Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow “ቱሪዝም ያላደገው በሚኒስቴር ደረጃ...
“ቱሪዝም ያላደገው በሚኒስቴር ደረጃ... Print E-mail
Sunday, 03 February 2008
Image
አቶ ጌታቸው ደስታ
“ቱሪዝም ያላደገው በሚኒስቴር ደረጃ ባለመቋቋሙ ነው”

አቶ ጌታቸው ደስታ

ቱሪዝም የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ሌቱር” ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል እንደመጣ የሚነገር ሲሆን፣ የተለያዩ ምሁራን የተለያየ ትርጓሜ ሰጥተውታል፡፡ ሔርማን ቮን ሹርላርድ “የኢኮኖሚ ባህሪ ያላቸው፣ በቀጥታ ከውጭ ዜጐች በአንድ አገር ከተማ ወይም አካባቢ መግባት፣ መቆየትና መንቀሳቀስ ጋር በተዛመዱ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ድምር ውጤት ነው” ብሎታል፡፡
ሉንዚከርና ክራፕት ደግሞ “ቱሪዝም ከእንግዶች ጉዞና ቆይታ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚነሱ ክስተቶችና ግንኙነቶች ጠቅላላ የሆነ የተግባር ስያሜ ነው፡፡ የእነዚህ የእንግዶች ቆይታ በቦታው ቋሚ መኖሪያ ከመመሥረት ወይም ትርፍ የሚያስገኙ ተግባራት ላይ ከመሰማራት ጋር ያልተገናኘ ነው” ሲሉ ገልፀውታል፡፡

በዓለም ላይ በርካታ አገሮች የተጠቀሙበትንና ያደጉበትን ያህል አገራችን ኢትዮጵያ በቱሪዝም አልተጠቀመችም፡፡ ለዚህ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች በቱሪዝም እንቅስቃሴ ዙሪያ ጥናት አለመደረግ፣ ቅስቀሳ አለመሰራትና በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን አለማዘጋጀት ይገኙበታል፡፡ ከእነኝህ ችግሮች አንዱን ለማስወገድ እንዲረዳ አቶ ጌታቸው ደስታ በ1999 ዓም መጨረሻ መረጃን በጥናት ያስደገፈና “ቱሪዝም በኢትዮጵያ” የሚል መፅሃፍ አዘጋጅተዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በጐጃም፣ ባህርዳር ተወልደው ያደጉ ሲሆን በህግና በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ ባለትዳርና የ4 ልጆች አባት የሆኑት አቶ ጌታቸው የላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ሳይት ፈርስት ኃላፊ፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ ም/ሊቀመንበርና የሺና ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ሲሆን በተለያዩ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ሠርተዋል፡፡

“ቱሪዝም በኢትዮጵያ” በሚል ያሳተሙትን መፅሃፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውን ምክንያት ሲናገሩ “ለፀሐፊነት የሚያበቃ የእውቀት ዝግጅት ባይኖረኝም ለማጥናትና ለመፃፍ የገፋፋኝ ለቱሪዝም ያለኝ ስሜት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ከዓለም ቁንጮ ከነበሩና በጣት ከሚቆጠሩ አገሮች አንዷ ነበረች፡፡ አሁን በእኛ ዘመን ደግሞ የዓለም ጭራ ሆናለች፡፡ ይሄ የሆነው ለምንድንነው? ቢያንስ መካከለኛ ከሚባሉ አገሮች እንኳን እንዴት መድረስ አልቻለችም? የሚለው ሁልጊዜ ያሳስበኛል፡፡ እንደዜጋ ምን ማድረግ አለብኝ እያልኩ አስብ ነበር፡፡ ከሃያ ሶስት ዓመታት በላይ በተለያዩ በጐ አድራጐቶች ብሳተፍም ተጨማሪ ሌላ ነገር መሥራት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ የምንለው ቱሪዝም ደግሞ ያልተጠቀምንበት የዕድገት ቁልፍ ነው፡፡ ስለዚህ ትንሽ ነገር ላበርክት ብዬ ወደጥናቱ ገባሁ፡፡ የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ ቃኘሁ፣ ከሁለት ዓመት በላይ የአገራችንን ነባራዊ የቱሪዝም ሁኔታ አጠናሁና እንዲታተም አደረግሁ” ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በጥናታቸው እንዳረጋገጡት ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብቷ ከአፍሪካ አገራት በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ አሁን ባለው የቱሪዝም ሁኔታ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዙት የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች (በተለይ ደቡብ አፍሪካ) ሲሆኑ የሰሜን ምዕራብ አፍሪካ በሁለተኛነት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በሶስተኛነት ተመድበዋል፡፡

ግብፅ በዩኔስኮ የተመዘገቡላት ታሪካዊ ቅርሶች ከሚለው ጐራ የሚመደቡት ስድስት ቅርሶች (ሲፊኒክስና ፒራሚዶችን) ሲሆን በኬንያ ግን በዩኔስኮ የተመዘገበ ምንም የተፈጥሮም ሆነ ታሪካዊ ቅርስ የለም፡፡ በኬንያ ቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡት የዱር እንስሳት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ቅርሶቿ ቁጥር ስምንት ቢሆንም በቱሪዝም ተጠቃሚነት ከኬንያና ግብፅ ከሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ያነሰ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የቱሪዝምን በኢንዱስትሪ መልክ መገለፁን አይስማሙበትም፤ እርስዎ ግን መድበውታል ምክንያትዎ ምንድን ነው ብለን ላቀረብነው ጥያቄ ሲመልሱ “በመጽሐፌ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ቱሪዝም ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህንን አገላለፅ መጠቀምን አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች አይግባቡበትም፡፡ ለዚህም በዋናነት የሚያስቀምጡት ፣የራሱ የሆነ የምርት ውጤቶች የሉትም፣ በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ቱሪስቶችን እንደ ፍላጐት፣ የቱሪስት አገልግሎት መስጫዎችን እንደ አቅርቦት እንዲሁም የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን እንደ ምርት ውጤቶች አድርገን ማየት እንችላለን” በማለት ያስረዳሉ፡፡

“በታዘብኳቸው ሶስቱ መንግሥታት (የአፄ ኃይለሥላሴ፣ ደርግና የኢህአዴግ መንግሥታት) ቱሪዝም የሚጠበቀውን ያክል ለውጥ አላመጣም” ያሉት አቶ ጌታቸው ለዚህም ምክንያቱ ቱሪዝም ራሱን ችሎ በሚኒስቴር ደረጃ አለመቋቋሙ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ አቶ ጌታቸው እንደሚሉት በሶስቱም መንግሥታት ቱሪዝም አንዴ ከንግድና ኢንዱስትሪ ከባህል፣ አንዴ ከስፖርት፣ ሌላ ጊዜ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመዳበል የቆመ መሆኑ ዕድገቱን እንዳላፋጠነው አስረድተዋል፡፡ እንደ አጥኝው ገለፃ “በሌሎች አገራት ቱሪዝም ብቻውን ቆሞ “ቱሪዝም ሚኒስቴር” ሆኖ እየተሠራበት በመሆኑ ዕድገቱ ሊፋጠን ችሏል” ብለዋል፡፡

ቱሪዝም ከነዳጅ እናገኛለን ብለን ከምንጠብቀው ያልተናነሰ ኢኮኖሚያችንን ሊገነባ እንደሚችል የሚያምኑት አጥኚው በተፈጥሮአዊና በታሪካዊ ቅርሶች በዩኔስኮ የተመዘገቡትና ገና ወደፊትም ሊመዘገቡ የሚችሉ ቅርሶች ስላሉ ከፍተኛ ገቢ ልናገኝባቸው እንችላለን ብለዋል፡፡ በዓለም የቅርስ መዝገብ ከተቀመጡ አምስት መስፈርቶች አንዱን ያሟላ በዩኔስኮ የሚመዘገብ ሲሆን የአገራችን ቅርሶች ከመስፈርቶች ሁለትና ከዚያ በላይ አሟልተው መገኘታቸውን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ “ይህ ከሌሎች አገሮች የተሻለ የቱሪዝም ሃብት እንዳለን ያስገነዝባል፤ ይህንን ለመጠቀም ደግሞ መፍጠን አለብን” ብለዋል፡፡

ለቱሪስቶች ወደ አንድ አገር መጉረፍ የሚረዱ መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ “ቀዳሚው መሠረታዊ ጉዳይ ሰላም ነው፡፡ አንድ ቱሪስት ከአገሩ ወጥቶ ሌላ አገርን ሊጐበኝ የሚሄደው በቦታው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ቱሪዝም ለሰላም ፣ሴንሲቲቭ፣ የሆነ ነገር ነው፤ አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያክል በዚያድባሬ የሶማሊያ ጦርነት ወቅት የቱሪስቶች ቁጥር ቀንሶ ነበር፡፡ በቅርቡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜም እንዲሁ፡፡ በመሆኑም ሰላም ለቱሪስቶች መምጣት ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ሌላው መሠረታዊ ነገር መሠረተ ልማት ነው፡፡ ከሚፈለገው ቦታ ሊያደርሰው የሚችለው መንገድና ትራንስፖርት፣ ሊያርፍና ሊዝናናበት የሚችል ደረጃውን የጠበቀ ሆቴልና የመሳሰሉት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው”

በሰለጠኑ አገራት እንደሚስተዋለው ቱሪዝም፣ የቅርስ ቱሪዝም የጀብድ ቱሪዝም፣ የባህል ቱሪዝም፣ ኢኮ ቱሪዝም፣ የቁማር ቱሪዝም፣ የዝሙት ቱሪዝም፣ የጠፈር ቱሪዝም እና የመሳሰሉት የቱሪዝም ዓይነቶች ቢኖሩም፣ አቶ ጌታቸው እንደገለፁት በአገራችን የሚተገበረው ከተፈጥሮና ታሪካዊ ቅርሶች ጋር የተያያዘ ቱሪዝም ነው፡፡ በአገራችን የሚተገበረው ዋነኛ የቱሪዝም ዘርፍ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው እግረ መንገዱን የተለያዩ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ጥናታዊ ፅሑፋቸውን በመፅሐፍ መልክ አዘጋጅተው በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ካበቁ በኋላ መፅሐፉ የመጀመሪያ እንደመሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች አበረታች መልስ ሰጥተዋቸዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትና የመሳሰሉት እየተጠቀሙበት እንደሆነ የገለፁት አጥኚው የተለያዩ አስጐብኝ ድርጅቶችም እንዲገለገሉበት ጠቁመዋል፡፡

በጥናታዊ መፅሐፉ የኢትዮጵያ የታሪክ ዘመን ዕድሜ ከ8200 ዓመት በላይ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ብዙሃኑ የሚያውቀው “ኢትዮጵያ የ3 ሺህ የታሪክ ዘመን” እንደሆነች ነው ሃሳቡ አይጋጭም ወይ ብለናቸው ነበር፡፡ አቶ ጌታቸው ሲገልፁልን ጥናታቸውን የተሟላ ለማድረግ መረጃ ሲያገላብጡ አንድ የውጭ አገር የታሪክ ፀሐፊ በማስረጃዎች አስደግፎ የኢትዮጵያን የታሪክ ዕድሜ 8200 ዓመት ያደርሰዋል፡፡ በመሆኑም ከቱሪዝም ዕውቀት ጋር ብሎም ለጐብኝዎች የታሪክ ጥናት እንዲረዳ በማሰብ መጠቀማቸውን ገልፀውልናል፡፡

በደመቀ ከበደ
 
< Prev   Next >