Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow የሩዋንዳ አማጽያን በዴሞክራቲክ ኮንጎ...
የሩዋንዳ አማጽያን በዴሞክራቲክ ኮንጎ... Print E-mail
Sunday, 27 January 2008

የሩዋንዳ አማጽያን በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተቃወሙ

በዴሞክራቲክ ኮንጎ የሩዋንዳ ሁቱ አማጽያን ያለፈው ረቡዕ ከስምምነት ላይ ከተደረሰው የሰላም ስምምነት እራሳቸውን ሊያገልሉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዴሞክራቲክ ኮንጎ አምባሳደርን በመጥቀስ ቢቢሲ ዘገበ፡፡

በኮንጎ የሩዋንዳ ቱትሲዎችን ከጥቃት ለመከላከል በሚል የሚዋጉት ጀነራል ላውረን ንኩንዳ የሰላም ስምምነቱን መፈረማቸው ተገልጿል፡፡ የሁቱ አማጽያን መሪ ግን ሩዋንዳ ለመደራደር እስካልተስማማች ድረስ በስምምነቱ ውስጥ አንሳተፍም በማለት አሳውቀዋል፡፡ አማጽያኑ ኮንጎን ለቀው ወደ አገራቸው የማይመለሱ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በቱትሲዎች የሚመራው የሩዋንዳ መንግስት በኮንጎ የሚገኙ የሁቱ አማጽያንን ለማጥቃት በሚል ዴሞክራቲክ ኮንጎን ሁለት ጊዜ መውረሩ አይዘነጋም፡፡ ጀነራል ንኩንዳ የሩዋንዳ ደጋፊ ናቸው የሚለውን የኮንጎን ውንጀላ በተደጋጋሚ አስተባብለዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት በኮንጎና በሩዋንዳ አዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ ከሃያ በላይ የታጣቂ ኃይሎች ትጥቅ ለመፍታት ተስማምተው ነበር፡፡

የደቡብ አፍሪካ የማዕድን ጣቢያ በኃይል እጥረት ምክንያት ሥራውን አቋረጠ

የደቡብ አፍሪካ ትልቁ የወርቅና የፕላቲኒየም ማዕድን ማውጫ ተቋም በአገሪቱ በተከሰተው የኃይል ምንጭ እጥረት ምክንያት ሥራውን ማቆሙን ቢቢሲ አስታወቀ፡፡

በደቡብ አፍሪካ በደረሰው ድንገተኛ የኃይል እጥረት ምክንያት የአገሪቱ የማዕድን ማምረቻ ጣቢያዎች ሥራቸውን አቁመዋል፡፡ የአገሪቱ የህዝብ ድርጅት ተቆጣጣሪ ሚኒስትር አልክ ኡርዊን የኃይል እጥረቱን ተከትሎ "ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ" አውጀዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ወርቅና ፕላቲኒየም በማምረት በአለም ከፍተኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ የደቡብ አፍሪካ የማዕድን ምርት መቋረጥን ተከትሎ የወርቅና የፕላቲኒየም ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡

ግብጽ ከጋዛ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር እንደምትዘጋ አስታወቀች

ግብጽ የጋዛ ነዋሪዎች የሚያደርጉትን ፍልሰት ለማስቆም ከጋዛ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር እንደምትዘጋ የአገሪቱን የደህንነት ኃይል ባለስልጣናት በመጥቀስ ቪኦኤ ዘገበ፡፡

የግብጽ ፖሊሶች በድንበር አካባቢ ከጋዛ የሚፈልሱትን ሰዎች ውሃ በመርጨት እንዲመለሱ እያደረጉ ነው፡፡ የጋዛ ስደተኞች ወደ ከተማቸው እንደሚመለሱ ግብጽ ብታስጠነቅቅም፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ወደ ግብጽ ለመግባት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

እስራኤል በበኩሏ ግብጽ በድንበር አካባቢ የሚደረገውን የመሳሪያ ዝውውር እንቅስቃሴ እንድታስቆም አሳስባለች፡፡ በዚህም ያለፈው ሐሙስ በድንበር አካባቢ በሰነዘረችው የአየር ጥቃት አራት የሀማስ አባላትን መግደሏን አስታውቃለች፡፡

ተመድ በኢራን ላይ ማዕቀብ ለመጣል የቀረበውን ረቂቅ ሃሳብ ተቀበለ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የቀረበውን ረቂቅ ሃሳብ መቀበሉን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡

እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ሩሲያና ጀርመን በጋራ ያቀረቡት በኢራን ማዕቀብ የመጣል ሃሳብ ተመድ ተቀብሎ ለውሳኔ ያቀረበው መሆኑ ታውቋል፡፡ በረቂቁ መሰረት ኢራን በምታደርገው የንግድ እንቅስቃሴና የአገሪቱ የኒውክሊየር ተመራማሪዎች እንቅስቃሴን የሚያግድ መሆኑ ታውቋል፡፡

ኢራን የምታደርገው የዩራንየም ማበልፀግ እንቅስቃሴ ለኃይል ምንጭነት ብቻ መሆኑን በመጥቀስ ለወታደራዊ አገልግሎት የማይውል መሆኑን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገልፀዋል፡፡

 
< Prev   Next >