| የአፍሪካ ህብረት ከአፍሪካ አንድነት... |
|
|
| Wednesday, 30 January 2008 | |
|
የአፍሪካ ህብረት ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይለያልን? በሰላም ሥልጣናቸውን የለቀቁ አፍሪካውያን እነማን ናቸው? ተብሎ ቢጠየቅ ዝርዝራቸውን መጥራት ጊዜ አይወስድም፡፡ ኔልሰን ማንዴላ፣ ቻርለስ ቴይለር፣ አዲስ አብዱሌ ኦስማን፣ ሴዳር ሴንጎር፣ አህማዱ አሂጆና ጁሊዬስ ኔሬሬ፤ በቃ የተቀረው የአፍሪካ መሪ ወይ በመፈንቅለ መንግሥት አልያም በተጭበረበረ ምርጫ ገደብ ለሌለው ጊዜ ሀገሩን ይመራል፡፡ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ህዝቡ ከማያውቀው ቅኝ ገዢ ወደ ሀገሩ ልጆች ጨቋኝ አገዛዝ አሳልፎ ተሰጥቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1963 በአዲስ አበባ የተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋነኛ አላማ አባል ሀገሮችን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ማውጣት፣ የዘር መድልኦን ማስወገድ፣ አንድነትና ወንድማማችነትን ማስፋፋት፣ ለእድገት ትብብር መፍጠር፣ ሉአላዊነትና የግዛት መከበርን መጠበቅ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ህግ መሠረት ዓለም አቀፍ ትብብርን ማስፋፋት ነበር፡፡ አፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል ሀገሮቹን በተሳካ ሁኔታ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ አውጥቷል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የዘር መድልኦን አስቀርቷል፡፡ በተጨማሪም በ1980 በሌጎስ በተደረገ ስብሰባ ራሱን የቻለ የእድገት ስትራቴጂ ቀርጿል፡፡ በ1981 በናይሮቢ በተደረገው ስብሰባ የአፍሪካ ሰዎችና ህዝቦች መብት ቻርተር አፅድቋል፡፡ በ1990 የህዝቦች ተሳትፎ ቻርተር ፀድቋል፡፡ በ1991 የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚውኒቲ (AEC) ታውጇል፡፡ በ1993 የግጭት መከላከያ አስተዳደርና አወጋገድ ፀድቋል፡፡ በ1997 በውጭ እዳ ጉዳይ ላይ ስምምነት ተደርጓል፡፡ በ1999 ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥን አስመልክቶም መግባባት ተችሏል፡፡ ከእነዚህ አዎንታዊ ውጤት በዘለለ በጦርነት፣ በበሽታ፣ በድህነትና በዲሞክራሲ እጦት ለምትሰቃየው አህጉር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የፈየደላት ነገር አልነበረም፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚውኒቲ ቅልቅል የተፈጠረው የአፍሪካ ህብረት 53 አባል ሀገራት አሉት፡፡ ለምዕራብ ሰሀራ ሳህራዊ አረብ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እውቅና በመስጠቱ አኩርፋ ከአባልነት ውጭ የሆነችው ሞሮኮ ነች፡፡ በ2ዐዐ1 የተቋቋመው የአፍሪካ ህብረት ያወጣቸው ህጎች ያቋቋማቸው መሥሪያ ቤቶችና አካሎች በአህጉሪቷ ለሚኖሩት የተጨቆኑ ሚሊዮኖች ሰብአዊ መብት መከበር ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ተስፋ ተደርጐ ነበር፡፡ በ40 ዓመት እድሜው ከሞተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በንፅፅር ሲታይ አፍሪካ ህብረት የ7 ዓመት እድሜ ብቻ ያለው ቢሆንም “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው የእስከአሁኑ አካሄድ ተስፋ ፈንጣቂ አልሆነም፡፡ የአፍሪካ ህብረት “አፍሮ” የሚባል አንድ መገበያያ፣ አንድ መከላከያ ሰራዊት እና በርካታ ተቋሞችን ለመመስረት አላማ ያደረገ ሲሆን ይህም በአፍሪካ ዲሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት እና የሚያድግ ኢኮኖሚ በመመስረት የእርስ በርስ ግጭቶችን በማቆም ውጤታማ የጋራ ገበያ ለመፍጠር ነው፡፡ ይህን ሊያግዙ የሚችሉ ተቋሞች የተመሰረቱ ሲሆን ከአባል ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተዋቀረው አስፈፃሚው፣ ከመሪዎቹ የተዋቀረው ጠቅላላ ጉባዔ፣ የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ፣ የፓን አፍሪካ ፓርላመንት፣ ሶሻል፣ ኢኮኖሚና ባህል ምክር ቤት፣ እንዲሁም የሲቪክ ማህበረሰብ አማካሪ አካል ይገኙበታል፡፡ ዛሬ በሱዳን፣ ሶማሊያ፣ አይቮሪኮስት፣ ብሩንዲና ኮንጎ አንፃራዊ ሠላም ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ አፍሪካ ህብረት በአውሮፓ ህብረት ሞዴል እንዲሰራ የሚጠበቅ ሲሆን የጋራ የንግድ እድገትና መከላከያ ፖሊሲ እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ በዚህም መሠረት የአፍሪካ ሀገሮች እርስ በርስ እንዲረዳዱ፣ ግጭቶችን እንዲያስወግዱና ችግር ውስጥ ለገቡ መንግሥታት ሠላም አስከባሪ ኃይል እንዲልኩ እድል ይሰጣል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ግን ከላይ በተገለፁት አገሮች ሁሉ ሠላም አስከባሪ ኃይል በመላኩ የተከፋፈለው ኃይል ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ የአፍሪካ ህብረት በአባል ሀገራት ላይ የፈፀመው የመጀመሪያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የተፈፀመው በግንቦት 2ዐዐ3 ሲሆን የደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ወታደሮች ሠላም አስከባሪ ኃይሉን በመወከል ወደ ብሩንዲ ያመሩ ሲሆን አላማውም የተለያዩ ስምምነቶችን አፈፃፀም ለማየት ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ግጭትን ለማስወገድ ከፈጠረው ስልት ባሻገር ለመከላከል የሚረዱ በርካታ ጠቃሚ ሰነዶችን ያፀደቀ ሲሆን አህጉራዊ ልማዶችን ለመመስረት እና ቀደም ብሎ በስራ ላይ ያሉትን ስምምነቶች አፈፃፀም ለማገዝ እንደሚጠቅሙ ተስፋ ተደርጓል፡፡ በ2ዐዐ3 ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት የወጣ ስምምነት፣ በ2ዐዐ7 የአፍሪካ የዲሞክራሲ ምርጫና መልካም አስተዳደር ቻርተር ከወጡት በተጨማሪ አዲስ ጥምረት ለአፍሪካ እድገት እና የአፍሪካ ዲሞክራሲ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና አህጉራዊ አስተዳደር ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡ አፍሪካ ህብረት በርካታ ፈተናዎች ከፊቱ ተጋርጠዋል፡፡ የወባና ኤች.አይ.ቪ ወረርሽኝ፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ መንግሥቶችን መጋፈጥ፣ የርስ በርስ ጦርነትን ማብረድ፣ የአፍሪካውያንን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ ትምህርት እንዲያገኙ መርዳት፣ ረሀብና የበረሃ መስፋፋትን መቀነስ፣ የሞሮኮንና የምዕራብ ሰሀራን ጉዳይ በህጋዊ መንገድ መቋጨት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ህገ መነግሥት በግልፅ እንዳስቀመጠው ዲሞክራሲያዊ መርሆዎች እና ተቋሞችን ህዝባዊ ተሳትፎን እና መልካም አስተዳደርን ማስፋፋት በአፍሪካ ሰዎችና ህዝቦች መብቶች ቻርተርና በሌሎች ሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች መሠረት ለሰዎችና ለህዝቦች ህጋዊ ከለላ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ አፍሪካ ህብረት ከዚህ በተጨማሪም ኢ-ህገመንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥን እንደማይቀበልና ከህግ የበላይነት መርህ የመጣ አባል ሀገር የሚፈፅመው ውሳኔና ፖሊሲ ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ይገልፃል፡፡ ይህ መፈንቅለ መንግሥትን ለመሰናበት ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ ቢሆንም በተግባር የታየው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ ከ2ዐዐዐ ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባዎች በዚምባብዌ የሰብአዊ መብት ረገጣ ዙሪያ ብዙ ነገሮች ቢባሉም ችግሩን የሚቀርፍ አስገዳጅ ውሳኔ ዛሬም አልተሰጠም፡፡ በየካቲት 2ዐዐ5 የቶጎ ኘሬዚዳንት የነበሩት ኛሲንጌ ኢያደማ ሲሞቱ ልጃቸው ፋውሬ ኛሲንጌ የስልጣናቸው ወራሽ መደረጉን የአፍሪካ ህብረት “ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት” ሲል አጣጣለው፡፡ የቶጎ ህገ መንግሥት ኘሬዚዳንቱ ከሞተ የፓርላማው አፈ ጉባዔ እንደሚተካው ይገልፃል፡፡ በህጉ መሠረት አፈ ጉባኤው በ6ዐ ቀናት ውስጥ ህዝቡ በብሄራዊ ምርጫ አዲስ ኘሬዚዳንት እንዲመርጥ ያደርጋል የአፍሪካ ህብረት ተቃውሞ ኛሲንጌን ምርጫ እንዲያካሂድ አስገደደው፡፡ ምርጫው እንደተጭበረበረ ቢገለፅም በግንቦት 2ዐዐ5 ኛሲንጌን ኘሬዚዳንት ከመሆን ያገደው ነገር የለም፡፡ በነሐሴ 2ዐዐ5 በሞሪታኒያ መፈንቅለ መንግሥት ተካሄደ፡፡ የአፍሪካ ህብረት ሀገሪቱን ከማንኛውም የድርጅቱ እንቅስቃሴዎች አገዱት፡፡ አገሪቱን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ካውንስል በሁለት ዓመት ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ ቃል ገባ፡፡ ምርጫው እርግጥም በ2ዐዐ7 ተካሄደ፡፡ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የተስማማበት ተቀባይነት ያለው ደረጃ በተሰጠው ምርጫ ለአገሪቷ የመጀመሪያ ነበር፡፡ አፍሪካ ህብረት እንዲህ ዓይነት በጎ ተፅእኖዎችን ለመጫወት የቻለ ቢሆንም የኢትዮ-ኤርትራን አለመግባባት፣ የሱዳንንና የሶማሊያን የርስ በርስ ግጭት ለመፍታት ያደረገው ጥረትና ያልተሳኩ ውጤቶቹ ድርጅቱን ከህልውናው ጀምሮ ያለበትን የአቅም፣ የአሰራርና የእውቅና ብሎም ልዩነት የመፍጠር ችግርን በገሀድ ያሳየ ነው፡፡ በቅርቡም በኬንያ ድህረ ምርጫ የተከሰተውን ቀውስ በማብረድ ጥረቱተደግሟል፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ግጭት ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያና ኤርትራ ዛሬም ውጥረት ውስጥ ሲሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ግጭቱን ለማብረድ የተሰማራው አፍሪካ ህብረት የመራው የአልጀርስ ስምምነት ተፈፃሚ ባለመሆኑ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደታየውም የአፍሪካ ህብረት ውጤታማ ያለመሆኑ በተባበሩት መንግሥታት እንዲታገዝ ያደረግ ሲሆን ለህብረቱ ተገቢውን ክብር እንዳይሰጠውም አድርጓል፡፡ በሱዳን ያለውም ሁኔታ እጅግ የተወሳሰበ ሲሆን መንግሥት፣ የሱዳን ነፃ አውጭ ጦር፣ የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ እና የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ በዳርፉር ላይ የፈጠሩት ፍጥጫ ሱዳንን ከምስራቅ አፍሪካ ዜጐቿን ለሰብአዊ ቀውስ አጋልጣ የሰጠች አገር አድርጓታል፡፡ የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ሚሽን የተቋቋመው በ2ዐዐ4 በ15ዐ ወታደሮች ሲሆን በ2ዐዐ5 ቁጥሩ ወደ 7000 ከፍ ብሏል፡፡ በዳርፉር ግዛት የተከሰተውን ብጥብጥ በአግባቡ መቋቋም ያልቻለው ይህ ሚሽን በመስከረም 2ዐዐ6 በተባበሩት መንግሥታት የሱዳን ሚሽን እንዲተካ ሀሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም በሱዳን መንግሥት ተቃውሞ ምክንያት በ2ዐዐ7 መጨረሻ ቀናት ነው የተባበሩት መንግሥታት የሱዳን ሚሽን ከአፍሪካ ህብረት ላይ የማረጋጋት ሥራውን የተረከበው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች ውጤታማ ያልሆኑት በገንዘብ እጥረት፣ በሰው ሀይል እጥረትና በባለሙያዎች እጥረት ነው፡፡ የገንዘብ እጥረቱን ለመደገፍ በሐምሌ 2ዐዐ6 አሜሪካ 173 ሚሊዮን ዶላር ለአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ሀይል አበርክታለች፡፡ በ2ዐዐ5 ብቻ አጠቃላይ 450 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ መሪ ሞሀመድ ሳልህ “አፍሪካ ህብረት ከሱዳን እንዲወጣ እንፈልጋለን፡፡ በእኛ ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች እንዳይንቀሳቀሱ አስጠንቅቀናቸዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አናውቅም ለማወቅም አንፈልግም፡፡ እነሱ ችግር አስወጋጅ ሳይሆኑ ችግር ፈጣሪዎች ናቸው” በማለት በ2ዐዐ5 የነበረውን የሱዳን ገፅታ ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ በሶማሊያ ያለውም ጉዳይ ከሱዳን የማይሻል ሲሆን ሀገሪቱ ከ1991 የዚያድ ባሬ ሥልጣን መልቀቅ በኋላ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ችግር ለመፍታት ያደረገችው ተከታታይ ጥረት ከሁሉም አካሎች ድጋፍን አላስገኘላትም፡፡ ሶማሊያን ከማረጋጋትም ባሻገር ሌላ የፖለቲካ ግብ አላት ተብላ የምትተቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ከዛሬ ነገ ይተካታል ተብላ ብትጠበቅም ህብረቱ ከሚጠብቀው 8000 ወታደሮች ውስጥ ኡጋንዳ፣ ናይጄሪያና ማላዊ ብቻ 2500 ወታደሮችን አዋጥተዋል፡፡ የተቀሩት የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ግን ዝምታን ብቻ አዋጥተዋል፡፡ እሱም የከበዳት ደቡብ አፍሪካ የህብረቱ ኃይል ሀገር ብትሆንም ለሰላም አስከባሪ ኃይሉ ምንጭ ወታደር እንደማትልክ ባለፈው ሳምንት አሳውቃለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች የተሰበጣጠሩትን ወታደሮቿን፣ የምዕራባዊያን የእርዳታ ቃል አለመጠበቁንና በህብረቱ በኩልም የሚያስማማ የሰላም እቅድ አለመኖርን በምክንያትነት አስቀምጣለች፡፡ ከበርካታ ዓመታት ውትወታ በኋላ በ2006 የሠላም ስምምነት የተፈረመ ቢሆንም የሽግግር ፌደራል መንግሥቱ መቋቋም የተጠበቀውን ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ተስኖታል፡፡ በአዲስ አበባ እየተደረገ ባለው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባ አባል ሀገሮች ተጨማሪ ወታደሮችን እንዲያዋጡ ጥሪ ተደርጓል፡፡ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ኘሬዚዳንት አብዱላሂ የሱፍ ከአሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት ከተደረገባቸው ጫና አንፃር የስምምነት ውይይት ከሃይማኖትና ጎሳ መሪዎች እንዲሁም አክራሪ ካልሆኑ በመንግሥትና በኢትዮጵያ ወታደሮች ትብብር የተገረሰሱት እስላማዊ ኃይሎች ጋር ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ አውሮፓ ህብረት 2ዐ ማሊዮን ዶላር ለሰላም አስከባሪው ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ አሜሪካም ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች፡፡ የእስላማዊ ኃይሎች በኦፊሴላዊ የመረጃ መረባቸው አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል በሶማሊያ እንደወራሪ እንደሚቆጥሩትና አደጋ እንደሚያደርሱበት አስጠንቅቀዋል፡፡ አፍሪካ ህብረት ማስፈራሪያውን ችላ ብሎ ሥራውን ቢቀጥል በሶማሊያ ብቻ በመጪዎቹ ስድስት ወራት 16ዐ ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል፡፡ ሪቻርድ ክሮምዌል የተባለ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ “ሕብረቱ የሰላም እቅድ የለውም፡፡ ፖለቲካዊ አሊያም ዲኘሎማሲያዊ ማዕቀፍም እንዲሁ የለውም፡፡ ወታደሮችን እንደሚያሰማራ እንጂ ለምን እንደሚያሰማራ አያውቅም” ሲሉ ህብረቱን ይተቻሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ሶማሊላንድ በሰሜን ሶማሊያ እንደ አንድ ነፃ ሀገር በሚገባ ያለ አፍሪካ ህብረት እንዲሁም ሌላ ዓለም አቀፍ ድርጅት እውቅና በመንቀሳቀስ ላይ ያለችው፡፡ በኬንያም ምርጫውን ተከትሎ በተካሄደው የተለያዩ ኃይሎች ግጭት የአፍሪካ ህብረት ነገሩን ለማብረድ ያደረገው ሚና የተጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ ከህብረቱ ይልቅ ሁለቱን ባላንጣዎች ኘሬዚዳንቱን ኪባኪንና ተቃዋሚውን ኦዲንጋን ፊት ለፊት እንዲወያዩ ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ኮፊ አናንና አሜሪካዊቷ ጃንዳይ ፍሬዘር ናቸው፡፡ ኮሚሽነሩ ኘሮፌሰር አልፋ ኦማር ኮናሬ የተቻላቸውን (የሰላም ሀሳብ በማፍለቅ) ቢጥሩም የተሻለ ግምት የተሰጣቸው ለደቡብ አፍሪካው ለሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገሮች አጠቃላይ ድምር ኢኮኖሚ ከሆላንድ ኢኮኖሚ ያነሰ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ አባል ሀገሮች ለአፍሪካ ህብረት የሚያዋጡት መዋጮ የህብረቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመሸፈን የሚያስችል አይደለም፡፡ ይባስ ብሎ በኢኮኖሚ ከአፍሪካ ሻል ይላሉ የሚባሉት አገሮች እና ግብፅ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ መዋጮውን በወቅቱና በአግባቡ የማይከፍሉ በመሆናቸው ህብረቱ ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ህብረት የወደፊት እቅዶች ነፃ የንግድ አካባቢ፣ ተመጣጣኝ ታሪፍ፣ አንድ ገበያ፣ ማዕከላዊ ባንክና የጋራ መገበያያ መፍጠር ናቸው፡፡ በ2023 ሥራ ላይ እንደሚውል የሚጠበቀው “አፍሮ” መገበያያና ኢኮኖሚ ውህደትን ለአፍሪካ እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ቀደም ብሎም የተቋቋሙት የፓን አፍሪካ ፓርላማ፣ የአፍሪካ ህብረት ጠቅላላ ጉባዔ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ የፍትህ ፍርድ ቤት፣ የአፍሪካ ህብረት ሥራ አስፈፃሚ፣ ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ፣ ሰላምና ደህንነት ካውንስል፣ የኢኮኖሚ ማህበራዊና ባህላዊ ካውንስል፣ ልዩ ቴክኒካዊ ኮሚቴዎች፣ የገንዘብ ተቋሞች እና ሰብአዊ መብት ተቋሞች በሙሉ አቅማቸው ለመደራጀትና ለመሥራት ትልቅ የገንዘብ ምንጭ ይሻሉ፡፡ አፍሪካ ዛሬም ትናንት ለዛሬው ችግሬ ተጠያቂ የምትላቸውን ምዕራባዊያንን እርዳታ ትሻለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታት የተቋቋመ በብዙ ህጎች፣ ተቋሞችና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች መርሆዎች የታጨቀ ቢሆንም ልብ ከሚያነጥር የወረቀት ሥራ በዘለለ የሚያመረቃ ሥራ አልሰራም፡፡ ከህግ ውጭ የተሰሩ ሥራዎችን እየተቃወመ መግለጫ ማውጣቱ አንድ ጥሩ ሥራ ቢሆንም መግለጫውን ተከትሎ የሚሰሩት ሥራዎች ኢምንት ናቸው፡፡ መከታተል፣ ማስፈፀምና መፍትሄ መስጠት አልቻለም፡፡ መሪዎቹም ቢሆን ፣እከሌ ከመጣ አልመጣም፣ በማለት የሚሊዮን ህዝቦችን ጭቆና ለማስወገድ በተወከሉበት ሥርዓት የግል ክብራቸውን ለማስጠበቅ ሲጣጣሩ ይታያል፡፡ ሰላምና ጦርነት፣ ረሃብና ድርቅ፣ ነፃነትና ጭቆና፣ አንድነትና ብልፅግና የግል ጐጆአቸው እስኪሞላ ድረስ የቅንጦት ቃል ናቸው፡፡ የድሮው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሪዎች በጣም ጨቋኝ በመሆናቸው “የአምባገነኖች ክለብ” በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ እነዛ መሪዎች ዛሬም በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት መርሆዎች ሆነው የቀጠሉ በመሆናቸውና የሰባት ዓመታት የሥራ ውጤቱን ያዩ እንደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ሁሉ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ህዝቦችን ተስፋ አጨልሟል የሚሉ በርካታ ቢሆኑም ህብረቱ ከህዝቦቹም ሆነ ከመርሆዎቹ የሚጠበቀውን ክብርና መፈራት፣ ድጋፍና ትብብር በገንዘብ፣ በሰው ኃይልና በባለሙያ እያገኘ አይደለም፡፡ የአፍሪካም ችግር በአሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት እጅ ወድቋል፡፡ በመሆኑም ምርጥ የወረቀት ላይ ሥራ የሰራው አፍሪካ ህብረት ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት በስም እንጂ በምግባር ብዙም አልተለየም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |