Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Monday
Sep 08th
Home arrow Sections arrow “ጭካኔን ተውኖ ርህራሄን...
“ጭካኔን ተውኖ ርህራሄን... Print E-mail
Wednesday, 30 January 2008
Image
ግሩም ኤርምያስ
“ጭካኔን ተውኖ ርህራሄን ማሳየት ይቻላል”
ግሩም ኤርምያስ

ሔርሜላ፣ ፅዮን፣ መስዋዕትና ስርየት በተሰኙ ፊልሞች ተውኗል፡፡ ግሩም ኤርምያስ በቅርቡ ደግሞ ራሱ በደረሰውና ዮናስ ብርሃነ ዳይሬክት ባደረገው “የሞሪያም ምድር” በተሰኘ አዲስ ፊልም ብቅ ብሏል፡፡
ግሩም ውልደቱም እድገቱም አዲስ አበባ ተክለሃይማኖት አካባቢ ነው፡፡ በትወና፣ በዳይሬክቲንግና በስክሪፕት አፃፃፍ በአድቫንስድ ዲፕሎማ ተመርቋል፡፡

በተለያዩ ፊልሞች የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን ወክሎ ተጫውቷል፡፡ በ”ሔርሜላ” ፊልም ላይ ከሚያፈቅራት ወጣት በጎ ምላሽ በማጣቱ የተነሳ በሃይል ለማግኘት የሚጥር ጨካኝ አፍቃሪ (በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ፊልም ነው”፣ “ስርየት” ላይ አመዛዛኝና ትሁት አፍቃሪ፣ በቅርቡ በተሰራው የሞሪያም ምድር ደግሞ ለገንዘብና ለሃብት ሲል ሰው የሚገድልና ወደኋላ የማይመለስ ስግብግብ ነጋዴ ሆኖ ተውኗል፡፡

ገፀባህሪያትን ቀያይሮ ስለመተወን ሲናገር “የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን ወክሎ መስራት ያስደስተኛል፡፡ እንደ አክተር የሚሰጠኝን ሁሉ በብቃትና በተሻለ ሁኔታ ለመስራት እጥራለሁ፡፡ ትወና ከሌሎች ሙያዎች ለየት የሚያደርገው ዘወትር በአንድ መስመር የማትጓዝበት መሆኑ ነው፡፡ ዛሬ የተወንከውን ገፀባህሪይ ነገ በሚመጣ አዲስ ፊልም ላይ አታገኘውም፡፡ እኔም በእያንዳንዱ በምሰራቸው ሥራዎች ላይ ጥልቅ የሆነ ባህሪይን መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ባህሪያትን ለመጫወት ጥረት እያደረግኩ ያለሁት” ብሏል፡፡

ግሩም እንደሚለው እስካሁን ወክሎ ከተወናቸው ገፀ ባህሪያት መካከል በሔርሜላ ላይ የተጫወተውን “ካሳሁን”ን የበለጠ ይወደዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እውነተኛ ታሪክ መሆኑ ነው ይላል፡፡ ሁሉንም ሲተውን (በስርየትና በየሞሪያም ምድር ያሉትን ጨምሮ) የራሳቸው የሆነ ፈታኝ ባህሪይ ቢኖራቸውም ገፀባህሪይውን ለመላበስና ለመዋሃድ የሔርሜላው ካሳሁንን ተጨንቆበት እንደ ሰራው ገል”ል፡፡ እንደ ስኬት ግን በሶስቱም ፊልሞች ላይ እንደተሳካለት ያስባል፡፡

በሔርሜላና በስርየት ፊልሞች ከተወነበት ብቃቱ አንጻር ሲታይ የሞሪያም ምድር ፊልም የተላበሰውን ገፀ ባህሪይ (ዘድንግል) አልተዋጣለትም የተባለውን አስተያየት አስመልክቶ ከገፀ ባህሪይ ገፀ ባህሪይ ሲለዋወጥ በተመልካች የሚፈጠረው ስሜት መለያየት እንደሚኖርና እሱ ግን በጣም ወዶት እንደተወነውና ተሣክቶልኛል ብሎ እንደሚያምን ገል”ል፡፡

በሔርሜላና የሞሪያም ምድር ላይ ጭካኔን ተላብሰህ ተውነሃል፡፡ የበለጠ ጭካኔ ያለበት በየቱ ነው፣ በአንተነትህ ላይ ጭካኔ ተፅዕኖ አላሳደረብህም ወይ ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ “በሞሪያም ምድር ላይ የተወንኩት ዘድንግል በጣም ጨካኝ ነው፡፡ ምንም ከማድረግ አይመለስም፡፡ የሔርሜላው ካሳሁን ግን በፍቅር የተነሳ የጨከነ ነው፡፡ ተመልካቹም የሚያዝንለት ዓይነት ነበር፡፡ ዘድንግል ግን በጣም አውሬ ነው፡፡ ዘድንግል እኮ በአካባቢያችን አንዳንዴ የምናስተውላቸው ጨካኞች አይነት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ለህብረተሰቡ የጤና ጠንቅ የሚሆኑ ነገሮችን የሚሸጡ (በቅቤ፣ በበርበሬ ወዘተ. ላይ ተመሳሳይ ነገር ቀላቅለው የሚሸጡ) ሰዎች ዓይነት ነው፡፡ ልክ እንደዚያ ሁሉ ጊዜው ያለፈበት መድሃኒት ሊሸጥና ትውልድ ሊጨርስ የተነሳ ገፀ ባህሪይ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት የተለያዩ ጭካኔዎች በእኔ ላይ ተፅዕኖ አያመጡም፡፡ እኔ ግሩም ነኝ የራሴ ባህሪይ አለኝ፡፡ እንደ ተዋናይ ግን ተጫውቻቸዋለሁ፡፡ ጭካኔን ተላብሰህ በመተወን ርህራሄን ማስተማር ትችላለህ ብዬ አስባለሁ” ነበር ያለን፡፡

የሞሪያም ምድር የሚለውን ድርሰት መፃፍ የጀመረው ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ የተናገረው ግሩም ከታሪኩ ጋር አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ተጨባጭ ነገሮች በጥናት ለመደገፍ ሞክሯል፡፡ ስለአክዩት ሉኩሚያ በሽታ፣ ስለመድሃኒት ዝውውር፣ ስለኩላሊት ሽያጭ፣ ስለሙስናና ተያያዥ ነገሮች የተለያዩ ቢሮዎች በመሄድ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡

ኪነ ጥበብ ዩኒቨርሳል (ድንበር ተሻጋሪ) ባህሪይ አለው ብሎ የሚያምነው ግሩም የኩላሊት ሽያጭን አስመልክቶ በአገራችን ስለመኖሩ ማስረጃ ባይኖረውም የታዳጊ አገሮች ችግር መሆኑን ስለተረዳ ለማንሳት እንደፈለገ አስረድቷል፡፡

ፊልሞች የአብዛኛውን ማህበረሰብ ጉዳይ አያነሱም ወይም አገራዊ ማዕቀፍ የላቸውም በሚለው አይስማም፡፡ ይልቁንስ እንደ ሙዚቃና ስፖርት ሁሉ ፊልም ዩኒቨርሳል በመሆኑ በፊልም ውስጥ የሚነሱ ጉዳዮች ሁሉ ሁለንተናዊ ናቸው ይላል፡፡ በእርግጥ አብዛኞቹ በከተማ ህይወት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው በሚለው ይስማማል፡፡ “የፊልም ሰሪዎች ህልም ዓለም አቀፍ ገበያን ሰብረው የሚገቡ ፊልሞችን መስራት ነው፡፡ ለዚህ ስነነሳ ምን ዓይነት ጭብጦች ይዘን ብንጓዝ ጥሩ ነው ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ የተሻለ ሊሰራበት ይቻላል በምንለው እናተኩራለን” የሚለው ግሩም በአገራችን ትውፊቶች ብዙ እንዳልተሰራ እንዲያውም በርካታ የኢትዮጵያ ታሪኮች እንዳልተነኩ ይገልፃል፡፡

ሆሊውድ ውስጥ የመተወን ህልም ያለው ወጣቱ ተዋናይ የአገሩን ትውፊቶችና ያልተዳሰሱ ታሪኮች ወደፊት መስራት ያስባል፡፡ “ዓለምን ሁሉ ሊያስደንቁ የሚችሉ ህልቆ መሳፍርት ታሪኮች አሉን፡፡ ዳሩ ግን የበጀት ጉዳይ ለፊልም ሰሪዎች ማነቆ ነው፡፡ ቢሆንም ጥሩ ጅምር አለ፡፡ እኔም ወደፊት የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ ቋንቋዎችን አሰባጥሬ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛና የመሣሠሉት ቋንቋዎችን አንድ ላይ አቀላቅለን ብንሠራ የውጭ ፊልም ሰሪዎችን ለመሳብም ሆነ ተመልካቾችን ለማስደሰት እንችላለን” ብሏል፡፡

በሞሪያም ምድር ላይ ግነታዊ ነገሮች ይበዛሉ ለሚለው፣ “ፊልም በጥበብና በፈጠራ መጎልበት አለበት፡፡ እንዲሁ ደረቅ እውነት ብቻ ለተመልካች አያስደስትም፤ በሚታዩ አንዳንድ ወጣ ያሉ (የተጋነኑ) ነገሮች ተመልካች ሊዝናና መቻል አለበት” ብሏል፡፡ አይይዞም ከገፀባህሪያት አንዱ የሆነውና እሱ የተወነው ዘድንግል ፀጉር ነጭ ቀለም መቀባት ምክንያቱን ሲገልፅ “ገፀባህሪው አብዛኛውን ጊዜ ኑሮው ውጭ ነው የምዕራቡ ዓለም ተፅዕኖ አድሮበታል፡፡ በመሆኑም የነጮች ተፅዕኖን ለመወከል (ሲምቦላይዝ ለማድረግ) ነው ነጭ እንዲሆን የመረጥነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በትዕይንቱ መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይኛ መነጋገሩ ውጭ አገር ብዙ ጊዜ እንደኖረ ለመጠቆም ነው”

ግሩም እንደሚለው የሞሪያም ምድር ማለት የመስዋዕት ቦታ እንደማለት ነው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ አብርሐም ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር ለመግለፅ ልጁን ይስሃቅን ለመስዋት ወደ ተራራ ይዞት ይወጣል፡፡ ያ ተራራ ሞርያ ይባላል፡፡ በፊልሙ ማስታወቂያና ርዕስ ላይ ግን “የሞርያም ምድር” ሲፃፍ “የ”ን እንደ አመላካች ለመጠቀም የገባች ሲሆን “ም” ግን በህትመት ስህተት መውጣቷን ተናግሯል፡፡ “የሞሪያ ምድር” ትክክለኛ ነበር ማለት ነው፡፡

በታሪኩ ውስጥ ጨካኙና መድሃኒት ነጋዴው ዘድንግል የመድሃኒት ቁጥጥር ኃላፊው ከውጭ ያስገባውን ጊዜው ያለፈበት መድሃኒት “አልተበላሸም” ብሎ እንዲፈርምለት በተዘጋ መጋዘን ውስጥ በጭካኔ ቢደበድበውም እምቢ በማለት በአኩዩት ሉኩሚያ የምትሰቃይ ህፃን ልጁን በሽጉጥ ይገድልበታል፡፡ ይሁን እንጅ ከቆይታዎች በኋላ ህፃኗ ሳትሞት ትቀራለች፡፡ ለምን ቢሉ በደብተር መያዣ ቦርሣዋ በያዘችው መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጥይቷ እርሳስ ተቀርቅራ በመገኘቷ ነው፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ? አልነው፡፡ “ከርዕሱ መረዳት እንደሚቻለው መስዋዕትነት የሚበዛበት ታሪክ ነው፡፡ አብርሐም ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር ልጁን በመሰዋት ሊገልፅ ነበር፣ የፊልሙ ገፀባህሪይ ዮፍታሔም ለህፃናት ሲል ጊዜ ያለፈበት መድሃኒት ይሰራጭ ብዬ አልፈርምም በማለቱ ነው ያን ሁሉ ስቃይ የተቀበለው በፊልሙ ላይ ጎን ለጎን ከተነሱ ጭብጦች በተጨማሪ ዋናው ጭብጥ ፍቅር ነው፡፡ ዮፍታሔም ቀድሞውኑ አልፈርምም ብሎ ህፃን ልጁን ሰውቷት ነበር፣ ግን አልሞተችም፡፡ ፊልሙ ላይ እንደሚታየው ህፃኗ ቦርሣዋን በደረቷ አቅፋ ይዛው ነበር፡፡ አንድ የጥይት እርሳስ ደግሞ ሊበሳው የሚችል ራሱን የቻለ ቲክነስ (ውፍረት) አለ፡፡ የጥይትን የመብሳት አቅም ባለሙያዎች የበለጠ የሚናገሩት ቢሆንም ውፍረት በጨመረ ቁጥር ጥይት የመብሳት አቅሙ የጎላ አይሆንም፡፡ ለማጣራት እንደ ሞከርኩት በተወሰነ ሴንቲሜትር ላይ ቀድዶ የመግባት አቅሙ አነስተኛ ነው፡፡ አሊያም በስቶ እዚያው ይቀራል፡፡ እኔ እንደ ደራሲ የፃፍኩት በቲክነስ (ውፍረት) ላይ ተመስርቼ ቢሆንም ተመልካች ግን እምነቷ ነው ያዳናት አሊያም ቲክነስ ነው ያዳናት የሚለውን እንደየራሱ እንዲተረጉመው ታስቦ ነው፡፡ ጥይቱ በስቶት የሞሪያም ምድር ከሚለው ቃል ላይ እርሳሷን ማሳየት የፈለግን ቢሆንም መፅሐፍ ቅዱስን መብሳት ፈርተን ተውነው” ብሏል፡፡

መፅሐፍ ቅዱሱን መቼና እንዴት እንደያዘችው ግራ ያጋባል /በነገራችን ላይ ህፃኗ ታማ ወደ ሆስፒታል አባቷ (ዮፍታሔ) ይዟት ሄዶ ተሽሏት ሲመለሱ የዘድንግል ጋሻ ጃግሬዎች መንገድ ላይ ጠልፈው አባቷንም እሷንም ወደ ዝግ ቤት ይዘው ገብተዋል/ እንዴት ነው ሊሆን የቻለው? ለሚለው “አንድ ትዕይንት ነበር ተቆርጦ ነው፡፡ በቀረፃ ጊዜ ሆስፒታል ተኝታ እያለ መፅሐፍ ቅዱስን ያነብላትና በቦርሣዋ ሲከትላት የሚታይበት ትዕይንት ነበር” ያ ትዕይንት ተቆርጦ መቅረቱ ግርታን እንደፈጠረ ጠቁሟል፡፡

ለተናዋናዩ ያቀረብንለት የመጨረሻ ጥያቄ ለመተወን ውድ ክፍያ እንደሚጠይቅ በፊልም ሰሪዎች መነገሩን ነበር፡፡ ውድ ክፍያ እንደሚጠይቅ አምኖ አንድ ሥራ ለመስራት ከተዋዋለ በኋላ ያንን ተውኖ ሳይጨርስ ሌላ መዋዋል እንደማይፈልግና ያንን ለማካካስ ውድ ክፍያ እንደሚያስፈልግ አብራርቷል፡፡ ተዋናዩ የአገራችን ፊልም ክፍያ ከውጭው አንፃር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁሞ ወፍ እንዳገሯ ትጮሃለች እንደሚባለው ያልተጋነነና የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ክፍያ እንደሚጠይቅ ተናግሯል፡፡    

በደመቀ ከበደ
 
< Prev   Next >