| በኢትዮጵያ የሀይማኖት መቻቻል... |
|
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
|
ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው፣ "ኢንሃንሲንግ ሪሊጂየስ ቶለራንስ ኢን ኢትዮጲያ ኢን ዘ ኒው ሚሌኒየም" ወይም "በአዲሱ ሚሊኒየም በኢትዮጵያ የሀይማኖት መቻቻልን ማበልፀግ" በሚል ርዕስ ጥር 8 ቀን/2000 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ ኮንፈረንስ ተካሄዶ ነበር፡፡ በኮንፈረንሱ ከቀረቡት ሦስት ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅና በዶክተር አህመድ ሀሰን የቀረቡትን ጥናታዊ ፅሁፎች እንዲሁም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ያነሷቸውን አስተያየቶችና ጥያቄዎች ጠቅለል ባለ መልኩ ልናቀርብ ወደድን፡፡ በጥናታዊ ፅሁፉ ኢትዮጵያ በአለም ላይ የሚገኙትን ሶስት ታላላቅ እምነቶች የያዘች መሆኑ ተገል..ል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ የአይሁድ፣ የክርስትና እና የእስልምና እምነቶች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ አስራ አምስት በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ የጥንታዊ አምልኮ እምነትን ከላይ ከተጠቀሱት የእምነት አይነቶች ጋር በተደራቢነት ይከተላል፡፡ የታሪክ መዛግብትን በማጣቀስ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ሀምሳ በመቶ የሚሆኑት የሀገሪቱ ዜጎች የአይሁድ እምነት ተከታዮች እንደነበሩ የፕሮፌሰሩ ጥናታዊ ፅሁፍ ያመለክታል፡፡ በፅሁፉ እንደቀረበው በአሁኑ ጊዜ ሰላሳ አምስት በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ነዋሪ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው፡፡ እስልምና በነቢዩ መሀመድ ተወካዮች አማካይነት በመጀመሪያው የእስልምና ስደት ወይም የ"ሂጅራ" ጉዞ "የፍትህ ምድር" የተባለችው ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ ከሁለቱ እምነቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና የሚገኝ ሲሆን የሀገሪቱ ብሄራዊ እምነት በመሆን እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል፡፡ ከሀገሪቱ ሕዝቦች በግምት አርባ አምስት በመቶ የሚሆነው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ፕሮፌሰሩ በተጠቀሱት እምነቶች መካከል ለረጅም ዘመናት የመቻቻል መንፈስ እንደነበረና ኢትዮጵያም በበርካታ የታሪክ መዛግብት ለሀይማኖት መቻቻል በተምሳሌነት ተጠቃሽ መሆኗን አትተዋል፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ በክርስትና እምነት ተከታዮችና ከክርስትና እምነት ውጭ በነበሩት መካከል በርካታ ግጭቶች መከሰታቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ የግጭቶቹ መንስኤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንደነበረ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ክርስቲያኖችም ሆነ ሙስሊሞችም ከእምነታቸው ሀገራቸውን በማስቀደም የውጭ ወራሪዎችን በጋራ ይከላከሉ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ክርስቲያኖች የሙስሊሞች መስጊድ ሲሰራ እርዳታ እንደሚያደርጉና በተመሳሳይ መልኩ ሙስሊሞች ለቤተክርስቲያን ግንባታ የሚውል ገንዘብ የሚያዋጡበትን ሁኔታ አውስተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ኤፍሬም በኢትዮጵያ ውስጥ በክርስትና እና በእስልምና ሀይማኖቶች መካከል ከነበረው መልካም ግንኙነት አንጻር የኢትዮጵያ ባህል እስልምና በአለም ላይ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ በርካታ የቁርዓን ቃላት የግዕዝ አሻራ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ቅዱስ ቁርዓን አል መጽሀፍ መባሉን እንዲሁም አድባር፣ አልሀዋርዮን፣ አልመናፊቅ፣ አልሙናፊቃን፣ አህዛብ፣ ወዘተ የግዕዝ አሻራ ያላቸው የቁርዓን ቃላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የውጭ ሀይሎች ሀገሪቱን ለመውረር ከነበራቸው ፅኑ ፍላጎት በዋነኝነት እንደ ስልት አድርገው ይጠቀሙበት የነበረው በኢትዮጵያ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መካከል ልዩነት በመፍጠር የሀገሪቱን አንድነት መሸርሸር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በፅሁፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ልዩነት የመፍጠር ሙከራዎች ውስጥ የደቡብ አረቢያ ሀገራትና የግብፅ፣ የኦቶማን ቱርክ እና የአውሮፓ ሀገራት በተለይ የፓርቱጋሎች ሙከራ በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለመጥቀስ ያህል በግብፆች የይፋትና ፈጢጋር አካባቢ ገዢ የነበረውን ሰብረ አደንን በማጉሳሳት በንጉስ አምደፅዮን ላይ አመፅ ማስነሳታቸው ይታወቃል፡፡ ግብጾች በተከታታይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በማነሳሳት እንዲሁም የጦር መሳሪያና የወታደራዊ ድጋፍ ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አለመቻሉን ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡ በፕሮፌሰሩ ገለጻ መሰረት የግብፆች ሙከራ ያልተሳካው አንድም በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች አለመተባበር በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበራት ጠንካራ ወታደራዊ ሀይል ምክንያት መሆኑን አትተዋል፡፡ የግብፅ የወረራ ፍላጎት እስከ አፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ቢቀጥልም አልተሳካም፡፡ ከግብጾች በመቀጠል የአቶማን ቱርክ የመከፋፈል ሙከራ ተጠቃሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች እርስ በርስ በመተማመን አብረው ተሰባጥረው ይኖሩ ነበር፡፡ ይህንን የስብጥር ሰፈራን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኦቶማን ቱርክ ሀይሎች ሙስሊሞችን በማነሳሳት ክርስቲያኖችን እንዲቆጣጠሩ ጥረት ማድረጋቸውን ነገር ግን አለመሳካቱን የፕሮፌሰሩ ፅሁፍ ያስረዳል፡፡ ፕሮፌሰር ኤፍሬም በወቅቱ ቱርኮች የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በማስታጠቅ ወገኖቻቸውን እንዲወጉ ያደረጉት ጥረት ጣሊያን ክርስቲያኖችን በማስታጠቅ በሀገራቸው ላይ በባንዳነት እንዲንቀሳቀሱ ካደረጉት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከአውሮፓ ሀይሎች መካከል ፓርቱጋሎች ክርስቲያኖችን ለመርዳት በሚል ሰበብ ያደረጉት የወረራ ዕቅድ አለመሳካቱም ተብራርቷል፡፡ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በአንድነት የክርስቲያንና የሙስሊም ወረራዎችን ተዋግተዋል፡፡ ከሀይማኖታቸው ይልቅ የአገራቸውን አንድነት፣ ነፃነት ማስከበራቸውን አብራርተዋል፡፡ በሀያኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ሱዳን፣ ሱማሊያና ሶሪያ ከነበራቸው ድብቅ የመገነጣጠል ፍላጎት አንፃር እ.ኤ.አ በ1964 እና በ1965 በሞቃዲሾና በመካ ላይ በተደረጉት የአለም አቀፍ የሙስሊም ሀገራት ስብሰባና የእስልምና ኮንግረንስ ላይ በይፋ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዜጎቿን እየጨቆነች መሆኑንና ለዚህም የኢትዮጵያ ሶማሌዎች እንዲሁም አፋሮች አንዲገነጠሉ ጠይቀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በጥናታዊ ፅሁፋቸው ማጠቃለያ በኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መካከል ለበርካታ ጊዜያት የተቀሰቀሱት ግጭቶች ምንጫቸው ከውጭ መሆኑንና በፍፁም ኢትዮጵያዊ ገፅታ እንዳልነበራቸው አብራርተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ በሀይማኖት መቻቻል በተለይ ደግሞ በእስልምና እና ክርስትና መካከል ተቻችሎ በመልካም አብሮ በመኖር የምትታወቅና የአለም ተምሳሌት እንደሆነች ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አህመድ ሀሰን በበኩላቸው "ፕሪሉሚናሪ ኖት ኦን ሪሊጅየስ ቶለራንስ ኢን ኢትዮጲያ - ኤ ሂስቶሪንል ሪቪው ኦፍ ዲስኮርስ አባውት ኢዝላም" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ የዶ/ር አህመድ ጥናታዊ ጽሁፍ የኢትዮጵያንና የእስልምናን ግንኙነት በአራት የተለያዩ የጊዜ አንቀፆች ተመልክተዋል፡፡ የመጀመሪያው ምልከታ የጥንታዊ ጊዜ ሲሆን ኢትዮጵያ በነበራት ስትራቴጂካዊ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ የተነሳ ከውጭ ሀይሎች ጋር በነበራት ግንኙነት በመጀመሪያ ክርስትና ቀጥሎ እስልምና በሀገሪቱ መስፋፋቱ ተገል..ል፡፡ በዚህም "ኢትዮጵያ በእስልምና እና በፓጋን ባህር ውስጥ የምትገኝ የክርስቲያን ደሴት" የሚለው አባባል እንዲሻር ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ እስልምናን ከመቀበል አንፃር በቀደምትነቷ ተጠቃሽ ነች፡፡ ይህም ከአክሱማይቱ ንጉስ አህመድ ነጃሺ በፊት ኢትዮጵያዊው ቢላል እስልምናን በመቀበል ሀገሪቱ ቀዳሚነቱን ስፍራ ይዛለች፡፡ በክርስትና እና በእስልምና መካከል የመቻቻል ሁኔታ በኢትዮጵያ እንደነበር የቢላልና የንጉስ ነጃሺ በሀይል ሳይሆን በሰላም የእስልምናን መቀበል ሁኔታ እንደሚያመለክት ዶ/ር አህመድ አብራርተዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በመካከለኛው ዘመን በሙስሊሙ ህብረተሰብና በክርስትያኑ መካከል በርካታ ግጭቶች መከሰታቸው ተገል..ል፡፡ የግጭቶቹ ምክንያት ግን የፖለቲካ የበላይነትን ለመያዝ የሚደረግ ትግል እንጂ ሀይማኖታዊ አለመሆኑን የዶ/ር አህመድ ጥናት አትቷል፡፡ በዚህ ረገድ በግራኝ መሐመድ በክርስቲያኖች ላይ ያደረገው ወረራ ሀይማኖታዊ በተለይ የጅሀድ ጦርነት መባሉን የማይቀበሉ መሆኑን ዶ/ር አህመድ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም በጦርነቱ ወቅት በአህመድ ግራኝን በማገዝ ክርስቲያኖች መሰለፋቸውን እንዲሁም ሙስሊሞች ደግሞ የአፄ ልብነ ድንግል አጋር ሆነው በጦርነት መሰለፋቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከመካከለኛው ዘመን ፍፄሜ እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ ባለው ጊዜ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ሰላም መንገሱን ነገር ግን ሙስሊሞች ላይ የማግለል፣ የመሬት ይዞታ መብት መንፈግና በንግድና በእደ ጥበባት ስራዎች ውስጥ እንዳይሳተፉ የማድረግ ሁኔታ እንደነበር የዶ/ር አህመድ ፅሁፍ ያመለክታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ቀስ በቀስ መለወጡን በተለይ በ19ኛው ምዕተ አመት የሀይማኖት መቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር ሁኔታ መፈጠሩ ተብራርቷል፡፡ በመጨረሻም በሀይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት ወቅት ሙስሊሞች ከሀገሪቱ ሕገመንግሥት ጎን ለጎን የሸሪዓን ሕግ እንዲጠቀሙ ተፈቅዷል፡፡ በሌላ በኩል ግን የአፄው መንግሥት የሙስሊሞችን በዓል በብሄራዊ በዓልነት ባለመቀበሉ ሲያስኮንነው እንደነበር ዶ/ር አህመድ ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም በድህረ የኢትዮጵያ አብዮት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ አንፃር ሙስሊሞች በአብዮቱ እንቅስቃሴ ወቅት የፊውዳሉን አገዛዝ በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡ በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ክርስቲያኖች የሙስሊሞች ወገኖቻቸው አጋር በመሆን በተቃውሞ ሰልፉ ተሳትፈዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ውስጥ የሙስሊሙና የክርስቲያኑ ህብረተሰብ የነበረውን የመቻቻል የመፈቃቀር ሁኔታ ያሳየ ነበር፡፡ ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ የሙስሊሞች በዓል እንደብሔራዊ በዓል መከበር ጀምሯል፡፡ የዶ/ር አህመድ ጽሁፍ ከፕሮፌሰር ኤፍሬም ጥናታዊ ጽሁፍ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዘመናት የሀይማኖት መቻቻል እንደነበረ የተለያዩ የእምነት አይነቶችን በሰላም አብረው መኖር መቻላቸውንና የሀይማኖት እኩልነት እንደነበረ አትተዋል፡፡ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በምሁራኑ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ትችት፣ ድጋፍና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል በኢትዮጵያ የሀይማኖት መቻቻል በርግጥ አለ፤ ግን የሀይማኖት መቻቻልን ርዕሰ ጉዳይ በማስታከክ ከውጭ የሚመጡ ምሁራን ለግጭት ተነሱ እያሉ እየቀሰቀሱን ነው፤ ይህ ጉዳይ አንድ መፍትሄ ያስፈልገዋል በማለት አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ በኢትዮጵያ የሀይማኖት መቻቻል ፅንስ ሀሳብ ዙሪያ የተዛባ አመለካከት መኖሩን በመጥቀስ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሀይማኖትን መሰረት በማድረግ ግጭቶች እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሁሴን አፄ ሱሲኒዮስ ሀይማኖትን በመለወጡ ምክንያት ከስልጣን መወገዱን፣ ዮዲት ጉዲትን የአይሁድ እምነትን ለማስፋፋት ባደረገችው ጥረት ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ጋር ግጭት መፈጠሩንና በዚህም በርካታ ቤተክርስቲያናት፣ ገዳማትና ንዋየ ቅድሳት መውደማቸው፣ በአህመድ ግራኝም ወቅት የተከሰተው ተመሳሳይ ሀይማኖታዊ ግጭት መከሰቱን እንዲሁም በቅርቡ በጅማ የተከሰተውን ግጭት ለአብነት በመጥቀስ፣ "ኢትዮጵያ ውስጥ የሀይማኖት መቻቻል አለ ልንል አንችልም" ሲሉ የምሁራኑን ፅሁፍ ተችተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ እነዚህ ክስተቶች የሀይማኖት ግጭት መኖሩን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ መሸፋፈን ከጠቀሜታው ጉዳቱ እንደሚያመዝንና በግልፅ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ በድፍረት መወያየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ትኩሳቱን በመሸፋፈን ማለፍ መቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ሊያደርስ ይችላል በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሁሴን በምሁራኑ ጽሁፍ ላይ ልጅ እያሱ የእስልምና እምነትን እንዳልተቀበሉ ተደርጎ መቀመጡ ታሪክን የሚያዛባ መሆኑን ጠቁመው፤ በዶ/ር አህመድ ጥናታዊ ጽሁፍ ውስጥ የቀረበውን "ልጅ እያሱ የተወለደውም የሞተውም ክርስቲያን ሆኖ ነው" መባሉን ተቃውመዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ልጅ እያሱ ከስልጣናቸወ የተወገዱት በመስለማቸው ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ አብዛኛው የጦርነት ታሪክ መሆኑንና የጦርነቱ መጨረሻ ደግሞ ተቻችለናል፤ የሚል መሆኑ እንዳሳዘናቸው ከተሳታፊዎች መካከል ሀሳብ ቀርቧል፡፡ አንዳንድ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ታሪክ በጥልቀት ሲታይ ከመቻቻል ይልቅ ጭቆናና አፈና የበዛበት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የአህመድ ግራኝና የአፄ ልብነ ድንግል ግጭት፣ አፄ ኃይለ ስላሴ በሙስሊሞች ላይ ያደረጉት በደል፤ የልጅ እያሱ ከስልጣን መወገድ በሀይማኖት ምክንያት መሆኑ፣ በ1966 ከ100ሺ በላይ ሙስሊሞች የተቃውሞ ሰልፍ የወጡበት ጉዳይ፣ በተለይ ለረዥም ጊዚያት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሳይሆን በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች ተብለው ይጠሩ እንደነበርና እንደዜጋ ሙስሊሞች ሳይቆጠሩ መቆየታቸውን በማንሳት ኢትዮጵያ ውስጥ የሀይማኖት መቻቻል የለም የሚል ትችት ቀርቧል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ፖለቲከኞችና ምሁራን በግርድፉ ፣ተቻችለናል፣ ከማለት በግልፅ ነገሮችን በጥልቀት ሊመረምሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ በግለሰብ ደረጃ የመቻቻል ገፅታ የሚታይ መሆኑን ነገር ግን በማህበረሰብ ደረጃ የሀይማኖት መቻቻል እንደሌለ ተብራርቷል፡፡ ልጅ ኢያሱ እስልምናን ተቀብለዋል፤ ተብሎ በመጠርጠሩ እንግልት እንደደረባቸው፣ ኃይለስላሴ የሙስሊሙን በዓል ብሄራዊ በዓል አለማድረጋቸውንና መሰል ጉዳዩች በኢትዮጵያ የሀይማኖት እኩልነት አለ ለማለት አያስደፍርም ተብሏል፡፡ አህመድ ግራኝ በክርስቲያኑ ዘንድ ወረሪ፣ ነፍጠኛ፣ ቤተክርስቲያንን ያቃጠለ ወዘተ. ይባላል፤ በተቃራኒው ደግሞ በሙስሊሙ ዘንድ ከክርስቲያኖች የሚሰነዘረውን ጭቆና የተከላከለ ጀግና ነው የሚል ግንዛቤ በመኖሩ የታሪክ ምሁራን ሁለቱንም ባገናዘበ መልኩ በተጨባጭ መረጃ ላይ የተደገፈ ጥናት ሊያጠኑ ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ ተሰንዝሯል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ወደኋላ የቀረችበት ዋነኛ ምክንያት መሪዎቿ የሙስሊሙን ህብረተሰብ በጥርጣሬ ስለሚከታተሉ ለልማት የሚያስቡበት ጊዜ ስለሌላቸው ነው፤ የሚል ፣የአልፎርስ፣ ጋዜጣን ፅሁፍ በመጥቀስ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል በአይነ ቁራኛ የመጠባበቅ ሁኔታ መኖሩ ተጠቁሟል፡፡ "በሀይማኖት እኩልነት እንዲሁም በሀይማኖት መቻቻል ጽንሰ ሀሳቦች ዙሪያ ጠንከር ያለ ጥናት በማቅረብ መሻሻልና መታረም ያለባቸውና መበረታታት ያለባቸው ጉዳዮችን መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ በደፈናው ተቻችለናል ማለት ተገቢ አይደለም" በማለት በምሁራኑ ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ጠንከር ያለ ሂስ ቀርቧል፡፡ ዶ/ር አህመድ ሁሴን ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የተነሳውን ትችት በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤተክርስቲያንና መስጊድ በአጥር ተለያይተው የሚገኙባቸውን ሁኔታዎች በመጥቀስ የሀይማኖት መቻቻል እንደነበረ አሁንም እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር አህመድ አንዳንድ ስህተት ሊባሉ የሚችሉ ነገሮች በታሪክ ውስጥ በመኖራቸውን ገልፀው ስህተቶች ታርመው በተሻለ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ከተያዘ የጤፍ ፍሬ ውስጥ የሚንጠባጠብ ፍሬ መኖሩ አይቀርምና የሚንጠባጠበውን ከማየት ይልቅ "በእጅ ያለውን አብዛኛውን ፍሬ ማየት ከጉዳቱ ጠቀሜታው ያመዝናል" በማለት አስረድተዋል፡፡ ማጠናከር ያለብን መልካም ጎኖችን እንጂ አፈትልኮ የሚወጣውን ህፀፅ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡ ዶ/ር አህመድ በኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት የሙስሊሙ በዓል ብሄራዊ በዓል እንዳልነበረ፣ ፍሬ ከናፍር ዘቀዳማዊ ሀይለስላሴ ከ 1 እስከ 7 ያለው ክፍል ውስጥ ስለሙስሊም አለመገለፁና መሰል ጉዳዮች ስህተት ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ስህተቶች እንዳይደገሙ በማድረግ ኢትዮጵያ በሀይማኖት መቻቻል ምሳሌ ሆና እንድትቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በኢትዮጵያ ውስጥ የፅንፈኝነት፣ የአክራሪነት ሁኔታ እየታየ መሆኑንና በሀይማኖት መቻቻል ዙሪያ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክራሪነት በፍፁም የኢትዮጵያ ገፅታ እንዳልሆነና ከኢትዮጵያ ወግና ባል ጋር የማይጣጣም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚዳንት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ በበኩላቸው "በሌላ ሀገር መቻቻል የሚመጣው ከተቋሰሉ በኋላ ነው፤ በኢትዮጵያ ግን መቻቻል የመጣው በመቋሰል አይደለም፡፡ መቻቻል እሴት ነው አካሄድም ነው" ካሉ በኋላ መቻቻልን እንደ እሴት መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መቻቻል የሌላውን ባህል ከነአሰስ ገሰሱ መቀበል ማለት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ፕሮፌሰር እንድርያስ በመቻቻል ሰበብ የጭቆና መቻቻል ሊኖር እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የሃይማኖት እኩልነትና ነፃነትን፣ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነትን ለማስከበር የተማሪዎች ንቅናቄንና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን አስታውሰዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |