዓይነትም ከኬንያ፣ ከኡጋንዳና ከታንዛኒያ አናንስም፡፡ በአያያዛችንና ለቱሪዝም መስህብ በመጠቀም አንፃር ከእነሱ ጋር ስንወዳደር ግን እጅግ ኋላ ቀር ነን፡፡ ብሔራዊ ፓርክ ለውጥ ሊኖረንም አልቻለም፡፡ ለቱሪዝም መጠቀም አልቻልንም፡፡ ብርቅዬ አራዊቶቻችን ወደ ጎረቤት ሃገር እንዳይፈልሱም መከላከያ የለንም፡፡ ይህ አደጋ እያለ "ታፍራና ተከብራ" እያልን ብቻ አንዘዋወር፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ መብራት ሃይል፣ አየር መንገድ ወ.ዘ.ተ ስታስተዳድር በራስዋ ነው፡፡ ቅኝ ግዛት ስላልነበራት ቅኝ ገዢዎች አላበሩለትም፡፡ የራስዋ ስልክና መብራት አላት እያልን ተኩራርተናል፡፡ አሁን ግን መመዘኛው ይቀየር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስልክና መብራት ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላት የኢነርጂ በሌላ የአፍሪካ አገር የለም፡፡ በአንድ ጊዜ አራት አዳዲስ የሃይል ማመንጫዎች እየተሰሩ መሆናቸውም አንዱ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሌላ አገር የቴሌ አገልግሎት የእኛን እያለፈ ነው፡፡ በመብራት አጠቃቀም ሌሎች ይበልጡናል፡፡ አየር መንገዳችን ጥሩ ነው፡፡ ግን ተወዳዳሪዎች እየመጡበት ስለሆነ የጀመርነው እኛ ነን፤ ማለትና በዚህ ተኩራርቶ መቀመጡ የትም የሚያደርሰን የማያፀድቅ ፀሎት እየሆነ ነው፡፡ ይህን ተገንዝበን በአዲስ መመዘኛ አዲስ ስፍራ ለመያዝ እንስራ እንሯሯጥ፡፡ ይህን እያደረግን ግን ያ የተደረገው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ በተሻለ መንገድ እንዲጠናቀቅ ማድረግና በስራም እንዲያድግም ማድረግን አንርሳ፡፡ ሰሞኑን በሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ለመሳተፍ ሚኒስትሮች መጥተዋል፡፡ መሪዎችም ሊመጡ ነው፡፡ የጨዋ አቀባበልን አንርሳ፣ ፀጥታ አጠባበቅን አንዘንጋ፣ ሕዝብ ከፀጥታ ጥበቃ ሃይል ጋር መተባበር አለበት፡፡ ዋና ፅህፈት ቤት ከኢትዮጵያ ይውጡ የሚሉና ለፀጥታ አይመችም የሚሉ ኢትዮጵያን የማይወዱ ሃይሎች እንዳሉ አንዘንጋ፡፡ እንደሕዝብ ፀጥታን ራሳችን እያከበርን እንዲከበርም እናድርግ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን በአፍሪካ ውስጥ በአዲስ መመዘኛ አዲስ ስፍራ መያዝ ነው! በኢኮኖሚ፣ በዴሞክራሲ፣ በስነ ጥበብ፣ በስፖርት፣ በሰላምና መረጋጋት፣ በኢንቨስትመንትና' በኢንፍራስትራክቸር... ቀድሞ መገኘት ነው፡፡ ይህ ነው አዲሱ መመዘኛ!!!! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |