| የውጭ ኃይል ጥገኝነት ስሜት፣... |
|
| Sunday, 16 November 2008 | |
|
የውጭ ኃይል ጥገኝነት ስሜት፣ ኢትዮጵያ 51ኛዋ የአሜሪካ ስቴት?
በጌታቸው ንጋቱ የባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ ማሸነፍ ወሬ በቀላሉ ሊቀዘቅዝ አልቻለም፡፡ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ጥቅም አንፃር መከራከሪያ መሆንም ጀምሯል፡፡ ኦባማ ማሸነፋቸው ለኢትዮጵያ ይበጃል የሚሉና የኦባማ ማሸነፍ ምንም አይጠቅመንም፣ ከኢትዮጵያ ጋር አይገናኝም በሚሉ መካከል፡፡ ኢትዮጵያ ለኦባማ፤ ኦባማ ለኢትዮጵያ እየተባለ መነገሩን ኢትዮጵያ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት ሆናለች ወይ በማለት የሚጠይቁም አሉ፡፡ ዴሞክራቶችንና ኦባማን ተስፋ የሚያደርጉና በኦባማ የመመካት ስሜት ያደረባቸው የፖለቲካ ኃይሎችና ቡድኖች የኦባማን መመረጥ ተከትሎ “የኢትዮጵያ መንግሥት ጉድ ፈላበት”፣ “ኦባማ ጣልቃ ገብተው ኢሕአዴግ ላይ ጫና ይፈጥራሉ"፣ “ኦባማ ይህንን መንግሥት አይደግፉም” እና ሌሎችንም ቢሉም፤ በተቃራኒው ሌሎች ኃይሎች እንዲህ የሚሉ ወገኖች በአገራቸው ካለው መንግሥትና ሕዝብ በላይ በውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ የመሆን አዝማሚያ እንዳደረባቸው በመግለጽ ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ መሪዎች ታላቅ ተስፋ ከወደ አሜሪካ የወጣ መሆኑን በመግለጽ ከአሜሪካውያን እኩል ፈንድቀዋል፡፡ “ለምን ኢትዮጵያውያንም ድምጽ አይሰጡም” በማለት ሁኔታውን የተመለከቱ እና የተናገሩበት ሁኔታም አለ፡፡ የኦባማን መመረጥ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስሉ ሰዎች፤ “ኦባማ ከአፍሪካ (ኬንያ) የወጣ ነው”፣ “ኦባማ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር”፣ “ኦባማ ኢትዮጵያዊ ይመስላል” ከሚሉ ቀለል ካሉ አስተሳሰቦች “የዴሞክራቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስለሚቀየር እንደ ሪፐብሊካኖቹ አይሆንም፣ ሪፐብሊካኖቹ አይፀድቅም ብለው ያስቀሩት ኤች.አር 2003 ሕግ አሁን ይፀድቃል” የሚሉ አመለካከቶችም ይሰነዘራሉ፡፡ የቡሽ አስተዳደር ኢትዮጵያን የደገፈውና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሰራው የኢትዮጵያን መንግሥት ስለወደደው ሳይሆን የአሜሪካን ጥቅም ለማስከበር ነው፤ የአሜሪካ ጥቅም ካልተፃረረ ኃይል ጋር አብረው እንደሚሰሩም አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ ጥቅም ምንድ ነው? አሜሪካ ከኢትዮጵያ ምን ትፈልጋለች? የፈለገችውን አግኝታለች አላገኘችም? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ መልስ ሳይሰጥ በቀጥታ የኦባማ ማሸነፍ ለኢትዮጵያ መንግሥት ችግር እንደሚሆን እየገለፁ ያሉ አካላትም አሉ፡፡ ሰሞኑን የወጣ አንድ ጽሁፍም የአሜሪካ ዴሞክራት ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደማይደግፉ በመግለጽ ተሰራጭቷል፡፡ ”ባማ ድል በኢትዮጵያ የኢሕአዴግ አገዛዝ ማብቂያ መድረሱን የሚያበስር ነው” በሚል በተለይ በዲያስፖራ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አዲስ የተቃዋሚዎች አጀንዳ ሆኗል፡፡ የኦባማ መመረጥ የአምባገነነት ማብቂያ (Obama's victory the end for Ethiopian Dictatorship) በሚልም የኦባማንና የኢትዮጵያን ግንኙነት የዘር አገራቸው የሆነችው ኬንያውያን እንኳን ከሚጠብቁት በላይ ተደርጎ እየተነገረ ነው፡፡ የትኛውም የጥቁር ዘር ያለው ሕዝብ በኦባማ ፈታኝ ትግልና የማይታሰበውን ማሳካት ደስተኛ መሆኑ እንደማያጠያይቅ የሚገልፁ አካላት ጥቁር ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝቦች በአጠቃላይ የዓለም ስርዓት ላይ ለውጥ ይመጣል በሚል ታላቅ ተስፋ ሰንቀዋል ይላሉ፡፡ ኦባማና ኢትዮጵያን በዚህ ረገድ የሚያገናኛቸው እንደሚጠበቀው የዓለም ሥርዓት ለውጡ ተጠቃሚ የመሆን ዕድል ኢትዮጵያም ሊኖራት መቻሉ እንጂ ኦባማ እረፍት የሚያሳጣውን የአገራቸውን ሥራ ትተው የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካ ያቦካሉ ብሎ መጠበቀ የዋህነት መሆኑን የሚመክሩ አሉ፡፡ ኦባማ ሳይሆኑ ሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናትም በየደቂቃው የሚቀያየረውን የዓለም ሥርዓት ከመታገልና የአገራቸውን ጥቅም ከማስከበር አልፈው እርስ በርሱ ተስማምቶ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት መፍጠር ላልቻለ አገር፣ ፖለቲከኞቹ መደማመጥ ለማይችሉበት አገር፣ የሌላ አገር መንግሥት መጥቶ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ያሰፍናል ብሎ መጠበቅ የጥገኝነት መንፈስ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ኢዴአፓ-መድህን አሁን ያለው አስተሳሰብ እንዳሳሰበው ገልጾ ባወጣው መግለጫ “ከአሜሪካ ምርጫ መማር የሚገባን በራስ መተማመንን እንጂ ጥገኝነትን አይደለም” ይላል፡፡ ከአሜሪካ ምርጫ መማር ያለብን ብሎ ድርጅቱ ያስቀመጣቸው አምስት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የአሜሪካ መንግሥት የሆነው የቡሽ አስተዳደር በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ጣልቃ ሳይገባና ተጽዕኖ ሳይፈጥር ምርጫ ማካሄዱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ሊማርበት የሚገባ ተብሏል፡፡ ሁለተኛው ከአሜሪካ ምርጫ የተገኘ ትምህርት ዕጩዎችና ተፎካካሪዎች እርስ በርስ መከባበራቸውን የምርጫውን ውጤት ተከትሎ እንኳን ደስ ያለህ መባባላቸው ነው፡፡ ሦስተኛው የአሜሪካ ምርጫ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ያስተማረው የአገሪቱ መራጭ የፈለገውን መምረጡና ማንም ሳያስገድደው ምርጫውን ማስፈሩን፣ በአራተኛነት የምርጫ ኮሚሽኑ ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ ሆኖ ከ120 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ድምጽ ሳይጭበረበር ሁለቱንም ወገኖች በሚያረካ መልኩ መፈፀሙ፤ የመገናኛ ብዙሃንም ከአድሎና ከወገንተኝነት የፀዱ በሕዝብና በተመራጮች መካከል ድልድይ ሆነው መስራታቸውን ለኢትዮጵያ ትምህርት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ፓርቲዎች በማይከባበሩበት አገር፣ ነፃ የምርጫ ቦርድ የለም በሚባልበት አገር፣ ሚዲያዎች ፍጹም አድሎአዊ በመሆን በሚሰለፉበት አገር፤ ሕዝቡ ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በሆነበት ሁኔታ፣ የምርጫውን ውጤት ከመቀበል ይልቅ ወደ ሌሎች አማራጮች በሚኬድበት አገር፣ “ኦባማ አድነን’ ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል የሚገልፁ ሲኖሩ በዚያው ልክ አሜሪካ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ ምርጫ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ መራብ እንደ እግር እሳት ስለሚለበልባት ኦባማ እንደ ሃምሳ አንደኛ የአሜሪካ ግዛት ኢትዮጵያን ቆጥረው ‘ምላሽ ይሰጡናል” የሚሉና አዳዲስ ሕጎች ኢትዮጵያ ላይ እንዲፀድቅ የሚጠብቁ አሉ፡፡ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ምዕራባዊያን አገራትም በደሃ እና ታዳጊ አገራት ላይ ታላቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳትፉና በብድርና በእርዳታ ብቻ የአገራቱን መንግሥትና ሕዝብ ማመሳቀል እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ያ ማመሳቀል ግን በዚምባብዌም፣ በሱዳንም፣ በኮንጎም ሠላምና ልማት አላመጣም፡፡ ይህንን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የአቶ ልደቱ ፓርቲም “እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ረኦባማ ለውጥ ያመጡልናልሪ ኢትዮጵያውያን በራስ የመተማመን ስሜት የራሳችንን ችግር በራሳችን ለመፍታት የምናደርገውን ሰላማዊ ትግል በሂደት የሚሸረሽርና የአሜሪካንን መንግሥት የዲፕሎማሲ ታሪክ በውል ያላገናዘበ ስሜታዊ አስተሳሰብ በመሆኑ በጥንቃቄ ሊጤን የሚገባው ነው” ይላል፡፡ ከአሜሪካ ምርጫም መማር የሚገባው በራስ መተማመንና የመንፈስ ጥንካሬን እንጂ የውጭ ሃይሎች ጥገኛ መሆን እንደሌለበት ፓርቲው ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለባራክ ኦባማ “የእንኳን ደስ አለዎት” መልዕክት የላከ ሲሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው በዚህ ጉዳይ የተለያዩ መግለጫዎች ማውጣታቸው ይታወቃል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |