Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የአይ.ኤስ.ኦ ሰርተፊኬት የምርት...
የአይ.ኤስ.ኦ ሰርተፊኬት የምርት... Print E-mail
Sunday, 27 January 2008

Image
ዶ/ር ኢንጂነር ዳንኤል ቅጣው
የአይ.ኤስ.ኦ ሰርተፊኬት የምርት ጥራት ማረጋገጫ አይደለም

የአይ.ኤስ.ኦ ሰርተፊኬት አንድን ሥራ ደጋግሞ በተመሳሳይ መልክ ማምረት መቻልና ምርቶቹ ተመሳሳይ መሆናቸውን እንጂ የአንድን ምርት ጥራት ማረጋገጫ እንደማይሆን ተገለፀ፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች በጥራት የማምረት አቅማቸው አናሳ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ መምህር፣ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትብብር ፕሮግራም ዳይሬክተርና በኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ፀሐፊ ዶክተር ኢንጂነር ዳንኤል ቅጣው ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የአይ.ኤስ.ኦ ሰርተፊኬት አንድን ዕቃ በተመሳሳይ መልኩ ማምረትን ማረጋገጫ ነው፡፡ የአይ.ኤስ.ኦ ሰርተፊኬትን ያገኙ ምርቶች ጥራት ያላቸውም የሌላቸውም ሊሆኑ እንደሚችሉም አመልክተዋል፡፡

በአገራችን የጥራት ጽንሰ ሃሳብ፣ ነገሮችን በትክክል የመስራትና ደንበኛን የማክበር ባህላችን በአነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት ዶ/ር ዳንኤል የግልና የመንግስት አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የተወዳዳሪነት አቅም እንዲገነቡም ሆነ እንዲያድጉ በጥራት ማምረት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች በማደግ ላይ ያሉ በመሆናቸው ይህን አቅም መያዛቸው እያደገ በመጣው ገበያ ውስጥ እንዲካተቱና በራሳቸው እንዲቆሙ እንደሚያደርግም፣ ጥራት ማለት ደንበኛን ማስደሰት ብክነትን መቀነስና አንድን ነገር በትክክል በተደጋጋሚ መስራት መሆኑን፣ ገበያው ምን ይፈልጋል?፣ ሸማቹ ማነው? የተሻለን እቃ በአነስተኛ ዋጋ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ መሠረታዊ ስልጠና አስፈላጊ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ዶክተር ዳንኤል እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ሽልማት በምርትና አገልግሎት ፈር ቀዳጅና ምሳሌ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን ለማበረታታት ሲረዳ የጥራት አቅማቸውን ለማሻሻል፣ ደንበኛን ከሚጠበቀው በላይ እንዲያስደስቱ ብቃታቸውን ለማሳደግና እርስ በርስ በመተጋገዝ የተሳኩ ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡ ያግዛል፡፡

ድርጅቱን የመሰረቱት የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በበጀት የሚተዳደሩ መሆናቸው ሽልማቱን እንዴት ቀጣይ ማድረግ እንደሚቻል ለተጠየቁት ሲመልሱ ዋልታና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በበጀት ቢተዳደሩም ያላቸውን በጀት ፈሰስ አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንና የሽልማት ውድድሩ ሲጀመር ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎች ለመወዳደር የመመዝገቢያ ክፍያ እንደሚከፍሉም ገልፀዋል፡፡

በሽልማቱ አገር ውስጥ ያሉ በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የንግድ ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ማኑፋክቸሪንግና ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አትራፊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች በጥራት የማምረት አቅማቸውን በማየት ሽልማት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

በድርጅቱ በቦርድ የሚመራ ሲሆን ዳኞች፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስና ልዩ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴዎች እንዳሉ ያመለከቱት ዶ/ር ዳንኤል ሁሉም ኮሚቴ በወጣለት መመሪያና ሕግ እንደሚሰራና የቴክኒክ ኮሚቴው በልዩ ልዩ ሙያዎች ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎችን ያቀፈ እንደሆነ ተናገረዋል፡፡ የሽልማት ሂደቱ በየዓመቱ ሲሆን የዚህ ዓመት የጥራት ተሸላሚዎች እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

በሽልማት ሂደቱ በመጀመሪያ ዙር የራስ ምዘና ጥያቄ በባለ ድርጅቶች እንደሚሞላ በዚህ አጥጋቢ ውጤት ያገኙ ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ፣ በሁለተኛ ዙር የቴክኒክ ኮሚቴዎች በየድርጅቱ በመገኘት ሙያዊ ጉብኝትና ግምገማ አድርገው የሚያመጡት ውጤት በጋራ ታይቶ ለዳኞች በማቅረብ ከማጣራትና ማረጋገጥ ሂደት በኋላ በቦርድ ፀድቆ ተሸላሚ እንደሚሆኑም ገልፀዋል፡፡

በአገራችን ጥራት ያላቸው ምርቶችም ሆኑ አገልግሎት ዋጋ የሸማቹን ፍላጎት፣ የመግዛት አቅምና የሚገለገሉበትን አካባቢ መሰረት ያደረገ እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡

በአገራችን ኢንዱስትሪዎች የሚዘጉበትና ከገበያ የሚወጡበት ሂደት በአብዛኛው የማምረቻም ሆነ ልዩ ልዩ ወጪያቸው ከገቢው ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ፣ የሠራተኞች ምርታማነት አናሳ መሆንና አላስፈላጊ ወጪ ብዙ መሆንን በምክንያትነት ገልፀዋል፡፡
 
በጥራት በማምረት ሂደት የአመለካከትና የቴክኒክ ችግር እንዳለ ገልፀው ባለን አቅም ምን መስራት እንችላለን የሚለውን ማወቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በአብዛኛው ኢንዱስትሪዎች በጥራት ለማምረት ማሽኖችን ከማስመጣት ጎን ለጎን የማስተዳደር፣ የመጠገን፣ የድርጅት አስተዳደር አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ውድደር ላይ በመሆናቸው የድጋፍ አቅጣጫ በመስጠት ብዙ መስራት አስፈላጊ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲ በኩል መስራት የሚገባውን ያህል በውህደት እንዳልተሰራ፣ የኢንዱስትሪዎች የምርምርና የልማት አቅማቸው አናሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ካሉ ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ ለመስራት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ክፍል በመክፈት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በቤዛዊት ስዩም

 
< Prev   Next >