| የአበባ አልሚዎች ከ10 የበለጡ ጥያቄዎች አቀረቡ |
|
|
| Wednesday, 30 January 2008 | |
|
በአበባ ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በችግሮቻቸው ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ተወያዩ፡፡ ሊፈፀሙልን ይገባሉ ያሉዋቸውን ከአስር የበለጡ ጥያቄዎች አቀረቡ፡፡
ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተካሄደው በዚሁ ውይይት የአበባ አምራቾቹ ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መካከል የመሬት ሊዝ ዋጋ እንዲቀነስ፣ የባንክ ብድርና አከፋፈል እንዲስተካከል፣ የግብር ቅነሳና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡ ያነጋገርናቸው የአበባ አምራች እንደገለፁት ከሆነ በአበባ አምራቾች በኩል የቀረቡትን ጥያቄዎች ታይተው አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጣቸው እንደሆኑም ይገልፃሉ፡፡ በውይይቱ ወቅት የንግድና ኢንዲስትሪ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከአበባ ልማት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በብድር አሰጣጥና አመላለስ ዙሪያም ከባንክ የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ መስጠታቸውም ታውቋል፡፡ የመሬት ጥያቄን በተመለከተ መንግሥት አስፈላጊውን የቦታ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጭ በባህርዳር 700 ሄክታር ለአበባ ተብሎ የተዘጋጀ ቦታ መኖሩንና ይህንንም ማልማት የሚፈልጉ ቦታውን በነፃ እንደሚያገኙ ተገልፆላቸዋል፡፡ እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ አበባ የበለጠ ገበያ እንዲያገኝ ለማድረግ መንግሥት ገበያ በማፈላለግ ጭምር ተባባሪ እንደሚሆንም እንደተገለፀላቸው በውይይቱ ወቅት የነበሩ የአበባ አልሚዎች ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡ በአበባ አልሚዎችና በሠራተኞቻቸው መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችም በአገሪቷ የሠራተኛ መተዳደሪያ ህግ ጋት መሠረት እንዲሠሩ ለአልሚዎቹ ተገልፆላቸዋል፡፡ ችግሩን በእንጭጩ ለመቅጨትም አልሚዎች ከሠራተኛ ማህበራት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተገልፆላቸዋል፡፡ በሶስትዮሽ ወገን ድርድርም በማድረግ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚቻል መሆኑንና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን በአበባ አልሚዎች መካከል እየተፈጠረ የመጣው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአበባ እርሻ በሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ ከ80 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |