|
Wednesday, 30 January 2008 |
ለምን እባክህ? ለምን? በሚጠራጠሩ ሽፋሎች በሚያቃጥሉ አይኖች በሚታዘቡ ደሞች በሚመረምሩ ገጥታዎች ለምን እባክህ? ለምን?
በተለወጡ ቃሎች በተዳፈኑ ሳቆች በደመኑ እልልታዎች ባኮረፉ ፈገግታዎች ለምን እባክህ? ለምን?! ብበላ ገንፎ ብበላ እስክትደረጅ ጥርስ እስክታወጣ ብጠጣ አጥሚት ብጠጣ አፍና ምላስ እስክታወጣ እና. . ብበላ አንተ እስክትበላ ብጠጣ አንተ እስክትጠጣ ለምን ታዲያ እባክህ? ለምን? /ፈቃደ አዘዘ፣ ዐሻራ፣ 1994/
ግራሩ ሥር
ሰውየው ዘላን ነበር ይባላል፡፡ እናቱ ሞተችና ወደ ቤተ ክርስቲያን ሬሳዋ ሲሄድ ጉዞ ፍታት ሁኖ በአንድ ግራር ሥር አስከሬኗ ስላረፈ ልጅየው ያው ዘላን እንደዚህ ሲል በለቅሶ ዜማ አለቀሰ፡፡
ወዴት ጠጋ፣ ጠጋ ወደ ግራሩ ሥር ወተት ቢጌራራ የሚገኝ ይመስል አለ፡፡ ጌራራ ማለት የወተት ማለቢያ ነው፡፡ እሱ ግን ከእውነቱ ከአንጀቱ ነው ያለቀሰው፡፡
የቤተመንግሥት ጥሪ /በአንድ ወቅት የተፈፀመ የእጩ መኮንኖች አቀጣጠር/
ጊዜው ሐምሌ 1941 ዓ.ም ሲሆን ወራቱ ክረምት ስለሆነ ያካፋል፡፡ በሦስት የጦር ሰራዊት ካሚዮኖች ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ከተፈሪ መኮንንና ከጄነራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የመጡ ወደ 60 የሚሆኑ ተማሪዎች ቤተመንግስት እንደደረሱ በሰልፍ ሆነው በእልፍኝ አስከልካዩ አማካኝነት ወደ ጃንሆን ልዩ ጽ/ቤት ገብተው እጅ እየነሱ ከጃንሆይ ፊት ቆሙ፡፡ በእሳት ማንደጃው የተማገደው እንጨት ክፍሉን አሙቆታል፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱና ከማንደጃው ግራና ቀኝ መኳንንት ቆመዋል፡፡
ጃንሆይ ንግግራቸውን የጀመሩት "ምንድነው ይህ ሤራ" ብለው በመቀለድ ነበር፡፡ በመቀጠልም "እናንተ አሁን ልጆች ስለሆናችሁ ስለ አየር ኃይል ጥቅም አታውቁም፡፡ ምናልባት አሁን አየር ኃይላችን ትንሽ ስለሆነች ይሆናል እዚያ ለመግባትና ለመቀጠር የማትፈልጉት፡፡ ለወደፊት ከታሪክ እንደምትረዱት የእንግሊዝ ሮያል ኤይር ፎርስ የማልታን ደሴት በጀግንነት የተከላከሉት በሁለት አይሮፕላኖች ብቻ ነበር.. አሉ፡፡
ከዚያም ተማሪዎቹ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች አቀረቡ፡፡ ከተማሪዎቹ አንዱ ጌታሁን እጅጉ /አሁን ኮሎኔል/ ..እኔ መሐንዲስ መሆንና ቤተሰቦቼን መርዳት ነው የምፈልገው.. ሲል ሌላው "ገበሬ መሆን ነው የምፈልገው" አለ፡፡ ጃንሆይም ..መሐንዲስነት የሚፈልገው የአውሮፕላን መሐንዲስ መሆን ይችላል፡፡ የቤተሰብ ችግር ካለባችሁ በአሰፋ በኩል ይቅረብልንና ርዳታ ይደረግላችኋል፡፡ ማወቅ ያለባችሁ አገራችሁን ካልተከላከላችሁ መሬታችሁ ከተነጠቀ የት ሆናችሁ ነው የምታርሱት?.. በማለት መሪ ቃል ተናግረው ተማሪዎቹን አሰናበቱ፡፡ ከዚያ በኋላ በእልፍኝ አስከልካዩ "እጅ ንሱ".. ተብለው ከጽህፈት ቤቱ ወጥተው በመጡበት አኳኋን ወደየ ትምህርት ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ተማሪዎቹ መኪናው ላይ ከመሳፈራቸው በፊት ጄኔራል አሰፋ አየነ /በዚያ ጊዜ ሻለቃ/ ሰብስበው ትምህርት ቤቶቹ ለሦስት ወራት ተዘግተው እስከሚከፈቱ ወጣቶቹ አየር ኃይል እንዲቀጠሩ ለማበረታታትና ተጨማሪ ፍላጎት ለማሳደር ሳይሆን አይቀርም በትርፍ ጊዜያቸው በከተማው ውስጥ በዚያን ጊዜ ከታወቀ የወታደር ልብስ ሰፊ ኤድዋርድ ጋራቤዲያን ዘንድ እየሄዱ የገበርዲን ዩኒፎርም አንዲለኩ አዘዙ፡፡
/መኮንን በሪ፣ አሺዬሽን በኢትዮጵያ፣1995/
የሰውነት ክብደትና ጤና
ክብደትዎ ለጤናዎ ወሳኝ ነው፡፡ ከመጠን በላይ ወፍረው ከሆነ ጤናዎ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው፡፡ አዲስ ነገር ስላልሆነ፣ ይሄን አርስዎም ሳያውቁት አይቀሩም፡፡ ያለመጠን መወፈር እድሜ እንደሚያሳጥር ያውቁ ይሆናል፡፡ ከሞት መለስም ብዙ በሽታዎች ከክብደት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ድንገተኛ የልብ በሽታ፣ ስትሮክ /የአንጎል ደም ስር በሽታ/፣ ሌሎች የደም ሥር በሽታዎች፣ የደም ግፊት ብዛት፣ የስኳር በሽታ፣ የጡትና የማህፀን ካንሰር፣ የአንጀት እና የኩላሊት ካንሰር፣ የቁርጥማት በሽታዎች፣ መሀንነት፣ የሃሞት ጠጠር፣ አስምና የእንቅልፍ በሽታዎች ከክብደት መጨመር ሊመጡ የሚችሉ በሽታዎች ናቸው፡፡
ከሚበሉት አይነት ምግብ ይልቅ፣ የሚበሉት ምግብ መጠን ለውፍረት ወሳኝነት አለው፡፡ በዚ ምዕራፍ የምናተኩረውም በምግብ መጠን ይሆናል፡፡
የውፍረት ሦስት ገጽታዎች መጠን መወፈር ወይም መክበድ ሲባለ ሦስት ገጽታዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ እነዚህ ሦስቱም ለጤናዎ ወሳኝ ናቸው፡፡ ለቁመትዎ ያልመጠነ ክብደት፣ የጨመሩት ክብደት መጠንና የወገብ ወይም የመቀነትዎ ዙሪያ ያለመጠን መስፋት ናቸው፡፡
ለቁመትዎ ያልመጠነ ክብደት
የሰውነት ክብደትዎ ለቁመትዎ መመጠኑን ወይም አለመመጠኑን ለማወቅ ቢ.ኤም.አይ /ቦዲ-ማስ-ኢንዴክስ/ የሚባል አሀዝ ወይም ኢንዴክስ መጠቀም ይቻላል፡፡ መጀመሪያ ክብደትዎን /በኪሎ ግራም/ ያስቀምጡ፡፡ ቀጥለው የቁመትዎን ልክ /በሜትር/ ያስቀምጡ፡፡ የቁመትዎን ልክ እርስ በራሱ ያባዙት፡፡ በመጨረሻም ክብደትዎን በዚህ /በማባዛት ባገኙት ቁጥር/ ያካፍሉት፡፡ የሚያገኙት ቁጥር የቢ.ኤም.አይ አሃዝ ወይም ኢንዴክስ ይባላል፡፡
/ፕሮፌሰር ደረጀ ከበደ፣ ዶ/ር ትዕግስት ቀፀላ፣ እውቀት ለጤንነት/
ገራገር በምግብ ውስጥ የሰው ምላስ ተገኘ
በስሎቫኒያ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ለመመገብ የሄደ ዶክተር በሚመገበው ምግብ ውስጥ የተቆረጠ የሰው ምላስ ማግኘቱ ተገለፀ፡፡
በደቡበ ስሎቫኒያ በሚገኝ ሆስፒታል ዶሮ ለመመገብ የገባው ዶክተር በምግብ ውስጥ ያገኘው ቁራጭ ስጋ ምንነት በተደረገው ማጣራት ከሰው ልጅ ምላስ የተቆረጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የጤና ተቆጣጣሪዎች ሬስቶራንቱን ዘግተው ያለበትን የንጽህና ሁኔታ በማጥናት ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የሆስፒታሉ አስተዳደሮች ቁራጭ ምላስ በቀዶ ጥገና ላይ የነበረ ዶክተር ለመመገብ ሲመጣ ጥሎት ወይም ለምግብነት የሚጠቀሙበት ምግብ ከውጪ ሲመጣ ምላሱ ተቀላቅሎ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
በስሎቫኒያ የሚገኘው የዴይሊ ፔፐር ህዝብ ግንኙነት ምላሱ በምግብ ውስጥ ሊገኝ እንደቻለ የተረጋገጠ መረጃ እንደሌለ ገልጿል፡፡
አዛውንቱ ከ20 ዓመታት በኋላ ፓስፖርት አገኙ
በመቄዶኒያ የሚገኙ የ109 ዓመት አዛውንት እድሜያቸውን ለማጣራት ከ10 ዓመታት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ፓስፖርታቸውን ማግኘታቸው ተገለፀ፡፡ በየካቲት ወር 1898 የተወለዱት ማሪያ ኮስቶቫ በተወለዱበት ጊዜ የልደት ሠርተፊኬት መስጠት እንዳልተጀመረ ተገልጿል፡፡ የአካባቢው ባለሥልጣናት የኮስዮቫ የልደት ጊዜ የሚያሳየውን መረጃ በመጣላቸው መረጃዎች በመፈለግ ከ20 ዓመት በላይ እንደፈጀባው ተገልጿል፡፡ 110 ዓመት ልደታቸውን በሚያከብሩበት በሚቀጥለው ወር ፓስፖርታቸውን እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡ ኮስቶቫ ሁኔታውን አስመልክተው ..አስደሳች የሆነ አጋጣሚ ነው፡፡ በዓል እንዴት እንደሚያስደስት እያሰብኩ ነው፡፡ አሁን ልደቴን በደስታ ማክበር እችላለሁ.. ብለዋል፡፡
በጥርሱ ብዙ አሳ የሚይዘው ውሻ ሊሸጥ ነው ንድ የዓሳ አጥማጅ አብሮት አሳ የሚያጠምደውን ውሻውን ከእርሱ በተሻለ ብዙ አሳዎችን በመያዙ ሊሸጠው መሆኑን አስታወቀ፡፡
በክሮሺያ አድሪያቲክ ደሴት አቅራቢያ በሚገኝ የአሳ ማጥመጃ ሥፍራ በአሳ አጥማጅ ጓደኞቹ የሚደርስበት ዘለፋ ስላማረረው ውሻውን ለመሸጥ መወሰኑንም ተናግሯል፡፡
ስሎቦዳን ፖፖሬላ የተባለው ክሮሺያዊ ብዙ ጊዜ አሳ ለማጥመድ ሲሄዱ አስቸጋሪና ለምግብነት የማይውሉትን አሳዎች እንደሚያጠምድ ገልጿል፡፡ ሊኒ የተሰኘው ውሻው ግን ውሃ ውስጥ ዘሎ በመግባት በጥርሱ ደርዘን የሚሞሉ አሳዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው ተናግሯል፡፡
እንደ ፓፓራላ ገለፃ፣ አሳ ለማጥመድ ብዙ ደክሞ ከሚያገኘው በበለጠ በማግኘቱ ጓደኞቹ ስለሚስቁበት ውሻውን ከመሸጥ ውጪ ሌላ አማራጭ ማጣቱን ተናግሯል፡፡ |