Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow በሰው ኃይል ልማት ኢትዮጵያ...
በሰው ኃይል ልማት ኢትዮጵያ... Print E-mail
Sunday, 06 January 2008

በሰው ኃይል ልማት ኢትዮጵያ ከዓለም የመጨረሻ ተርታ ላይ ትገኛለች

ኢትዮጵያ የሰው ሃይል ልማትን በማረጋገጥና ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት የሚችሉበት የገቢ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ለማስቻል ብዙ ርቀት እንደሚቀራት መረጃዎች አመለከቱ፡፡ አገሪቱ አሁንም በተለያዩ የኢኮኖሚና የሰዎች ደህንነት አመልካቾች መስፈርት ከዓለም አገራት በመጨረሻ ደረጃዎች ላይ ትገኛለች፡፡

ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነው የሰው ኃይል ልማት መለኪያ /ሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ/ እንዳሳየው፣ ኢትዮጵያ የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም በማረጋገጥ ረገድም ከብዙዎቹ የዓለም አገራት ኋላ ቀር  ነች፡፡

እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ ..ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት.. የተሰኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት ..ሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ.. የተሰኘውን መረጃ ያወጣል፡፡ መረጃው ከዓመታዊ አጠቃላይ ገቢ /ጂዲፒ/ ባሻገር የሰዎችን ደህንነት የተመለከተ ዝርዝር የያዘ ነው፡፡ ይኸውም መለኪያው  የሰዎችን የኢኮኖሚ ሁኔታና አማካይ የመኖር ዕድሜ፣ የትምህርት ሁኔታና የኑሮ ደረጃ አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡

..ሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ.. አንድ አገር በሰው ሃይል ልማት /ሂውማን ዴቨሎፕመንት/ በኩል እያሳየ ያለውን አማካይ ዕድገት የሚለካ ነው፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ከተቀመጡ መስፈርቶች በታች ያሉትን ሰዎች ሁኔታዎች /የሰዎች አኗኗር የሚመለከት ነው፡፡ ሰዎች ተገቢ የኑሮ ሁኔታ አላቸው? ገቢያቸው መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በቂ ነው? የሚለውን በማካተትም በቀን 1 ዶላር ገቢ ከሚለው የድህነት መስፈርት ተጨማሪ መለኪያዎችን ያሳያል፡፡

ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገው በዘንድሮው የሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ አጠቃላይ መለኪያ ኢትዮጵያ ከ177 አገሮች 169 ደረጃን አግኝታለች፡፡ መረጃው የሚያጠቃልላቸው ሌሎች ነጥቦች ደግሞ ለምሳሌ በአማካይ የመኖሪያ ዕድሜ /51.8 ዓመት/ ከ177 አገሮች 153ኛ ስትሆን በአዋቂዎች የማንበብና መፃፍ ዕውቀት ከ177 አገሮች 132ኛ /35.9 በመቶ/ መሆኗ ተጠቁሟል፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ያለውን ውሳኔ /ሬሽዮ/ በተመለከተ የኢትዮጵያ ደረጃ 156ኛ /42.1 በመቶ/ ሲሆን በዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ /1..055 ዶላር/ 162ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

..ሂውማን ፖቨርቲ ኢንዴክስ.. የተባለውና የሰዎችን የኢኮኖሚ /የድህነት ሁኔታ በሚያየው የሪፖርቱ ሌላ መለኪያ ደግሞ ኢትዮጵያ ከ108 በማደግ ላይ ያሉ አገሮች 105ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ሂውማን ፖቨርቲ ኢንዴክስ የተባለው መረጃ የሚመለከተው በድህነት ምክንያት የጤና መቃወስ የሚገጥማቸውንና 40 ዓመት ማለፍ የማይችሉ ሰዎችን ሁኔታ የሚለካ ነው፡፡ የተሻለ የኑሮ ደረጃ /ስታንዳርድ/ የዚህ መለኪያ አንዱ ነጥብ ሲሆን የሚለካውም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ከክብደት በታች የሆኑትን ቁጥርና ለንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ያልበቁ ሰዎችን በማየት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ 40 ዓመትን የማለፍ ዕድል በሌላቸው ሰዎች ከ173 አገሮች መካከል ከ22ቱ ብቻ ተሽላ 23ኛ /ከህዝቧ 33.3 በመቶ 40 ዓመትን የማለፍ ዕድል የለውም/ ስትሆን ለንፁህ ውሃ አቅርቦት ያልታደሉ ሰዎች /78 በመቶ ሆነው/ ከ125 አገሮች 7 አገሮችን ብቻ በመሻል 8ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በዕድሜያቸው ሊኖራቸው ከሚገባ ክብደት በታች ያሉ ህፃናት /38 በመቶ ሆነው/ ኢትዮጵያ ከ134 አገሮች መካከል ከ12ቱ ብቻ ተሽላ 13ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡

የሴቶችን ችሎታ /አቅም በመገንባት ረገድ የተመዘገበውን ውጤት የሚያየው ሌላው የሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ ሥርዓተ ፆታን የሚመለከተው መለኪያ /ጀንደር ሪሌትድ ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ/ ነው፡፡ ይህ መለኪያ ድህነትን ለሚለካው መለኪያ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ በሴቶችና በወንዶች መካከል መለኪያው /ሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ/ም ሆነ በሥርዓተ ፆታ /ጀንደር ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ/ መለኪያው ኢትዮጵያ ከ141 አገሮች ኋላ ነች፡፡

የሥርዓተ ፆታን የሚያካትተው ሌላው መለኪያ የሴቶችን በኢኮኖሚ ራስን መቻል /ጀንደር ኢምፓወርመንት/ ሲሆን ሴቶች በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ያላቸውን ተሳትፎ ይመለከታል፡፡ ይኸው መለኪያ ሴቶች በውሳኔ ሰጪነትና በመንግስት ኃላፊነት ቦታዎች ያላቸውን ድርሻም የሚገመግም ነው፡፡ በዚሁ መለኪያ ኢትዮጵያ ከ93 አገሮች 72 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

በቤተልሔም ነጋሽ

 

 
< Prev   Next >