Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት ምኑ ናት
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት ምኑ ናት Print E-mail
Wednesday, 30 January 2008
ሴኔጋል ላይ በተደረገው የ1955ቱ የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ  የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ ከስምንቱ የልዑክ አባላት ጋር በጭንቀት ስሜት ተቀምጠዋል፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽህፈት ቤት በዳካርና ሌጎስ እንዲሆን ሴኔጋልና ናይጄሪያ ቀድመው ቀስቅሰው ስለነበር፣ የዚያን ዕለቱ የአአድን ዋና ፅህፈት ቤት የመምረጥ ስብሰባ አዲስ አበባን ሊያገልላት ይችላል፤ የሚል ጭንቀት አሳድሮባቸዋል፡፡

ሴኔጋል የአአድ መቀመጫ ዳካር እንዲሆን ቀደም ብላ 15 ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገሮችን ቤንን ላይ ስብስባ ድምፃቸውን ለዳካር እንዲሰጡ አግባብታቸዋለች፡፡ ኢትዮጵያ ግን ምንም ዝግጅት አላደረገችም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አአድ ከተቋቋመ በኋላ ዋና ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ለንጉሠ ነገሥተ ቢያመለክቱም ትኩረት ባለመሰጠቱ ለአሁኑ ጭንቀታቸው አግዟል፡፡

ነገር ግን ከርሳቸው ራስ አልወረደም፡፡ ማንኛውንም ተጋድሎ አድርገው ጽህፈት ቤቱን አዲስ አበባ እንዲያስደርጉ ከመንግሥታቸው ሲታዘዙ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን አላጡትም፡፡ ቢሆንም የዳበረ ልምዳቸውን ተጠቅመው ማሸነፍ እንዳለባቸው አምነዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ሴኔጋልና ናይጄሪያ ለዕጩነት ቀረቡ፡፡ ኢትዮጵያም በጊኒው ልዑክ የሞቀና የጠነከረ መግለጫ ተጨምሮበት ለዕጩነት ቀረበች፡፡ በእጩነት መቅረቧ ያሳሳባቸው፣ ዳካርና ሌጎስ፣ ለዲፕሎማቶች የተሟላ የቤት፣ የመብራት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ከተማ ማን ነው? የሚለው መለኪያ ታሳቢ እንዲሆን ሃሳብ አቀረቡ፡፡

የታወቁት ዲፕሎማትና ለአአድ መመስረት ቀዳሚ ተዋናይ የነበሩት አቶ ከተማ ይህን ሃሳብ ፈጥነው ተቃወሙ፡፡ አፍሪካውያኖች በራሳቸው መኩራት የሚገባቸው እንዲሆኑ እያሳሰቡ የኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌትነት እያመዘዙና እያጎሉ አስረዱ፡፡ ሃሳቡም ውድቅ ሆነ፡፡

በተጓዳኝ ስብሰባው ከተጀመረ ጀምሮ በየኮሪደሩና በየምሳ ቦታው አፍሪካውያንን የማነጋገር እንቅስቃሴያቸውን አጧጧፉት፡፡ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሆኑትንና በሴኔጋል የተሰበኩትን ሃገሮችም በጋራና በተናጠል እየቀረቡ አነጋገሩዋቸው፡፡ በካዛብላንካው ስብሰባ አብረዋቸው እንደነበሩ እየጠቀሱ፣ እስከዛሬ እንደደገፏቸው እያስታወሱ፣ አግባብተው አብዛኛዎቹ ሃገሮች ገንጥለው የራሳቸው አደረጉ፡፡

ከተማ ይፍሩ፣ ከሁሉም በላይ ከዚያ ጊዜው ፍጥጫ ለይተው በሞቀ ስሜት ሲያስታውሱት የሚኖሩት ትዝታ ነበራቸው፡፡ የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላ ኢሳ አብረው ምሳ እንዲበሉና በአንድ ቁም ነገር ላይ እንዲነጋገሩ ጠይቀዋቸው ከፕሬዚዳንታቸው የደረሳቸውን የቴሌግራም መልዕክት ይነግሩዋቸዋል፡፡ “አዲስ አበባን እንዳትመረጥ” የሚል ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን ቃል ገቡላቸው፡፡ “የፈለገው ቢሆን እኔ ድምፄን ለአዲስ አበባ እሰጣለሁ፡፡”

እውነትም ቃላቸውን ፈፀሙ፡፡ አቶ ከተማ “ጨዋ ሰው ነው” የሚሏቸው አብደላ ኢሳ በ1950ዎቹ የወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር በነበሩበት ወቅት የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ያረሙላቸው ከተማ ይፍሩ ነበሩ፡፡ ሁለቱም በአጋጣሚው ተደንቀው በደስታ ፈነደቁ፡፡
የመጨረሻው የድምጽ ውሳኔ ደረሰ፡፡ አስመራጩ ደግሞ ጊዜያዊ የአአድ ዋና ፀሐፊ የነበሩት ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚዕ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ከ32 ድምጽ 28ቱን አግኝታ አዲስ አበባ አሸነፈች፡፡ ከተማ ይፍሩ ሃገራቸው ማሸነፏን ያወቁት ውጤቱ ከመነገሩ በፊት ነበር፡፡ በኋላ ራሳቸው እንደተናገሩት የአስመራጭ ኮሚቴው ሃላፊ ተስፋዬ ገብረ እግዚዕ ፊታቸው በደስታ ፈክቶ ሲያዩት ለአጋሮቻቸው አፍሪካውያን ዘወር ብሎ “አደረግነው” (We did it) አሏቸው፡፡ በእንዲህ ያለ ትግል ነበር፤ አዲስ አበባ የአአድ ጽህፈት ቤት መቀመጫ የሆነችው፡፡

ኢትዮጵያ ለአአድ መጠናከርና ለአፍሪካ ሕብረት መፈጠር ወሰን የሌለው አስተዋፅኦ ማድረጓን ማንም አይከራከርም፡፡ በነፃነት የኖረችው ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሃገር ኢትዮጵያ፣ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ከቅኝ ገዥዎቻቸው የአገዛዝ ቀንበር የተላቀቁትን የአፍሪካ ሃገሮች በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር የመጠለላቸው አስፈላጊነቱን እንደነ ክዋሜ ኑክሩማህ ሁሉ የምታምንበት ነበረች፡፡

ኢትዮጵያ በራስዋ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች ስትለበለብና ስትደቆስ የቆየች ብትሆንም ለአፍሪካውያን የነፃነት ትግል፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መጠናከር ቅድሚያ በመስጠት መስዋዕትነትን የከፈለች ሃገር ሆና ቆይታለች፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም የወቅቱ መሪ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በሃሳብ የተራራቁትን አፍሪካውያን መሪዎች አንድ ላይ በማምጣት አዲስ ድርጅት እንዲያቋቁሙ የበሰለና የጠለቀ የዲፕሎማሲ ጥረት አድርገው ተሳክቶላቸዋል፡፡

በዚያን ጊዜ፣ ብቸኛና በቅኝ ገዥዎች ተገዝታ የማታውቅ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተክለሰውነት፣ የኢጣሊያን ቅኝ ገዥ በማባረር የፈጠረላቸው ግርማ ሞገስ፣ አዲሶቹ የአፍሪካ መሪዎች እንዲሰሟቸው ረድቷል፡፡ እንደ አቶ ከተማ ይፍሩ ያሉ የበሰለና የጠለቀ የዲፕሎማሲ እውቀት ያላቸው መሪዎች አስተዋፅኦም ቀላል አልነበረም፡፡

የካዛብላንካውና የሞኖሮቪያው ቡድን የተከፋሉትን የአፍሪካ መሪዎች በአንድ ላይ አገናኝቶ ራዕይ የነበራቸውን እንደ ኬንያታ፣ ኑክሩማና ሴኩቱሬ ያሉትን መሪዎች ይዞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መመስረት ታላቅ ተግባር ነበር፡፡ በዚያው ሳያበቁ ጽህፈት ቤቱን አዲስ አበባ ለማድረግ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በዚያ ጊዜ የነበራቸው ዕውቀትና የሃገር ፍቅር ስሜት ጥሩ መሳሪያ ሆኗቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚያ ጊዜው አቅሟ፣ ለአፍሪካ ተወካዮች በተቻላት አቅም አገልግሎት ሰጥታለች፡፡ በፖለቲካውም ረገድ በፀረ ቅኝ አገዛዙ ትግል ተሳታፊ ሆና ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት በዓለም አቀፍ መድረኮች አብራቸው በመቆም አጋርነቷን አሳይታለች፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በመፅሐፋቸው ውስጥ፣ በ1950ዎቹ ኢትዮጵያ መጥተው ኮልፌ አካባቢ ወታደራዊ ሥልጠና ማከናወናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያን አየር ሃይል አይተው በነፃይቷ ጥቁር አፍሪካዊ ሃገር የተሰማቸውን ኩራት ገልፀውታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥታት በውስጥ ፖለቲካቸው፣ በሕዝባቸው የሚነቀፉና የሚረገሙ ቢሆኑም ለአፍሪካ አንድነት ቻርተርን በማክበርና በማስከበር በኩል ግን አንዳችም ጊዜ ግንባራቸውን ያጠፉበት ጊዜ የለም፡፡

በደርግ መንግሥትም ይኸው ተጋድሎ ቀጥሏል፡፡ የዙምባቤዎቹ የሙጋቤና የጆሶዋ ኑከም የነፃነት ታጋይ ድርጅቶች፣ ለሚያደርጉት ትግል በሺዎች የሚቆጠሩ ሸማቂ ተዋጊዎች በተለያዩ ቦታዎች አሰልጥኖና አስታጥቆ ልኳል፡፡ ናሚቢያና ሞዛምቢክን በመርዳት የፀረ ቅኝ ግዛት የትግል አጋርነቱን አስመስክሩዋል፡፡

በተለይም በአንድ ወቅት የአፍሪካ መሪዎች በሊቢያ ላይ ባላቸው የቅሬታ አቋም፣ ትሪፖሊ ላይ የሚደረገው በወቅቱ የመሪዎች ስብሰባ ለመገኘት ባለመፍቀዳቸው ከሁለት ጊዜ ሙከራ በኋላ ስብሰባው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ በተወሰነበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ባሳየችው አቋም “አአድ አበቃለት” የሚለውን የምዕራባውያን ግምት አጨናግፎ የድርጅቱ እድሜ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡

በጊዜው ደርግ የኮሌኔል ጋዳፊ ወዳጅ ቢሆንም፣ ለአአድ ቻርተር ቅድሚያ በመስጠት ስብሰባውን የአፍሪካ መሪዎች ያለስጋት እንዲያካሄዱ በማድረግና ከሊቢያ መሪ አጃቢዎች ጋር እስከመጋጨት በደረሰ የደንብ አስከባሪነት አቋሙ ድርጅቱን ከጊዜው አደጋ ለመታደግ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላም ቢሆን ለአፍሪካ ሕብረት ያለው ታማኝነትና ቀጥተኛነት አላጓደለም፡፡ ከቶውንም የአፍሪካ ሕብረት ቻርተር ሲረቀቅ ቀድሞ የነበረው የፅሕፈት ቤቱ መቀመጫ ከተማ ጉዳይ አመርቅዞ፣ ጽህፈት ቤቱ አዲስ አበባ እንዲነሳ በመሪዎች ስብሰባ ሳይቀር የጋለ ክርክር ሲካሄድ፣ አቶ መለስ የሚደመጥና የሚያሳምን ክርክር አድርገው አዲስ አበባ በጽህፈት ቤትነቷ እንድትፀና አድርገዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ሌሎች የቻርተሩ አንቀጾች ከተወሰኑ በኋላ የፅህፈት ቤቱ ጉዳይ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የቀረበውን ረቂቅ የተንኮል ሃሳብ፣ አቶ መለስ አጥብቀው በመቃወምና በዚያን እለቱ ስብሰባ እንዲወሰን አድርገዋል፡፡ “ብዙዎቹን ጉዳዮች ወስነን የፅህፈት ቤቱን መቀመጫ መነጋገር ለምን እንቸገራለን?” ሲሉ በጋለ ስሜትና በጠነከሩ ቃላት የተናገሩት አብዛኛዎቹን የአፍሪካ መሪዎች ቀስቅሷቸዋል፡፡ “ከአዲስ አበባ የተሻለ ቦታ ካለ አሁኑ ተነጋግረን መወሰን አለብን” የሚለው አስተያየታቸውን የብዙዎችን ስሜት በመሳቡ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የቀረበው አስተያየት ውድቅ ሆኗል፡፡

አዲስ አበባ ለአፍሪካ ሕብረት መቀመጫነት ተስማሚ መሆኗንም በረጅሙ ንግግራቸው ውስጥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጉዳዮች ምንጊዜም ታማኝ መሆኗን አስረድተዋል፡፡ ““. ኃይለሥላሴ በሀገራቸው ኋላ ቀር ናቸው፡፡ ግን ማንዴላን ማን ነው ያሰለጠነው? ኋላ ቀር ኃይለሥላሴ አብዮተኛውን ማንዴላን አሰልጥነዋል፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም በሃገር ቤት አራጅ ነው፡፡ ነገር ግን የዙምባብዌን ታጋዮች ሲያሰለጥን ቆይቷል” የሚለው ኃይለ ቃላቸው ተደማጭነት አግኝቶ አዲስ አበባን የሕብረቱ መቀመጫ እንድትሆን አድርገዋል፡፡

በግልጽ እንደሚታየው ኢትዮጵያ በዚህ ንግግር ብቻ አላቆመችም፡፡ ለአፍሪካ ሕብረት ዲፕሎማቶች ምቹ የሥራና የመኖሪያ ቦታ ለመፍጠር ከአቅሟ በላይ እየሰራች በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡

ምንም እንኳ በድህነት ውስጥ የተዘፈቀች ሃገር ብትሆንም መዋጮዋቸውን ቀድመው ከሚከፍሉት ሃገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደሟ ሆና ቆይታለች፡፡

ለአፍሪካ ሃገሮች ኤምባሲ ለእያንዳንዳቸው 2000 ካሬ ቦታ በመስጠት ለአፍሪካ ያላትን ፅኑ ፍቅር አሳይታለች፡፡ በየትም ሃገር እንደዚህ ያለ የትብብርን ስሜት የሚያጠናክር ተግባር እንዳልታየ ለረጅም ጊዜ በዲፕሎማሲ ሥራ ተሰማርተው የቆዩት ከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት የምትሰጠውን ትኩረት ለመግለፅ እንጅ ሃገሪቱ በካሬ መሬት መግዛት ያቅታቸዋል ከሚል ግምት እንዳልሆነ ከንቲባ ብርሃነ ያስረዳሉ፡፡
አልፎ ተርፎ የውጭ ሃገር ኤምባሲዎች ቦታ አግኝተው ለመግዛት ከመስተዳደሩ ጋር ለመፈራረም ያላቸው ፍላጎት ከፍ እያለ ሄዷል፡፡  

በተጨማሪም መንገዶች ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሃገር ስም እንዲሰየም ተደርጓል፡፡ እንዲህ አይነት የመንገድ ስያሜ ለብዙ ሃገር የተለመደ አለመሆኑን የሚጠቅሱት ከንቲባ ብርሃነ፣ በኒውዮርክ ያለውን የአሜሪካኖች አደባባይ ይጠቅሳሉ፡፡ በኒውዮርክ አንዳንድ ብሎክ በላቲን አሜሪካኖች ስም ሰይመዋል፡፡ ነገር ግን ያችኑም ቢሆን ኩባን ሲጣሉዋት ስያሜውን እንዳነሱት አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን “እንዲህ አይነት ወደር የሌለው ስጦታ” እገሌ ወዳጄ፣ እገሌ ጠላቴ ሳትል መስጠቷ ለአፍሪካ የምትሰጠውን የአክብሮት ቦታ እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡

የቻይና መንግሥት ለአፍሪካ ባቀረበው ስጦታ ለዋና ፅሕፈት ቤቱ አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ ሕንፃ ገንብቶ በሁለት አመት ውስጥ ለማስረከብ ቃል ገብቷል፡፡ 150 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ለተባለው ሕንፃ፣ ኢትዮጵያ ያደረገችው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍ ያለ  መሆኑን ከንቲባ ብርሃነ ጠቅሰዋል፡፡

ለሚገነባው የሕብረቱ ጽህፈት ቤት 120,000 ካሬ ሰጥቷል፡፡ ይኸም በገንዘብ ሲተመን ወደ 400 ሚሊየን ይጠጋል፡፡

አስተዳደሩ ከአካባቢው ለሚነሱ ነዋሪዎች፣ ለካሳ ክፍያና አካባቢውን ለማፅዳት አፈሩን ለማንሳት”. ከ12 ሚሊየን ብር ወጭ አድርጓል፡፡

ለግንባታው ለሚገነቡ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ በመፍቀድ የቫት ክፍያ ጭምር በማስቀረት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ሌሎችን ታክሶች ጨምሮ በአነስተኛ ግምት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ ያደረገ መሆኑን ከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ ይናገራሉ፡፡

በርግጥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቱ ከፍተኛ ተጠቃሚ ናት፡፡ በዚያው ልክ በሃብት ከሚበልጧት በርካታ ሀገሮች በላይ በአስተማማኝ ፀጥታ አፍሪካ ህብረትን ለመጠበቅ የላላችበት ጊዜ የለም፡፡

አንዳንድ ሃገሮች ኢትዮጵያ በተለይ በኮሚኒኬሽንና በመንገድ ያለባትን ኋላ ቀርነት እየጠቀሱ፣ ቢያንገራግሩም በሌላ በኩል ሌሎች የማያገኙት አየር ንብረት፣ ሰላም መኖሩ ብዙዎች ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጡታል፡፡
 
< Prev   Next >