| ሕገ ወጥነት |
|
|
| Sunday, 27 January 2008 | |
|
በቅርቡ እንደሰማነው በ1999 ዓ.ም የበጀት ዓመት አገሪቱ ከ44 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ እቃዎችን ወደ አገር ውስጥ አስገብታለች፡፡ የግዥ መጠኑ ቀደም ካሉት አመታት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡ ይህ አሃዝ አገሪቱ የምታስገባቸው የሸቀጦች፣ የመሳሪያዎችና የሌሎች ምርቶች መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆንን ብቻ ሳይሆን ምን ያህል በውጭ ምርቶች ተገልጋዮች እንደሆንን ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ተፈላጊ ናቸው ብለን የምናምንባቸውና ብዙ ተገልጋዮች እንዳላቸው የሚጠቀሱ የውጭ ምርቶች አምራች ኩባንያዎች እዚህ ወኪል በማስቀመጥ ምርቶቻቸውን እንደ ልብ ሲልኩም እናያለን፡፡ ይሁን እንጂ ህጋዊ ውክልና ተሰጥቷቸው የተለያዩ ምርቶች በቀጥታ ከውጭ በማስገባት (የጥራት ደረጃቸውን እየጠበቁ) ይሸጣሉ ቢባልም በጎን እነዚህኑ ምርቶች አስመስለው በመስራት ወይም አቃፊ እቃዎቻቸውን በጥንቃቄ በማስቀመጥ የተለወጡና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን በመክተት ሸማቹ እንዲገበይ የሚያደርጉ ህገወጦች ተበራክተዋል፡፡ እንደምሳሌ አንድ ሁለቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብዙው ኅብረተሰብ ከሚጠቀምባቸው የሣሙና ምርቶች እንጀምር፡፡ እነዚህ የሳሙና ምርቶች በተለያየ ስያሜ ከውጭ የሚገቡ ቢሆንም የተወሰኑት በሸማቹ ተቀባይነት አግኝተው በተደጋጋሚ የሚገዙ ናቸው፡፡ ተቀባይነት ካላቸው ምርቶች ውስጥ የተወሰኑትን እዚሁ በህገወጥ መንገድ በማምረት በስማቸው ሲሸጡ መታዘብ ይቻላል፡፡ ይህንንም ደፍሬ ለመናገር ያስገደደኝ በቤት ውስጥ ለልብስ ማጠቢያነት እንጠቀምበት የነበረው ሳሙና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደቀድሞው አይነት ደረጃው ሊያፀዳ አለመቻሉንና እጅ ላይም ባልተለመደ መልኩ መጣበቁን ስመለከት ሳሙናው ትክክል አለመሆኑን በመረዳቴ ነው፡፡ ችግሩ ቢታየኝም ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር፡፡ ነገሩ እየከነከነኝ እያለሁ በመገናኛ ብዙሃን እጠቀምበት የነበረው ሳሙና ስም በህገወጥ መንገድ ተመርቶ ገበያ ውስጥ እየገባ ስለመሆኑ ስሰማ ጥርጣሬዬ ትክክል መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ከሳሙና ሌላ በቅርብ የታዘብኩትን ሌላም መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ይህም የኮምፒዩተር ፕሪንተር ቀለምን (ቶነር) ይመለከታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብዙ ቦታዎች በኮምፒዩተር የመገልገል ልምድ እየተስፋፋ በመምጣቱ የቶነር ገበያ እንዲደራ አድርጎታል፡፡ ይህም ለህገወጦች በር ከፍቷል፡፡ ነገሩ የከነከነኝና ለምን እነዚህን ካርቶኖችና ያለቀለካቸው የቶነር እቃዎች በዚህ ዋጋ እንደሚገዛ ሳጠያይቅ ያገኘሁት መልስ አንዳንድ ቶነርና የኮምፒዩተር እቃዎችን የሚጠሹ መደብሮች እርሱ ከገዛበት ዋጋ በላይ በመስጠት ካርቶኑንና ቶነሩ ያለበትን እቃ የሚረከቡትና እነርሱም በእቃ ውስጥ ኦርጅናል ያልሆነ ቶነር ሞልተው አሽገው በውድ ዋጋ የሚሸጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ነገሩም የተለመደ ሆኗል፡፡ ሸማቾች እነዚህን እቃዎች ሲገዙም የቶነሩ እቃ ውስጥ የተሞላውን ሳይሆን የሚያዩት ካርቶኖቹንና እቃውን ስለሚሆን ያለ ጥርጥር ገዝተው ይሄዳሉ፡፡ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎችን ብዙ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ባለቀላቸው የሽቶና የቅባት እቃዎች መንደር ውስጥ በተሞሉ ለጤናም ጭምር ጠንቅ የሆኑ መሰል ምርቶች ተጭምሮባቸው እየተሸጩ ስለመሆኑም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እቃዎቹ ኦርጅናል በሚለው ካርቶን የሚታሸጉ በመሆናቸው ሸማቹ አይጠረጥርም፡፡ ነገር ግን የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት ሳይሰጡ ወይም ጤነነቱ ላይ ችግር ሲፈጥር ይታያል፡፡ እንደ ቶነሩ አይነት ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ብሮች የወጡበትን ንብረት ሊያበላሽ ይችላል፡፡ ምርቶችን አስመስሎ በማቅረብ የሚዘወተረው በአንድ ወይም ሁለት ምርቶች ላይ ሳይሆን በብዙዎች ላይ ነው፡፡ ድርጊቱን ለመቆጣጠርም እየተደረገ ስላለው ጥረት በቂ መረጃ የለም፡፡ ጉዳዩ አሳሳቢ ስለሆነ ይመለከተኛል የሚለው አካል ትኩረት እንዲሰጥበት ማስታወሱ ጠቃሚ ነው፡፡ ጎን ለጎን ሸማቾችም ማድረግ የሚገባቸውን መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ የዕቃ ማሸጊያ ካርቶኖችና የጋለገሉ ዕቃዎች በድጋሚ አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ ሸማቾችም ሊተባበሩ ይገባል፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |