|
Wednesday, 30 January 2008 |
|
ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የሸቀጦችና የተለያዩ ምርቶች ዋጋ እያሻቀበ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ጭማሪው እስከዛሬ ከተደረጉ ሁሉ ከፍተኛ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
በሐምሌ ወር 1996 ዓ.ም በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ በነበረበት ወቅት እንኳን በአንድ ሊትር ላይ ተጨምሮ የነበረው 0.72 ሣንቲም ብቻ ነበር፡፡
በሚያዚያ 1996 ዓ.ም በተደረገው ጭማሪ 0.29 ሣንቲም፣ በነሐሴ 1996 ዓ.ም ደግሞ 0.43 ሣንቲም እንደጨመረ ይታወሳል፡፡
አዲሱ ጭማሪ ተግባራዊ እንዲሆን እስከተደረገበት እስካለፈው ሳምንት ድረስም በተከታታይ በተደረጉ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያዎች ወቅት የተደረገው ጭማሪ በሣንቲም ቤት ነው፡፡
የአሁኑ ግን በተለይ በቤንዚን ላይ የተደረገው ጭማሪ በ1996 ዓ.ም በሁለት ጊዜ የነዳጅ ማስተካከያ ከተጨመረው ዋጋ በእጥፍ አድጎ በአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ከ1.60 በላይ ተጨምሯል፡፡
የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የምግብ እህሎችን አቅርቦት በመጨመር የማካካሻ ድጎማ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የዋጋ ቅናሽ እስከማድረግ የሚደርስ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪና የተለያዩ ምርት አቅራቢ ነጋዴዎች ደግሞ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ካነጋገርናቸው መካከል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ወልዳይ አመሃ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ መስጠት ካልቻለ የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የምግብ ምርቶችን አቅርቦት መጨመር አስፈላጊ ነው፡፡
የነዳጅ መጨመር በአገሪቷ ኢኮኖሚ በተለይ አነስተኛ ገቢ ባለው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ድጎማ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው አሁን የተፈጠረውን የነዳጅ ዋጋ ለውጥ ለማስተካከል ከሚያስፈልገው ድጎማ በተሻለ አነስተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይጎዳ ሌሎች አማራጭ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡
የነዳጅ ምርቶች ከማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ጋር ያላቸውን ከፍተኛ ትስስርና አኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አዋጅ የ1993 አዋጅና በ1995 በተደረገ ማሻሻያ በገንዘብ ሚኒስቴር በተከፈተ ልዩ የባንክ ሂሳብ ተቀማጭ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የፈንዱ ዓላማ በዓለም ገበያ በሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ ማደግ ምክንያት የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጐም ማረጋጋት፣ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ዓላማን ሳያደናቅፍ መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሥራዎች ወጪ መሸፈን እንደሚሆንም በአዋጁ ተገል..ል፡፡ ፈንዱ፣ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት ከሚገኝ ተራፊ ሂሳብ፣ ለነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ እንዲውል ከሚገኝ የውጪ እርዳታ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሠረት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መሠረት በማድረግ በነዳጅ ምርቶች የሃገር ውስጥ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ክለሳ በየ3 ወሩ ይከናወናል፡፡ የነዳጅ ዋጋን ለመደጎም ካለፈው ዓመት ታህሳስ 1999 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2000 ዓም ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሕዝብ ቁጥር እድገትና የኢኮኖሚ እድገት በነዳጅ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ እንዳላቸው፣ በአገራችን 65 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግድ ለነዳጅ ግዢ እንደሚውል ዶ/ር ወልዳይ ተናግረዋል፡፡
የዓለም የአንድ በርሜል የነዳጅ ዋጋ በ2002 ሃያ ዶላር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት እያደገ ከመጣው ፍላጐትና ዋጋ አንፃር ለነዳጅ ድጎማ ለመስጠት የመንግሥት አቅም አናሳ በመሆኑ ወደ ሕዝብ ማውረድ ግድ ማለቱንም ዶክተር ወልዳይ ይስማሙበታል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ለወደፊት ብዙም የመቀነስ አዝማሚያ እንደማይኖረው ገልፀው የዋጋ መቀነስ ቢኖረው እንኳ የሚያስፈልገውን ድጎማ አስልቶ ለሌሎች የሚወጣውን ወጪ ማሸጋገር ይቻል እንደነበርም ገልፀዋል፡፡
የሚፈጥረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ህብረተሰቡ በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኝ ድጎማ መስጠትና ፍላጐትን እንዲቀንስ ማድረግ እንደ አማራጭ ቢወሰድም ድጎማ መስጠት ካለው የመንግሥት አቅም ጋር የማይቻል መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ወልዳይ የነዳጅ ፍላጐትን በአጭር ጊዜ መቀነስ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ መጨመር የነዳጅ የኃይል ፍላጐትን ይቀንሳል የሚል ግምት ቢኖርም በነዳጅ ፍላጐት ላይ ብዙም ለውጥ እንደማይፈጥር ተናግረዋል፡፡ በሌሎች ምርቶች በተለይ በትራንስፖርትና በምግብ እህሎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ይህም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጎዳ አስረድተዋል፡፡
በሌሎች አገሮች በነዳጅ ጭማሪ የምግብ እህሎች ዋጋ የመጨመር አቅሙ አናሳ እንደሆነና በአገራችን ይህን ሁኔታ ለመፍጠር እጥረት ያለባቸውን ምርቶች በስፋት በማስገባት አቅርቦትን መጨመር አስፈላጊ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡
የነዳጅ ሃይል ፍላጐትን በሌላ በመተካት አማራጭ የሃይል ምንጮችን መጠቀም በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ለውጥ የማምጣት አቅሙ አነስተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የንግድና ኢንዲስትሪ ሚኒስቴር የነዳጅ ዋጋ መጨመርን አጋጣሚ ተጠቅመው በሸቀጣሸቀጥ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ቢገልፅም የተለያዩ ምርቶች ዋጋ በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ለመቆጣጠር ምን ማድረግ ያስፈልጋል ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ወልዳይ ሲመልሱ፣ ቁጥጥር በአግባቡ ተግባራዊ እንደማይደረግ፣ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ቁጥጥሩ ቀጣይ እንዳይሆን እንደሚያደርገው ገልፀው በገበያ ኢኮኖሚ ገበያ እንዲሠራ ማድረግ እንጂ ቁጥጥርና እርምጃ መውሰድ የሚጨምሩት ምርቶች ዋጋ የመቀነስ አቅም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ነዳጅ የማይነካው የኢኮኖሚ ክፍል እንደማይኖርና በተለያዩ ምርቶች ላይ የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ በተለያየ ደረጃና መጠን የዋጋ ግሽበትን እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡ በ1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት በሚፈጠር የአቅርቦትና የፍላጐት ግፊት እስከ 3 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ንረት ሊፈጠር እንደሚችልና አሁን ያለው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያለውን የዋጋ ንረት እንደሚያባብሰው አመልክተዋል፡፡
ከሰሞኑ የነዳጅ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ያነጋገርናቸው የተቆፋሪ ኮንስትራክሽን እቃዎች አቅራቢ ድርጅት ባለንብረት የሆኑት አቶ ሣምሶን አድሃኖም እንደገለፁት ደግሞ ከጥር 20 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በሚያቀርቧቸው ተቆፋሪ የኮንስትራክሽን እቃዎች ላይ ዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው የነዳጅ ጭማሪው በኢኮኖሚው ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን ተጽዕኖ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
አቶ ሳምሶን እንደገለፁት፣ የነዳጅ ጭማሪው ከመደረጉ በፊት 16 ሜትር ኪውብ አሸዋ አዲስ አበባ ውስጥ ከ2400 እስከ 2500 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ዋጋ ከ2500 እስከ 2600 ብር ሊያድግ ችሏል፡፡ ይህ ለተጠቃሚው ትልቅ ጭማሪ ነው ብለዋል፡፡
ዋነኛ ምክንያቱም አንድ መኪና አሸዋ ጭኖ ለመምጣት የ300 ብር ነዳጅ ያስፈልገው ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ዋጋ ከ365 እስከ 370 ብር ድረስ በመጨመሩ እንዲሁም የተለያዩ ዘይቶችና ለመኪናው የሚያስፈልጉ ምርቶች ጭማሪ በማሳየታቸው ዋጋው ሊያድግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
አቶ ሣምሶን አሁን ያደረጉት የአሸዋ ዋጋ ጭማሪ ብዙ እንዳልሆነና ከትናንት ጀምሮ ያደረጉት ጭማሪ ጊዜያዊ ሊሆን እንደሚችልና ይህ ጭማሪ ሊያዋጣ እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡትም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ከዚህ በኋላ በእያንዳንዱ የመኪና እቃ ዋጋ ላይ ጭማሪን ስለሚያስከትል ወጪ ሊበዛ ይችላል፡፡
ከእቃዎች ዋጋ መጨመር በተጨማሪ የሾፌርና የረዳቶች አበልና ደመወዝ ለማስተካከል ሊያስገድድ ይችላል፡፡
የድንጋይ ዋጋም ከአንድ መቶ ብር በላይ ጨምሯል፡፡ እስከ አሳለፍነው ሳምንት ድረስ 6 ሜትር ኪዩብ ድንጋይ በአማካይ 600 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ከተሰማ በኋላ ግን በአንዴ የአንድ መቶ ብር ጭማሪ አስከትሏል፡፡
ድንጋይ ብዙውን ጊዜ ጭማሪ የሚደረግበት ክረምት ክረምት ነው የሚሉት አቶ ሣምሶን ..ክረምት ክረምት ድንጋይ ከተለያዩ ካባዎች ለመጫን ያስቸግራል፡፡ መኪኖች ጭቃ ውስጥ ስለሚቀረቀሩ ለማምጣትና ለመሸጥ ስለሚያስቸግር ዋጋው ይጨምራል፡፡ አሁን ግን የተጨመረው በነዳጅ ጭማሪ ሳቢያ ነው.. ይላሉ፡፡
ከነዳጅ ጭማሪው ጋር በተያያዘ ይህንን ሪፖርት እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ዋጋቸው ጭምሯል ከተባሉ እቃዎች ውስጥ ለእንጨትና ለእንጨት ሥራዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ ግብአቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የመለስተኛ የቤትና የቢሮ እቃዎች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት እቃዎች በአንድ ቀን ልዩነት ዋጋቸው ከፍ ብሏል፡፡
ለምሳሌ የትናንት ሳምንት ማክሰኞ መርካቶ እንጨት፣ ብረት፣ ኮላ፣ ማስቲሽና የመሳሰሉትን ሲገዙ የዋጋ ጭማሪ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የአሁኑ ሰኞ ጥር 19 ቀን 2000 ዓ.ም ይህንኑ እቃ ለመግዛት ሲሄዱ እያንዳንዱ እቃ ላይ ከ5 እስከ 10 ብር ዋጋ መጨመሩን አስረድተዋል፡፡
በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ዋጋ ጨምሯል፡፡ ባለፈው ሣምንት 20x20 የሆነ ቱቦ ላሬ 42 ብር ነበር፡፡ በቀናት ልዩነት 48 ብር ገብቷል፡፡
ሁለት ጊዜ ጭማሪ የተደረገው የነዳጅ ዋጋ ከመጨመሩ በፊት እቃ ተወዷል ተብሎ ነው፡፡ ወዲያው የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ደግሞ ይህንኑ ምክንያት ተደርጎ ዋጋው ጨምሯል፡፡
የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ እስካሁን አነስተኛ ነው ቢባል እንኳን ከእንግዲህ አነስተኛ ነው ማለት አይቻልም ያሉት ደግሞ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡
መካከለኛ ገቢ ያለው ሰው እንኳ ፈጽሞ የሚችለው እንዳልሆነና በአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ላይም የራሱ የሆነ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አቶ ቡልቻ አመልክተዋል፡፡
ችግሩ ሰዎች ብዙ ገንዘብ ስለሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች ወደ ባንክ ሄደው እንዲበደሩም ያስገድዳቸዋል ያሉት አቶ ቡልቻ ..የቤንዚን ጭማሪው እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ይነካል፡፡ መንግሥትም ይህንን ችግር በሚገባ ይረዳል፡፡ ስለዚህ ይህንን ያህል ከፍተኛ ጭማሪ ሲያደርግ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በነዳጅ ጭማሪ ሰበብ እያንዳንዱ ተገልጋይ የሚደርስበትን ተጨማሪ ወጪ የሚሸፍን ማካካሻ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መንግሥት ማመቻቸት እንዳለበት፣ ይህ ሲባል ግን ስንዴን ለዝቅተኛ ኅብረተሰብ እንደታደለው አይነት ሳይሆን ሁሉም ኅብረተሰብ በዝቅተኛ ዋጋ ግብይት የሚያገኝበትን ሥርዓት ማመቻቸት እንደሆነ አቶ ቡልቻ አመልክተዋል፡፡ ላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ቤንዚን እንዲህ ሲጨምር ኅብረተሰቡ በጭማሪው ሳቢያ የትራንስፖርት ዋጋ ጨምሮ እንዲከፍል ከማድረግ ይልቅ መንግስት በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የሚጣለውን ቀረጥ መቀነስ ይኖርበታል፡፡
በሌሎች ከትራንስፖርት ዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቀረጦች ላይ ቅናሽ በማድረግ ኅብረተሰቡ ላይ የተደራረበውን የዋጋ ጭማሪ ማካካስ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ቡልቻ አሁን ግን ይህ እየሆነ ስላልሆነ መስተካከል እንደሚኖርበት ጠይቀዋል፡፡
እንዲህ አይነቱ የማካካሻ እርምጃዎች በሌሎች አገሮችም ይደረጋሉ፡፡ መንግስት ከጭማሪው በፊት እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ መዘጋጀት እንደነበረበትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በተለይ ከኮንስትራክሽን እቃዎች ጭማሪ ጋር በተያያዘ የግንባታ ሥራዎች ይጠናቀቃሉ ተብለው በተያዘላቸው በጀት እንደማይጠናቀቁ የገለፁልን ደግሞ የኮንስትራክሽን ባለሙያ ናቸው፡፡
እኚሁ ባለሙያ እንደገለፁት እንዲህ አይነት የዋጋ ጭማሪዎች ኮንትራክተሩ ጨረታ ካሸፈነበት ዋጋ በላይ ወጪ ይጠይቀዋል፡፡
ስለዚህ ሆነ በግለሰብ የሚሰሩ ግንባታዎች አሁን እየጨመረ የሚመጣውን ዋጋ ተንተርሶ ጉዳዩ እንዲታይላቸውና ተጨማሪ ገንዘብ እንዲጨመርላቸው ያስገድዳቸዋል ብለዋል፡፡
የማካካሻ ጭማሪው ተጠይቆ አዎንታዊ መልስ ቢያገኝ እንኳን ችግር መፈጠሩ እንደማይቀር ጠቁመዋል፡፡ መለቀቅ የሚፈለገው ገንዘብ በቶሎ መለቀቅ ካልተቻለ የግንባታ ጊዜው በመራዘም ተደራራቢ ወጪዎችን ያስከትላልና መንግሥት ከዚህ ጭማሪ ጋር በተያያዘ በኮስትራክሽን ዘርፍ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ለመቆጣጠር መዘጋጀት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በነዳጅ ላይ ድጎማ ማድረግ እንዳለበት ያምናሉ፡፡
ነዳጅ ተደጎመ ማለት አጠቃላይ የዋጋ ንረት እንዳይኖር በመከላከሉ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ባይ ናቸው፡፡
በዳዊት ታዬና በቤዛዊት ስዩም |