| ለትምህርትን ትኩረቱ ያደረገ ድርጅት |
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
![]() አቶ አበራ ሞልቶት አዲስ አበባ አስተዳደርንና ድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስልን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች ለተመረጡ ለእነዚህ ተማሪዎች ስኮላርሺፑን የሰጠው በ1995፣ በ1996 እና በ1999 መሆኑን ዋናው ሥራ አስኪያጅ አመልክተዋል፡፡ በ1997 በገንዘብ እጦት ምክንያት ምንም ዓይነት ስኮላርሺፕ አለመስጠቱን፣ በ1998 ገንዘቡ ቢገኝም አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽንን የማስፈቀድና ትምህርት ሚኒስቴርም እንዲያውቀው የማድረጉን ስራ በወቅቱ ለመጨረስ ባለመቻሉ የስኮላርሺፑ ጉዳይ መስተጓጎሉን አስረድተዋል፡፡ ተማሪዎቹ የስኮላርሺፑ ተጠቃሚ ሊሆኑ የቻሉት ድርጅቱ ያወጣቸውን መስፈርቶች በማሟላታቸው ነው፡፡ ከመስፈርቶቹም መካከል የ12ኛን ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት ያለፉ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወይም ከችግረኛ ቤተሰብ የወጡ፣ በትምህርት ቆይታቸው በልዩ ልዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴና ስፖርት ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑ ወዘተ ናቸው፡፡ ከመስፈርቶቹም መካከል 40 ከመቶ ነጥብ የሚሰጠው ለትምህርቱ ሲሆን የቀረው 60 ከመቶ ደግሞ ለተዘረዘሩት ተግባራት ይደለደላል፡፡ እነዚህን መስፈርቶች የያዘ የምርጫ መመሪያ ለትምህርት ሚኒስቴርና ለየክልሉ ትምህርት ቢሮዎች ተላልፏል፡፡ ቢሮዎቹና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በምርጫ መመሪያው መሰረት ተማሪዎቹን አወዳድረው የአሸናፊዎችን ስም ዝርዝር ለድርጅቱ ያስተላልፋሉ፡፡ የድርጅቱ የስኮላርሺፕ ኮሚቴ ደግሞ ጉዳዩን ያጣራና ለሥራ አስፈፃሚው አቅርቦ ያስወስናል፡፡ "ስኮላርሺፑ የሚሰጠው ተማሪዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እስከሚያገኙ ድረስ ነው" ያሉት አቶ አበራ፣ ድርጅቱ ይሄ አይነቱን ስኮላርሺፕ ለመስጠት የቻለው በአገር ውስጥ የሚገኙ በጎ አድራጊ ግለሰቦች እንዲሁም አቢሲኒያ ባንክ፣ ኒያላ ኢንሹራንስ አክስዮን ማህበርና ኢስት አፍሪካን ኢንቬስትመንት ኮርፖሬሽን በለገሱት የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለአንድ ተማሪ ወጪ የሚሆነው የአንድ ዓመት ስኮላርሺፕ ክፍያ 1500 ብር ነው፡፡ የመጀመሪያውን ዲግሪ ለማግኘት በአማካይ አራት ዓመት ይፈጅበታል፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገው ወጪ 6ሺህ ብር ይመደብለታል፡፡ ድርጅቱ ስኮላርሺፕ ከሰጣቸው 150 ተማሪዎች መካከል ከ80 ያላነሱ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው በተለያዩ የሥራ መስክ ተሰማርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ወጣት ከመጀመሪያው ወር ደመወዙ ላይ 50 ብር ለድርጅቱ የለገሰ ሲሆን ዕርዳታው የማይቋረጥና የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ ለማበርከትም ቃል ገብቷል፡፡ በቴክኒክ ሙያ የተመረቁትም የድርጅቱን ልዩ ልዩ ዓይነት የመገልገያ ዕቃዎች ለመጠገንና ለማሻሻል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ድርጅቱ በትምህርት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በሚመለከት ከፍተኛ ምርምር ለሚያካሂዱ ተመራማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት፣ ቤተመጻሕፍት ለማቋቋም፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያን የመርዳትና የመንከባከብ፣ እንዲሁም በመንግሥት የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የመሆን እቅዶች አሉት፡፡ ከእነዚህም እቅዶች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ትልቅ ቤተ መጻህፍት፣ እንዲሁም ቤተመጻህፍት በሌሉባቸው ትናንሽ ከተሞች አነስተኛ ቤተመጻህፍት ለማቋቋም አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል፡፡ ለእንቅስቃሴዎቹም ስኬታማነት ተመሳሳይ ሥራ ከሚያከናውኑ አንድ ሮተሪ ኢንተርናሽናል ከመሳሰሉት ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ ከዋናው ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ አዲስ አበባ ውስጥ በቦሌና በአራዳ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ በተወሰኑ ቀበሌዎች ውስጥም የተቀነባበረ የልማት ፕሮግራም ለማከናወን የሚያስችለውን የፕሪሊሚነሪ (መነሻ) ጥናት አጠናቅቆ ወደ ዝርዝር ጥናት ገብቷል፡፡ የመነሻ ጥናቱም የተካሄደው በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 16፣ 18፣ 21፣ እና 22 እንዲሁም በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15/16 ነው፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተጠቀሰው ቀበሌ የተካሄደው መነሻ ጥናት ትምህርት ቤትና ክሊኒክ በመገንባት፣ በኤች.አይ.ቪ ኤድስና በሌላም ምክንያት ወላጅ አልባ የሆኑ ሕጻናትን በመንከባከብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚሁ ቀበሌ ይህ አይነቱ ሰብዓዊ የአገልግሎት ሥራ ማከናወን ያስፈለገው ቀበሌው በቅርቡ ወደ ከተማው የተከለለ በመሆኑና ገጠር ነክነት ላላቸው ለሌሎች ከተሞችም እንደሞዴል ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ከሚል ሀሳብ በመነሳት ነው፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15/16 ውስጥ ይህንኑ የልማት ሥራ ለማከናወን ያስፈለገው ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩበት አካባቢ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የእነዚህ ወገኖች ኑሮ የሚደጎምበት፣ አቅመ ደካሞች የሚረዱበትና አረጋውያን የሚጦሩበትን መንገድ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ግድ ይላል፡፡ ይህም በከተማ መካከል ውስጥ ከድህነት ወለል በታች ለሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግላቸው እርዳታና እንክብካቤ ለሌሎች እንደመነሻ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለአፍሪካ ሕብረት ብዙ ውለታ ውለዋል፡፡ በአውሮፓም በአሜሪካም ብዙ ወዳጆች አላቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ድርጅቱ ለሚያከናውነው ሥራ የዕርዳታ እጆቻቸውን እንዲዘረጉለት የሚያሳስብ ደብዳቤ ለብዙዎቹ ተልኳል፡፡ ይሁን እንጅ ከዚህ ቀደምም ቢሆን አሁንም ከእነዚህ ወገኖች ምንም ዓይነት ዕርዳታ አላገኘም፡፡ እስካሁንም እየተንቀሳቀሰ ያለው በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ቀደም ሲል የተጠቀሱት ድርጅቶች በሚያደርጉት አስተዋፅኦ ነው፡፡ አሁን ያለው በኪራይ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ከተወረሱ ሕንፃዎች መካከል ለቢሮ ያህል የተወሰኑ ክፍሎችን በነፃ እንዲሰጠው የሚያመላክት ጥያቄ ለመንግሥት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ በታደሰ ገብረማርያም |
|
| Last Updated ( Sunday, 27 January 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |