| በዓለም የቆዳ ምርቶች ገበያ የኢትዮጵያ... |
|
|
| Wednesday, 30 January 2008 | |
|
በዓለም የቆዳ ምርቶች ገበያ የኢትዮጵያ ድርሻ አነስተኛ ነው
በዓለም የቆዳ ምርቶች ገበያ የኢትዮጵያ ድርሻ አናሳ መሆኑ ተገለፀ፡፡ ጥራት ያለው ያለቀለት ቆዳ በሚፈለገው ጊዜና በበቂ መጠን ስለማይገኝ በውጪ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሆነ አቅም ለመፍጠር እንቅፋት እንደሆነባቸው ተጠቆመ፡፡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ የኢንቨስትመንት ፎረም ባለፈው ቅዳሜ ጥር 17 ቀን 2000 ዓ.ም በአራራት ሆቴል በተካሄደበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪና የልማት ድርጅት ተወካይና የኢንዱስትሪ ልማት ኦፊሰር ሚስስ አውሬሊያ ካላብሮ ኢን ቤላሞሊ እንደተናገሩት፣ ያለቀላቸውን የቆዳ ምርቶች ወደ ውጪ የሚልኩ ባለሃብቶች ጥራት ያለው ግብዓት በበቂ መጠን አለማግኘታቸው ተወዳዳሪ አቅም ለመገንባት አላስቻላቸውም፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ቆዳ በጥራት ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን እንዲያገኙ የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስና የመሰረተ ልማት የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በቆዳ ውጤቶች ሰፊ አቅም እንዳላት የገለፁት ሚስስ አውሬሊያ፣ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ 23 የቆዳ ማዘጋጃ ፋብሪካዎች፣ 12 በዘመናዊ መልክ የተደራጁ የጫማ ፋብሪካዎች፣1200 በአነስተኛ ደረጃ የተደራጁ የጫማና የቆዳ ውጤት አምራቾች እንዳሉ አራት ድርጅቶች ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን መመዘኛ በማሟላት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ በማምረት ሥራ ላይ ከተሰማሩት የጫማ ፋብሪካዎች የውጪ ገበያ የማግኘት እድላቸው ሰፊ ቢሆንም በለሰለሰ ቆዳ፣ ልዩ ልዩ ግብአቶችና ኬሚካሎች ችግር ምርታቸውን በወቅቱ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግርን ለመቀነስ የቆዳና ቆዳ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት አቅም ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በአነስተኛ ዋጋ የሚቀርቡ የእስያ አገሮች የቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለማሸነፍ ተወዳዳሪ አቅም መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በሰለጠነ የሰው ኃይል በአስተዳደር፣ በቴክኖሎጂና ገበያ በሚያገኙበት ሂደት የዘርፉን ባለሃብቶች መርዳት እንደሚገባ፤ በአገር ውስጥ የሚገኙ ባለሃብቶችን ድርሻ ለማሳደግ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የተሰማሩ ባለሃብቶችን አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑንም ሚስስ አውሬሊያ አስረድተዋል፡፡ በፎረሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ መንግስት የቆዳና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች አቅም ለማጠናከር ያለውን የቢዝነስ አካባቢ የተመቻቸ በማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን፣ ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያ የጫማ ምርቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ጀርመንና ጣሊያን በመላክ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆኗን ገልፀዋል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት 90 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 75 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ብልጫ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡ በዓለም ላይ ያለው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ገበያ ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም ኢትዮጵያ ያላት ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የቆዳ ውጤቶች ምርት ሳይጠናቀቅ ወደ ውጪ የሚላክ እንደነበር፣ አሁን ወደ ውጪ የሚላክ ያለቀለት የቆዳ ምርት 60 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ ያለቀላቸውን የቆዳ ምርቶችን ለመላክ በሚደረገው ሂደት በሚፈገለው መጠን ጥሬ እቃ አለማግኘት፣ የገበያ፣ የቴክኒክ እውቀት አናሳነትና በተለያየ ደረጃ በማምረት ላይ የተሰማሩት ባለሃብቶች ትስስር ደካማ መሆን ችግር መፍጠሩን አቶ ኃይሌ አመልክተዋል፡፡ በቆዳና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ቁጥር በመጨመርና በቴክኖሎጂ ሽግግር በሚደረገው ሂደት የአገር ውስጥ የቆዳ ምርቶችን ድርሻ ለማሳደግ እንደሚረዳም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ በግልና በመንግሥት ዘርፍ መካከል ያለውን ተቋማዊ ጥምረት በማጠናከር፣ የውጪ ባለሃብቶችን ተሳትፎ በማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በፎረሙ በአገር ውስጥ ኢንቨስት አድርገው የሚንቀሳቀሱት ባለሃብቶች ተሳታፊ ሲሆኑ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶች ከቀረጥና ታክስ ነፃ መግባታቸው በአገር ውስጥ በግብአት ማምረት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን እንደሚያበረታታ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የነፃ ቀጣና አባል አለመሆኗ፣ የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነት አለመፈረሟ ያለቀላቸው የቆዳ ውጤቶች የገበያ ችግር እንዲኖር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |