| የልማት ባንክ ለውጥ አራማጅ... |
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
|
የልማት ባንክ ለውጥ አራማጅ እንጂ ችግር ፈጣሪ አይደለም ሕገ መንግሥታችን በሰጠው መብት በመጠቀም ባለፉት ዓመታትም ሆነ አሁን በርካታ የመንግሥትና የግል ጋዜጦች ለኀብረተሰባችንም ሆነ ለውጪው ዓለም በሀገራችን እየተካሄዱ ስላሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊና እንዲሁም ስለ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴዎች ጭምር በርካታ መረጃ ለአንባቢያን በማቅረብ ጠቃሚ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ አሁንም እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በሠራተኛው ዘንድ በስፋት ከሚነበቡና ከሚዘወተሩ ጋዜጦች መካከል እንደ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ካፒታል፣ አዲስ አድማስና የመሳሰሉት የግል ጋዜጦች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በ4/05/2000 በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ የውብዳር በሚል ስም በእኔ የምለው ገጽ "ትንኝ ያጣራሉ ግመል ይውጣሉ "የባንኮች ኃላፊዎች" የበልቼው ልሙት አሠራር" በሚል ርዕስ የባንኮችን የሥራ አፈፃፀም በተለይ የብድር አገልግሎቶች አሰጣጥ አስመልክቶ መከናወን ስላለበት የተጠናከረ የቁጥጥር አስፈላጊነት ጠቃሚ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በየሳምንቱ እሁድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው የፎርቹን ጋዜጣ እ.ኤ.አ በ30/12/2007 በፊት ገፁ "ኢንቨስትጌሽን ፕሮብ ስቴት ዴቨሎፕመንት ባንክ ኤክሰኩቲቭ" እና "ጎሲፕ" በሚል ገጽ ስለ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ በስፋት ያሰፈራቸውን እጅግ የተጋነኑና የተሳሳቱ መረጃዎች ዋቢ በማድረግ በባንኩ ከግምት በላይ ከፍተኛ ብድር በቅርቡ እንደተሰጠና ኃላፊዎቹም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፌደራል ፀረ ሥነ ምግባርን ሙስና ኮሚሽን እየተመረመሩ እንደሆነ መዘገቡን የፅሁፉ አቅራቢው በማጣቀስ በምሳሌነት የተጠቀመበት መረጃ የተሳሳተ ነው፡፡ የፎርቹን ጋዜጣ የባንኩን አስተያየት ሳይጠይቅ ከአንድ ወገን አገኘሁ ያለውን የተሳሳተ መረጃ ብቻ የጆርናሊዝም ሥነ-ምግባር ከሚፈቅደው ውጭ አትሞ በማውጣት በወሰደው እርምጃና ባደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የባንኩ ኃላፊዎች፣ ሠራተኛውንና ደንበኞቹ ጭምር በዚህ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን የባንኩንም ሆነ የሀገርን የልማት ገፅታ በጎዳው አፍራሽ መልዕክቱ ቅር ተሰኝተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በህዝብ ግንኙነት አገልግሎት አማካይነት የጋራ መድረክ ተዘጋጅቶ የጋዜጣው አዘጋጆችና የባንኩ አመራር በጋራ ውይት አድርገዋል፤ ይህ አፍራሽ መልዕክት በሀገር ውስጥና በውጭ ሚዲያዎች ጭምር የተሰራጨ በመሆኑ ሊታረም ስለሚችልበት ሁኔታ ከመፍትሄ ላይ ለመድረስና ቀጣይ ሥራ ለማከናወን ከጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህም በሂደት ላይ ይገኛል፣ ውጤቱም ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ ሳይጠናቀቅ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የፃፉት ፀሐፊ ከፎርቹን ላይ ያገኙትን ብቻ በመጠቀም የሰጡት አስተያየት ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ባንኩ ስለጀመረው የመሠረታዊ አሠራር ለውጥም ሆነ ስለሚሰጠው የብድር አገልግሎት ከጋዜጠኞችም ሆነ ከሌሎች ወገኖች የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርና የሙያው መርሆዎችም ሆኑ የሀገሪቱ ሕጎች በሚፈቅዱት ሁኔታ በሀቅ ላይ ተመስርተው የሚሰሟቸውን ገንቢ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን ባንኩ ተገቢ ቦታና አክብሮት ይሰጣል፡፡ በተቃራኒው እውነትነት የሌለውና ጎጂ መልዕክቶችን በባንኩ ላይ ሲሰነዝሩ አመራሩ በዝምታ አይመለከትም፡፡ ባንኩ እንዲህ ዓይነቱን ተግባሮች በሰከነና አርቆ አስተዋይነት ባለው ሁኔታ በማየት እንካ ሰላንቲያ ሳይገጥም፡፡ እንደ ጉዳዩ አግባብነት በአስተዳደራዊ፣ በዲኘሎማሲያዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ መብቱንና ጥቅሙ፣ መልካም ገፅታውን ለማስጠበቅ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ወገኖች በቅርቡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም የራሳቸውን ድብቅ ፍላጐት ለማሳካት ሲሉ ትናንትም ሆነ ዛሬ ለሀገሪቱ የሚጠቅም አኩሪ የልማት ኘሮጀክቶችን በመላው ሀገሪቱ ክልሎች (ቀድሞ የኢትዮጵያ አካል የነበረችውን ኤርትራን ጨምሮ) ፋይናንስ ሲያደርግና ለቀጣዩ ትውልድም ጭምር የሚሆን ቅርስ እየፈጠረ የነበረውንና ያለውን ስትራቴጂክ የልማት ፋይናንስ ተቋም መልካም ገፅታ ለመጉዳትና ተቀባይነቱንም ጭምር ለማሳጣት የሚደረጉትን ማናቸውንም አፍራሽ ድርጊቶች በቸልታ አይመለከትም፡፡ በእናንተም በኩል ለፅሁፍ አቅራቢው የተጠቀሙበት መረጃ መሠረተ ቢስና የተሳሳተ መሆኑ እንዲገለፅላቸው ከአክብሮች ጋር እንጠይቃለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ መግለፅ የምንፈልገው አንድ ቁም ነገር ይህ አሁን ባንኩን እየመራ የሚገኘው የሥራ አመራር አካል፣ ባንኩ እንደ ማንኛውም የልማት ፋይናንስ ተቋምነቱ ከሌሎች የንግድ ባንኮች በተለየ ሁኔታ ቀድሞ በሥልጣን ላይ የነበሩ የሀገሪቱ መንግሥታትን የልማት ስትራቴጂዎች መሠረት በማድረግ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጭምር በገጠርም ሆነ በከተማ እየገባ የልማት ኘሮጀክቶችን ለረጅም ዘመናት ፋይናንስ ሲያደርግ ያጋጠሙትንና ተንከባለው የመጡትን ግዙፍ ችግሮችን ጭምር የወረሰና መንግሥትም በሚያደርግለት ተገቢ እገዛ እነዚህን ሊፈቱ የሚችሉ፣ ነገር ግን ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ መላው የባንኩን ሠራተኛ በማንቀሳቀስ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እየታገለ ያለ ለውጥ አራማጅ ኃይል እንጂ ችግር ፈጣሪ ለመሆን፣ ወይም ጎታች ሥራ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ያለ እንዳልሆነ ተገቢው ግንዛቤ እንዲወሰድ እንሻለን፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መልካም ተሞክሮዎችን በግብአትነት በመጠቀም የመንግሥት የልማት አቅጣጫን በመከተል ልማታዊ ባለሀብቶች በሀገር ግንባታ ላይ ተገቢውን ድርሻ ማበርከት እንዲችሉ የብድርና የምክር አገልግሎቱን በተቀላጠፈና ጥራት ባለው ሁኔታ ለመስጠት የጀመረውን የመሠረታዊ አሠራር ለውጥ ጥናት አጠናቆ ትግበራውን ከዳር ለማድረስ መላው የባንኩ ሠራተኛና የሥራ አመራር አባላቱ የጀመሩትን ጉዞ በፅናት የቀጠሉ መሆናቸውን ለእናንተም ሆነ ለመላው ኀብረተሰባችንና የልማት አጋሮቻችን እንገልፃለን፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |