Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 25th
Home arrow Sections arrow “የማኅበረሰቡ ጥያቄ ሰፊ ነው...
“የማኅበረሰቡ ጥያቄ ሰፊ ነው... Print E-mail
Wednesday, 30 January 2008
“የማኅበረሰቡ ጥያቄ ሰፊ ነው፤ ያለን ሀብት ግን ውሱን ነው”

አቶ አይናለም መርስዔ
የዜማ ሴቶች ለፍትህ የተጠቂ ሴቶችና ህፃናት ማዕከል አስተባባሪ

አቶ አይናለም መርስዔ በዜማ ሴቶች ለፍትህ የተጠቂ ሴቶችና ህፃናት ማዕከል አስተባባሪ ናቸው፡፡ ከአስር ዓመት በፊት በተቋቋመውና ቀደም ሲል “ፕሮጃይኒስት” እየተባለ ይጠራ በነበረው አሁን “ዜማ ሴቶች ለፍትህ” በሚባለው ተቋም በተለያዩ ደረጃዎች ሠርተዋል፡፡
ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በተቋሙ አማካኝነት በተቋቋመው ማዕከል አስተባባሪነት በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በማዕከሉ አገልግሎቶች፣ በአጠቃላይ የድርጅቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ ቤተልሔም ነጋሽ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ መቼ ተመሠረተ?

አቶ አይናለም፡-
ማዕከሉ ከተመሠረተ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ ዜማ ሴቶች ለፍትሕ ከሚያካሂዳቸው ዋና ዋና ፕሮግራሞች አንዱ ነው፡፡ ስለ ድርጅቱ ብናወራ ከ10 ዓመታት በፊት የተቋቋመና “ፕሮጃይኒስት” በሚል ሲጠራ የቆየ ነው፡፡ “ዜማ ሴቶች ለፍትሕ” የሚለውን ስያሜ የያዘው ከአንድ ዓመት ወዲህ ነው፡፡

ዋና ራዕዩ ሴቶች ከወንዶች እኩል በሀገር ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉ ለማድረግ ሲሆን በሴቶችና በህፃናት ላይ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ ለማድረግ ይሠራል፡፡ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ ደግሞ ትምህርትና ሥልጠናዎችን ያከናውናል፡፡ ከዚህ ሌላ የትምህርት ዕድል ያጡ ሴት ህፃናትን በማሰባሰብ አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት የሚሰጥበት ፕሮግራም አለው፡፡ ይህ ፕሮግራም ወደግልም ሆነ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ገብተው መማር ያልቻሉ ህፃናትን አሰባስቦ የሚያስተምርበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ፕሮጀክት አዲስ አበባ የሚከናወን ነው?

አቶ አይናለም፡-
አዲስ አበባ እና በደቡብ ሕዝቦች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል ጉራጌ ዞን ሁሉም ወረዳዎች ይካሄዳል፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ስር ለሴት ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የቤተ መጽህፍት አገልግሎትም አለው፡፡

ሌላው የጤናና የአካባቢ እንክብካቤ ዲፓርትመንት ሲሆን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራምም በዚህ ስር ነው፡፡ ሴቶች ሁለንተናዊ አቅማቸው መገንባት ስላለበት የውሀ አቅርቦት እንዲኖር ቦኖ መገንባት፣ የልብስ ማጠቢያ ገንዳዎችንና መፀዳጃ ቤቶችን መገንባት፣ የሕዝብ ገላ መታጠቢያዎችን የመገንባት ሥራ ይሠራል፡፡ በጤና በኩል ስልጠና ይሰጣል፡፡ የመፀዳጃ ቤት፣ ውሀ በሌለበት በቅድሚያ ተጐጂዎች ሴቶች በመሆናቸው ይህንን ማድረግ የግድ ነው፡፡

ሌላው ፕሮግራም ሴቶች የንግድ ክህሎት ስልጠና የሚያገኙበት ዲፓርትመንት ነው፡፡ በዚህ በኩል ሴቶች እየተደራጁ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ስልጠና ሲጨርሱ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በድርጅቱ አማካኝነት የተቋቋመ “መክሊት” የተሰኘ ብድርና ቁጠባ ተቋም አለ፡፡ ለዚሁ ተብሎ የተቋቋመ ነው፡፡ መክሊት ከአዲስ አበባ ውጪ ፕሮጀክቱ በሚንቀሳቀስበት ቦታዎች ጭምር ይሠራል፡፡ ድርጅቱ በአራቱ ፕሮግራሞች በኩል የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለመገንባት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

አቶ አይናለም፡-
በአዲስ አበባ ሁለት ክፍለ ከተሞች ላይ ይሠራል፡፡ ረጅም ጊዜ ሲሠራ የቆየው ልደታ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ተጨምሯል፡፡

ሪፖርተር፡- እነኝህ አካባቢዎች የተመረጡበት ምክንያት አለ?

አቶ አይናለም፡-
ቀደም ሲል የአዲስ አበባ አደረጃጀት በወረዳ ስለነበር፣ የቀድሞው ወረዳ 4 ነበር የሚባለው፡፡ ለመርካቶ ቅርብ የሆነና በብዙ ችግሮች ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ድርጅቱ ባስጠናው ጥናት ከአዲስ አበባ አካባቢዎች የከፋ ችግር ያለበት እንደሆነ በማወቁ ነው፡፡ የድህነት መጠኑ ከፍ ያለበት ስለሆነ፣ የንፅህናውም የትምህርት አለመዳረሱም አለ፡፡ በዚህ ወቅት ተጐጂዎቹ ሴቶች እንደመሆናቸው፣ የክፍለ ከተማው ሴቶችም ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ ስለነበር ከዚያ አንፃር ወደዚያ ገብተናል፡፡ ነፋስ ስልክ የተመረጠበት ደግሞ የመጀመሪያው 5 ዓመት ተግባራችን ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጋችን ታይቶ እንድንቀጥል ሲፈቀድልን ተጨማሪ ክፍለ ከተማ እንዲጨመር ተወሰነ፡፡ አጐራባች ሲመረጥ ነፋስ ስልክ ተወሰነ፡፡ ቀጥሎ ወደ አዲስ ከተማ ለመግባት እያሰብን ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ውጪ በጉራጌ ዞን ሁሉም ወረዳዎች ላለፉት 5 ዓመታት ሠርተናል፡፡ የእዚያ ውጤት በታየው መሠረት ስልጤ ዞንንና የኦሮሚያ አካል የሆኑ ሌሎች ዞኖች ለመጀመር እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አስመዝግበናቸዋል የሚሉት ዋና ዋና ውጤቶችስ?

አቶ አይናለም፡-
የፆታ ጥቃት ተከላካይ ቡድን በጉራጌ ዞን ሁሉም ወረዳዎች ላይ ማቋቋም መቻላችን አንዱ ነው ምክንያቱም ለሌላ አካባቢዎች በሙሉ ሞዴል ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ቡድኖቹ በሁሉም የጉራጌ ዞን ወረዳዎች ተቋቁመዋል፡፡ ውጤት የተገኘበት ስለሆነ ያንን በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ለመድገም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ሌላው ይህ የተጠቂ ሴቶች ማዕከል መከፈቱ ትልቁ የለውጥ መጀመሪያ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ጊዜ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በተከታታይ ይሠራል፡፡ ነገር ግን ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መደመጥ ይፈልጋሉ፣ የደረሰባቸውን የሚናገሩበት ስፍራ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ማዕከል የተከፈተበት ዋና ዓላማ ጥቃት የደረሰባቸው የንፋስ ስልክና ልደታ ክፍለ ከተሞች ነዋሪ ሴቶችና ህፃናት እንዲሁም ወንዶች ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ የነፃ የስልክ መስመር አለን፡፡ የምክር አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በግንባር መጥተው ምክር አገልግሎት ይሰጣቸዋል፣ ወደህግ ጉዳያቸውን ለሚወስዱ የህግ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ ማዕከሉ ይህንን የሚያደርገው በሠራተኞችና በፈቃደኝነት በሚሠሩ የህግ ባለሙያዎች አማካኝነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁሉም ባለሙያዎች አገልግሎቱን የሚሰጡት በማዕከሉ ተገኝተው ነው?

አቶ አይናለም፡-
የህግ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቹ የሚሠሩት ባሉበት ነው፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ የሚሠሩ፣ በንፋስ ስልክ እንዲሠሩ የተመለመሉ ናቸው፡፡ ለዚሁ የሚረዳቸው  ስልጠና ወስደዋል፡፡ ስልጠናዎቹ በተሻሻሉት የቤተሰብና የወንጀል ህጐች፣ በአጠቃላይ ሰብዓዊ መብት በመሳሰሉ መሠረታዊ ህጐች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ሰልጣኞቹ ከፖሊስ፣ ከወጣት፣ ከሴት ማህበራትና ከሌሎችም አካላት የተውጣጡ ናቸው፡፡ ሁሉም በየካባቢያቸው እየተንቀሳቀሱ ጥቃት በሚደርስ ጊዜ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ጥቃት የመከላከል፣ ህብረተሰቡን የማስተማር ሥራም ይሠራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸው ሲመጡ ምን ዓይነት አገልግሎት ትሰጣላችሁ?

