| አፍሪካውያን የአፍሪካን ችግር መፍታት አለባቸው! |
|
|
| Wednesday, 30 January 2008 | |
በአሁኑ ጊዜ በርካታ አበረታች ነገሮች በአፍሪካ ይታያሉ፡፡ ያንኑ ያህል አሳዛኝ ነገሮችም እየታዩ ናቸው፡፡ በመሠረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በአኗኗር፣ በልማት አዎንታዊ የሆኑ እድገቶች ይታያሉ፡፡ ገና ጅምሮች ቢሆኑም የለውጡ ፍጥነት ግን በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ የዴሞክራሲና የፍትሕ ሂደትም በሽግግር ወቅት ያለ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ወደፊት እየተጓዘ ነው፡፡ ፍጥነቱ አዝጋሚ ቢሆንም አፍሪካ “የጨለማ አህጉር” እየተባለች የምትጠራበትን ምክንያት በተግባር እየተቃወመች ትገኛለች፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ በላይ በሁሉም መስክ መሄድ ይቻል ነበር፡፡ ወደ ተሻለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ደረጃ መድረስ ይቻል ነበር፡፡ ሊደረስ ያልተቻለበት ምክንያትም የራስዋ የአፍሪካ የውስጥ ችግርና ከአፍሪካ ውጭ ያለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ ነው፡፡ አፍሪካውያን ቢበረቱ ቢተባበሩና ለለውጥ ቢዘጋጁ ኖሮ የውጭንም ጫና መቋቋም በቻሉ ነበር፡፡ ይኸን እንዳያደርጉ በዋነኛነት ተጠያቂው የውስጥ ችግርን ለመፍታት አለመቻላቸው ነው፡፡ አፍሪካውያን አሁን ላለው ግሎባላይዜሽን በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው፡፡ የራሳቸው የውስጥና የእርስ በርስ ገበያ ለማጠናከርና ለማስፋት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይህን ያህልም አይደለም፡፡ አሁንም የውጭው ዓለም ሸቀጥ ማራገፊያ ናቸው፡፡ አፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካው ብቻ ሳይሆን በቻይናና በህንድ ሸቀጣ ሸቀጦችም የተጥለቀለቀ አህጉር ሆኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከቀረጥ ነፃ የሆነ የጨርቃ ጨርቅ ኤክስፖርት ይፈቀዳል ብላ አሜሪካ የአጎዋ ፖሊሲ ብታወጣም ጨርቁ ከአፍሪካ ቢሄድም የጨርቁ ባለቤት ግን ቻይናና ህንድ እየሆኑ ናቸው፡፡ አስፈላጊው ውጤትም አልተገኘም፡፡ የአፍሪካ አገሮች በተናጠልም በጋራም የአፍሪካ ሕብረት ኢኮኖሚን የሚያጠናክር እርምጃና ትብብር ወስደው የውጭውን ጫና መቋቋም አልቻሉም፡፡ አሁንም በዓለም ባንክና በአይ.ኤም.ኤፍ ስር አሁንም በአበዳሪዎች ተፅዕኖ እየወደቁ አስፈላጊ ላልሆነ ወለድና ጫና እንደተጋለጡ ናቸው፡፡ አካባቢያችን የአፍሪካ ቀንድም የኢኮኖሚ ትብብር የሚታይበት አይደለም፡፡ እንኳን የአካባቢው አገሮች ተባብረው የጋራ ገበያ ሊያቋቁሙ ለኢኮኖሚ ችግር ተጨማሪ ምክንያት የእርስ በርስ አለመግባባት የሆነውን መፍታት ተስኗቸዋል፡፡ በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን አሁን ደግሞ በኬንያ ውስጥ ያለው ችግር በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር የሚፈጥር እንጂ የሚያቃልል አይደለም፡፡ ሊኖር የሚችለውንም አመቺ ዕድል መጠቀም የማያስችል ነው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ሀገሮች በተናጠልና በጋራ ሊንቀሳቀሱበት የሚገባ ትልቁ ዓብይ ነጥብ የእርስ በርስ የኢኮኖሚ ግንኙነትና ገበያን ማጠናከር ነው፡፡ ከኢኮኖሚው ውጭ ያለው የፖለቲካ ስርዓት ሲታይ አበረታች ነገር ያለበትን ያህል አሳሳቢና አሳዛኝ ሁኔታ እየታየበት ነው፡፡ ደህና የመረጋጋት ሁኔታ ይታይባት የነበረችው ኬንያ እየወዳደቀች በመሆኗ ያሳስባል፡፡ ጥያቄያችን ምርጫው ትክክል ነበር ወይስ አልነበረም አይደለም፡፡ ትክክል ካልነበረስ ይህ ችግር መነሳት ነበረበት፡፡ ትክክል ቢሆንስ ይህ ችግር መፈጠር አለበት፡፡ ችግሩ ከምርጫው ባሻገር መታየት ያለበት ነው፡፡ በየፖለቲካ ፓርቲ አሸናፊነት ላይ ጥርጣሬ ቢፈጠርም ቤትና ንብረት መቃጠል አለበት ወይ? ሕዝብ እርስ በርሱ መጨፋጨፍ አለበት ወይ? ሕዝብ የሚፀልይበት ቤተክርስቲያን ከነሕዝቡ ከነንብረቱ መቃጠል አለበት ወይ? የኬንያን ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ጫና አይቻልም ወይ? የአፍሪካ መንግሥታት ዝም ማለት አለባቸው ወይ? የውጭው ዓለምና መገናኛ ብዙሃንስ መረጃና መፍትሄ እየጠየቁ ናቸው ወይስ እያባባሱ? ይህ በአፍካውያን ሳይሆን ከኬንያውያን እጅም ማለፍ አልነበረበትም፡፡ መፍታትም ይቻል ነበር፡፡ በአፍሪካ የመደማመጥና የመተጋገዝ አቅምና ልምድ ስለሌለ ትንሽ ነገር ትልቅ ሆኖ አገርን ወደ ኋላ ሲጎትት እየታየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምርጫ ነበር፡፡ ምርጫውን ተከትሎ ችግር መጣ፡፡ ግብጽ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ተከትሎ ችግር፡፡ ኬንያ ምርጫ ይካሄዳል፤ ተከትሎ ችግር፡፡ ምርጫ አኩሪ ወይስ አስፈሪ? ለሚለው ጥያቄ አፍሪካ ትክክለኛ መልስ መስጠት አልቻለችም፡፡ የማይቻል ሆኖ ሳይሆን በተናጠልም በአፍሪካ ሕብረት ደረጃ አመለካከትም፣ ፖሊሲም መቀየሩም ስለሌለ ነው፡፡ የመንግሥታት ችግር ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችም፣ ሲቪል ማህበረሰብም መገናኛ ብዙሃንም አቅመ ደካማና አመለካከተ ደካማ ስለሆኑ ነው፡፡ ሰሞኑን የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ የተለመደው “አንድ አፍሪካ” እናጠናክር የሚል አጀንዳ ብቅ ማለቱ አይቀርም፡፡ የማይነሳ ከሆነ አንመጣም የሚሉ አኩራፊ መሪዎች ያሉባት አህጉር ናት፡፡ መነሳት ያለበትም ይነሳ፡፡ ችግሩ ግን ዋናውን ችግር እያድበሰበሰና እያለባበሰ ላይ ላዩን አቆነጃጅቶ ለማለፍ የሚሞክር አጀንዳ ነው፡፡ አፍሪካ አሁን ያለባትን ችግር እንዴት ትፍታ የሚለውን እናስብ፡፡ “አፍሪካ ምን ብትሆን ያምርባታል?” የሚል ጥያቄ ለጊዜው ችግር ፈቺ አይሆንም፡፡ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ደፋርና ሃቀኛ መሪዎች ያስፈልጓታል፡፡ ያለውን የአፍሪካ ችግር አፍረጥርጠው አውጥተው መፍትሄ የሚሹ መሪዎች ያስፈልጓታል፡፡ ከእውነት ከመሸሽ ይልቅ እውነታውን እንይ! እንፈትሽ፣ እንፍታ የሚሉ መሪዎች ያስፈልጓታል፡፡ የአገራችን መሪዎች ይህን ሚና ሊጫወቱ ይገባል እንላለን፡፡ አፍሪካ የአፍሪካን ችግር ትፍታ ብለው መቆም አለባቸው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |