Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow የሦስት ትውልድ የሥዕል ቅብብሎሽ
የሦስት ትውልድ የሥዕል ቅብብሎሽ Print E-mail
Sunday, 27 January 2008

በቅርቡ በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ሃርን ሙዚየም አማካኝነት የኢትዮጵያውን ሠዓሊያን የሥዕል ሥራዎች በአሜሪካ ለኤግዚቢሽን ቀርበው ነበር፡፡ "ኮንቲኒዩቲ ኤንድ ቼንግ ስሪ ጄኔሬሽንስ ኦፍ ኢትዮጵያን አርቲስትስ" በሚል ርዕስ የቀረበውን የሥዕል ኤግዚቢሽን አስመልክቶ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ዶ/ር ርቤካ ናጅ እና ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ራስ መኮንን አዳራሽ ገለፃ አድርገው ነበር፡፡

ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚያስረዳው ዘመነ ኃይለሥላሴ፣ ዘመነ ደርግና ድህረ ደርግ በሚል ተከፋፍሎ የ23 ኢትዮጵያዊያን ሠዓሊያን ሥራና የህይወት ታሪክ ቀርቧል፡፡ እኛም የሦስቱን ዘመን አርቲስቶች ማንነት ለማየት የተወሰኑትን መርጠን አቅርበናል፡፡

እስኩንድር ቦጐስያን

በኢትዮጵያ የሥዕል ጥበብ ውስጥ ፈር ቀደዋል ከሚባሉት አገኘሁ አዳነ፣ አለ ፈለገ ሰላም ገብረክርስቶስ ደስታ እና አፈወርቅ ተክሌ የዕድሜ ዘመን የሚመደበው እስክንድር ቦጐስያን የተወለደው በ1930 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው፡፡ ሥዕልን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከተፈሪ መኰንን ት/ቤት የተማረው እስክንድር በ1948 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ነበር፡፡ ባቀረባቸው የሥዕል ኤግዚቢሽኖች ለሽልማት ከበቃ በኋላ የውጭ ትምህርት ዕድል በማግኘት ወደ እንግሊዝ በማቅናት በሴንት ማርቲን ስኩል፣ በዘ ሴንትራል ስኩል እና በዘ ሰላድ ስኩል የፋይን አርት ትምህርት አጥንቷል፡፡

ከእንግሊዝ ትምህርቱ በኋላ ወደ ፓሪስ በመሄድ ዘ አኮለ ናሽናሌ ስፔርየር ዲ ቢዩአክስ እና አካዳሚ ዲ ላ ግራንድ ቹሜሬ በተሰኙ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች ተምሯል፡፡ በፓሪስ ቆይታው ብዙ ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው በካፌዎች፣ በጃዝ ክለቦች፣ በሙዚየሞች፣ በአርቲስቶች ስቱዲዮ አካባቢ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ፖለቲከኞችና ታዋቂ የፈረንሳይ ፈላስፎች ጋር ነበር፡፡ በመሆኑም ፓን አፍሪካኒዝም በውስጡ እንዲሰርፅ ምክንያት ሆኖታል፡፡ በዚህም የተነሳ የአፍሪካውያን የሥነ ጥበብ ዓይነቶችን አጠና፡፡

በፓሪስ ቆይታውም ካልዲዮስኮፒክ በመባል የሚታወቀውን የቀለምና ዲዛይን ጥበብ በመጠቀም ስለ አፍሪካዊነትና ኢትዮጵያዊነት የሚሰማውን የውስጡን ስሜት አንፀባርቋል፡፡

በ1959 ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥዕል ትምህርት ቤት ለሦስት ዓመት ያህል አስተምሯል፡፡

በዋሽንግተን ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር (መምህር) ሆኖ ከ1964 እስከ 1994 ያገለገለ ሲሆን የስዕል ሥራዎቹ ፓሪስ ውስጥ በሚገኘው ሚዩዜ ዲ አርት ዴላ ቪሎ ዴ ፓሪስ እና ኒዮርክ በሚገኘው ሙዚየም ኦፍ ሞደርን አርት እንዲሁም በአፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያንና በሌሎች የአሜሪካ ሙዚየሞች ተሰባስበው በብዙ ሰዎች ተጐብኝተዋል፡፡

ከሥራዎቹ ውስጥ ፓሪስ እያለ የሳለው "ናይት ኦፍ ድሪድ ኤንድ ዲላይት" እና ሆዋርድ ዩኒቨርሲቲ በሚያስተምርበት ወቅት የሳለው "ዘ ኢንድ ኦፍ ቢግኒንግ" የተሰኙት ሥራዎቹ ተወዳጅነትን ያተረፉለት ናቸው፡፡ 

እስክንድር ቦጐስያን በ1996 ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

ዮሐንስ ገዳሙ

በዘመነ ኃይለስላሴና በዘመነ ደርግ መሃል እንደ ድልድይ ነው የሚባለውና በደርግ ዘመን ከተፈጠሩ ሠዓሊያን አንዱ የሆነው ዮሐንስ ገዳሙ ውልደቱም እድገቱም አዲስ አበባ ነው፡፡ በ1960 ዓ.ም ከአዲስ አበባ የሥዕል ት/ቤት የተመረቀው ዮሐንስ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዲዛይነርነትና በስክሪን አርቲስትነት የሠራ ሲሆን ጐንደር ውስጥም በመምህርነት አገልግሏል፡፡

የቀስተ ደመና ሥነ ጥበብ ድርጅትና ጋለሪ ከመከፈቱ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ለሁለት ዓመታት በግራፊክ ዲዛይነርነት ሙያ ሠርቷል፡፡ ወደ ኬንያ በማምራትም በሞምባሳ ለአምስት ዓመታት የግራፊክ ዲዛይነርነት ሥራ ሠርቶ የተመለሰው ዮሐንስ ገዳሙ ከኬንያ ቆይታው በኋላ በቀጥታ ወደ ጀርመን አቅንቶ አርአያየና መምህሬ የሚለው ገብረክርስቶስ ደስታ ከተማረበትና ኰሎኝ በሚገኘው ወርክስኩሌ ፈር ቢልደንዴ ኮንሴ አንድ ጉስታልተንግ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡

ከ1973 እስከ 1980 ኰሎኝ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ሠዓሊ ሆኖ ከሠራ በኋላ በ1981 ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የሥዕል ሥራውን እያጧጦፈ ቀጠለ፡፡ በጐተ ኢንስቲትዩትም ሌክቸር በመስጠት የሚታወቀው ዮሐንስ በተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የዩናይትድ ስቴትስ ሙዚየሞች ስዕሎችን ለእይታ አብቅቷል፡፡

ዮሐንስ ገዳሙ በአብስትራክት ስዕሎች የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡ በሊላ ጋለሪ ሥዕሎቹን ለእይታ አቅርቦ ነበር፡፡

በቀለ መኰንን

በደርግ ዘመን ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይተዋል ተብለው በሪፖርቱ ከቀረቡት ከነ ደስታ ሃጐስ፣ ልዑል ሰገድ ረታ፣ ዮሐንስ ገዳሙ፣ ዘሪሁን የትምጌታ፣ ጥበብ ተረፋ፣ አብዱራህማን ሸሪፍ፣ እሸቱ ጥሩነህ፣ ታደሰ መስፍን፣ ብስራት ሽባባው፣ ጌታ መኰንን መዝገቡ ተሠማ፣ በሃይሉ በዛብህ፣ አዲሱ ወርቁና ኤልሳቤጥ ሃብተወልድ መካከል በቀለ መኰንን በቀራፂነት የተመደበ ነው፡፡

በቀለ መኰንን በደርግ ዘመን ሠዓሊያንና በድህረ ደርግ አርቲስቶች መካከል የሚገኝ በመሆኑ የሁለቱ ዘመናት ተፅዕኖዎች እንደሚስተዋሉበት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ደብረ ዘይት ውስጥ በ1957 የተወለደው በቀለ ከአዲስ አበባ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በ1976 በቅርፃ ቅርፅ በዲፕሎማ የተመረቀ ሲሆን ከተመረቀበት እስከ 1980 ድረስ በዚያው ትምህርት ቤት መምህር ሆኖ ሠርቷል፡፡

ሞስኮ በሚገኘው ሲርኮቭ ስቴት አካዳሚክ ኢንስቲትዩት ኦፍ አርት ከ1981 እስከ 1986 ተምሯል፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የቅርፃ ቅርፅ መምህር ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡

በቀለ መኮንን ከ1993 እስከ 1996 የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ሆኖ የሠራ ከመሆኑም ባሻገር የዳይሜንሽን ግሩፕ መስራች አባል ሆኖ ከ1988 እስከ 1994 ድረስ የቡድን ኤግዚቢሽን አሳይቷል፡፡ በውጭ አገር የመጀመሪያው የሆነውን የግሉን ኤግዚቢሽን ኪፕዮ በሚገኘው የፊንላንድ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባና በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት ሥራዎቹን ለእይታ አብቅቷል፡፡

በቀለ በችካጐ አርቲስትስ ኢንተርናሽናል ፕሮግራም አዋርድ ያሸነፈ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሲሆን በቅርፃ ቅርፅ የሚያሳየው የፖለቲካ ትችም ተወዳጅነትን አትርፎለታል፡፡ በጣሊያን፣ በኦሃዮ፣ በሜሪላንድና በተለያዩ ኢንስቲትዮቶች የተሳተፈ ሲሆን የሚሌኒየሙን አርማ የሰራም አርቲስት ነው፡፡

ኤልያስ ስሜ

በድህረ ደርግ ብቅ ካሉና ተስፋ ከተጣለባቸው ወጣት አርቲስቶች የተመደበው ኤልያስ የሦስቱ ዘመን የሥዕል ሥራ ቅብብሎሽ ተረካቢዎች መካከል አንዱ ነው ይላል ሪፖርቱ፡፡

ኤልያስ ስሜ የተወለደው አዲስ አበባ ሲሆን በ1983 በግራፊክ አርትስ ዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ዘሪሁን የትም ጌታ ለኤልያስ ስሜ ፈር ቀዳጅ መምህሩ እንደሆነ ያመለከተው ሪፖርቱ የመጀመሪያው የሆነውን የግል ኤግዚቢሽኑን ያቀረበው በ1986 በአሊያንስ ኢትዮፍራንሴስ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ከዘመነ ኃይለሥላሴና ዘመነ ደርግ ሠዓሊዎች የተሻለ የሥዕል ሥራ ነፃነት በሥራቸው ይስተዋልባቸዋል የሚባሉት የድህረ ደርግ ሠዓሊያን ተፅዕኖ በኤልያስም አርፎበታል፡፡ በራሱ ስቱዲዮ የሚሠራው ኤልያስ የገቢ ምንጩም በሥዕል ሥራዎቹ የተመሠረተ መሆኑን ከሪፖርቱ መረዳት ይቻላል፡፡

በዞማ ኮንቴምፓራሪ አርት ሴንተር በ1995፣ በብሔራዊ ሙዝየምና በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የሥዕል ሥራዎቹን ለእይታ ያበቃው ኤልያስ ከአሠፋ ገብረኪዳን ጋር በመሆን 28 የአፍሪካ አገር አርቲስቶች የተካፈሉበትን የ1997ቱን የሴኔጋል ዳካር የሥዕል ኤግዚቢሽን ተካፍሏል፡፡ ከዚያ በኋላ ቬና ላይ በተካሄደ ኤግዚቢሽን ለመካፈል ችሏል፡፡

በደመቀ ከበደ

 
< Prev   Next >