Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow "ሴት ሕፃናት ጥቃት ተፈጽሞባቸው...
"ሴት ሕፃናት ጥቃት ተፈጽሞባቸው... Print E-mail
Sunday, 27 January 2008

Image"ሴት ሕፃናት ጥቃት ተፈጽሞባቸው ቢናገሩም ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ አለ"

ሴት ልጆቻቸውን የሚከታተሉ ወላጆች ምን ያህል ናቸው? መከታተል ሲባል የስሜታቸውን ለውጥ የሚያጤኑ፣ እንግዳ ነገር አጋጥሟቸው እንደሆነ የሚመለከቱ ማለት ነው፡፡ ለጋ ታዳጊዎችን መድፈር እየተለመደ በመጣበት ዘመን አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው የጥቃት ሰለባ ቢሆኑ እንኳን ላይረዱ የሚችሉበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ቀጥሎ ያለው ታሪክም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡

እናትና አባት የ9 ዓመት ልጃቸውን መደፈር የሰሙት ድርጊቱ ከተፈፀመ ከ2 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ እናቷ እንደሚሉት የቤታቸው ዘበኛ በልጃቸው ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመው ከሁለት ዓመታት በፊት ሲሆን ጉዳዩን ያወቁት ግን ልጅቷን ከድርጊቱ ሁለት ዓመት በኋላ አጥቂውና ተባባሪዎቹ ጠልፈው ከወሰዷት በኋላ ነበር፡፡ ጉዳዩ ለፖሊስ ሪፖርት የተደረገው ደግሞ በጠለፋው ወቅት ነበር፡፡ ፖሊስ ታዳጊዋ ወሲባዊ ጥቃት የተፈፀመባት ለመሆኑ የህክምና ማስረጃ ጠየቀና ከሆስፒታል የተሰጠ ማስረጃ ልጅቷ ቀደም ሲል ጥቃት የተፈፀመባት መሆኑን አረጋገጠ፡፡

ሆኖም ጉዳዩ ለፖሊስ በደረሰ ጊዜ ጥቃቱን ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ አዲስ አበባን ለቆ ወጥቷል፡፡ የታዳጊዋ ወላጅ እናት ወደ ህፃናት የህግ ከለላ ማዕከል እርዳታ ፍለጋ ሲመጡ የተናገሩት በቅርቡ የተፈፀመው የታዳጊዋ ጠለፋ ጉዳይ በህግ ተገቢው ክትትል እንዲደረግላቸው ለመጠየቅ ነበር፡፡

ጉዳዩ በፖሊስ እጅ ያለ ቢሆንም ወላጅ እናት ጉዳዩ ተገቢው ትኩረት ስለማግኘቱ እርግጠኛ አልነበሩም፡፡ በሌላ በኩል በታዳጊዋ ጠለፋ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት ሰዎች ከታዳጊዋ ወላጅ አባት ጋር በፍትሐብሄር ጉዳይ የተካሰሱ ሲሆን ክሱ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ነው፡፡ ከጠላፊዎቹ የተወሰኑት ደግሞ ከታዳጊዋ ቤተሰቦች ከጠለፋው በፊት ንብረት መስረቃቸው ሲገለጽ የታዳጊዋ አባት እንደሚሉት ግለሰቦቹ ወንጀሉን ለመደበቅና ከቅጣት ለማምለጥ የተቻላቸውን ሁሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ከፖሊስ ያገኙት መረጃ ደግሞ ጉዳዩን የሚከታተለው ፖሊስ መቀየሩን ፋይሉም መጥፋቱን የሚጠቁም ነበር፡፡

ማዕከሉ ለታዳጊዋ ሊያደርግላት የሚችለውን ሲያስብ የመጀመሪያው ለታዳጊዋ ከሥነልቦናዊ ጉዳቷ እንድታገግም ምክር መስጠት፣ ቀጥሎ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ ነበር፡፡ ጉዳዩን የሚያንቀሳቅስ የህግ ባለሙያ ከመደቡ በኋላ የጠፋው ፋይል እንዲገኝ፣ ጉዳዩም ዐቃቤ ህግ ቢሮ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ ታዳጊዋም በተደረገላት የምክር አገልግሎት ከጉዳቷ እንድታገግምና ከወላጆቿ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻሻል ሆኗል፡፡

በአፍሪካ ህፃናት ፖሊስ መድረክ አማካኝነት የተቋቋመው የህፃናት የህግ ከለላ ማዕከል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሔለን ሰይፉ እንደሚሉት ማዕከሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ህፃናቱ በሁለት መልኩ ሊመደቡ የሚችሉ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ የተለያዩ ጥቃቶች ፈጽመው የሚመጡ፣ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ወንጀል ፈጽመው የሚመጡ ናቸው፡፡ ወንጀል ፈጽመው የሚመጡት በአብዛኛው ወንድ ሕፃናት በመሆናቸው በዚህ ጽሁፍ ሊተኮር የተፈለገው ደግሞ ሴት ሕፃናት ላይ በመሆኑ ሁለተኛውን ጉዳይ አናነሳም፡፡ 

ወ/ሮ ሔለን እንደሚሉት ጥቃት ተፈጽሞባቸው ከሚመጡት ውጪ የሚታዩ የህፃናቱ ጉዳዮች ደግሞ ልጆች ማንጋ ይደጉ? የሚለው (በትዳርም ሆነ በፍቺ ጊዜ) ከሚለው ጀምሮ እናቶች የሚጠይቋቸው የቀለብ ጥያቄዎችና አባትነትን ማረጋገጥ የሚሉ ጉዳዮች ይመጣሉ፡፡

የጥቃት ሰለባ ሆነው የሚመጡት ሴት ህፃናት ደግሞ በአብዛኛው በሚያውቋቸው ሰዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው የሚመጡ መሆናቸውን ወ/ሮ ሔለን ይገልፃሉ፡፡ የጥቃት ዓይነቶቹ ደግሞ ተገዶ መደፈር፡ የጉልበት ብዝበዛና ህገወጥ ዝውውር ናቸው፡፡

ከሴት ህፃናቱ መካከል ከገጠር እናስተምራቸዋለን በሚል አምጥተዋቸው ለተለያዩ ጥቃቶች የሚያጋልጧቸው ይገኙበታል፡፡

ወደ ማዕከሉ ከሚመጡ ሴት ህፃናት ላይ በአብዛኛው ወሲባዊ ጥቃቶች የሚደርሱባቸው ናቸው፡፡ በቅርብ ዘመዶቻቸው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ደግሞ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ ማዕከሉ ደግሞ ጉዳያቸው የፍርድ ቤት ክትትል እንዲያገኝ እገዛ ማድረግ፣ ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዳይለቀቁ አቤቱታ ማስገባት የሚሉ ናቸው፡፡ ይህንን አቤቱታ የሚያስገቡት እንደ ወ/ሮ ሔለን ገለፃ ጥቃቱን የሚያደርሱት በአብዛኛው ከህፃናቱ ጋር አብረው የሚኖሩ ሰዎች እንደመሆናቸው በዋስ ቢለቀቁ በህፃናቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ በፍ/ቤት ጉዳዮች ሲታዩ አግባብ ያለውን አንቀጽ ጠቅሶ ክስ እንዲመሰርት ዐቃቤ ሕግን ግፊት ያደርጋሉ፡፡

ከህግ አስፈፃሚው አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ ፣በአብዛኛው ጥሩ አቀባባል ነው ያለን ለሴት ህፃናት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለልጆች የሚግዚት ውሳኔ ለመስጠት አልያም ከተወሰነ በኋላ የመጎብኘት ፈቃድ ተፈፃሚ ሳይሆን ሲቀር ፍ/ቤት ወደ እኛ ይልካል፡፡ ማዕከሉ ማጣራት አድርጎ የት ቢያድጉ ጥሩ ነው የሚለውን ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ባለፈው ዓመት (በ2007) ለምሳሌ 29 ጉዳዮች ወደእኛ ተልከው አስተያየት ሰጥተንባቸው በዚያ መሰረት ተወስኗል፣፡፡

ከፖሊስና ከዐቃቤ ሕግ ቢሮ ጥሩ ግንኙነት ቢኖርም አንዳንድ ጊዜ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ዳይሬክተሯ ሲገልፁ ለዚህ የጠቀሱት ምሳሌ አንድን ጉዳይ ነው፡፡

አንዲት የ9 ዓመት ሴት ልጅ ቤት ውስጥ አብራው ትኖር በነበረች ሰው ትደፈራለች፡፡ ተጠርጣሪው እንዲያዝ ለፖሊስ ቢጠቆምም ሳይያዝ ይቀራል፡፡ ማዕከሉ ወደ ፖሊስ ቢሄድም "ቋሚ አድራሻ የለውም፣ የሚሰራበት አይታወቅም" በሚሉ ምክንያቶች ሳይይዘው ይቀራል፡፡ በኋላ ተጠርጣሪው ሊያዝ የቻለው በቤተሰብ አባላቱና ጉዳዩን በድብቅ በሚያውቁ በት/ቤት አካባቢ በሚገኙ ሰዎች ግፊት ነው፡፡

እናም በአሰራሩ ላይ ችግር እንደሚያጋጥም፣ የህጉ አፈፃፀም ላይም ችግሮች እንዳሉ ወ/ሮ ሔለን ይጠቁማሉ፡፡

ወደ ማዕከሉ ከሚመጡ ህፃናት የሴቶች ቁጥር ምን ያህል ነው? ለሚለው ካለፈው ሐምሌ 1999 እስከ መስከረም 2000 ወደ ማዕከሉ ከመጡ 146 ህፃናት (ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጡ) 320 በድጋሚ የመጡ ነበሩ፡፡ አዲስ ከመጡት 62 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ 84 ወንዶች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ ጉዳዮች የሞግዚትነት አወሳሰንን የሚመለከቱ ሲሆኑ ሌሎቹ በኤች.አይ.ቪ ወላጆቻቸውን ያጡና በሞግዚቶቻቸው ንብረቶቻቸውን የተነጠቁ ናቸው፡፡ አሳዳጊዎች በሚፈጽሙባቸው ድብደባ አካላቸው ጎድሎ የሚመጡ ልጆች ጉዳዮችም ሌሎች ናቸው፡፡

በአብዛኛው ጥቃት የተፈፀመባቸው ህፃናት ተመልሰው ጥቃቱ ወደ ተፈፀመበት ቦታ (ወደ መኖሪያ ወይም ሰፈር አካባቢ) ለመመለስ የሚቸግራቸው በመሆኑ ማዕከሉ ጊዜያዊ መጠለያ የሚያገኙበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ወ/ሮ ሔለን ይገልፃሉ፡፡ ይህ የመጠለያ አገልግሎት የሚሰጡና ማዕከሉ 6 ከሚሆኑ ተመሳሳይ (የመጠለያ) አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ነው፡፡ ሕፃናቱ በመጠለያ የሚቆዩት ደግሞ ጥቃት ያደረሱባቸው ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እስኪውሉ ነው፡፡ እነኛ ድርጅቶች የህግ አገልግሎት ሲፈልጉ ደግሞ የሕፃናት የህግ ከለላ ማዕከሉ አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡

ሴት ሕፃናት ላይ ሲሰሩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተ ወ/ሮ ሔለን ሲገልጹ ፣የአመለካከትና የግንዛቤ አነስተኛ መሆን ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፣ ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ጥቃት ሲፈፀም ጉዳዩን የመደበቅ ሁኔታ አለ፡፡ ጉዳዩን ተከታትለው የሚደርሱበት ትምህርት ቤቶች አልያም ጓደኞች ናቸው፡፡ ወላጆች ለፖሊስ ሪፖርት የሚያደርጓቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ፣ጉዳዩን ብናወጣ እልባት አያገኝም፣ ከሚል አመለካከት ሊሆን ይችላል፣ ወደ ኋላ የማለት ሁኔታ አለ፡፡

በሕግ አፈፃፀሙ ላይ ያለው ችግር አንዱ ሲሆን በፖሊስ በኩል ያለው የአቅም ማነስ ሁኔታ ሕጉን ለማስፈፀም አዳጋች ሁኔታ መፈጠሩን ወ/ሮ ሔለን ያመለክታሉ፡፡ በተለይ የሴት ሕፃናትን ጉዳይ ትኩረት በቤተሰብ፣ በኅብረተሰቡም ውስጥ አናሳ መሆኑን፣ ሕፃናት ብዙ ላያውቁ ይችላሉ፣ የሚሉት እውነትነት ላይኖረው ይችላል በሚል ጥቃት ደርሶባቸው ሲናገሩ ተገቢውን ትኩረት ያለመስጠት ነገር እንዳለ ወ/ሮ ሔለን ይገልፃሉ፡፡

በቤተልሔም ነጋሽ

 
< Prev   Next >