Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የፖሊሲ አለመኖር ለአካል ጉዳተኞች...
የፖሊሲ አለመኖር ለአካል ጉዳተኞች... E-mail
Sunday, 27 January 2008

የፖሊሲ አለመኖር ለአካል ጉዳተኞች ተጨማሪ ችግር

በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተመቻቸ ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችላቸው ፖሊሲ እንዲወጣ አስፈላጊው ግፊት በመደረግ ላይ መሆኑን ዶክተር መንግሥቱ ለገሠ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡

ፖሊሲውም አንድ አካል ጉዳተኛ ተማሪ ምን ዓይነት ኮርስ መውሰድ እንዳለበት፣ የትኛውን የትምህርት መስክ መከታተል እንደሚገባው፣ ነጥቡ ስንት መሆን እንዳለበት፣ ሲወድቅ ምን መደረግ እንዳለበት መብቱና ግዴታው ምን መሆን እንደሚገባው ወዘተ. ማካተት እንደሚኖርበት ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት 415 የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ዶ/ር መንግሥቱ አመልክተው፣ ከእነዚህም መካከል ማየት የተሳናቸው 205፣ የመራመድና የሌላ አካል ጉዳት ያለባቸው 200፣ የመስማት ችግር ያለባቸው አሥር መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ የላቸውም፡፡ ይህም በመሆኑ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በኃይል በመጮህና ብዙ ጊዜ በማንበብ መሆኑን፣ በዚህም የተነሳ የምልክት ቋንቋ የሚችሉ ሙያተኞችን ለመቅጠር መታቀዱን ከዶክተር መንግሥቱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

"አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡና ከገቡም በኋላ የምናደርግላቸው ክትትል የተወሰነ ነው" ያሉት ዶክተር መንግሥቱ ተማሪዎቹ ከደሀ ቤተሰብና ከማደጎ ቤት የመጡ ወይም አንዳንድ ሚሽነሪዎት እየረዷቸው የኖሩ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ በዚህም ብዙ ችግሮችን ታግለው አሁን ያሉበት ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡ የትምህርት ክትትላቸው ምን ይመስላል የሚለውን ለማወቅ የሚያስችል ዳታ (ዝርዝር መረጃ) የለም፡፡ ነገር ግን በሕግ ትምህርት ቤትና በኤጂዩኬሽን ፋክልቲ የሚማሩ ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች በጣም ጐበዝና የተሻሉ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በብቸኝነት እየተቀበለ በማስተማር የብዙ ዓመታት ልምድ ቢኖረውም ፖሊሲ ግን የለውም፡፡ በዚህም የተነሳ ማዕከሉ አንድን መምህር ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንዲህ ይደረግላቸው የሚል ሀሳብ ቢያቀርብ መምህሩ ሊሰማም፣ ላይሰማም ይችላል፡፡ ፖሊሲው ቢኖር ግን  የቀረበው ሀሳብ የመብት ጥያቄ ስለሆነ መምህሩም የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን መብት የማክበር ግዴታ ስላለበት ሀሳቡ መፍትሄና ተቀባይነት ሊያገኝ ይችል ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር የፖሊሲው አለመኖር የግንኙነት ችግር ያስከትላል፡፡ አለመግባባትም ይፈጥራል፡፡

በዩኒቨርሲቲው አሮጌው ሕንፃ ውስጥ ያለው ሊፍት (አሳንሰር) በጊዜ ብዛት በማርጀቱ የተነሳ ተበላሽቶ ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ሁለተኛና ሦስተኛ ፎቅ መውጫና መውረጃው በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) እና የአካል ድጋፍ በትር (ክራንች) ለሚጠቀሙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህንኑ ሊፍት በቅርብ ጊዜ ውስጥ አስጠግኖና አሳድሶ ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡


ከዚህም ሌላ በእያንዳንዱ ዶርሚተሪ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎቹ አገልግሎት የሚውል ሻወርና መፀዳጃ ቤት ለማሠራት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ገንዘብም ተገኝቷል፡፡ የሊፍት ማደሻውን ጨምሮ ለሻወርና ለመፀዳጃ ቤት ማሠሪያ የሚውለው ገንዘብ የተገኘው ከፊንላንድ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር፣ መቀመጫውን ለንደን ላይ ካደረገው ኢትዮጵያ ኤይድ ከተባለው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ነው፡፡

ለዕርዳታውም መገኘት የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ወይም የበላይ ኃላፊዎች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ማዕከሉ የክፍል ጥበት፣ የሰው ኃይል እጥረትና የማስተማሪያ መሣሪያ እጥረት አለበት፡፡ ይህንን ችግር አስመልክቶ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት መደረጉን፤ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) ተገቢውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጀመሪያው የሆነው ይህ ማዕከል ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች አገልግሎት የሚውሉ አራት ኮምፒውተሮች እንዳሉት፣ ወደፊት ግን የኮምፒውተሮችን ቁጥር ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳለው፣ የተጫነውን (ሎድ) ማቴሪያል ራሱ የሚያነብ ሶፍትዌር እንዳለው ይህም ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች እየተገለገሉበት እንደሆነ ዶክተር መንግሥቱ ተናግረዋል፡፡

መጽሐፍም ሆነ ሌላ የታተመ ወረቀት ወደ ብሬል የሚቀየር፣ እንዲሁም የታተመውን ወረቀት ስካን በማድረግ ጽሑፉን ወደ ድምፅ የሚቀይር መሳሪያዎች አሉት፡፡ ወደ ድምፅ የተቀየረውንም ወደ ሲዲ በመለወጥ ማየት ለተሳናቸው ተማሪዎች ይሰጣል፡፡

ዶክተር መንግሥቱ እንዳመለከቱት ማዕከሉ የጋይዳይንስ ካውንስሊንግ ሰርቪስ ይሰጣል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በየጊዜው እየመጡ "ከቁሳቁስ ወይም ከገንዘብ ዕርዳታ ይልቅ የትኛውን ትምህርት እናጥና ይህ ትምህርት ለኛ አይስማማንም" በማለት ይጠይቃሉ፡፡ አንድ አካል ጉዳተኛ ተማሪ ሦስተኛ ዓመት የእንግሊዝኛ ሜጀር ነበር፡፡ በኋላ "ስፖክን እንግሊሽ" ውሰድ ተባለ፡፡ ይህ ልጅ ለካ የመስማት ችግር አለበት፡፡ "እምችለው አይደለም" በሚል "ወደ ሌላ ዲፓርትመንት ልቀየር የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡"

በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው ሳይወጡ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ መሥሪያ ቤቶችን፣ ፋብሪካዎትንና ተቋማትን እየተዘዋወሩ ቢጐበኙና በየቢሮው በየሥራ ቦታ ያሉት አካል ጉዳተኞችን ቢያነጋግሩ ሞራላቸው ከፍ ይላል፡፡ የወደፊት ተብፋቸውም ይለመልማል፡፡

በታደሰ ገብረማርያም

 
< Prev   Next >