አቶ አይናለም፡-
ሶስት ዓይነት አገልግሎቶችን ያገኛሉ፡፡ አንደኛው የምክር አገልግሎት ነው፣ ሁለተኛው የህግ ድጋፍ ሲሆን ሶስተኛው የህክምና አገልግሎት ነው፡፡ የህክምና አገልግሎቱ ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ጋር በአጋርነት የምንሰጠው ነው፡፡ ወደ ቤተሰብ መምሪያና ማዕከሉ አቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ይላካሉ፡፡ የሚያወጡትን ወጪ እንተካላቸዋለን፡፡ አደጋው በጣም አነስተኛ ሲሆን ደግሞ ከማዕከሉ የምክር አገልግሎት ሰጪዎች አንዷ የህክምና ባለሙያ በመሆኗ እዚሁ የመጀመሪያ ዕርዳታ ይደረግላቸዋል፡፡ ማዕከሉ የሚሰራው ብቻውን አይደለም፡፡ ለምሳሌ የሁለቱን ክፍለ ከተሞች ፖሊስ አባላት በዚህ አጋጣሚ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ አብረውን እየሠሩ ነው ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ያለበትን መረጃ በአግባቡ በማጠናከርና ተገቢውን እገዛ በማድረግ ማዕከሉ ውጤታማ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ፍርድ ቤትም ጥሩ ድጋፍ እናገኛለን፡፡ አልፎ አልፎ የፍርድ መዛባት፣ ቶሎ አለመወሰን፣ ቢኖሩም ትብብሩ ጥሩ ነው፡፡ የህክምና ድጋፍ ከሚሰጡ ተቋማት ጋርም ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ ከሴቶች ማህበራትና ከመንግሥት አካላትም ጋር እንዲሁ፡፡

ድርጅቱ ያቋቋመው ማዕከል ውስጥ የተያያዙ ሥራዎችን ነው የምንሠራው እዚህ ባለን የሥርዓተ ፆታ ጉዳይ ክፍል አማካኝነት ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የ”ሴቶች ለፍትሕ” ቡድኖችን እናስተባብራለን ለህብረተሰቡ መድረስ ያለባቸውን መረጃዎችና መልዕክት አዘል የማስተማሪያ ህትመቶች እናዘጋጃለን ከየትምህርት ቤቱ በሲቪክ ክለብ የነበሩትን አደራጅተን የሥነ ፅሑፍና ድራማ ክለብ በማቋቋም በየአካባቢው እያሳዩ እንዲያስተምሩ እያደረግን ነው፡፡

ከዚህ ሌላ ተጠቃሚዎችን በተመለከተ አንዲት ሴት ልጇ የመሠረታዊ ትምህርት ተጠቃሚ ከሆነ፣ እርሷ የብድር አገልግሎትና ስልጠና እንድታገኝ ይደረጋል፡፡ አካባቢዋ ንፁህ ውሀና መፀዳጃ ከሌለ ያንን እንድታገኝ ይደረጋል፡፡ ልጆቿ ሁለተኛ ደረጃ ሲደርሱ የቤተመጻህፍት አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል በዚህ መልኩ የተቀናጀ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ አቅማቸው ጐልብቶ የሚታየውም ይህን መሰሉን አገልግሎት ሲያገኙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቃት ላይ ከሚሠሩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር ተቀናጅታችሁ ትሠራላችሁ?

አቶ አይናለም፡-
በጥቃት ዙሪያ ከሚሠሩ፣ በቀጥታ በሴቶች ላይ ባይሆንም በጐዳና ተዳዳሪ ልጆች ላይ፣ በወላጅ አልባ ልጆች፣ ከቤት ተባረው በወጡ ሴቶች ላይ በመሳሰሉት ላይ የሚሠሩ፣ መጠለያ የሚሰጡ አሉ፡፡ ስድስት የሚሆኑ ተመሳሳይ ድርጅቶችን ጐብኝተን፣ ውይይት አድርገን መስራት ጀምረናል፡፡ ተጠቂዎች ሲኖሩ እነኝህ ድርጅቶች የምክር አገልግሎት ከሌላቸው እዚህ ይልኳቸዋል፡፡ የህግ ድጋፍ የማይሰጡ ድርጅቶችም ሲኖሩ እንደዚሁ፤ የህክምና ድጋፍ ማድረግ የማይችሉም እንዲሁ ወደእኛ ማዕከል ይልካሉ፡፡ ጥቃት ደርሶባቸው ለአንድ ቀንም ቢሆን ማደሪያ የሌላቸው እዚህ መጥተው መጠለያ ወዳላቸው የላክናቸው አሉ፡፡ የተወሰኑ ድርጅቶች በዚህ መልኩ አብረን እየሠራን ያለን አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙውን ጊዜ ሁሉም በየራሱ ይሮጣል፤ ሥራው አይቀናጅም ለውጥ የማይታየውም ለዚህ ነው ሲባል ስለሚሰማ ነው፤

አቶ አይናለም፡
- እውነት ነው፡፡ ተቀናጅቶ መሥራቱ ያለንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀምም ያስችለናል፡፡ አብሮ መሥራቱ ጠቃሚ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት የተማርነውም ይህንኑ ነው፡፡ ዜማ ሴቶች ለፍትሕ ከተቋቋመ 10 ዓመቱ ቢሆንም የሠራው ሥራ ግን ብዙ ነው፡፡ ይህ ማዕከል እንኳን በ1 ዓመት ውስጥ ለ243 ተጠቂዎች አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው ሲባል በራሱ ብቃት ብቻ ስለሠራ ሳይሆን በጥሩ ግንኙነት ስለተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ባለን ጥሩ ግንኙነት አጥቂዎች በዋስ ተፈተው፣ ተከታትለን ያስያዝንበት ሁኔታ አለ፡፡ በይግባኝ ውሳኔዎች እንደገና እንዲታዩ አድርገናል፡፡ ተገቢ ያልሆኑ ውሳኔዎች በሚሰጡበት ወቅት ይግባኝ እየጠየቅን፣ እያመለከትን እንዲታይ እያደረግን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ከሌሎች ጋር ተቀናጅተን መሥራታችንን ነው፡፡ ፖሊስም፣ አቃቤ ህግም ተባባሪዎቻችን ናቸው፡፡ ፖሊሶች ጭምር ጥቃት ሲፈፀም እየጠቆሙ ነው፡፡ ተባብሮ መሥራቱ ልምድ ለመለዋወጥም ይረዳል፡፡ ፖሊሶች ረጅም ጊዜ የሠሩ ሲሆኑ በአካሄድ በኩል ምን መደረግ እንዳለበት የተሻለ የሚያውቁበት አጋጣሚ አለ፡፡ ከድርጅቶች ጋ መገናኘቱ ተደራራቢ ሥራ እንዳይሠራ፣ አንዱ የያዘውን ሌላው እንዳይገባበት (ሌላ መሥራት ሲችል) ለማድረግ ጭምር አስፈላጊ ነው፡፡ አብሮ  የመሥራትን ጥቅም ስላወቅነው ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በሴቶች መብት ማስከበርም ሆነ ጥቃት ላይ ሲሠራ የሚያጋጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎችስ ምንድናቸው?

አቶ አይናለም፡-
ትልቁ ፈተና የመጠለያ ጉዳይ ነው፡፡ አዲስ አበባ እንደሚታየው የቦታም ችግር አለ፡፡ እዚህ አገልግሎቱን እንሰጣለን፡፡ ተጠቂዎች ጉዳያቸው ከፍርድ ቤት ጋር፣ ከወንጀል ጋር ሲያያዝ፣ ክሱን ለመከታተል ተመልሰው ወደቤታቸው መግባት አዳጋች ይሆናል፡፡ ባሏን ከሳ በፍርድ ቤት የምትሟገት ሴት ተመልሳ ወደሱ ቤት እንዴት ትገባለች? ቢያንስ ጉዳዩ መስመር እስኪይዝ መጠለያ ትፈልጋለች፡፡ የሴቶችና የህፃናት ጉዳይ ቶሎ ቶሎ እየቀረበ፣ በተዘዋዋሪ ችሎቶች እየታየ ነው፡፡ ይህ ጥሩ ነው፤ ለውጥ አለ፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ አንዲት ሴት ጉዳይዋ በሦስት ወር ውስጥ እንኳን ቢታይ እስከዚያ የት ትቀመጣለች? የሚለው አሳሳቢ ነው፡፡

ባለፈው አንድ ወር ተኩል አካባቢ አንዲት ልጅ ወደ ማዕከሉ መጥታ አባቷ ሊደፍራት እንደሆነ ምልክቶችን እንዳየች ተናገረች፡፡ መጠለያ ስለሌለን ምንም ልናደርግላት አልቻልንም፡፡ ወደ ቤቷ ተመልሳ ሄደች፣ አባቷ ደፈራት፡፡ መጠለያ ቢኖር ልጅቷን ማዳን ይቻል ነበር፡፡ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የት ይሆናሉ የሚለው ትልቅ ችግር ነው፡፡ ብዙ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሴቶች ችግርን የመቋቋም ኃይል አላቸው ብለን እናምናለን ሆኖም ከችግራቸው ተለይተው የሚረጋጉበት፣ ቢያንስ ጉዳያቸው መስመር እስኪይዝ የሚቆዩበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል”.

ሌላው ችግራችን የገንዘብ ነው፡፡ ሰፋ ያለ ነገር እንዳንሠራ የገንዘብ አቅማችን ይወስነናል፡፡ የህብረተሰቡ ጥያቄ ሰፊ ነው ያለን ሀብት ውሱን ነው፡፡ ማዕከላችን ሁሉንም ክፍለ ከተሞች  እንዲያጠቃልል እንፈልጋለን፣ ነገር ግን አንችልም፡፡ ድርጅቱን የሚያውቅ ሁሉ በግልም፣ በድርጅትም ይደውላል፡፡ እኛ ግን አገልግሎት መስጠት የምንችለው ለሁለት ክፍለ ከተሞች ብቻ ነው፡፡ አንዴ አልፈን ከወጣን አስቸጋሪ ነው፡፡ ከአጐራባች የሚመጡና አገልግሎቱን የሚያገኙ አሉ፡፡  ክፍለ ከተሞች እየጠየቁ ነው፡፡ ከዚህ ክፍለ ከተማ ነው ሲሉን (ሰው ተደፍሮ ሊሆን ይችላል) መምጣት አትችሉም ማለት ይከብዳል፡፡

ሪፖርተር፡- በህብረተሰቡ በኩልስ ችግሮች የሉም?

አቶ አይናለም፡-
ሦስተኛውና ትልቁ ችግር የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ ነው፡፡ ሴቶች ላይና ህፃናት ላይ ብዙ ድርጅቶች እየሠሩ ነው፡፡ ለውጥ እየታየ ቢሆንም የህብረተሰቡ ግንዛቤ ገና ነው፡፡ ባህላዊ የሆነው፣ ስለሴቶች ያለው አመለካከት ገና ነው፡፡ የተፈለገውን ያህል ለውጥ አልመጣም፡፡ ህጐች ደንቦች ይወጣሉ፡፡ ህብረተሰቡን የማስተማር ሥራ እየሠራን ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ህጐች ለህብረተሰቡ አይተዋወቁም፡፡

ሚዲያ ራሱ ህጐችን የማስተዋወቅ ሥራ ቢሠራ ጥሩ ነው፡፡ ወቅት ጠብቆ ከሚሆን መተዳደሪያችን ስለሆኑት ህጐች ህብረተሰቡ ማወቅ እንዳለበትና በየጊዜው መሥራት እንዳለብን ሊሰማን ይችላል፡፡ ተጠቂዎች እዚህ መጥተው ህጉ እንደሚደግፋቸው ሲያውቁ እፎይታ ሲሰማቸው እናያለን፡፡ ውጤታማ እንሆናለን ብለው ይነሳሉ፤ ይሳካላቸዋልም፡፡ ከህግ በላይ የሚሆን የለምና ጥሩ ህጐች አሉ፡፡ ጥቃትን የሚመለከቱ፣ ጥቃት ፈፃሚዎችን የሚያስደነግጡ አንቀፆች አሉ፡፡ እነዚያ ቢወጡ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ሊለውጡት ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጥቃት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ሥራ እንዲቀላጠፍና ጥቃት እንዲቀንስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ አይናለም፡-
ተባብሮ የመሥራት፣ ከሁሉም በላይ መረጃ የመለዋወጡ ነገር ወሳኝ ነው፡፡ መረጃ መስጠት ጠቃሚ ነው፡፡ መረጃ የማይወጣ ከሆነ ሰዎች ሊማሩ፣ ነገሮች ሊለወጡ አይችሉም፡፡ የመረጃ የመደበቅ ባህል አለን፡፡ አንዲት እናት ባሏ የገዛ ልጃቸውን ቢደፍር “አይሰማብኝ” ትላለች፡፡ የገዛ ወንድም እህቱን፣ የአክስቱን ልጅ እየደፈረ ባል የሚስቱን ዘመዶች፣ የልጆቹን ሞግዚቶች እየደፈረ እያየን ነው፡፡ አውጥተን መነጋገር መልመድ አለብን፡፡ ይህ ጉዳይ ስር እየሰደደ በመሆኑ ስለዚሁ መረጃው ሊወጣ ይገባል፡፡ ካልወጣ ችግር እንዳለ አይታወቅም፡፡ መፍትሄም አይፈለግለትም፡፡
 
< Prev   Next >