Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 25th
Home arrow Sections arrow አንቺም ወይ እድልሽ፤ እኛም ወይ እዳችን!
አንቺም ወይ እድልሽ፤ እኛም ወይ እዳችን! Print E-mail
Sunday, 27 January 2008

በአፍሪካ አህጉር፣ በአህጉሩ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የስፖርቱ አፍቃሪ እና እንዲሁም የኢንዱስትሪው ባለጉዳዮችና ባለጥቅሞች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውን 26ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ የዋንጫ ጨዋታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ጋና የምታስተናግደውን ይህንን ከአህጉሩ ሌሎች "ኢንስቲቲዩሽኖች" ሁሉ ለየት ያለውን፣ በዓለም ደረጃ ከፍ ያለ የተወዳዳሪነት ብቃት አግኝቶ እንክብካቤ የሚፈረጀውን፣ ከሌሎች አህጉሮችና አገሮች መሰል ክንዋኔዎች ጋር በአቻነት የሚታየውን ጨዋታ በቴሌቪዥን የማየት እድል አላመለጠንም፡፡ እድሉ ያላመለጠን እኛ ማን ነን? ምን ያህል ነን? የሚለው እንደተጠበቀ እና ሌላ ጉዳይ ሆኖ ማለት ነው፡፡

የአፍሪካ አህጉር እያንዳንዱ አገር እና የእያንዳንዱም አገር ህዝብ ጋና በመካሄድ ላይ እንዳለው የእግር ኳስ ዋንጫ ተሳትፌበታለሁ፣ ተወክዬበታለሁ ወይም በተቃራኒው አልተወከልኩበትም፣ አልያም እንደተመልካች አመለጠኝ ወይም አላመለጠኝም እያለ የሚነጋገርበት ጉዳይ ስለመሆኑ ቢያንስና ሌላው ቢቀር አይታወቅም እንጂ አፍሪካ በዚሁ ወቅት የምታካሂደው ሌላም አህጉራዊ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ነው፡፡ የአፍሪካን የእግር ኳስ ዋንጫ በቅርብና በትኩረት እንደሚከታተሉት የዘርፉ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ እንዲሁም አገራዊ ተቋማትና ድርጅቶች አቻ የፖለቲካ ተቋማት የህብረቱ ስብሰባ ላይ እኩልና ያንን ያህል ደንታ ያላቸው ስለመሆኑ አሁንም ቢያንስ ቢያንስ አይታወቅም፡፡ ወይም አጠራጣሪ ነው እንጂ የአፍሪካ ህብረት በርካታ አህጉራዊ ችግሮች ላይ ይነጋገር ዘንድ ቢያንስ ቢያንስ እንደ አጀንዳነት የሚርመሰመሱ በርካታ ጉዳዮች አሉት፡፡ ኬንያ፣ ሶማሊያ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በጋና በመካሄድ ላይ እንዳለው ብዙ ተመልካች የማይኖረው፣ በቀጥታ ስርጭት የማይተላለፈው፣ በአብዛኛውም በዝግ ስብሰባው የሚታወቀው እንደ ቡድኖቹ፣ እንደ ተጫዋቾቹ፣ እንደ አሰልጣኞቹና እንደ ዳኞቹ እንዲሁም እንደጨዋታው እንደራሱ አገሮቹን፣ ዲኘሎማቶችን፣ የፖለቲካ ተዋናዮችንና ፖለቲካውን ሕዝቡ ነፃ ሆኖ መከታተል የማይችለው የህብረቱ ስብሰባ በያዝነው በጥር ወር ውስጥ እንደሚካሄድ ከመደበኛው የህዝብ ቁጥር በላይ ይሰማው ዘንድ አጋጣሚውና እድሉ የተገኘው በእግር ኳስ ጨዋታው ምክንያት ነው፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉትን ጥቂት አገሮች ብሔራዊ ቴሌቪዥን ለወትሮው ከሚመለከተው እጅግ በጣም ውሱን ተመልካች በላይ ብዙው ሰው የሚከታተለውን ይህንን ከጋና የሚተላለፍ ጨዋታ በተለየ ሁኔታ ከአገር የንግድና የኢንዱስትሪው ዘርፍ በላይ ይበልጥ "ያወቀበት" የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት፣ የመንግሥት ማስታወቂያና የኘሮፖጋንዳ ዘርፍ ስለመሆኑ እግር ኳሱን ብቸኛ እሱኑ ብለው ቴሌቪዥኑን ለሚከታተሉ እጅግ በጣም ግልፅ ነው፡፡

በመደበኛ አሠራር የንግድና የኢንዱስትሪ እንዲሁም የአገልግሎት ሰጪው የአንድ አገር የኢኮኖሚ ሥራ የማስታወቂያና የሽያጭ ዘመቻ ተግባር፣ አነፍንፎ የሚከተለውና መልዕክቱን የሚያስተላልፍበትን ሚዲያ ከመምረጥ አኳያ ውሳኔውን የሚመሰርተው የትኛው ራዲዮ፣ የትኛው ቴሌቭዥን፣ የትኛው ጋዜጣ ምን ያህልና ስንት አድማጭ ተመልካች አንባቢ አለው ብሎ ነው፡፡ የሚዲያው ተግባር በዋነኛነት መረጃ /ኢንፎርሜሽን ለህዝብ ማድረስ በዚያም አማካኝነትና በእሱም በኩል ተመልካቹን አድማጩን አንባቢውን ህዝብ ለአስተዋወቀው "ማቅረብ"፣ ከአስተዋዋቂው ጋር "ማገናኘት" ነው፡፡ የማስታወቂያ ሥራ የሚደራውም እንዲህ ያለ ስኬት በሚያስመዘግብ ሚዲያ ላይ ነው፡፡

በአገራችን ውስጥ የንግድ ማስታወቂያው ሥራ ወታደራዊው መንግሥት አዳፍኖትና አጥፍቶት ከቆየው ኢኮኖሚያዊው ተግባር ጋር አብሮ ጠፍቶ እንደ ሥራም፣ እንደ የኢኮኖሚ ዘርፍም ጭራሽ ጠፍቶ ከቆየ በኋላ እንደገና ማንሰራራት የጀመረው በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ወደነበረው ዓይነት ነፃ ኢኮኖሚ መመለስ በመጀመሩ ነው፡፡ የማስታወቂያ ክፍለ ኢኮኖሚ ግን ከሌላው ክፍለ አኮኖሚ እኩል አቻ እርምጃ ሊያስመዘግብ የሚችለው በሚዲያው ዘርፍ እንደ የዲሞክራሲ መሳሪያም እንደ የኢንቨስትመንት መስክም የተመዘገበ ድልና ስኬት ሲኖር ነው፡፡

ሚዲያው ግን እንኳንስ እንደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እንደ አነስተኛና ጥቃቅን የሥራ መስክም የሚበረታታ ሆኖ ባለመታደሉ ይልቁንም እንደ መንግሥት ያለ ወይም በመንግሥት ጐን የቆመ መንግሥት በመራው ጐዳና የሚጓዝ "ኃላፊነት" የሚሰማው "አካል ካልተያዘ በስተቀር ከሠ" በላይ አደገኛ ነው በመባሉ ኢትዮጵያ አሁንም ከመንግሥት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ውጭ ሌላ የማይገባት አገር ትሆን ዘንድ ተፈርዶባታል፡፡ ደብልዩ ኤም ዲ ማለት ፣ዌኘንስ ኦፍ ማስ ዲስትራክሽን፣ ነው፡፡ ሚዲያውን እንደ የፍጅትና የእልቂት መሳሪያ አድርገው በሚቆጥሩ የአፍሪካ አገሮች የህልውና ፈቃድ የተሰጣቸው ብቸኛ የመንግሥት ሚዲያዎች እውነትም (ዌኘንስ ኦፍ ማስ ዲሴኘሽን) መሆናቸው አልቀረም፡፡

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የጋናውን የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ ከሚከታተለው እጅግ በጣም ብዙ ተመልካች ጋር የንግዱን /የኢንዱስትሪውን ክፍለ ኢኮኖሚ ሊያገናኝ በሚችለው እና በሚያገኛቸው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከኢኮኖሚው እና ከንግዱ መልዕክት ይልቅ የፖለቲካው ማስታወቂያ ይበልጥ ደርቶና ጐልቶ እያየን ነው፡፡ ከወትሮው ሌላ ተመሳሳይ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ኘሮግራሙን (የዜናውን ጭምር) በእግር ኳሱ ጨዋታ መርሀ ግብር ልክ ባስተካከለው በቴሌቪዥኑ የምንሰማቸውና የምናያቸው "ማስታወቂያዎች" የምርጫ ምዝገባና የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን የሚመለከቱት ናቸው፡፡ ቴሌቪዥኑ የአፍሪካን ዋንጫ ጨዋታ ተቀብሎ (በአገር ውስጥ ብቻ) የማስተላለፉን መብት ያገኘው እንደምን ባለ ግዴታና ሁኔታ ውስጥ ስለመሆኑ ማወቅ ባንችልም፣ የተለመደውን የስፖንሰር ጥሪና ማስታወቂያ ደጋግመን መስማታችን፣ (ምናልባትም) "ስፖንሰር" አድራጊ ድርጅቶችን ማስታወቂያ በጨዋታው ውስጥ እና በጨዋታው መካከል ሲቀርብ ማየታችን የቀረ ባይሆንም በዚህ አጋጣሚ የመጠቀውን ከዚህ ቀደም በአንፃራዊነት ታይቶ የማይታወቅ "ዝግጅት" መመስከር የቻልነው ግን ከመንግሥት እና ከፖለቲካው ማስታወቂያ አኳያ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የአገራችንን ሚዲያና የሚዲያውን ኢኮኖሚ የተጨናገፈ አበቃቀል ነው፡፡ የዚህም መሰረት ሚዲያው በመንግሥት እጅ እንዲቀር እዚያም እያለ በዚያው ውስጥ እንኳን ሊኖር ይችል የነበረውን አንፃራዊ "ነፃነት" እንዳይኖረው ያደረገው ፖለቲካው ነው፡፡

ቴሌቪዥኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ የተቋቋመው በቶምሰን የብሪቲሽ ተቋም የቴክኒክ እርዳታ አማካኝነት ከዛሬ 44 ዓመት በፊት ነው፡፡ ለጣቢያው መቋቋም ምክንያት የሆነውም ከ44 ዓመት በፊት በዚያው ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች ስብሰባ የተሰበሰቡትን የአገር እና የመንግሥት መሪዎችን ስብሰባ ለማስተላለፍ ነው፡፡ እንደገናም የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ስርጭት ባለቀለም የሆነው በተመሳሳይ፣ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) ምስረታ ነው፡፡

ከምስረታው ጀምሮ አሁንም ድረስ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው የዚህ ተቋም የአሠራርና የይዘት ቁጥጥር አሁንም ከመንግሥት እጅ አለመውጣቱ ብቻ ሳይሆን የአገሪቷ የሌላ ተጨማሪ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ እድል በዚሁ ተመሳሳይ የመንግሥት ፖሊሲ ምክንያት ጥርቅም ብሎ ተዘግቷል፡፡

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የቴሌቪዥንና የሬዲዮን ጨምሮ የነፃ ኘሬስን ጉዳይ በኘሬስ ነፃነት አጀንዳ የአገር እና የዲሞክራሲ ጉዳይ አድርጌ ይዤዋለሁ ያለው ወዲያውኑና ሳይውል ሳያድር ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር፡፡ በ1985 ዓ.ም. ሁሉንም የኘሬስ አይነቶች፣ ሁሉንምና ማናቸውንም የመገናኛ ብዙሃን ሥራ የሚያከናውን ተቋም ነፃነትና አሰራር ይመለከታል የተባለው የኘሬስ ህግ ወጣ፡፡ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት በወቅቱ የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር የተረጋገጠ መሆኑን መነሻዬና መሰረቴ አድርጌያለሁ በማለት በህግ ቁርጠኝነቱን የገለፀው የሽግግሩ መንግሥት ከዚህም በላይ ሄዶ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ነፃ የሆነና የተጠናከረ ኘሬስ ሲኖር፣ ሲጐለብትና ሲስፋፋ ነው፡፡ ነፃ ኘሬስ ዜጐች ሀሳባቸውን በነፃ የሚገልፁበት መድረክ ከመሆኑም በላይ የግለሰቦችና የህዝቦች መብት እንዲከበርና ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር በማድረግ እንዲሁም ዜጐች በተለያዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በመንግሥት አሠራርና አሠራር ላይ ሃሳብ እንዲያቀርቡ በማስቻል ጉልህ ሚና የሚጫወት ኘሬስ ነው፡፡ ኘሬስ ይህንን ተግባሩን ሊያከናውን የሚችለው የቅድሚያ ምርመራ /ሴንሰርሽኘ/ እና ሌላ ተመሳሳይ ገደብ ሳይደረግበት በነፃና በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠርለት ነው አለ፡፡

ጥሩ ጅምር፣ ይበጅ የሚል መነሻ ነበር፡፡ ያኔና በወቅቱ ይህ "ቁርጠኝነት" በታወጀበት ህግን የመሰለ የሰነድ ማረጋገጫና ማስረጃ በተሰጠበት ጊዜም ቢሆን ቅሬታቸውን የገለፁ፣ ጥርጣሬያቸውን ያሰሙ አልጠፉም፡፡

በተለይም አሁን ላይ ሆነን ስናያቸው ያኔም ዙሪያ ገባውን አገናዝቦ ለሚመረምር ሁሉ ግልፅ የነበሩ፣ በወቅቱ ከተነሱት መካከል አንዳንዶቹን መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የ1985 ዓመቱ የኘሬስ ህግ ዜጐች በአመራርና አሠራር ላይ ሀሳብ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን ይገልፃል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዞ የኘሬስ ሚና የማንኛውም ሰው ሁሉ እንጂ የዜጐች ብቻ አይደለም፡፡ በመንግሥት አመራርና አሠራር ላይ ሀሳብ ማቅረብ የሚለውም "የሚፈራው" ነገር ያለ ይመስላል፣ የኘሬስ ሚና መንግሥትን መመርመር በመንግሥት ላይ "ቆቅ" ሆኖ መጠበቅም (ወችዶግ) ነው ብለው በወቅቱ "የቁንጫ ሌጦ" አመጡ የተባሉ ነበሩ፡፡ ሌላው አሁን እንደገና ነፍስ ዘርቶ የመጣው የኘሬስ ረቂቅ ህግ ካላፀደቅሁት የሚለው በተግባርና በተለያዩ ህጐች ግን የተካተተው የኘሬስ ምዝገባና ፈቃድ ጉዳይ ነው፡፡

እነዚህ ሰዎች በወቅቱና ከዚያም ወዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቢጮኹ የሰማቸውና እውነታቸውን ነው ያላቸው ብዙም አልተገኘም እንጂ ያነሷቸው በርካታ ቁም ነገሮች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው የኘሬስ ወይም የመገናኛ ብዙሃን ትርጉም በዋነኛነት የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ /ኘሬሶችን እንደሚያካትት ከቁጥር ውስጥ ከገባ ሁለቱንም ዓይነት ማለትም የህትመት ሚዲያውንና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን አንድ ላይና ሁሉንም እኩል የሚገዛ ህግ አወጣለሁ ማለት ልክ አይደለም የሚለው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀርበው የመጀመሪያውን ነጥብ እንደምሳሌ ሆኖ የሚያስረዳውና በገዛ ራሱ ምክንያት ከዋና ዋና የአንድ የኘሬስ ህግ አይነተኛ ጉዳዮች መካከል ራሱን የቻለ ጉዳይ የሆነው የምዝገባ እና የፈቃድ ጉዳይ ነው፡፡ የፈቃድና የምዝገባን ልዩነት አስቀድመው ከሚያውቁትና ካሳወቁት መካከል አንዱ፣ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ናቸው፡፡ ህዳር 1 ቀን 199ዐ ዓ.ም. አፍሪካ አዳራሽ ባደረጉት ንግግር የኘሬስ አዋጅ የኘሬስ ነፃነት ተግባራዊ የሚሆንበትን ሁኔታዎች የሚደነግግ መሆኑን ገልፀው፣ ፣የኘሬስ ድርጅት ለማቋቋም ምዝገባ እንጂ አይጠየቅም፤፣ ምዝገባንም በተመለከተ ፣ድርጅቱ ሲቋቋም ከባለቤቱ የሚጠየቀው መረጃ ስም አድራሻ የኘሬሱ ድርጅት አዘጋጅ ስም ብቻ ነው፣ ብለው ነበር፡፡

ፈቃድ ወይም መፍቀድ መከልከልም ያለው መከልከልንም ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ በተለይም ከህትመት ሚዲያ ነፃነት፣ ከነፃ የህትመት ሚዲያ ህግ ይዘት አኳያ ስለምዝገባ አስፈላጊነት ሳይሆን ስለምዝገባ እና ስለ ፈቃድ ግዴታ መደንገግ ቅድመ ምርመራን /ሴንሰርሽኘንና "ሌላም ተመሳሳይ ማናቸውም ገደብ በየትኛውም መልኩ የከለከለውን ሕገመንግሥት መጣስ ነው" ብሎ መከራከር ቀርቶ መናገርም በሚደንቅ ሁኔታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ "ክፍሌ ወዳጆ አዳራሽ" ውስጥ እንኳን የሚሰማ ቀርቶ የሚቻልም በጭራሽ አልሆነም፡፡ የብሮድካስት ሚዲያን በተመለከተ ግን ስለ ፈቃድ የመናገርና የመደንገግ ተገቢነትን እዚህ ውስጥ የምናስታወሰው ከሁለት ተጨማሪ ማስታወሻዎች ነው፡፡ አንደኛው ሚዲያዎችን ለያይቶና በየፈርጃቸው ከፍሎ ህግ የማውጣት አስፈላጊነት ከሌሎች ምክንያቶች መካከል ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ሁለተኛው ከብሮድካስቲንግ ህግ አንፃርም ዛሬ የብሮድካስት ኤጀንሲ ያገባኛል ብሎ ደንብ እያወጣባቸው ያሉት ሁሉ የፈቃድ ህግ ከሚገዛው ብሮድካስቲንግ ውጭ ያለመሆኑን ያለማወቅ ጉዳይ ነው፡፡

የ1984 ዓ.ም. የኘሬስ ህግ በኘሬስ ሥራ የመሰማራት መብት አንድ ራሱን የቻለ ክፍል ውስጥ ከደነገጋቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የምዝገባ ሌላው የፈቃድ ጉዳይ ነው፡፡ ማናቸውም የኘሬስ ሥራ የብሮድካስቲንግም ሆነ የህትመት ኘሬስ ሁሉም የምዝገባና የፈቃድ ግዴታ አለበት ይላል፡፡ ችግሩ የመነጨው ከዚህ መሰረታዊ ስህተት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የኘሬስ ህጉ የአየር ሞገድ አጠቃቀም ወደፊት በህግ ይወሰናል በማለት ከብቸኛው የመንግሥት ቴለቪዥን ሌላ ምንም ዓይነት ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን እንዳይኖር በሩን በህግና በወደፊት ተስፋ ዘጋው፡፡

ይህ ጥቅምት 1985 ተብሎ፣ የአየር ሞገድ አጠቃቀምና አደላደል ህግ እንደ ህግ የወጣው በ1991 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከአምስት ዓመት ተኩል በላይ በኋላ ነው፡፡ በዚህ የ1991 ዓ.ም. ህግ ከተቋቋመው የአየር ሞገድ አጠቃቀምና አደላደል ህግ አፈፃፀም ግን ለ1997 ዓ.ም. ምርጫ እንኳን "አልደረሰም" ወይም አልተፈለገም፡፡ የብሮድካስት ህጉ የፈቃድ ዓይነቶችን በአራት ዓይነት "ፈቃዶች" ለይቶ

1ኛ/ ኘሮግራም አዘጋጅቶ በራስ ትራንስሚተር የማሰራጨት ወይም
2ኛ/ የማሰራጫ መሳሪያ ተከራይቶ ኘሮግራም የማሰራጨት ወይም
3ኛ/ የማሰራጫ መሳሪያዎች የሌሎችን ኘሮግራም ብቻ ተቀብሎ የማሰራጨት ወይም
4ኛ/ በሳተላይት ወይም በኬብል የማሰራጨት ብሎ ይፈርጃቸዋል፡፡ ይህ አይነት የፈቃድ ዓይነቶች ክፍፍል አዲሱ ብሮድካስት ህግ ውስጥ አልተካተተም፡፡ የሁለቱም ሳይንስና ጥበብ ባይገባንም ፣ቲቪ አፍሪካ፣ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ የኘሮግራም ስርጭት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 2ኛ ቻናል ይተላለፍ የነበረው የውጭ አገር ሰው/ ኩባንያ ፈቃድ አይሰጠውም የሚል ክልከላ ያለው ህግ ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ቲቪ አፍሪካ የቀረውም በገዛ ራሱ የውስጥ (የኩባንያው) ሥራ መቀጠል አለመቻል ምክንያት ነው፡፡

ቲቪ አፍሪካን በአጭር ጊዜ ቆይተው ውስጥ አዲስ አበባና አካባቢው ብቻ በሚተላለፍበት በዚያ የቆዳ ስፋት ክልል ውስጥ ብዙ ሰው ግልብጥ ብሎ ከኢቲቪ ፊቱን አዙሮ ወዶት ነበር፡፡ ያንኑ ያህልም ከባህል ከወግ አኳያ ልጆቻችን ጠፉ፣ ተበላሹ ብሎ የጮኸው ጥቂት አልነበረም፡፡ ቲቪ አፍሪካ የኢቲቪን የአዲስ አበባ አድማጭ ብቻ ሳይሆን የማስታወቂያ ገበያ ገልብጦ ሊወስድ ጥቂት ሲቀረው በገዛ ራሱ የቲቪ አፍሪካ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ የውስጥ ችግር ምክንያት ኘሮግራሙ በአጋጣሚ ተቋረጠ፤ በዚያውም ቀረ፡፡

ቲቪ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር የተዋዋለው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሌላ ቻናል ኘሮግራም ስርጭት ማስተላለፍ የጀመረው የኢትዮጵያም ቴሌቪዥን ተጨማሪ ቻናል ይኑረኝ ያለው የህጉን ተፈፃሚነት በመከተል በህግ እየተገዛ አለመሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የጠየቀ፣ ሃይ ብሎ ድምፁን ያሰማ ባለሥልጣን ኤጀንሲም አልነበረም፡፡ የጥሩ ነገር መምጣት ምክንያት አጋጣሚና እድል እንጂ መብት አልነበረም፡፡ በቲቪ አፍሪካ ዘመን ጥሩ ነገር አየን፣ መፎካከሪያና ማስፈራሪያ አግኝተን ለኢቲቪም ቢሆን መልዕክት አስተላለፍን የሚሉት የደስታና የእርካታ ምንጭ "የበላይ አካላት ፈቃድ" እንጂ የህግ ተፈፃሚነት አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ የገለፅኳቸው የኳስ ጨዋታው ሳያመልጠን የቀረበትን እድልና አጋጣሚ ጨምሮ ብዙዎቹ የመብቶቻችን ተፈፃሚነት ያስገኛቸው ናቸው የምንላቸው፣ ነገም የምንጠብቃቸው ስለመሆናቸው እርግጠኛ አይደለንም፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው በሁሉም ዘርፍ በሁሉም የመብት መስክ ነፃነትና መብትም ወይ እድላቸው እኛም ወይ እዳችን የምንለው፡፡

 
< Prev   Next >