Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የኢጋድ የሚኒስትሮች ቡድን ወደ ኬንያ ይሄዳል
የኢጋድ የሚኒስትሮች ቡድን ወደ ኬንያ ይሄዳል E-mail
Wednesday, 30 January 2008
Image
አቶ ሥዩም መስፍን
“የኬንያና የኢትዮጵያ ምርጫ አይገናኝም”
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሥዩም መስፍን
የኬንያ ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ የሚረዳ የኢጋድ የሚኒስትሮች ቡድን ወደ ናይሮቢ እንደሚጓዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሥዩም መስፍን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ “የኬንያና የኢትዮጵያ ምርጫም አይገናኝም” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በኬንያ የሚታየው ግጭት ከፖለቲካ ድንበር የዘለለ መሆኑንና በዘር ላይ ተመስርቶ እየተካሄደ ያለው ጭፍጨፋ ለኬንያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ችግር የሚፈጥር መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሥዩም መስፍን ገልፀው፣ የኢጋድ የሚኒስትሮች ቡድን ችግሩን ለመፍታት በጉዳዩ ላይ መነጋገሩን ገልፀዋል፡፡ የኢጋድ የልኡካን ቡድንም ወደ ኬንያ ሄዶ የሰላም ድርድሩን ማገዝ የሚችልበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡

ኬንያ ላለፉት አስር ዓመታት የክልሉ የሰላም ማዕከል ሆና ብዙ ድጋፍ ስትሰጥ መቆየቷን የጠቆሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሰላም አስተናጋጅ ሆና ስትሰራ የቆየችው አገር ግጭት ውስጥ መግባቷ በክልሉ አደጋ እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡ በኬንያ የተፈጠረው ችግርም ከኬንያውያን ቀጥሎ የክልሉን አባል አገራትና ሕዝቦች እያደማ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“የተደራረበ ኃላፊነት መውሰድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዲያመዝን ያደርጋል የሚል እምነት አለን” ያሉት አቶ ሥዩም የቀድሞው የተመድ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን በኬንያ የመሩት ቡድን በሰላም ድርድሩ ጥሩ ሥራ እየሠራ ቢሆንም ኢጋድም እንደ ክልል ጥረት ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ስዩም እንዳሉት የኬንያ መንግሥት የጋራ መንግሥት ማቋቋም እንችላለን የሚል እምነት አለው፡፡ የተቃዋሚው መሪ ሚስተር ኦዲንጋ በበኩላቸው ችግሩን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልፁም እንደገና አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የሚፈልጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኬንያ መንግሥትና ተቃዋሚ ፓርቲው ከተስማሙ የጥምረት መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል እድል መኖሩን የጠቆሙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሁለቱ ወገኖች የጥምረት መንግሥት ለመመስረት ከተስማሙ በሚተማመኑበት ጊዜ ምርጫ የሚጠሩበትን መንገድ ማመቻቸት ይቻላል፡፡

ምርጫን ተከትሎ በኢትዮጵያና በኬንያ ስለተፈጠረው ግጭት ሲናገሩም “የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰረታዊ ጉዳይ ከፖለቲካ ባሻገር የአገርን ጥቅም ማየት መሆን አለበት” ብለዋል፡፡

ምርጫ ሁልጊዜ ውዝግብ ሊያስከትል እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ሥዩም አሜሪካኖች የገጠማቸውን የምርጫ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ መፍታታቸውን፣ ኢትዮጵያም ለሰላም ስትል የወርቅ እንቁላል የምትጥለውን ዶሮ ከማረድ ወደ ኋላ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ አያይዘውም “አሁን ያልተመረጠ ፓርቲ ነገ ሊያሸንፍ ይችላል፤ ህግና ህገመንግሥትን ብቻ ተከትሎ መሄድ አስፈላጊ ነው” በማለት በብጥብጥ በደም መፋሰስና በግጭት ህግና ስርዓትን መለወጥ እንደማይቻል አብራርተዋል፡፡ የኬንያም የምርጫ ችግር ከህግና ስርዓት ውጭ ሊረታ እንደማይችል አመልክተዋል፡፡

አሁን በኬንያ ለተፈጠረው ግጭት ዋና ምክንያት በምርጫ ማግስት የተከሰተ አለመሆኑን ያመለከቱት አቶ ሥዩም በኬንያ ሀብታምና በድሀው መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄድ ለግጭቱ መነሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከመሬት፣ ከሥራና ከድህነት ጋር የሚያያዘው ችግር ለማንም መጠቀሚያ የሚያደርግ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልፀው ችግሩ የቆየ በመሆኑ በአንድ የምርጫ ጊዜ የሚፈታ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግንቦት 97ቱ ምርጫና በኬንያ ምርጫ ስላለው ሁኔታ ለተጠየቁት ጥያቄ “የኬንያ ምርጫና የኢትዮጵያ ምርጫ አይገናኝም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ አቶ ሥዩም  እንደሚሉት በፖለቲካና በሀሳብ ልዩነት መቧጨቅ ያለ ጉዳይ ቢሆንም አሁን በኬንያ የሚታየው ግጭት ግን ከፖለቲካ ድንበር የዘለለ ነው፡፡

በኃይሌ ሙሉ
Last Updated ( Thursday, 31 January 2008 )
 
< Prev   Next >