Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow የዘመን ታሪክ ትዝታዬ
የዘመን ታሪክ ትዝታዬ Print E-mail
Sunday, 27 January 2008

Image
ከግራ፡- ዶ/ር ፈቃደ፡ ዶ/ር ደጃዝማች ዛዴ፡ ዶ/ር ማስረሻ፡ ፕ/ር ባህሩ እና አቶ አመሃ
"መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፤ አንድ ለእናቱ ለኢትዮጵያ
አንተ ቀጥቀጥትከ አርእስቲሁ ለዕበድ፤
ወወሀብኮሙ ሰዋስዎሙ ለዘሕዝበ ኢትዮጵያ ውሉድ"
(መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፤ አንድ ለእናቱ ለኢትዮጵያ
የስንፍናን ራሶች ቀጥቅጠህ ሰዋስዋቸውን

ለኢትዮጵያ ሰዎች ልጆች የሰጠሃቸው አንተ ነህ፡፡) ይህ ቅኔ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በሃያኛው ምእት ዓመት ጎልተው ለታዩት ታላቁ ደራሲ፣ የአማርኛ ሰዋሰው አዘጋጅ፣ የሥነ ጽሑፍ ሰውና የታሪክ ተመራማሪ ለሆኑት ለብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (1891 - 1971) የተቀኙት ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኰንን አዳራሽ በአምሀ መርስዔ ኀዘን አዘጋጅነት ለእይታ በበቃው የብላታ መርስዔ ኀዘን "የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት" መጽሐፍ ምረቃ ላይ የተለያዩ ምሁራን አስተያየቶች ከአዲስ አበባና ከአሜሪካ ቀርበው ነበር፡፡

ከአሜሪካ በጽሑፍና በቪዲዮ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንደገለጹት፣ ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ለኢትዮጵያ የሰጡትን ልባዊ አገልግሎትና እሳቸውን በአካል የሚያውቅ ሰው በየምእት ዓመት አንድ ጊዜ የሚታዩ የዕውቀትና የጥበብ ሰዎች ካሉ ክቡርነታቸው አንዱ መሆናቸውን አይጠራጠርም፡፡

ብላታ የተገኙበት ዘመን ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም በይበልጥ የተገናኘችበት ዘመን መሆኑን ያወሱት ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ የአማርኛ ሰዋስው መጻሕፍታቸው የምዕራቡን ምርምር በሀገራዊ ሥርዓት ለማስተናገዳቸው ጉልሕ ምሳሌ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ፕሮፌሰሩ አያይዘውም ብላታ "በአማርኛ ስምንት የንግግር ክፍሎች አሉ" ብለው ሲያስተምሩን የአማርኛን ሰዋሰው ከአባቶቻቸው ሊቃውንት በወረሱት የግእዝ ሰዋስው ስልትና በምዕራባውያን ምርምር መመገባቸው ነው፡፡ ሰዋሰው እንደ ቁጥር ሎጂክ መሆኑን ያልተገነዘቡ ሰዎች የእንግሊዝኛን ሰዋስው ለአማርኛ እንዳወረሱ ይቆጥሯቸዋል፡፡  ሰዋስው ሀገር የለውም፤ ሰዋስው ማለት "መሰላል" ማለት ነው፤ ለምን መሰላል እንደተባለ የሚያውቁት ያበደሩን ዐረቢኛ የሚናገሩ ቅብጢዎች መሆናቸው የጠቆሙት ፕሮፌሰር አሁን ደግሞ ዓለም የሚከተለው (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም) የአሜሪካዊውን የናሆም ቾምስኪን ሰዋስው ሆኗል ብለዋል፡፡

የብላታ ሌላው ዐቢይ አስተዋጽኦ ጵጵስናን ከግብጽ ማስመጣታቸው ነው፡፡ ይህንንም ፕሮፌሰር በየታሪክ ማስታወሻቸው ያትቱታል፤ እንዲህ ሲሉ "ብላታ መርስዔ ኀዘን እንደትልቁ አጎታቸው እንደ አለቃ ገብረ ክርስቶስ ስለጵጵስና ጉዳይ ግብጽ ሄደው ነበር፡፡ ግን በሁለቱ መካከል ታላቅ ልዩነት አለ፤ አለቃ ገብረክርስቶስ ግብጽ የወረዱት ጳጳሳት ለማምጣት ስለነበረ የሰጧቸውን ይዘው ተመልሰዋል፤ ብላታ የሄዱት ራሱን የጵጵስናውን ሥልጣን ለማምጣት ስለነበረ የሰጧቸውን ሳይሆን የፈለጉትን ይዘው በድል አድራጊነት ገብተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ጳጳስ ለማስመጣት ወደ ግብጽ ልኡካን መላክ የተለመደና የተደጋገመ ነበር፤ ከልኡካኑ ውስጥ አንዳቸውም የሆነውን በጽሑፍ አላቆዩልንም፤ ብላታ ግን በነበሩበት ተልእኮና ውጤቱ ግን በብላታ ብዕር በዝርዝር ተመዝግቦ ከስማቸው ጋር ለዘለዓለም ነባር ሆኗል፡፡

"የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፤ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት፣ 1896 - 1922" በሚል ርእስ በአንድ ጥራዝ የታተመው መጽሐፍ በረቂቅ ደረጃ በነበረበት ጊዜ አቀራረቡ በሦስት ቅጽ ሆኖ "የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፤ ካየሁትና ከሰማሁት"፣ "የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት፤ ካየሁትና ከሰማሁት"፣ "የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት፤ ካየሁትና ከሰማሁት" በሚሉ ርእሶች የቀረበ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አማካይነት የታተመው አዲሱ እትም 36 ገጾች ቅድመ አካል፣ 410 ገጾች ደግሞ የመጽሐፉ አካል፣ 43 ገጾች ድኅረ አካል በድምሩ 489 ገጾች አሉት፡፡ መጽሐፉ በተጨማሪ ስድሳ ገላጭ ፎቶግራፎችንና ሁለት ካርታዎችን አካትቷል፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት በደራሲውና በመጽሐፉ ላይ ቀዳሚውን አስተያየት የሰጡት የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽ፤

ብላታ መርስዔ ኀዘን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እናት ከሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፈለቁ ምሁር ናቸው፡፡

በሥነ ጽሑፍ ረገድ ባገራችን የታየው ሥራ መሆን ነበረበት ብለን ከምንገምተው ጋር ሲተያይ እጅግም ቢሆንም ብላታ መርስዔ ኀዘን በግላቸው ያበረከቱት መጻሕፍት በኢትዮጵያ ጥናት ላይ ለሚተጉ ምሁራን ለታሪክ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ያዘለው  የዕውቀት በረከት የላቀ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የግል ታሪክና ትውስታ (ሜሟር) መጻሕፍት ለማሳተም የተያዘው ሥራ ሊበረታታና ይበል ሊባል የሚገባው ተግባር መሆኑን ያሳሰቡት ደጃዝማች ዶክተር ዘውዴ፣ በቅርቡ የታተሙት አንዳንዶቹ፣ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ተጽፈው ለሕትመት ባለመብቃታቸው የተነሳ ከተወሰኑ የምርምር ሰዎች በስተቀር ለቀረው አንባቢ መድረስ እንዳልቻሉ፣ ከእነዚህም መካከል የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት "ኦቶባዮግራፊ (የሕይወት ታሪክ"፣ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ "የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል"ና የብላታ መርስዔ ኀዘን ሥራዎች እንደሚገኙበትና፡፡ እነዚህ ሥራዎችም ከረዥም ዘመን የብቸኝነት ዓለም ተላቀው በአብዛኛው አንባቢና ምርምር ሰዎች እጅ መግባት መቻላቸው በጣም እንደሚያስደስት ገልፀዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ጋዜጣ በ1917 ዓ.ም ሲመሠረት የድርጅቱ ዋና ፀሐፊና በልዩ ልዩ አርዕስት ጥናቶች እያዘጋጁ በማሳተም የተሳተፉት ብላታ የተፈሪ መኰንን ት/ቤት ሲቋቋም  የአማርኛ መምህር ሆነው በማገልገል እያሉ የአማርኛ ሰዋሰው ማዘጋጀታቸው ዐቢይ ነገር መሆኑና አሁን የታተመው መጽሐፍ ደራሲው ያዩትንና ሌሎች የነገሯቸውን መሠረት በማድረግ በመሆኑ ታሪካዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

ደጃዝማቹ ከመሰጣቸው ታሪክ ውስጥ አቤቶ ኢያሱ ከአዲስ አበባ ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ወደ ሐረር እንደሄዱ የምክሩ ተካፋይና የአቤቶ ኢያሱ ባለሟል የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን ጠይቀው የነገራቸውን መዝግበዋል፡፡

አቤቶ ኢያሱ አዳል በረሃ ሳሉ ተከታዮቻቸው ከፈረንሳይ ወይም ከኢጣልያ መንግሥት መሣሪያ ለማግኘት ብንላላክ ይሻላል ቢሏቸው፣ "እኔ ወደ ፈረንጆች ተጠግቼ ለአንዱ ብፈርም አገሬን መሸጤ ነው፤ ብዙ ዘመን ተከብሮና ተፈርቶ የኖረውንም የኢትዮጵያ መንግሥት ማዋረዴ ነው፡፡ አሁን መንግሥቱን የያዙት እህቴና ወንድሜ ናቸው እንጂ ባዕድ አልቀማኝም"  ማለታቸውን ዘግበዋል፡፡

ብላታ በመጽሐፋቸው የማኅበረሰብ ሁኔታዎችንም በተመለከተ አዶ ከበሬ እንዴት እንደተስፋፋ፣ በእጣን ታጅቦ ቡና የመጠጣት ባህል መቼና እንዴት በከተማ እንደተለመደ፣ የሙጀሌ፣ የጣጣቴ፣ የኅዳር በሽታ አመጣጥ፣ ምክንያቱ ሳይታወቅ በ1911 ዓ.ም ከግንቦት 11 ቀን እስከ ግንቦት 21 ቀን በአዲስ አበባ ላይ የታየው የመዓት ቃጠሎ የመሳሰሉትን በመግለጽ የታሪኩን አድማስ ማስፋፋታቸው ከተለመደው ታሪከ ነገሥት አጻጻፍ የተለየ እንደሚያደርገው ደጃዝማች ያስረዳሉ፡፡

ሁለተኛው ተናጋሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባሕሩ ዘውዴ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የዳበረ ሥነ ጽሑፍ ያላት አገር እንደመሆኗ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከሚታየው ከፍ ባለ ደረጃ በአገር ቋንቋ ተጽፈው ሲተረኩ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ዜና መዋዕሎች መሆኑን ያወሱት ፕሮፌሰሩ ከ14ኛው ምእት ዓመት ከአፄ ዐምደ ጽዮን አንስቶ እስከ 20ኛው ምእት ዓመት አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ ዜና መዋዕሎች ተዘጋጅተው ቀርበዋል፡፡ አብዛኛዎቹ በግእዝ ሲሆኑ ከ19ኛው ምእት ዓመት ወዲህ፣ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ በአማርኛም መቅረብ ጀምረው የመጨረሻው የጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ የአፄ ምኒልክ ዜና መዋዕል ነው፡፡ ዜና መዋዕሎች በመኖራቸው አገራዊ ታሪክ መጻፍ መቻሉን ያስረዱት ፕሮፌሰሩ፣ በተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች መተርጐማቸው ታሪካዊ ፋይዳቸው እንዲጎላ አድርጓል፡፡ ከ20ኛው ምእት ዓመት ወዲህ ዜና መዋዕል እየከሰመ ሲመጣ በምትኩ ትዝታዎች መውጣት ጀምረዋል፡፡

አገራዊ ሰነድ በሚፈለግበት ጊዜ የውጪውን ሰነድ ሊያርቅ የሚችል፣ ሙሉ ለሙሉ በውጪው ላይ እንዳንመካ የሚያደርገን የብላታ መርስዔ ኀዝን መጻሕፍት መሆናቸው የጠቆሙት ፕሮፌሰር ባሕሩ፣ ከብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ መጽሐፍ "ዝክረ ነገር" ጋር የ20ኛውን ክፍለ ዘመን መባቻ ከኢትዮጵያውያን አንፃር ለመግለጽ አገልግሎት የሰጡ መሆናቸውን ያወሳሉ፡፡

የብላታ ሦስት ቅጽ መጻሕፍት በየዓመቱ የነበሩ ድርጊቶችና ክንዋኔዎች በሚያስደንቅ ምልአትና ጥንቃቄ ተዘግበው ይገኛሉ፡፡

የመጽሐፉ አደረጃጀት ጠቃሚ ገጽታ ደራሲው በየዓመቱ ከነበሩት ዋና ዋና ክንዋኔዎችና ድርጊቶች ባሻገር የታሪኩ እምብርት ባይሆኑም ከተለያየ አንፃር ታሪካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሁኔታዎች ባጭር ባጭሩ መተረካቸው ነው፡፡

ፕሮፌሰር ባሕሩ እንደገለፁት ባንድ ቅጽ ተጠቃልለው ለኅትመት የበቁት የብላታ መርስዔ ኀዘን ትዝታዎች የሀገራችንን የሃያኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ አሠርት ዓመታት በዝርዝር ለማወቅ ለሚሻ አንባቢ ትልቅ የታሪክ ድግስ ናቸው፡፡

በአገራችን ብዙ ጊዜ የማይገኝ ማኅበራዊ ታሪክን በመተረክ ተጠቃሽ መጽሐፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሥነ ጽሑፍና የፎክሎር ባለሙያው ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ናቸው፡፡ የብላታ መጽሐፍ በአጫጭር ዐረፍተ ነገሮች ተለጣጣቂነትና የነገሩን ተጠየቅ አጣጥሞ ለአንባቢ በማያነቅፍ ሰተት ብሎ በሚፈስ ግልጽ መንገድ መጻፍ አንድ ራሱን የቻለ ተክህኖ የሚገልጽና የገለጻ ችሎታቸውም በብዙ ቦታ እንደሚታይ በተለይም የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የንግሥ በዓል አከባበር ገለጻ ልዩ ችሎታ ነው፡፡

በአማርኛ የተጻፉትን ጥንታዊ ጽሑፎች፣ ዜና መዋዕሎች አዕምሮና ብርሃንና ሰላምን በመሳሰሉ ቀደምት ጋዜጦችና መጻሕፍት ውስጥ የነበረውን የቋንቋ አጠቃቀም እስከ ዛሬ ሙያዬ ብሎ የምር ያጠና እንዳላጋጠማቸው የገለጹት ዶ/ር ፈቃደ፣ አንድ ቋንቋ ከምን ተነስቶ እምን እንደደረሰ እየተከታተለ በቃላዊና በጽሑፋዊ መረጃ ላይ በየጊዜው እየተመረኮዙ ካላጠኑትና አካሄዱን በውል ካልመዘገቡት ሳይንሳዊ ዕውቀትን፣ ረቂቅ መንፈሳዊና ዓለማዊ ሐሳቦችንና ስሜቶችን ለመግለጽ ወደሚችልበት ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ባጭሩ ቋንቋውን ለማልማት የሚደረገው ጥረት ሁሉ በነሲብ መጓዙ እንደሚቀጥል አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡

እንደ ዶክተር ፈቃደ ማጠቃለያ አስተያየት ሦስቱን የብላታ ትዝታዎች ሳነብ ያስደሰተኝ ማኅበራዊ ታሪክ መያዛቸው ነው፡፡ የታሪክ ከፍተኛ ጉጉት ሰዎች ምን በሉ? ጠጡ? ምን ውስጥ ኖሩ ወዘተ. ሰዎች ምን አሰቡ? ተመኙ? አዲስ ነገር እንግዳ ነገር ሲመጣ ምን ተናገሩ? ምን አደረጉ ወዘተ. እያሉ ማሰብ የታሪክ ፍላጎት ነው፡፡

የብላታ መጽሐፍ ውስጥ እነዚህ ነገሮች ነቅሶ ለማውጣት ብዙ ነገሮች አሉበት፡፡ ባህልን በሚመለከት ግጥሞች፣ ተረቶች፣ ወጎች፣ ቀልዶች በመጽሐፉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በቃል ሲናገሩ ዐውዳቸው አይታወቅም፡፡ ብላታ ግን ሰማሁ፣ አየሁ እያሉ ሲነግሩን ለብዙዎቹ ዐውድ መስጠታቸው ለሥነ ቃል ጥናት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በዘመኑ ስለ ታየ እንግዳ ነገር

• በዚህ ዘመን (1907 ዓ.ም) "አዶ ከበሬ" የተባለ የዛር ዓይነት በሽታ በሸዋ ባላገር ላይ ተናኝቶ ሴቱንም ወንዱንም ያስጨፍረው ጀመር፡፡ በሽታው ከትግሬ የመጣ ነው ስለሚባል በሽተኛው የትግርኛ ዓይነት እየተናገረ ይቀባጥራል፡፡ በሽታውንም ለመሸኘት ድግስ መደገስ ስለሚያስፈልግ ድኻው ሕዝብ ባለጣጣ ሆነ፡፡
• ዳግመኛ "ሞያሌ" የተባለ በእግር ላይ የሚገባ የቁንጫ ዓይነት በሽታ በዚህ ዘመን ስለመጣ የሁሉም እግር በወረንጦ ሲዘነጠል ይውል ጀመር፡፡ ስሙ ሞያሌ መባሉ በሽታው የመጣው በቦረና ውስጥ ካለው ሞያሌ ከተባለው ስፍራ በመሆኑ ነው እየተባለ ይነገር ነበር፡፡
• "ጣጣቴ" የተባለ በሽታ ደግሞ በዚሁ ዘመን መጣ፡፡ የትኩሳት በሽታ ነው፡፡ የዣንጥላ መገንተሪያ ብረት በእሳት አግሎ የበሽተኛውን ገላ በተኰሱት ጊዜ ይንጣጣ ነበርና ከዚህ የተነሣ የበሽታው ስም ጣጣቴ ተባለ፡፡
• ዕጣን እየተጨሰ ቡና የመጠጣት ልማድ በሸዋ ባላገር ዘንድ የተጀመረው በዚሁ ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ይህ ዓይነት ልማድ የሚታየው በነጋዴዎችና በእስላሞች በተለይም በቃልቾች ዘንድ ነበር፡፡ በበረሃ ስፍራ የሚኖሩ ነፍጠኞችም የዚሁ የቡና ሱስ አለባቸው፡፡ እነዚያ ነፍጠኞች ወይም ነጋዴዎች ወደ አገር ቤት በተመለሱ ጊዜ ዕጣን እያጨሱ ቡና ይጠጡ ነበርና ሌላው ሰው እነርሱን አይቶ ተከተለ፡፡ ይልቁንም የየመንደሩ ሴቶች የቡና ወንፈል እያበጁና ተራ በተራ እየተጠራሩ ቡና ሲያፈሉና ሲጠጡ መዋል ጀመሩ፡፡ ይህ ልምድ በባላገር ሆነ በከተማ እየተስፋፋ ስለ ሄደ ብዙ ሰው የቡና ሱሰኛ ሆነ፡፡ የቤተ ክህነት ሰዎችም በቤተ ክርስቲያን የሚጨሰውን ዕጣን ለቡና ማጨስ አምልኮ ባዕድ ነው እያሉ ተቃውመውት ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ውሎ አድሮ እየተለመደ ሄደ፡፡

ከመፅሃፉ የተወሰደ

በሔኖክ ያሬድ

 
< Prev   Next >