| "በሙስና ላይ እንደ ቻይና ትንሽ እንጨክን?" |
|
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
|
(መኮንን ሻውል ወ/ጊዮርጊስ) ሀገራዊ የብልጽግና ራዕይ የሌላቸውን "የግል ልክፍተኞች" ጨከን ብለን ከልማት ጎዳናችን ላይ ካላስወገድናቸው በስተቀር የልማት እንቅፋቶች ስለሚሆኑብን በአቀድነው መሰረት ተጉዘን የብልጽግና ግብ ላይ መድረስ ያዳግተናል፡፡ ይህ የጽሑፌ አጠቃላይ ጭብጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት አጠቃላይ ሕዝብን የሚያንቀሳቅስ ተግባራዊ የልማት እንቅስቃሴ በማድረግ እ.ኤ.አ በ2020 ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍ እንዳለበት ከወዲሁ የሚያረጋግጥ ግልጽ ራዕይ ሰንቆ ለተግባራዊነቱ ..በየአቅጣጫው.. በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ መንግሥት ሕዝቦቹን አስተባብሮ እያንዳንዷ ደቂቃ እንዳትባክን ከጊዜ ጋር መሽቀዳደም በጀመረበት በዚህ "የሕዳሴ ወቅት" ከዜጎች መካከል አንዳንድ "የግል ጥቅም ልክፍተኞች" ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅመው የልማት ገንዘቡን፣ የሚመነትፉ ከሆነ እድገታችን በእጅጉ አዝጋሚ ወይም የካሮት እድገት እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ዛሬ ላይ ሆኜ ስለነገው ሀገራዊ የብልፅግና ራዕይ ሳስብ፣ ለዚች አገር ፈጣን እድገት እውን መሆን ምናልባት እንደቻይና ሕዝባዊት ሪፐብሊክ መንግሥት ዐይነት ፀረ ሙስና እንቅስቃሴ እና ተመሳሳይ ፀረ ሙስና ፖሊሲ ያስፈልገናል የሚል ድምዳሜ ላይ እደርሳለሁ፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ እንደቻይና ዓይነት ጠንካራ የፀረ ሙስና ትግል፣ የፀረ ሙስና ፖሊሲ፣ የፀረ ሙስና ሕግ ያስፈልገን እንደሆን በጥልቀት ማሰብ የምንጀምርበት የፈተና ወቅት ላይ እንደደረስን አንዳንድ ሁኔታዎች ያሳብቃሉ፡፡ የህዝብ አስተያየቶችም ይመሰክራሉ፡፡ ከሕዝብ አስተያየት በመነሳት፣ ቀን ከለሊት ያለ እረፍት እዚያና እዚህ የሚሸረቡትን፣ በድብቅና በስውርም የሚፈፀሙትን ሙስናዎች ለማክሸፍ እና በራዕያችን መሰረት በአቀድነው ጊዜ ሀገራችንን የበለፀገች ለማድረግ ከፈለግን ከቻይና ሕዝብ የሥራ ባህል እና ከቻይና መንግሥት የፀረ ሙስና ተመክሮ የምንወስደው ትምህርት መኖሩ አያጠያይቅም፡፡ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች በተለይም የሀገርን ብልፅግና የሚናፍቁ ሰርቶ አደሮች እና ገበሬዎች እንዲሁም በጥቃቅን የጎጆ ኢንዱስትሪና የዕለት ጉርስ የማግኛ ሥራ ላይ የተሰማሩ ምንዱባኖች በዚች አገር ሥር ነቀል የፀረ ሙስና አብዮት እንዲካሄድ እና የብልፅግናችን እንቅፋቶች ከመንገዳችን ላይ እንዲወገዱ በብርቱ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የቻይናን ተመክሮ ተግባራዊ ለማድረግ አያሌ ሳንካዎች ከፊታችን ተደንቅረውብናል፡፡ ከነዚህ አያሌ ሳንካዎች መካከልም የዕውቀት (የልምድና የአመራር) የባህል ችግሮች፣ በዋነኝነት የሚጠቀሱ የፀረ ሙስና ደንቃራዎች ሆነው እንደፀሀፊው አስተውሎት፡፡ እነዚህን የፀረ - ሙስና ደንቃራዎች በጥቂቱ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ 1ኛ የዕውቀት ችግር እውቀት በእጅጉ ከትምህርት ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ መጠንም (የተግባርና የቀለም ትምህርት መኖሩ ሳይዘነጋ) ያለእውቀት በቂ ትምህርት ለማግኘት እንደማይቻል ይታወቃል፡፡ ትምህርትን ለመማር የተሟላ አእምሮ (ጤነኛ አእምሮ) ብዙ ልምምድ እና ያላሰለሰ "የህሊና ኩረጃ" ማድረግ መቻልን ይጠይቃል፡፡ የህሊና ኩረጃ ስል ከሊቅ እና ከፈላስፋ በቀር፣ ሌላው ምሁር እና ባለካባ የሌላውን ህሊና ኮርጆ ምሁር እንደተባለ እና ካባውን እንደለበሰ ለመግለፅ ነው፡፡ አስተማሪ አስተማሪ የሆነው መጀመሪያ አስተማሪ አስተዋይነት የማስተማር ክህሎትን አስኮርጆ ነው፡፡ ከቀለምም ሆነ ከተግባር ትምህርት አንፃር ስንመለከተው አንድ ሰው ትምህርት ለመማር ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የቀለምና የተግባር ትምህርቶች መስፋፋት የመላ ዜጎችን የእውቀት አድማስ ስለሚያሰፋ ዜጎች ከሀገርና ከአህጉር አልፈው አለም አቀፋዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው በማገዝ ሁሉንም እንደወረደ የሚያቀብሉ እና "እንዴት? ለምን? መቼና የት?" ብለው የሚጠይቁ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፡፡ በእውቀት የዳበሩ ዜጎች ከተበራከቱ ለሕግና ለሥርዓት መከበር ዐይነተኛ አስተዋፅኦ ከማበርከታቸውም በላይ ሙስናን የማይሸከሙ ስለሚሆኑ፣ ለፀረ ሙስና ትግል አጋር፣ ሀገርን የማበልፀጊያ ትልቅ መሣሪያዎች ይሆናሉ፡፡ ዛሬ በሀገራችን በእውቀት የዳበሩ ዜጎች ባለመብዛታቸው እና ያለአዋቂ ቁጥር በእጅጉ በመብዛቱ፣ ጥቂቶች የተግባርና የቲዎሪ እውቀት ያላቸው በሙስና ተዘፍቀው ስናስተውላቸው "ዕውቀት የብልፅግና ቁልፍ ነው፡፡" ሲባል፣ "በሀገራችን እውቀት የድንቁርና እና የሙስና ቁልፍ ይሁን?" በማለት ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ ይህ እንግዲህ በሀገሪቱ የእውቀት ያለመስፋፋት የፈጠረው ችግር በመሆኑ፣ ምን ማድረግ ይቻላል? በእርግጥ መንግሥት አሁን ለትምህርት የሰጠው ትኩረት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ወደፊት ችግሩ ከመሰረቱ እንደሚፈታ ይታመናል፡፡ 2ኛ ችግር አንዳንዶች ግን በአጭር ጊዜ የናጠጠ ቱጃር ባለ ቪላ፣ ባለመኪና ወዘተ. የሚሆኑትን ግለሰቦች በማስተዋል "የቻይና የፀረ ሙስና ተመክሮ አሁኑኑ" በማለት መፈክር ያሰማሉ፡፡ እንደውም አንድ በቅርቡ በተደረገ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ቀጥታ የስልክ ውይይት ላይ እንዳዳመጥኩት ከሆነ ይሄ ስሜት የብዙዎች እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ የብዙዎቹ ቁጭት በቅርብ የሚያውቁት ሰው ካጠገባቸው እንደሮኬት ተተኩሶ በአጭር ጊዜ "የናጠጠ" ሲሆንባቸው በማየታቸው የተነሳ የተከሰተ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ "የሙስና አድናቂዎች ነን" ብለው (ሙሰኞችን ሂደው ፊርማ እንዲፈርሙላቸው ከመጠየቅ እንደማይመለሱ እስከምናምን ድረስ) በቁጭት አፊዘዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከልባቸው ሙስናን የሚያደንቁ እና አሥር ብር የሰረቀን ሌባ "ልክስክስ" የሚሉ ሰዎች በበዙበት ሀገር የነሱ ማድነቅ እብዛም አያስገርምም፡፡ 3ኛ ችግር የባህል ችግር ከፀረ ሙስና ትግሉ አንፃር የባህል ተፅዕኖ እንዴት ደንቃራ እንደሚሆን ከተለያየ አቅጣጫ መመልከት እንችላለን፡፡ በዚህ ሀገር የግለሰባዊ የውርስ አመለካከቶች ተጽዕኖ የገነነበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ከቤቱና ከኅብረተሰቡ የወረሰው በብልጣ ብልጥነት እና በጮሌነት በዛም ሆነ በዚያ ሀብት ያከማቸውን የበለፀገውን እና የደረጃውን እያደነቀ ስለአደረገ ሙስናን የማድነቅ የተሳሳተ ባህል በደሙ ውስጥ ተሰራጭቷል፡፡ ጥቂቶች (የከተሜ ኗሪዎች) ብዙሃኑ (የገጠር ኗሪዎች) ግን ይህንን የምንቸገረኝ ባህል ያወግዛሉ፣ ይፀየፋሉ፡፡ መንግሥትም ከብዙሃኑ፣ ከገበሬው ጋር ስለሚራመድ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ የቻይናን ተመክሮ ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፀረ ልማት፣ ፀረ እድገት የሆኑት ሙሰኞች ከግባችን ሳንደርስ ጠልፈው ሊጥሉን ይችላሉ፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን እንደመዥገር ከተጣበቁበት የሙስና ስፍራ መንግሥት እጅግም ሳይዘገይ ቢያስወግዳቸው በ2020 ራዕያችን እውን ሊሆን ይችላል፡፡ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ እጅግ ከዘገየ ግን የብልጽግና ራዕያችን መደናቀፍ አይቀፉ ነው፡፡ የብልፅግና ራዕያችንን የሚያደናቅፍ እንቅፋት ሁሉ ወደ ብልፅግና ከሚያደርሰን የልማት ጎዳና ላይ መጠረግ ወይም መወገድ ይኖርበታል፡፡ ክቡር ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር ሲወያዩ በመሬት ጉዳይ ለተነሳ ጥያቄ በሰጡት መልስ ሕገወጥ ብልጽግናን በቸልታ እንደማያዩ እና ተገቢውን እርምት እንደሚወስዱ በአፅንኦት መናገራቸው ይህንኑ የሚያረጋግጥልን እውነት ነው፡፡ ወደፊት መንግሥት የፀረ ሙስና ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚወስደው እና ተጨባጭ ለውጥ እንደምናይ የተስፋ ጭላንጭልም እንዳለ በዛ ውይይት ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ በበኩሌ ግን መንግሥት እንደ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና በሙስና ላይ ትንሽ ጨከን ያለ እርምጃ ቢወስድ ለሀገር እድገትና ብልፅግና ይበጃል ብዬ አምናለሁ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |