| "በመስኖ ላይ የተመሠረተ ግብርናን... |
|
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
|
ዶክተር አበራ ደሬሣ፣ የተወለዱት በቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሀገር በበጁጨርቆሳ ወረዳ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሙቅለሚ ትምህርት ቤት፣ የመለስተኛ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታውን በበጂድርመጂ፣ በጊምቢና በነቀምቴ አጠናቅቀዋል፡፡ በአምቦ እርሻ ኮሌጅ ገብተው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በቀድሞው ሶቪየት ሕብረት (ሩስያ) በአግሪካልቸር የማስተርስና የፒ.ኤች.ዲ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሥራ ዓለም የነጆ ግብርና ምርምር ጣቢያ ኃላፊና በባኮ እርሻ ምርምር የተመራማሪዎች ቴክኒካል ረዳት ሆነው ሰርተዋል፡፡ በመልካሳ ግብርና ምርምርም በተለያዩ ዲፓርትመንት በኃላፊነትና በምርምር ጣቢያው በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራልነት አገልግለዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ወንዶች ልጆች አባት የሆኑት ዶክተር አበራ ደሬሳን የግብርናውን ዘርፍ እንቅስቃሴ በሚመለከት ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ለግብርና ልማት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ፣ ምርትና ምርታማትን ሊያግዙ በሚችሉ ሀብቶቻችን በአግባቡ ተጠቅመናል? ዶ/ር አበራ፡- የሀገራችን የኢኮኖሚ መሰረቱ ግብርና ነው፡፡ ሀገሪቱ ለእርሻና ለእንስሳት እርባታ የሚሆን በቂ መሬት አላት፡፡ አንዱ ትልቁ ሀብቷ መሬት ነው፡፡ ይህም በተለያየ ስነ ምህዳር በደጋ፣ በወይና ደጋና በቆላማ አካባቢ የሚገኝ መሬት ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ወደ 32 የሚጠጉ ዋና ዋና ስነምህዳር (አግሮ ኢኮሎጂካል ዞን) አሉ፡፡ በእያንዳንዱ ስነምህዳር የተለያዩ አይነት ሰብሎችን፣ ደንና የእንስሳት አይነቶችን ማልማት እንደሚቻል ነው፡፡ ሁለተኛው የሀገሪቱ ትልቁ ሀብቷ የሰው ኃይል ነው፡፡ የሰው ኃይሉም በአብዛኛው በገጠር የሚኖርና በግብርና ዘርፍ የተሰማራ ነው፡፡ ከብሄራዊ የስታስቲክስ ኤጄንሲ ከተገኘው መረጃ ለመረዳት እንደተቻለው 85 ከመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ የሚኖረው በገጠርና በግብርና ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሰው ኃይል የተማረና በቂ ዕውቀት አለው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ባህላዊ ግብርናን ለዓመታት ሲሰራ የነበረ ሃይል ነው፡፡ ይህን የሰው ኃይል አቅም በመገንባት መሬትና የሰው ኃይልን በአንድ ላይ በማቀናጀት የግብርናን ምርት በበለጠ ለማሳደግ እንደሚቻል ነው፡፡ ውሀም አንዱ ሀብታችን ቢሆንም በአቅም ውስንነት ሳቢያ ግብርናው በዝናብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በመስኖ ላይ የተመሰረተ ግብርናን እውን ለማድረግ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲው፣ ስትራቴጂውና አቅጣጫው አለ፡፡ የተለያየ ዓይነት ስነምህዳር መኖርም በአንድ በኩል ሀብት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ችግር ነው፡፡ እንደ ሀብትነቱ እስካሁን የታወቁት ዋና ዋና ስነምህዳሮች የተለያየ የአየር ጠባይና የአፈር አይነት የያዙ ናቸው፡፡ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ አልተጠቀምንባቸውም፡፡ በዚህ በኩል ብዙ ይቀረናል፡፡ በሂደት ግን በአግባቡ መጠቀማችን አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህን ሀብቶች ለመጠቀም የተማረየሰለጠነ የሰው ኃይል ካፒታል ይጠይቃል፡፡ ሌላው እንደመልካም አጋጣሚ አድርገን የምናየው ለግብርና ልማት የተመቻቸና ሊያሰራ የሚችል ፖሊሲ መኖሩን ነው፡፡ የገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቷል፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው በትክክል ሥራ ላይ በመዋላቸው የዕድገት ፍንጭ ታይቷል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ ውለዋል ለማለት ግን አይቻልም፡፡ ሪፖርተር፡- በልማት ሥራ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ቀርቶ በባለሀብት ብቻ ቢካሄድ ምን ችግር ያመጣል? ዶ/ር አበራ፡- በግብርና ልማት ሥራ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል 85 ከመቶ ያህሉ በገጠርና በግብርና ላይ የሚኖር ባለባት አገር ውስጥ መንግሥት እጁን ከልማት አውጥቶ ባለሀብት ብቻ እንዲያንቀሳቅሰው ማድረጉ አያዋጣም፡፡ ባለሀብት ማለት ከትርፍ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያከናውን ማለት ነው፡፡ ካላተረፈ በምንም ዓይነት መንገድ ልማት ውስጥ አይገባም፡፡ ከዚህም ሌላ ባለሀብቱን ሊያሳትፍ የሚያስችል ኢንፍራስትራክቸር የለም፡፡ መንግሥት ግን ለዜጎች ስለሚጨነቅ ባያተርፍም የግድ እየከሰረ መስራት ይኖርበታል፡፡ በዚህም መሰረት መንግሥት 25 የግብርና ኮሌጆች አቋቁሟል፡፡ የኮሎጆቹ ወጣቶችም በግብርና፣ በእንስሳት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በገበያና በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ሰልጥነው በእያንዳንዱ ገበሬ ማህበር አጠገብ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ ገበሬውም ከእነሱ የቴክኖሎጂ፣ የማዳበሪያና የገበያ መረጃዎችን ያገኛል፡፡ ምን እንደሚያመርትና ገበያው ምን እንደሚፈልግ ገበሬው እያወቀ መጥቷል፡፡ የትኛው አይነት ጤፍ ነው ገበያው የሚፈለገው የሚለውን እያወቀ ያለበት ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም ትልቁና ዋናው ሥራ ገበሬው ገበያው የሚፈልገውን አይነት ምርት ማምረቱና ያመረተውንም በፈለገው ዋጋ መሸጥ መቻሉ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በዚህ አይነት የምርት ሂደት አምራች ያልሆነውና የከተማው ነዋሪ እየተጎዳ ነው፡፡ የምርት ዋጋ በጨመረ ቁጥር የመግዛት አቅሙ እያነሰ ይሄዳል፤ ዶ/ር አበራ፡- ሰማንያ አምስት ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ ካደገና ምርታማ ከሆነ የሚያገኘውን ገቢ ሁሉ የት ላይ ነው የሚያውለው የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ በዚህ በኩል ከታየ አምራቹ ገበሬ እህሉን ሸጦ የሚያገኘውን ገንዘብ የሚያወጣው ከተማ ላይ ነው፡፡ ልዩ ልዩ አልባሳትንና ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከተማ መጥቶ ይገዛል፡፡ ስለዚህ የገንዘብ ጠቀሜታን የሚያውቀው ከተማ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የገጠሩ ሕዝብ አደገ ማለት የከተማው ሕዝብና በአጠቃላይም የአገር ኢኮኖሚው አደገ ማለት ነው፡፡ ከገጠር የመጣውን ምርት ገዝቶ ፕሮሰስ አድርጎ መልሶ የሚሸጠውም ከተማ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ አሁን በየቦታው የሚታዩት ልዩ ልዩ አይነት ብስኩቶች፣ ዳቦ፣ ፖስታና ሞኮሮኒ ከስንዴ የተገኘ ነው፡፡ ተቆልተው የሚሸጡ የተለያዩ ምግቦች ምርታቸው የተገኘው ከገጠሩ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሂደት እያደገ በሄደ ቁጥር ግብርናና ኢንዱስትሪ ግንኙነት እየፈጠሩ ይሄዳሉ ማለት ነው፡፡ አንዱም የዕድገት መንገድ ይኸው ነው፡፡ ለዚህ ነው ግብርና መር ኢንዱስትሪያሌዜሽን ስትራቴጂ ቀይሰን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ግብርና ከኋላ ቀር አሰራር አላቅቆ በገበያ የሚመራ ዘመናዊ አካሄድን እንዲከተል ያስፈልጋል፡፡ ሪፖርተር፡- መንግሥት ግብርናን በዋንኝነት ትልቅ የሥራ ዘርፍ አድርጎ ወስዷል፡፡ ውጤቱ ግን አበረታች ነው ማለት ይቻላል? ዶ/ር አበራ፡- አንዱና ትልቁ ጉዳይ 85 ከመቶ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ነው፡፡ አንድ አገር ያመረተውን ለምግብ ብቻ ካዋለ ዕድገት አይመጣም፡፡ በስተመጨረሻም ወደ ውድቀት ይወርዳል፡፡ አምርቶ መብላትና አትርፎም ለውጭ ገበያ መሸጥ ይኖርበታል፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪ የሚመጣው ከግብርና ዘርፍ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ግብርናው በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አጠቃላይ የአገሪቷ ገቢ (ጂዲፒ) ወደ 50 ከመቶው ከግብርና ነው፡፡ ያለግብርና የአገር ሕልውናም ሊኖር አይችልም፡፡ በግብርና እየተመራን ወደ ኢንዱስትሪ እንሸጋገራለን የሚለውን ስትራቴጂ ያስቀመጥነው ለዚህ ነው፡፡ መንግሥትም ትኩረቱን በዚሁ ዘርፍ ላይ ያጠናከረው ወሳኝ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የልማት አቅጣጫ ምን ውጤት አስገኘ ተብሎ ነው የሚጠበቀው? ዘመናዊ ግብርና ሲባልስ ምን ማለት ነው? ዶ/ር አበራ፡- ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የልማት አቅጣጫ አንደኛ ፈጣን ዕድገትን ያመጣል፡፡ ነፃ ገበያን ያዳብራል፤ ከድህነት ያላቅቃል፡፡ ሕዝቡም ከዚህ አይነቱ ልማት የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ሲዳብርም ከቀረው ዓለም ጋር ግንኙነት ይፈጠራል፡፡ በዚህም ምርትና ምርታማነት ያድጋል፡፡ የውጭ ምንዛሬም ከፍ ይላል፣ ኢንዱስትሪዎቻችንም ይጠናከራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በሚገባ ከተከናወኑ ሌሎች አገሮች የደረሱበት የዕድገት ደረጃ በቶሎ ለመድረስ አንችላለን፡፡ ዘመናዊ ግብርና በቴክኖሎጂ፣ በምክርና በኢኪስቴንሺን የታገዘ፣ ገበያው የሚፈልገውን ምርት በወቅቱና በጊዜው የሚያመርት፣ ምክር በወቅቱ የሚያገኝ አቅሙ የተገነባ ገበሬ ማፍራት የሚችል የተለያዩ አይነት ሰብሎችን የሚያመርትና ይህም በተቀናጀ መልኩ እንዲከናወን የሚያደርግ ማለት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የግብይት ሥርዓትን መዘርጋት ወይም ማስፋፋት ነው፡፡ ለዚህም እውን መሆን የተመረተው ምርት የትና መቼ ይሸጣል? በሚል እስከ ማዳረሻ ገበያ ድረስ የሚጠቁም መረጃን ማግኘትን ያካትታል ዘመናዊ እርሻ፡፡ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ የመያዝ፣ የመጠቀምና የማልማት ሥራ ማከናወን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን የዘመናዊ ግብርና አካል ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ዱሮ ምርምር የሚባል ሳይኖር የምርት መትረፍረፍ ነበር፡፡ አሁን ግን ምርምር መጣ ቴክኖሎጂና ማዳበሪያ ከውጭ ገባ፡፡ ዋጋ ግን እየጨመረ ሄደ፡፡ ይህ ከሆነ ምርምር ማካሄድ ለምን አስፈለገ? ዶ/ር አበራ፡- የተቀመጠው ስትራቴጂ፣ ተልዕኮና ራዕይ ግቡን እንዲመታ ለማድረግ የምርምር ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ ያለምርምር ውጤት ምርትና ምርታማነት ሊያድግ አይችልም፡፡ ላለፉት ሺህ ዓመታት የኖርንበት የግብርና ሥርዓታችን የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ የዛሬ 50 እና 60 ዓመት አካባቢ አንድ ኩንታል ጤፍ 12 ብር ነበር፡፡ ፍየል አራትና ግፋ ቢል አምስት ብር ነበር፡፡ የዛን ጊዜ የነበረው የሕዝቡ ብዛትና ፍላጎትም በጣም ትንሽ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የአሁኑ አይነት ገበያ ተስፋፍቶ ሕዝቡም ትምህርት አግኝቶ ፍላጎቱን መለየት አልቻለም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ችሏል፡፡ ዛሬ ጥሩ ምግብ (ኒውትሪሺናል ኢምፖርታንት) መብላት ይፈልጋል፡፡ ልጆቹን ማስተማር፣ ጫማ መርጦ መግዛትና ማሰራት ይፈልጋል፡፡ የሕዝቡ ቁጥር አድጓል፡፡ ፍላጎቱም አድጓል፣ ዕድገትና ሥልጣኔ መጥቷል ምርት ጨምሯል፡፡ በዚያው መጠንም ዋጋ ንሯል፡፡ እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት ምርትን በበለጠ ማሳደግ ግድ ሆኗል፡፡ ለዚህም እውን መሆን የምርምር ውጤትን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ሪፖርተር፡- ፈጣን ዕድገት ያስፈለገበት ምክንያት ለምንድነው? ዶ/ር አበራ፡- ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ያስፈለገበት ምክንያት ድህነቱ እየፈጠነ በመምጣቱ ነው፡፡ በአንጻሩም የአገር ኢኮኖሚ በጣም እያደገ ሄዷል፡፡ ከዚህ አኳያ ቀስ ያለና አዝጋሚ የሆነ ዕድገት አያዋጣም፡፡ ምክንያቱም የበለጠውን እንሞታለን፡፡ መሮጥ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ውድድር ውስጥ ገብተናል፡፡ ሁሉም አንዱን ጥሎ የሚያልፍበት ጊዜ ነው አሁን፡፡ የተጣለው ደግሞ እዛው ይቀራል፡፡ ፈጣን ዕድገትን ለማስመዝገብ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ ጥራትን መሰረት ያደረገ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ በጥራትም፣ በምርምርም ከተወደቀ ችግር ይኖራል፡፡ በምርምር ውጤት ተጠቅመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያ ውስጥ መግባት ይገባናል፡፡ ዕድገት አስመዝግቧል የተባለው አብዛኛው የምርት የተገኘው ወይም የወጣው ከምርመር ነው፡፡ ስለሆነም የፌዴራልና የክልል ምርምር ሥርዓታችንን አጣምረን በየክልሉ አኮሎጂካ ዞን ወይም በየስነምህዳሩ የምርምር ሥራን አቋቁመን፣ የተቋቋመውንም አጠናክረን ገበሬውን ከችግር የሚያወጣ የአምራቹን፣ የሸማቹንና የኤክስፐርተሩንም ፍላጎት የሚመልስ ችግር ፍቺ ምርምር መካሄድ ይኖርበታል፡፡ ሪፖርተር፡- ለግብርና ወሳኝ ግብዓቶች ምንድናቸው? ዶ/ር አበራ፡- ለግብርና ግብዓቶች ወሳኝ የሆኑት ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ፀረ አረምና ፀረ በሽታ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ የትም ዓለም ከድህነት የወጡት ማዳበሪያን በብዛት ተጠቅመው ነው፡፡ ምርጥ ዘርና ሌሎች አሰራሮችን አቀናጅቶ ከተሰራ ምርትና ምርታማት ያድጋል፡፡ በሳይንስም የተደረሰበት ነው፡፡ ማዳበሪያ አጠቃቀማችን በጣም የሚያበረታታ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 358 ሺህ ሜትሪክ ቶን ወይም 3.5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተጠቅመናል፡፡ በ1982 ደግሞ ከ50ሺህ ሜትሪክ ቶን በታች ነበር የማዳበሪያ አጠቃቀማችን፡፡ ይህም ማለት በስድስት ዓመታት ውስጥ ከ358 ከመቶ ጭማሪ አምጥቷል፡፡ ይህም የሚያሳየው የግብዓት አጠቃቀማችን እያደገ፣ የምርምር ሥርዓታችንና የብዙሐ ሕይወት አያያዛችን እየተሻሻለ መሄዱን ነው፡፡ ከበሽታና ከተባይ ነፃ የሆነና ለተፈለገው ዓላማ የሚውል ዝርያ ለምርት ዕድገት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በ1982 የምርጥ ዘር አጠቃቀማችን 100ሺህ ኩንታል አካባቢ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ደግሞ ከ253 ሺህ ኩንታል በላይ ተጠቅመናል፡፡ ይህም 250 ከመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህም የምርጥ ዘር አጠቃቀማችን መሻሻሉን፣ የገበሬው የተሻሻለ ዝርያ መጠቀምን መፈለጉን ያመለክታል፡፡ ሪፖርተር፡- የኤክስፖርት አቅማችንስ በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ዶ/ር አበራ፡- ኤክስፖርት የማያደርግ አገር ዕድገት ብሎ ማሰብ የለበትም፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ ነው ያለችው የሚለውን ለመመለስ የአምስት ዓመቱን የውጭ ገበያን ስታትስቲክስ እንደሚያስረዳው ኤክስፖርቶቻችን በጣም አድገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2002 ከግብርናው ዘርፍ ብቻ 274 ሚሊዮን ዶላር (የውጭ ምንዛሬ) ተገኝቷል፡፡ ይህም በጉምሩክ በኩል ተመዝግቦ የሚታወቅ ነው፡፡ በ2006 ደግሞ ከዚሁ ዘርፍ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም 258 ከመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ሪፖርተር፡- ይህን ያህል ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የተቻለው እንዴት ነው? ዶ/ር አበራ፡- መንግሥት ልዩ ትኩረት ስለሰጠው ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመራ ብሄራዊ ኮሚቴ አለ፤፤ ኮሚቴወ ሁልጊዜ በየወሩ ይሰበሰባል፡፡ ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ብሄራዊ ባንክ፣ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ሌሎችም በአባልነት የተሳተፉበት በወር አንድ ሙሉ ቀን የኤክስፖርት ዕቅድ ክንውን ይገመገማል፡፡ ስብሰባው እስከዛሬ ድረስ አንድም ቀን አልተስተጓጎለም፡፡ ለዚህ ነው ይህ ዕድገት የመጣው፡፡ ሪፖርተር፡- የተመዘገበውን ዕድገት ቀጣይ ለማድረግ መንግሥት ወይም የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ምን ማድረግ አለበት? ዶ/ር አበራ፡- እስካሁን የተገኙ ልምዶችን ቀመር መያዝ፡፡ ለየክልል ገበሬዎች የፓናል ውይይት በማዘጋጀት ልምዶቻቸውን እንዲለዋወጡ ማድረግ፡፡ ለምርት ዕድገት ዋና ዋና የሆኑ ማነቆዎችን መለየት፡፡ የኮትቻ አፈር አጠቃቀምን ማሻሻል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ መሰረት ከ12 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ኮትቻ አፈር በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ነው፡፡ የኮትቻ አፈር በአብዛኛው ጥሩ ዝናብና አየር ባለበት በደጋና በወይና ደጋ ነው የሚገኘው፡፡ በቂ ውሃ የመቋጠር አቅም አለው፡፡ ዘር በሚዘራበት ጊዜ እህሉ ይቀጭጭና እዛው ይሞታል፡፡ ምክንያቱም የተጠራቀመው ውሃ ከአቅሙ በላይ ነው፡፡ ሊያድግ አይችልም፡፡ ትልቅ የምርት ቅነሳን ያመጣል፡፡ ውሃውን በአግባቡ በማውጣት ለሰብል ብቻ እንዲኖር ከተደረገ ምርትን በሦስት እጅ ማሳደግ ይቻላል፡፡ ይህም በቱሉ ቦሎ ወረዳ ታይቷል፡፡ በአንድ ሔክታር ስምንት ኩንታል ምርት ያገኝ የነበረ ገበሬ ውሃውን በአግባቡ አውጥቶ ለሰብል ብቻ እንዲቀር አድርጎና ወቅቱን ጠብቆ በመዝራቱ 36 ኩንታል ለማግኘት ችሏል፡፡ ውሃውን ቀዶ የሚያወጣና በምርምር የተገኘ ቢፒኤም የሚባል ቴክኖሎጂ አለ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ከ12 ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ያህሉን ሥራ ላይ ከተዋለ አሁን የተገኘው ምርት እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ችግር የአሲድማ አፈር (የአፈር ኮምጣጣነት) ችግር ነው፡፡ በተለይ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ (ጊምቢ፣ ነዲ፣ ነጆ) እንዲሁም ምዕራብ ጎጃም አካባቢ በጣም አሲዳማ አፈር ነው፡፡ አሲዳማ አፈር ደግሞ ምርትን በሁለት እጅ ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን በአሲዳማ አፈር ላይ ኖራ (ላይም) ከተጨመረ አፈር ውስጥ ያለውን አሲድ መቀነስ ይቻላል፡፡ በዚህም ምርትና ምርታማነት ያድጋል፡፡ ኖራን የሚፈጭ (ክራሽ) ማሺን እያስገባን ነው፡፡ ይኸው ማሽን በዋና ዋና አካባቢዎች ይቆማል፡፡ ሌላው የጨዋማ አፈር ነው፡፡ በብዛት የሚያስቸግረው በመስኖ አካባቢ ነው፡፡ በውሃና በአፈር ውስጥ ያለው ጨው መስኖ በሚሰራበት ጊዜ እላዩ ላይ ይተኛል፡፡ ይህም ጨው ለምርት ዕድገት እንቅፋት ይሆናል፡፡ ይህንንም የመስኖ ሲስተሙን በአግባቡ በማስተካከል፣ በወቅቱ ኢሪጌት እንዲሆንና የሚፈለገውን ሰብል በወቅቱ እንዲዘራ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡ ለመስኖ በምንጠቅምባቸው በአዋሽና በዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች አካባቢ ያለውን የጨዋማ አፈር ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለተፈጥሮ ሀብት ምንም ዓይነት ትኩረት አልሰጠም፣ በግብርና ገጠር ልማት ሚኒስቴር በመምሪያ ደረጃ ነው የተዋቀረው የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ዶ/ር አበራ፡- ትክክል አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሀብት በሚኒስቴር ዴኤታ ደረጃ ነው የተዋቀረው፡፡ ራሱን የቻለ ሚኒስትር አለው፡፡ በዓለም ወስጥ ግሎባል ዎርሚንግ መጥቷል፡፡ የአየር ለውጥም ተከስቷል፡፡ ይህም የተከሰተበት ምክንያት አንዱ ያደጉ አገሮች ካርቦንዳይክሳይድን በብዛት ወደ አየር የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ፋብሪካዎችን በማቋቋማቸው ነው፡፡ በዚህም ታዳጊ አገሮች በጣም ተጎድተዋል፡፡ የበለፀጉ አገሮች ታዳጊ አገሮችን እንዲረዱና እንዲያግዙ መጮህ ይኖርብናል፡፡ በሀገራችንም እንደአቅማችን መጠን የተፈጥሮ ሀብታችንን መያዝና መንከባከብ ይኖርብናል፡ አፈሩ ታጥቦ እንዳይሄድ እርከን መስራትና ተክሎችን መትከል፣ የተራቆቱ አካባቢዎች ላይ ልዩ ልዩ አይነት የዛፍ ችግኞችን መትከል ነው፡፡ ለሚሌኒየሙ አንድ ቢሊዮን ያህል ችግኞች ተተክለዋል፡፡ መትከል ብቻ ሳይሆን ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ አንድ ቢሊዮን ችግኞች ከፀደቁና በየዓመቱም የችግኝ መትከል ልምድን ካዳበርን ግሎባል ዎርሚንግን መከላከል ይቻላል፡፡ የብዝሐ ሕይወት ሀብታችንም ታጥቦ ወይም ተሰርቆ እንዳይሄድ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ የሚሰራ አካል አለ፡፡ ሪፖርተር፡- በልማት ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል ተብለው የተሸለሙት ገበሬዎች በምን መስፈርት ተመዝነው ነው? ዶ/ር አበራ፡- ሁሉም በየአካባቢው በሰራው ነው የተሸለመው፡፡ ከግብርና ያገኘው ጠቅላላ ገቢው ምንድነው የሚለውም ታይቷል፡፡ የምርጫ መስፈርትም አለ፡፡ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞንና በከልል ደረጃ የሚሸለሙ ገበሬዎችን የሚለዩ አካላት አሉ፡፡ ምንሰርተው ተሸለሙ ለሚለው ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል አቶ ወልደጊዮርጊስ ገዳ የተባሉ አርሶ አደር የእርሻ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም የተቀናጁ ሥራዎችን በማከናወን ስምንት ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበዋል፡፡ እኒህ አርሶ አደር ተሸልመዋል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ 3.5 ሚሊዮን ብር፣ 2.7 ሚሊዮን ብር ካፒታል እያለ እስከ 100ሺህ ብር ያላቸው ተመዝግበው ተይዘዋል፡፡ ካፒታሉም የሚታወቀው የቀንድና የጋማ ከብቱ፣ ዶሮ፣ ጎተራ ውስጥ ያለው ምርት ወዘተ ተተምኖ ነው፡፡ ሽልማቱም ገበሬው ከዚህ የበለጠ ተግቶ እንዲሰራ፣ ሌሎችም የእሱን አርአያ ተከትለው እንዲያድጉ የሚያደርግ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በተበጣጠሰ ወይም የበሬ ግንባር በምታህል መሬት እየታረሰ ምርትና ምርታማነት እንዴት ሊያድግ ይችላል? ዶ/ር አበራ፡- የሀገሪቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ በዚህ አይነቱ ምርት ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በቻይና አንድ ገበሬ በአብዛኛው ያለው የእርሻ መሬት ነጥብ ሁለት ሄክታር ነው፡፡ በዚህ አምርቶ ነው የቻይናን ሕዝብ ቀልቦ የሚያኖረው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የቻይና ሕዝብ የምግብ ችግር የለበትም፡፡ ሰፋፊ እርሻም የለም፡፡ ታይዋንና ኮሪያም የጀመሩት የመሬት መጠን ከዚህ ያነሰ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ በአብዛኛው ያለው የእርሻ መሬት ከነጥብ አምስት ሄክታር በላይ ነው፡፡ በዚህ አይነቱ መሬት ላይ በአግባቡ ምርትና ምርታማነቱ ከጨመረ በተለይ ገበያ ተኮር ሥራ ከተከናወነ ከፍተኛ ጠቄሜታ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬ ቢያመርት ከዚህ የሚያገኘው ገቢ ለራሱና ለቤተሰቡ ተርፎ ለሌላው ይበቃል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |