| የአእምሮ ሕሙማኑ |
|
| Wednesday, 30 January 2008 | |
|
አማኑኤል ሆስፒታል ስንደርስ ከረፋዱ አራት ሰዓት ሆኗል፡፡ መግቢያው አካባቢ ባሉት ክፍሎች ዙሪያ ሰዎች በዛ ብለው ይታያሉ፡፡ የተወሰኑት አዲስ ሌሎቹ ደግሞ ተመላላሽ ታካሚዎች መሆናቸው ተነገረን፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ የሆስፒታሉን የህመምተኛ ዩኒፎርም የለበሱ ቋሚ ታካሚዎች ሲንቀሳቀሱ ተመለከትን፡፡ የአእምሮ ህመምተኞቹ በሆስፒታሉ ያላቸው ቆይታን በሚመለከት በሆስፒታሉ የትምህርት ክፍል መምህርና ሳይካትሪ ነርስ አቶ አሸብር ባዬን አነጋግረናቸዋል፡፡ አቶ አሸብር በአማኑኤል ሆስፒታል ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በተመላላሽና በቋሚ ታካሚዎች ክፍል በሳይካትሪ ነርስነት ሰርተዋል፡፡ የነርሲንግ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ደግሞ በሆስፒታሉ የትምህርት ክፍል በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
አቶ አሸብር ቢሮ በመሄድ ላይ እያለን ዩኒፎርም የለበሱ አንዳንድ የሆስፒታሉ ታካሚዎች (ወንዶች) ወደኛ ቀረቡ፡፡ ከዚህ በፊት የጠበቀ ትውውቅ ያለን በሚመስል ሁኔታ ሰላምታ ሰጡን፡፡ አንዳንዶቹ ከኋላችን በመከተል በተደጋጋሚ ሰላምታ ሲሰጡን፣ ሌሎቹ ደግሞ ሲጋራ እንድንገዛላቸው ይጠይቁናል፡፡ በአማኑኤል ሆስፒታል ሴት የአእምሮ ህመምተኞች በቋሚነት ህክምና የሚከታተሉባቸው ሦስት፣ ለወንዶች ደግሞ ስምንት ዋርዶች (ክፍሎች) አሉ፡፡ በእያንዳንዱ የሴቶች ዋርድ ሀያ ሁለት ህመምተኞች የሚገኙ ሲሆን በአንድ የወንዶች ዋርድ ከሀያ አምስት እስከ ሀያ ስድስት የሚሆኑ ህመምተኞች ይስተናገዳሉ፡፡ በሆስፒታሉ በቋሚነት ተኝተው ህክምና እንዲከታተሉ የሚደረጉት ስለህመማቸው የተወሰነ ግንዛቤ ኖሯቸው በተገቢው ሰዓት መድኃኒት መውሰድ የማይችሉና ከተለያዩ ሱሶች ጋር በተያያዘ የአእምሮ ችግር ያለባቸው መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል፡፡ በእያንዳንዱ ዋርድ ደጃፍ ላይ የተወሰኑ የአእምሮ ህሙማን ሰብሰብ ብለው እዚያም እዚያም ተቀምጠው ተመለከትን፡፡ ከስምንቱ የወንዶች ዋርድ በህግ ቁጥጥር ሥር ያሉ የአእምሮ ህመምተኞች የሚታከሙበት ዋርድ ደጃፍ ላይ የአእምሮ ህሙማኑና እነሱን የሚጠብቁ ፖሊሶች አንድ ላይ ተቀምጠው ሲነጋገሩ አየን፡፡ ይህ በህግ ቁጥጥር ሥር ያሉ የአእምሮ ህመምተኞች ዋርድ ከሌሎቹ ዋርዶች ጠበብ ይላል፡፡ በሆስፒታሉ የሚታከም ማንኛውም የአእምሮ ህመምተኛ በሆስፒታሉ እንደፈለገ መዘዋወር የሚችል ሲሆን በህግ ቁጥጥር ሥር ያሉት የአእምሮ ህሙማን እንቅስቃሴ ግን የተገደበና ከሆስፒታሉ ጠባቂዎች በተጨማሪ በፖሊሶች ይጠበቃሉ፡፡ የህሙማኑ እለታዊ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ አሸብር ሲመልሱ “የወንዶችና የሴት አእምሮ ሕሙማን ዋርዶች የሚገኙበት ግቢ የተለያየ ነው፡፡ ሴቶች ወደ ወንዶች፣ ወንዶቹም ወደ ሴቶች ዋርድ የሚሄዱበት ሁኔታ የለም፡፡ ጠዋት ጠዋት ተመላላሽ ወይም አዲስ ተካሚዎች በሆስፒታሉ በሚበዙበት ወቅት እነዚህ ሰዎች ወደ ሚስተናገዱበት አካባቢ ቋሚ ታካሚዎቹ እንዳይሄዱ ይደረጋል፡፡ ይህ የሚሆነው አዳዲሶቹ ታካሚዎች እንዳይጨነቁና ፍርሀት እንዳያድርባቸው በማሰብ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የአእምሮ ህሙማኑ ሰዎችን የመተናኮል ባህሪይ ስለሌላቸው በግቢ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከለከሉበት ሁኔታ የለም” በማለት መልሰውልናል፡፡ በቁርስ በምሳና፣ በእራት ሰዓት ወደ መመገቢያ አዳራሽ በመሄድ በምግብ አዳራሹ ሠራተኞች እገዛ ራሳቸውን በማስተናገድ እንደሚመገቡ፣ ምሽት ላይም እስከ አራት ሰዓት ቴሌቪዥን ተመልክተው ወደየመኝታቸው እንደሚሄዱ ከዋርድ ተቆጣጣሪዎች ለመረዳት ችለናል፡፡ አብዛኞቹ የወንድ ዋርዶች መስኮት መስታወት የተሰነጣጠቀ ሲሆን የእጅ መታጠቢያ ሲንኮች ተሰባብረውና ቧንቧዎቹም ተነቃቅለው ይታያሉ፡፡ በተቃራኒው የሴቶች ዋርድ መስኮት መስታወቶች ያልተሰነጣጠቁ፣ የመታጠቢያዎቹ ሲንኮቹም ያልተበላሹ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አዲስ የሚገቡ ወንድ የአእምሮ ህመምተኞች የሚሰጣቸው መድኃኒት በበቂ ሁኔታ ተፅእኖ እስኪያሳድር ድረስ ለተወሰኑ ቀናት በሚያሳዩት የሀይለኛነት ባህሪይ እቃዎችን እንደሚሰባብሩና እንደሚረብሹ አቶ አሸብር ገልፀውልናል፡፡ በሆስፒታሉ ውስጥ እንደማንኛውም ሜዲካል ህክምና ለሴትና ለወንድ የአእምሮ ህመምተኞች የሚሰጠው የመድኃኒት መጠን እኩል አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ በገባንባቸው ዋርዶች ውስጥ ተኝተው ያየናቸው ህመምተኞች ጥቂት ሲሆኑ የእነዚህ ህመምተኞች የአእምሮ ችግርና የሚሰጣቸውም መድኃኒት ለየት ያለ መሆኑ ተነግሮናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንድ ለመተኛት እየተዘጋጀ የነበረን የአእምሮ ህመምተኛ ልትተኛ ነው ወይ? በማለት ስንጠይቀው “አልተኛም” በማለት ከፊት ለፊቱ በሚገኝ አልጋ ላይ ተሸፋፍኖ ወደ ተኛ ሌላ ታካሚ በማመልከት “እሱ የተኛው ስለሚያመው ነው” ብሎ ነግሮን በመውጣት ከዋርዱ በራፍ ላይ ከተቀመጡ የአእምሮ ህመምተኞች ጋር ተቀላቀለ፡፡ እንደ አቶ አሸብር ገለፃ፣ በአማኑኤል ሆስፒታል የስነ ልቦና ህክምና፣ የመድኃኒትና የኤሌክትሪክ ንዝረት ህክምና ይሰጣል፡፡ ቀደም ሲል የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን በማሠራትና በተለያዩ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች (ሪክሬሽናል ቴራፒ) ይሰጥ ነበር፡፡ ይህ ሪክሬሽናል ቴራፒ በአሁኑ ወቅት በመደበኛ ሁኔታ እየተሰጠ ባይሆንም የአእምሮ ህሙማኑ ቴሌቪዥን ከመመልከት ባሻገር መረብ ኳስና ቴኒስ የሚጫወቱበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ከሆስፒታሉ ሠራተኞች በተለይም ከሳይካትሪ ነርሶች ጋር ያላቸው ቅርበት የጠበቀ ነው፡፡ ከአራት ዓመት ወዲህ ደግሞ ከተለያዩ አደንዛዥ እፆች ጋር በተያያዘ ለሚፈጠር የአእምሮ ችግር ህክምና የሚሰጥ ማዕከል የተቋቋመ ሲሆን በዚህ ማዕከል ህክምናቸውን የሚከታተሉ ህሙማን አሉ፡፡ በአማኑኤል ሆስፒታል በቋሚነት ተኝተው የሚታከሙ የአእምሮ ህሙማን አልጋ ከመያዛቸው በፊት እንደ ሞባይል፣ ገንዘብ፣ የጣትና የአንገት ሀብሎቻቸውን ለቤተሰቦቻቸው እንዲያስረክቡ ይደረጋል፡፡ በሆስፒታሉ አልጋ ለመያዝ በመጡበት እለት የለበሱት ልብስ በሆስፒታሉ ውስጥ ሲቀመጥ በሆስፒታሉ እስካሉ እንዲለብሱ የሚፈቀድላቸው የሆስፒታሉን የህመምተኛ ዩኒፎርም ነው፡፡ ይህ ዩኒፎርም በየሳምንቱ ገላቸውን በሚታጠቡበት ወቅት ይቀየራል፡፡ በአንድ ወቅት በአጋጣሚ ወደ ሆስፒታሉ ሄደን የተወሰኑ የአእምሮ ህመምተኞች ተሰባስበው ሲጨፍሩ መመልከታችንን ለአቶ አሸብር ስንገልፅላቸው “የአንዳንዶቹ ህመም እንዲኮምኩና እንዲዘፍኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ባህሪያቸው የሚንፀባረቀው ወደ ሆስፒታሉ በመጡ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ነው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ይለቃቸዋል” ብለዋል፡፡ በህግ ቁጥጥር ሥር ያሉት የአእምሮ ህመምተኞች ወደ ሆስፒታሉ የመጡበት ቀዳሚ ዓላማ እንደሌሎቹ የአእምሮ ህመምተኞች ህክምና ለማግኘት ሳይሆን በህግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያደርጋቸውን ወንጀል የመፈፀማቸው ዋና ምክንያት የአእምሮ ህመም ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ እንዲጣራ መሆኑን አስረድተውናል፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |