| ዕድሜ 40ዎቹ ሲደርስ ጭንቀት ይባባሳል |
|
|
| Thursday, 31 January 2008 | |
|
ከሰሞኑ የወጣ የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያመለክተው የሰው ልጅ ጭምት መሆን በሚጀምርበት (እንደ አገራችን አባባል ምራቁን የዋጠ መባል በሚጀምርበት) የዕድሜው ክልል ጭንቀታምነቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
በተለያዩ 80 የዓለም አገራት የተደረገ ጥናትን መሠረት አድርጐ ቢቢሲ ይፋ እንዳደረገው ዕድሜ ከ40 እስከ 44 በሚደርስበት ወቅት ጭንቀት እንደሚጨምር አስረድቷል፡፡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው ከወጣቶች የበለጠ ጭንቀት የሚበዛባቸው ጐልማሶች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በአሜሪካዎቹ ዋርዊክ ዩኒቨርሲቲና ዳርትማውዝ ኮሌጅ በተደረገ የማህበራዊ ህክምና ጥናት መሠረት ከየትኛውም የዓለም አገራት የበለጠ ጭንቀት እየበረታባቸው የመጡት የአሜሪካ ዜጐች ናቸው፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ ሴቶቹ ዕድሜያቸው 40 ሲደርስና ወንዶቹ ወደ 5ዐ ሲጠጉ የደስታ ማጣትና የጭንቀት እንዲሁም የመንፈስ ውጥረት ደረጃቸው ይጨምራል፡፡ ቀደም ባሉ ጥናቶች ጭንቀት በዕድሜ ሙሉ አንፃራዊ ሆኖ እንደሚጓዝ ተረጋግጦ የነበረ ቢሆንም አዲሱ ጥናት ግን በጉልምስና ጊዜ ጫፍ እንደሚደርስ አረጋግጧል፡፡ የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት አንድሪው ኦስዋልድ እንደተናገሩት ቀድሞ ጭንቀት ከሰው ሰው የሚለያይ ነው ተብሎ ቢታመንም በአዲሱ ጥናት ግን በሴቶችም ሆነ በወንዶች፣ ባገቡም ይሁን ባላገቡ ብሎም በድሃም ሆነ በሃብታም ሰዎች እንደሚከሰት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ ጭንቀት ውስብስብና ለመረዳትም አስቸጋሪ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ ድክመትንና ጥንካሬን መረዳት መቻልና ማዳበር አማራጭ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለው እንደገለፁት የደስታ ጊዜን ደጋግሞ ማስታወስና ራስን ከሌሎች ጋር እያነፃፀሩ መቆዘምን መተው ሌሎች መፍትሄዎች ናቸው፡፡ ደስታ በአንዴ የሚገኝ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰሩ ከ50ዎቹ የዕድሜ ክልል በኋላ ጭንቀት እየቀነሰ እንደሚሄድም አብራርተዋል፡፡ በጥናቱ እንደተመለከተውም ዕድሜ 70ዎቹ ሲጠጋ በአካል ጠንካራ ከሆኑ ልክ እንደወጣትነት ዘመን ጭንቀት ተወግዶ በምትኩ ደስታ ይነግሳል፡፡ የእናት ጡት ወተት አለርጅክን ሊከላከል እንደሚችል ተጠቆመ ለህፃናት ዕድገትና ጤንነት ተወዳዳሪ የለውም የሚባለው የእናት ጡት ወተት አለርጅክንም ሊከላከል እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በፈረንሳይ የተደረገ “ኔቸር ሜዲሲን” የተሰኘ ጆርናል እንዳመለከተው ሴት አይጦች በጡት ወተታቸው አማካኝነት የአለርጅክ መከላከያን ወደ ልጆቻቸው አስተላልፈዋል፡፡ ይህም የእናት ጡት ወተት ህፃናትን ከአለረጅክ በተለይም ከአስም ሊከላከል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ አለርጅክን ወይም አስምን የጡት ወተት መከላከል አለመከላከሉ በቤተ ሙከራ ባይረጋገጥም በአይጦች የተደረገው ሙከራ የአለርጅክ በሽታን ለመከላከል እየተደረጉ ላሉ ጥናቶች አጋዥ ነው ብለዋል አጥኝዎች፡፡ ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የዓለማችን ኗሪዎች በአስም አለርጅክ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ የጠቆመው ጥናቱ የወጣትነት ዕድሜ ለበሽታው ስር መስደድ አመች ወቅት መሆኑንም አመልክቷል፡፡ አስም የመተንፈሻ አካልን ከበሽታ የሚከላከሉ ንጥረ ነገሮች እንግዳ ነገር ሲያጋጥማቸው (ማለትም የቆሻሻ ሽታ ዓይነት) የሚከሰት መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ መተንፈስ መቸገርም ውጤቱ ይሆናል ብሏል፡፡ የፈረንሳይ “ኢንሰርም” ኢንስቲትዩት አጥኚዎች እንዳሉት ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች የእናት ጡት ወተት እንደ አስም ያሉ የአለርጅክ በሽታዎች መተላለፊያ ቢሆንም የአሁኑ ጥናት የተገላቢጦሽ መሆኑንና አስምን ሊከላከል እንደሚችል ፍንጭ አሳይቷል ብለዋል፡፡ በመሆኑም እስከ 6 ወር ድረስ ጡት ማጥባት ለህፃናት ጤንነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በግላስጐው ዩኒቨርሲቲ ኢሚዩኖሎጂስት የሆኑት ዶ/ር ቻርልስ ማክሻሪ በበኩላቸው “ጥናቱ የእናት ጡት ወተትን ጥቅም ከማስረዳት የዘለለ ቲዮሪ አይደለም፣ የአይጥና የሰው ልጅን የጡት ወተት ማነፃፀር አስቸጋሪ ነው” ብለዋል፡፡ ቡና የስኳር በሽታን ያባብሳል ተባለ በየዕለቱ የቡና፣ የሻይና የለስላሳ መጠጦችን ማዘውተር “ካፌይን” የተሰኘውን ንጥረ ነገር ስለሚያበዛ የስኳር ህመምን ያባብሳል ሲል ቢቢሲ አንድ ጥናትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ጥናቱ ይፋ ባወጣው መረጃ መሠረት ካፌይን የደም ውስጥ የስኳር መጠንን ስለሚያበዛ “ዲያቤትስ 2” የተባለውን የስኳር ህመም ያባብሳል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ አጥኝዎች እንዳረጋገጡት አራት ስኒ ቡና በቀን ውስጥ መጠጣት የደምን ስኳር መጠን 8 በመቶ እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ የካፌይን ንጥረ ነገር ያለባቸውን ነገሮች አለመጠቀም ለችግሩ መፍትሄ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የእንግሊዝ ኤክስፐርቶች በበኩላቸው ካፌይን ስኳርን ያባብሳል ብሎ ከመምከር በፊት ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል ሲሉ የአሜሪካውያንን ጥናት አጣጥለውታል፡፡ ቀድሞ በተደረጉ ጥናቶች ካፌይን የግሉኮስን መጠን የሚቆጣጠረውን ሆርሞን እንደሚያጠናክር ተጠቁሞ የነበረ ቢሆንም እንደ አሜሪካውያን አጥኝዎች ግን ያባብሳል ተብሏል፡፡ የዱክ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ስኩል መምህር የሆኑትና የጥናት ቡድኑ መሪ ዶ/ር ጀምስ ሌይን እንደተናገሩት የስኳር ህመም በሌለባቸ ው ግን ካፌይን ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አያመጣም፡፡ ዶክተሩ አክለውም የግሉኮስ መጠንን መቆጣጠሪያ ዋነኛው መንገድ የተመጣጠነ ምግብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ናቸው ብለዋል፡፡ የኤድስ ቫይረስን የመላመድ አቅም የሌለው መድሃኒት ተገኘ ኤች.አይ.ቪ ከመድሃኒቶች ጋር ሊላመድ እንደሚችል የእንግሊዝ ዶክተሮች ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሰባ ሦስት ሺህ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች እንደሚኖሩባት በሚገመተው እንግሊዝ አሁን ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች እየተሰጠ ያለውን መድሃኒት ሊተካ የሚችል ራልቲግራቪየር የተባለ መድሃኒት ማግኘታቸውን ዘገባው ያመለክታል፡፡ ይህ መድሃኒት የኤች.አይ.ቪ ቫይረስን ለመራባት የሚያስችለውን ኢንዛይም በመገደብ ቫይረሱ ከመድሃኒቱ ጋር እንዳይላመድ የማድረግ አቅም አለው፡፡ የፀረ ኤድስ መድሃኒት ከሚጠቀሙ ከአሥር እንግሊዛውያን የቀድሞው መድሃኒት ከቫይረሱ ጋር የመላመድ ሁኔታ እንደሚያሳይ ጥናቶችን በመጠቆም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ..ቫይረሱን ለማጥቃት የተለያዩ መንገዶችን በተጠቀምን ቁጥር በሽታውን የመቆጣጠር እድላችን ይሰፋል.. በማለት የተናገሩት የቼልሲና የዌስት ሚኒስትር ሆስፒታል ዶክተር ማርክ ኔልሰን በእንግሊዝ የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሃኒቶች የሕመምተኞቹን እድሜ በማርዘም ረገድ ዓይነተኛ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም የመድሃኒቶች ከቫይረሱ ጋር መላመድ ግን ከፍተኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ የወፍ ጉንፋን በኢንዶኔዢያ እየደረሰ መሆኑ ተጠቆመ በኢንዶኔዢያ በወፍ ጉንፋን የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ መቶ ከፍ ማለቱ ተገለፀ፡፡ ከጃካርታ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ የሚኖሩ ሁለት ኢንዶኔዢያዊያን በያዝነው ሣምንት በበሽታው መያዛቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ የወፍ ጉንፋን ማዕከል ቃል አቀባይ ጃክ ሱዮኖ ተናግረዋል፡፡ ደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ የወፍ ጉንፋን ቫይረስ ከተገኘ በኋላ ሁለት መቶ ሀያ ሰዎች በበሽታው የሞቱ ሲሆን ኢንዶኔዢያ በወፍ ጉንፋን ከተጠቁት አገራት ቀዳሚዋ ናት፡፡ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ አንድ የአሥር ዓመት ታዳጊና የሀያ ሦስት ዓመት ሴት በወፍ ጉንፋን መሞታቸውን ለአሶሼትድ ፕሬስ የገለፁት ጃክ ሱዮኖ ኢንዶኔዢያ ውስጥ የወፍ ጉንፋን ቫይረስ እንዳለባቸው ከተረጋገጡ መቶ ሀያ አራት ኢንዶኔዢያዊያን መካከል መቶ የሚሆኑት መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |