| ቤተ-እስራኤላዊ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን... |
|
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
|
ቤተ-እስራኤላዊ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን የእስራኤል አካል አድርገው አይቆጥሩም አብዛኞቹ በድህነት ውስጥ ይኖራሉ ወደ እስራኤል ከገቡ ቤተ እስራኤላዊ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ ከእስራኤል ማኀበረሰብ ለመቀላቀል እንደሚከብዳቸውና ራሳቸውን የሀገሪቱ አካል አድርገው ለመቁጠር እንደሚቸገሩ የጀሩሳሌም ፖስት ዘገባ ያስረዳል፡፡ የሀገሪቱ አንድ ተቋም በከፍተኛ ሁኔታ ለጭንቀት ተጋልጠዋል የተባሉትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለማቋቋም ከ500 ሺህ ዶላር በላይ የተመደበለት አዲስ ኘሮጀክት እያካሄደ ነው፡፡ ጆዊሽ ኤጀንሲ ፎር ኢዝራኤል (ጃፊ) የተሰኘውና በቤልሃይ ኮሌጅ የማኀበረሰብ ጭንቀት መከላከያ ማዕከል ዳይሬክተር ኘሮፌሠር ሙሊ ላሀድ የሚመራው ኘሮጀክት በሳይኮሎጂ፣ ሳይካትሪ፣ ሶሻል ወርክና ኤዱኬሽን ባለሙያዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ይኸው ኘሮጀክት በአነስተኛ መልኩ የእስራኤልና ሊባኖስ ጦርነት ወቅት በሰሜናዊው የእስራኤል ክፍል በሚገኙ ካምፖች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአካባቢው ይወድቁ ከነበሩ ሮኬቶች ጩኸት ጋር እንዲለማመዱ በማድረግ በኩል ተተግብሮ እንደነበር ዘገባው ያስረዳል፡፡ የጃፊ ሶሻል ዌልፌር ዳይሬክተር ዶ/ር ሚራ ኬይዳር "በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ያሉን ለመርዳት የሚያስችሉ ዘዴዎች በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ኘሮፌሠር ላሀድ በቡድን በሚደረግ ካውንስሊንግ ሲረዷቸው ነበር፡፡ በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት የሚሰጥና ፍርሀታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ የሚረዳ በባለሙያ የተዋቀረ የቀጥታ ስልክ አገልግሎትም ተዘጋጅቶላቸው ነበር" ይላሉ፡፡ ከዚያ ወቅት ጀምሮ ይላል ዘገባው የጃፊ ስታፍ አባላት በሙሉ በተለይ ጭንቀትን በመከላከል ሥራ ላይ የተሠማሩት እንዲሁም ከአደጋ በኋላ የሚፈጠር ችግርን ለመከላከል የሚሠሩ በሙሉ ኢትዮጵያውያኑን ለመርዳት ኘሮጀክት ሲቀርፁ ይታያል፡፡ እንደ ዘገባው ኢትዮጵያውያኑ በአብዛኛው የሚገጥሟቸው ችግሮች አዲስ ሀገር ከመግባት፣ አዲስ ቋንቋና ባህልን ከመቀላቀል ጋር የተያያዙ ሲሆኑ በአብዛኛው የችግሩ ሰለባዎች ህፃናትና ወጣቶች ናቸው፡፡ ዶ/ር ኬይዳር እንደሚሉት ቤተ እስራኤላዊ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው በማኀበረሰብ ላይ ያተኮረ የጭንቀት ማስወገጃ ዘዴዎች ላይ የሚተማመኑ ናቸው፡፡ እንደባለሙያዎቹ ገለፃ የኢትዮጵያውያኑን ጭንቀት ለማስወገድ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ህፃናትና ታዳጊዎችን በአሻንጉሊት ትርዒቶች ማስተማርና ጭንቀትን ለመቀነስና ዘና ለማለትና ተስፋ ለማሳደር የሚረዱ የአማርኛ ፊልሞችን ማሳየት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ 38 የሚደርሱ አማርኛ ተናጋሪ የማኀበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች (ሶሻል ወርከርስ) አሰልጥኖ በተለይ አዲስ የሚመጡ ስደተኞችን ጭንቀት ለመከላከል የሚያግዝ ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ በቴል-ሀይ ኮሌጅ በቅርቡ በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተደረገን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳመለከተው ከአዲስና ከቆዩ ቤተ እስራኤላዊ ኢትዮጵያውያን 71 በመቶው የእስራኤል ማኀበረሰብ አካል ለመሆን ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ 67 በመቶው ደግሞ ራሳቸውን የማኀበረሰቡ አካል አድርገው አይቆጥሩም፡፡ በተጨማሪም 65 በመቶ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ዓይነት ጭንቀት የሚያጋጥማቸው ሲሆን 46 በመቶው ደግሞ አንድ ዓይነት መገለል እንደደረሰባቸው ገልፀዋል፡፡ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ስደተኞች የማኀበራዊ አገልግሎት ለማግኘት ፋይል የከፈቱ ሲሆኑ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆኑት ከድህነት መስመር በታች ይኖራሉ፡፡ በወጣቶች ዘንድ ደግሞ እርስ በርስ ጥቃት መሰንዘር ሌላው ችግር ነው፡፡ አዲሱ ኘሮጀክት ፣ሴፍ ኤድ፣ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ባሉ ሦስት መኖሪያ ማዕከለላትና ናሃሪያ እየተባለ በሚጠራ ቦታ ባለ አንድ ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በናዝሬት፣ ቤርሳባህ እና ከፋር ሳባ አካባቢዎች ወደሚገኙ የኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ካምፖች ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳለ ዶ/ር ኬይዳርን ጠቅሶ ዘገባው አመልክቷል፡፡ በዚሁ ኘሮጀክት ኢትዮጵያውያኑ ካምፑን ለቀው ወደሚገቡበት የኢትዮጵያውያን ማኀበረሰብ ዘንድ እንደሚስፋፋ ዶ/ር ኬይዳር ዕቅድ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ መንግሥት በችግር ላይ ላሉት እነኝህ ወጣቶችና ልጆች ኘሮግራሙን ለማዳረስና አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ ጥረት እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ ዶ/ር ኬይዳር መግለፃቸን ዘገባው አመልክቷል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |