Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ሁልጊዜም መመዝገብ ለምን አስፈለገ?
ሁልጊዜም መመዝገብ ለምን አስፈለገ? E-mail
Wednesday, 30 January 2008
በተመስገን ሃይሉ

በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ካሌንደር መሠረት ኢትዮጵያ በ..መራጮች ምዝገባ.. ወቅት ላይ ነች፡፡ የመራጮች ምዝገባ እንደ ሌሎቹ የምርጫ ሥነ ሥርዓት አካሄዶች ሂደት (ማለትም እንደ እጩዎች ምዝገባ፣ እንደ ምርጫ ቅስቀሳ፣ እንደ ድምፅ መስጠት፣ እንደ ድምፅ መቁጠርና የምርጫ ውጤት ማስታወቂያ) ኢትዮጵያ ውስጥ በየምርጫው ዓመት፣ በየምርጫው ወቅት የሚካሄድ “ጊዜያዊ” ተግባር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ የምርጫ አስተዳደር እና አሰራር ቋሚ የመራጮች መዝገብ የለውም፡፡
ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስቀድሞ የወጣውን የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደት የጊዜ ሰሌዳ በማሻሻል የመራጮች ምዝገባ እስከ ጥር 3ዐ ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የተራዘመ መሆኑን ከመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ሰምተናል፡፡ በዚህ ዘገባ መሠረት ካለፈው ታህሳስ 18 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ሲካሄድ የቆየው የመራጮች ምዝገባ በተጨማሪ 13 ቀናት ማለትም እስከ ጥር 3ዐ ድረስ መራዘሙን የተራዘመም የሆነው (የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን በተለይም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምርጫ ቦርዱን ሰብሳቢ) ዶክተር መርጋ በቃናን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከክልል መንግሥታት ከህብረተሰቡ በቀረበ/በደረሰ ጥያቄ መሠረት መሆኑን ሰምተናል፡፡

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና ከቦርዱ አባላት መካከል አንዱ ጭምር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት በዚህ መግለጫ የቦርዱ ባለሥልጣናት የመራጮች ምዝገባ የተራዘመበትን ምክንያት፣ ማለትም ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የክልል መንግሥት አካላት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ይራዘምላቸው ዘንድ ያቀረቡት ጥያቄ በምን ምክንያት ላይ እንደተመሠረተ ተጠይቀውም ነበር፡፡ የቅዳሜ ጥር 17 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትም የመራጮች ምዝገባ መራዘሙን አስመልክቶ ባስነበበን ዜና ይህንን የባለሥልጣናቱን ምላሽ ሰብሰብ አድርጐ ያቀረበው በሚከተለው መልኩ ነው፡፡ “ለአንድ ወር ያህል ሲካሄድ በቆየው የመራጮች ምዝገባ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች በስራ ጫናና ሌሎች ምክንያቶች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ አለመወሰዳቸው መታወቁን ጠቁመዋል”፡፡

በዚህ መሠረት ከምክንያቶቹ መካከል አንዱ የሥራ ጫና ነው፡፡ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ፡፡ ያልተገለፀው ዝርዝራቸው ብቻ ነው፡፡ ከነዚህ ሌሎች ምክንያቶች መካከል የቦርዱ ሊቀመንበር ራሳቸው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በይፋ አንስተው የገለፁት ምክንያትም ይገኝበታል፡፡ ይህም በቦርዱ እቅድ መሠረት በተያዘው የአንድ ወር የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ይመዘገባል ተብሎ የተጠበቀውን ያህል ህዝብ ያለመመዝገቡ ነው፡፡

እስከ ጥር 18 ድረስ በተያዘው የመራጮች ምዝገባ የብሔራዊ ጊዜ ውስጥ ቦርዱ ከምርጫው ምዝገባ መራዘም በኋላ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የያዘው "እቅድ" 20 ሚሊዮን ነው፡፡ እንደ ቦርዱ መግለጫ እስከ ጥር 13/2000 ዓ.ም. ድረስ ተመዝግቧል የተባለው 18.3 (አሥራ ስምንት ነጥብ ሦስት) ሚሊዮን ነው፡፡ ለምርጫ ያቀደው ቁጥር ስንት ነው? ወይም ቦርዱ መጀመሪያ ያቀደው የአንድ ወር ጊዜ ይበቃል ተብሎ የታቀደው ለስንት ሚሊዮን ህዝብ ነው?

ሪፈረንደምን (ውሳኔ ህዝብን) ጨምሮ ማናቸውንም ዓይነት ምርጫ ከማካሄድና ከማስተዳደር የምርጫ ቦርድ ሥልጣንና ተግባሮች መካከል አንዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የማውጣት ነው፡፡ ይህ የወጣውን የጊዜ ሰሌዳ ዝርዝር እንደእኛ የመገምገም፣ የማሻሻል፣ የማራዘም፣ ተጨማሪ ጊዜ የመስጠት ወዘተ. ያካትታል፡፡ ከዚህ በፊትም ሲደረግ ያየነውና የምናወቀው ይህንኑ ነው፡፡ ትዝታውም፣ ቀውሱም ጣጣውም ገና ያልጠፋው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ በተለይም ከመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ አኳያ ክስ ባስመዘገበው የማይረሳ ትዝታ በስተጀርባ የተነሳው ጥያቄ ሁላችንም እንደ ምናስታውሰው ለምን የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ይራዘማል የሚል ሳይሆን በተቃራኒው ለምን አይራዘምም? የሚለው ነበር፡፡ የእጩዎች ምዝገባ ሳይጀምር ከዚያ በኋላም የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቅቆ እጩዎች ይፋ ሳይሆኑ በፊት የምርጫ ቅስቀሳው ባይጀመርም ፓርቲዎች በመራጮች የምዝገባ ጊዜ ውስጥ ህግ ይሁን ተግባር (ወይም ምርጫ 97 ራሱ ከሁሉም ሁለመናውን ነፃ አውጥቶ) በፈቀደላቸው የቅስቀሳ ዘመቻ ይወተውቱ የነበሩት የመምረጥ መብት ያለው ሁሉ እንዲመዘገብ የመራጭነት ካርዱን እንዲይዝ ነው፡፡

አሁን ዛሬ 2ዐዐዐ ውስጥ ሆነን ይህ ስሜት፣ ንቃት ፍላጐት ስለመኖሩ አላወቀም ወይም በደፈናው ስለመኖር አለመኖሩ መናገር ምናልባትም “ማወቅ” አስፈላጊ ነው አይደለም፡፡ ራሱ አስቸጋሪ ነው እንጂ ሰው የምርጫ ካርድ መያዝ ማለት በመራጭነት የመመዝገብ ጥቅም የገባው ምዝገባው ጊዜ ካለቀ በኋላ ነው፡፡ ለምን የመራጮች የምዝገባ ወቅት በአንድ ወር ወይም በተወሰነ ጊዜ ብቻ ይወሰናል? ምርጫው እስካለቀ ድረስ ለምን የመራጮች ምዝገባ መዝገብ ክፍት ሆኖ አይቆይም የሚል የአስረዱኝ፣ የአልገባኝም እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የቁጭት ጥያቄዎች የተነሱት ያን ጊዜ ነበር፡፡

አሁን እንደገና ዳግም የምርጫ 2ዐዐዐ (ይህንን ስም ስለማግኘቱ እንደ "ምርጫ 97 ይህን በመሰለ ስያሜ ህዝብ አዕምሮና ቀልብ ውስጥ ተመዝግቦ ስለመኖሩ ያጠራጥራል አይታወቅም) የመራጮች የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ በመራዘሙ የተነሳ ሌላ ጥያቄ ሌላ ግምት ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሰው እውነት የለውም አይባልም፡፡ ለምሳሌ በምርጫ 97 የምርጫ ምዝገባ ላይ የተነሳውን ጥያቄ ያብራራልን? የለም አሁን በ2ዐዐዐ የመራጮች ምዝገባ ለተጨማሪ 13 ቀናት ይራዘም ዘንድ የተሰጠው ውሳኔም በመግቢያችን ላይ እንደተገለፀው ምክንያቱ ግልፅ አልሆነም፡፡ “አንዳንድ የህብረተሰብ” ክፍሎች በሥራ ጫናና ሌሎች ምክንያቶች ተብሎ ነው የታለፈው፡፡ ለሚጠራጠር እንዲጠራጠር ከሁሉም አቅጣጫ “መከራ”ው ለበዛበት አላምንም ብሎ ለወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ሁሉን ነገር እንደመሰለውና በፈለገው ቢፈታው የሚፈረድበት አይመስለኝም፡፡

የመራጮች ምዝገባ እስከ ጥር 3ዐ ቀን ተራዘመ የሚለው ጉዳይ ከሁሉም በላይ የሚያስነሳው አሳሳቢና አንገብጋቢ ጥያቄ ግን የተራዘመበት የሚራዘምበት ምክንያት ግልፅ አለመደረጉ ወይም ግልፅ አልተደረገም የሚባለው ምክንያት ጀርባ አለ የሚባለው ሌላ ጉዳይ “አለነገር” አይደለም፡፡ የእኔ ጥያቄና ጉዳይ ከዚህ ሁሉ በላይ አሁንም የተቋም ጉዳይ ነው፡፡

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ኢትዮጵያ የውጭ አገር ታዛቢዎችን መጋበዟ በዚህም መሠረት እንደ ቡድን የአውሮፓ ህብረት የካርተር ሴንተር ታዛቢዎች መምጣታቸውን ምርጫውንም መታዘባቸውን እናውቃለን፡፡ ከእነዚህ ታዛቢዎች መካከል የአንዱ ማለትም የአውሮፓ ህብረት ታዛቢን የመሩት ወ/ሮ አናጐሜዝ እንደነበሩም እናውቃለን፡፡ ብዙዎቻችን ወይዘሮ አናጐሜዝን የምናውቀው ከተለያየ አቅጣጫና ወገንም ቢሆን በተለየ ምክንያት ቢሆንም እኝህ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሪፖርታቸውን ከማቅረባቸው ከዚያም በላይ ወደመታዘቡ ሥራ ከመግባታቸው በፊት አጠቃላይ የኢትዮጵያን የምርጫ የተቋም ብቃትና የተቋሙም የብቃቱም መገለጫዎች ናቸው ከሚባሉት መካከል የአንዱን ችግር አንስተው አስተያየት የሰጡበት የ”ውሳኔ ሀሳብ” ያቀረቡት እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይህም የመራጮች ምዝገባን የሚመለከት ነው፡፡

አናጐሜዝ ገና ምርጫው ሳይፋፋም ምናልባትም በህዝብ ስሜትና ብይን ተጀመረም ሳይባል የሰጡት አስተያየት ወደፊትም የመታዘቡን ሥራ አጠናቅቀው ከምርጫው ፍፃሜ በኋላ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ እዚያ ውስጥ እንደሚያካትቱት የገለፁት የመራጮች ምዝገባ ጉዳይ ኢትዮጵያ ቋሚ የመራጮች መዝገብ ሊኖራቸው የሚገባ መሆኑን ነው፡፡ ዛሬ ወይዘሮ አናጐሜዝን እርሳቸውንም ሥራቸውንም አካሄዳቸውን ሁሉ ጥልት አድርገው ያወገዟቸው ሰዎች ይህንን ጉዳይ ከሴትዮዋ ጋር ሳያያይዙ ለብቻቸውና በገዛ ራሱ ይዘት (ናሜሪት) ምክንያት እንየው የሚሉ ብዙ ሰዎች ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታና ምክንያት አናጐሜዝ የሰጡትን ይህንን የመጀመሪያ አስተያየትና የሥርዓትና የተቋም ማሻሻያ ሀሳብ በገዛ ራሱ ሜሪትና ይዘት ምክንያት ሳይሆን አና ጐሜዝ ስላሉት ብቻ እያነሱ እየጣሉ የክሳቸው መነሻ የሚያደርጉ አሉ፡፡

በእኔ በኩል የመራጮች ምዝገባ ሊይዝ ስለሚገባው የቋሚነት ባህሪይ ኢትዮጵያ ትምህርቱን የምታገኘው፣ እውቀቱን የምትቀስመው ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ከአናጐሜዝ ወይም ከወደ ፖርቹጋል ወይም በእነሱ አማካኝነት ከአውሮፓና ከህብረቱ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያችን የዘመናዊ መንግሥት፣ በየጊዜው ሥልጣን የሚይዙ ተከታታይ መንግሥታት እንደሚሉት የዲሞክራሲ ግንባታ ተግባርና ሂደት ሁሌም የእምቧይ ካብ እየሆነ መቀጠሉ የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ አገራችን ከመራጮች ምዝገባ አኳያ ይህን ሥርዓት ተቋም እመሰርታለሁ፣ በዚህም ላይ እገነባለሁ ብላ ቆርጣ የወሰነችው ከ1961 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር፡፡

የ1961 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ በ1948 እና በ1952 ዓ.ም. የወጡትን ምርጫን የሚመለከቱ ህጐችን በማሻሻልና በማጠቃለል ከመሰረታቸው ተቋሞች መካከል አንዱ የመራጮች መዝገብ የሚባለው ነው፡፡ በዚህም መሠረት የመራጮች መዝገብ ማለት ለ1961 ዓ.ም. የምርጫ ዓመት በመራጭነት የተመዘገቡ ሰዎች ሁሉ የሚገኙበትና በዚህ የ1961 ዓ.ም. አዋጅ መሠረት የመራጮችን ማጠቃለያ ዝርዝር ለማዘጋጀት መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ዝርዝር ከ1981 ዓ.ም. የምርጫ ዓመት በኋላ ለሚደረገው ማናቸውም ምርጫ የሆነ እንደሆነ የመራጮች መዝገብ ማለት የመራጮች ማጠቃለያ ዝርዝር ማለት ነው፡፡

የመራጮች ማጠቃለያ ዝርዝር ማለት ለ1981 ዓ.ም. የምርጫ ዓመት እንዲያገለግልና ከዚያም በኋላ የመራጮች ቋሚ መዝገብ ሆኖ እንዲያገለግል በአዋጁ መሠረት ከመራጮች መዝገብ የተዘጋጀ የተመዘገቡ መራጮች ሁሉ የሚገኙበት ማጠቃለያ ዝርዝር ነው፡፡

ስለዚህም በህጉ መሠረት በመራጭነት መመዝገብ ቋሚ ይሆንና (በህጉ ውስጥ የተዘረዘሩትን ሌሎች ድንጋጌዎችንና ውሳኔዎችን ሁሉ መሠረት በማድረግ) እንደገና መመዝገብ ሳይገደድ ወደፊት በሚደረጉት ምርጫዎች ሁሉ ድምፅ እንዲሰጥ ለተመዝጋቢው ሰው መብት የሚሰጥ ቋሚ መዝገብ ነው፡፡ የመራጮች መዝገብ አንዴ ቋሚ ከሆነ በኋላ ለየተከታዩ ምርጫ “ይሻሻል” እንጂ በየምርጫው ዓመትና ዘመን ሁሉም የመዝገብ ጥሪ የምዝገባ ቅስቀሳ የምዝገባ “ማራዘም” ጉዳይ አይኖርም፡፡ የመራጮች መዝገብ የሚሻሻልበት (በሞት በመለየት ለምርጫ አካለ መጠን መድረስ) አሠራር ዝርዝር ህጉ ደንግጓል፡፡ ዝርዝሩና ስልቱ በተጠቀሰው የ1961ኛም ህግ የተደነገገው ሁሉ በዚህ ፅሁፍ ይካተት ዘንድ በጣም ብዙና ሰፊ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከማንም ሳይሆን ከገዛ ራሷ ተሞክሮ መማር የምትችለው ቋሚ የሆነ የመራጮች መዝገብ መቋቋምን ብቻ ሳይሆን ተቋም መገንባት ምትክ የለሽ መሆኑን ያለዚያ ስንዝር መራመድ እንደማይቻል ባለበትም ቆሞ መጠበቅ የማይቻል መሆኑን ከስህተታችንና ከጥፋታችን መማር ይገባናል፡፡
 
< Prev   Next >