Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow ከንቲባ ብርሃነ ስለ ኢትዮጵያ ሲኒማ
ከንቲባ ብርሃነ ስለ ኢትዮጵያ ሲኒማ Print E-mail
Sunday, 03 February 2008
Image
ከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ
የአዲስ አበባ ከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ ጥር አጋማሽ ላይ በ”አልተኛም” ፊልም ምረቃ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ላሊበላ ፊልም ይህንን ጥሪ ሲያደርግልኝ አንድም ፊልሙን እንድመርቅለትና በፊልሙ ላይ ለተሳተፉ ተዋንያን እና በአገራችን የፊልም እድገት ተስፋ ለተጣለባቸው ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስጦታ እንድሰጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል፣ በሸራተን ሆቴል በሚያደርገው ዝግጅት እንድገኝ ላደረገልኝ ጥሪ አስቀድሜ ቃል ስለገባሁና ወደ እዛ ስለምሄድ የዚህ ኪነ ጥበብ አፍቃሪና አድናቂ እንደመሆኔ ፊልሙን በሌላ ጊዜ አየዋለሁ፡፡ በተደረገልኝ ጥሪ መሰረት ግን በመሃከላችሁ ተገኝቼ ተሳታፊዎችን ለማበረታታትና የፊልሙን ኢንዱስትሪ ለመደገፍ እድል በማግኘቴ የተሰማኝን ደስታ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡

አንድ ከንቲባ ጊዜያዊ ቢሆንም ብዙ አማካሪዎች አሉት፡፡ እኔም አትሂድ ተብዬ ተመክሬያለሁ፡፡ ምነው ስላቸው ብልግና ሊኖርበት ይችላል አሉኝ፡፡ አይ” የኪነጥበብ ባለጌ የለውም አልኩኝ፡፡ እንደ ሌሎቹ የበለፀጉ አገሮች ቢሆን ከመምጣቴ በፊት በሚዲያ የተሰጠውን ትችት ለማየት እድል ይኖረኝ ነበር፡፡ እንዲሁም ቅድመ ምልከታ /ስኒክ ፕሪቪው/ እንዳይ ይቀርብልኝ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ በአገራችን አልተለመደም ወይም እኔ አዲስ ነኝ፡፡ ለምንድነው እንደዚህ አይነት ነገር የሌለው ብዬ በአካባቢዬ ያሉ ሰዎችን ስጠይቅ የኮፒ ራይት ጉዳይ ነው አሉኝ፡፡ ኮፒ ራይት ስላልተጠናከረ በሌላ ሰው እጅ እንዳይገባ፣ እንዳይቀዳና አላግባብ እንዳይጠቀምበት በመስጋት ነው ተብያለሁ፡፡ ይሄም በከተማ ልማት አኳያ የገጠመኝን አንዳንድ ሁኔታ አስታውሶኛል፡፡ ይኸውም አንድ አልሚ መጥተው የልማት ሐሳባቸውን አካፍለውኝ እስቲ የፕሮጀክት ንድፉ የታለ ብላቸው አይ እሱንማ አልሰጥም ይሰረቅብኛል ሲሉ፣ ኧረ እኔ የንግድ ሃሳቡ የለኝም ብላቸው፣ ሌሎች ረዳቶችዎም ቢሆኑ አሳልፈው ለሌላ ሊሰጡብኝ ይችላሉ ነበር ያሉኝ፡፡ የፕሮጀክት ንድፉንም ይዘው ሄደው በዛው ቀርተዋል፡፡ ፊልሙ ግን እንደዚህ እንደማይሆን ተስፋ አድርጋለሁ፡፡

በቀድሞ ጊዜ ከኢትዮጵያ ፊልሞች የማስታውሳቸው ሦስት ናቸው፡፡ “ሒሩት አባቷ ማነው”፣ “ጉማ” እና “አስቴር”፡፡ እነዚህም በ16 ሚሊ ሜትር እና በ35 ሚሊ ሜትር የተሠሩ ነበሩ፡፡ በጊዜያቸው ተወዳጅነትን ያተረፉና ለዛሬው የፊልም ሥራም መነሻ ሆነዋል፡፡ አሁን እጅግ ያስደሰተኝ በዚች አምስት ዓመታት ውስጥ ከአንድ መቶ የማያንሱ ልዩ ልዩ ፊልሞች መሠራታቸውን መረዳቴ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ እርካታ ነው፡፡ በጣም የሚያበረታታና ለወደፊቱ የጥሩ ውጤት አመላካች ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

በቅርቡ የተሰራው “ውሳኔ” የተሰኘው ፊልም ገቢ በማስገኘት ረገድ አራት ሚሊዮን ብር ያህል በአንድ ዓመት ውስጥ እንዳስገባ ነው የተረዳሁት፡፡ ይሄ ደግሞ አበረታችና ኢንዱስትሪው እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ወጣቶች ወደዚህ ሙያ በፍላጎትና በስሜት መግባታቸው ለኪነጥበብ ያላቸውን ያልረካ ጉጉት ያመለክታል፡፡ መንግስትም ሆነ ብሔራዊ ተቋማት ይህ ወጣቱን የሚስብ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር የበለጠ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በፊልም ታሪክ አመራረጥ ላይ አንዳንድ ችግር ይታያል፡፡ ችግሩም ከውጭ በተወሰዱ ታሪኮች ላይ እየተመሰረቱ መሰራታቸው ነው፡፡ እንዲሁም የልምድ ነገር ሆኖ አንዳንድ ፊልም ሕውሰታዊ (ሴንቲሜንታል) ሆኖ ካላስለቀሰ ብዙም ፈላጊ አይኖረውም፡፡ ልክ “ፍቅርና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው እንጂ” እንደሚባለው ፈገግታና ፍንደቃ የሚያጎርፉ የቀልድና የፌዝ ፊልሞች ቦታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይሄ ሁሉ በሙከራና በጊዜ የሚስተካከል ይሆናል፡፡ ባህል ከአንዱ ወደ አንዱ የሚወራረስ ቢሆንም ውርስ ብቻ አመርቂ አይሆንም፡፡ በራሳችን ባህል ላይ ያተኮሩ ቢሆኑ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡

እነዚህ ሁሉ ፍሬያማ የሚሆኑት አንደኛ ከአስራ ሶስቱ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የቴአትርና አርት ትምህርት ክፍል ያለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነው፡፡ ይሄ በተቻለ መጠን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በግል ኮሌጆች እንዲስፋፉ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛው የስቱዲዮ ችግር ነው፡፡ ብዙዎቹ ፊልሞች በየቤቱ ነው የሚሰሩት፡፡ በቂ ስቱዲዮዎች ባለመኖራቸው የድምጽና የብርሃን አጠቃቀም ችግር ይታይባቸዋል፡፡ አንዳንድ የኪነጥበብ አዋቂዎች “ሲኒማ ኢዝ ፔይንቲንግ ዊዝ ላይት” ይላሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመቀነስ በየክፍለ ከተማው የሚገኙ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ድምጽ መከላከያና አንዳንድ ጥቃቅን ለውጦችን በማድረግ ለስቱዲዮ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ አንዱ አይነተኛ ዘዴ ነው፡፡

ሦስተኛው ችግር ለፊልሞቹ በቂ ሲኒማ ቤት በከተማዋ አለመኖር ነው፡፡ አሁን ያሉት የመንግሥትና የግል ሲኒማ ቤቶች እንደ ብሔራዊ ቴአትር፣ አገር ፍቅር፣ አምባሳደር ወዘተ. በዝቅተኛ ዋጋ ለሚሰሩ፣ ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ የሚጠይቁ ይሆናሉ፡፡ ይህም እየፈለቁ የሚገኙ ታታሪ ወጣቶች ዋጋው ከሚችሉት በላይ ይሆንባቸዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ለዚህም መፍትሄው በየቀበሌው ያሉ አዳራሾች አንዳንድ ጥገና ቢደረግላቸው በአንድ ጊዜ ዘጠና ዘጠኝ ሲኒማ ቤቶች ማግኘት ይቻላል፡፡ ሌላው የመገናኛ ብዙሃን ጉልህ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ለፊልሞቹ ደረጃ በማውጣትና በየዕድሜ ክልል (ሬቲንግ) የሚታዩ ባህልን ያስተዋሉ ፊልሞች የሚቀርቡበትን ሁኔታ መፈለግ ይኖርባቸዋል፡፡

አሜሪካ ዓለምን ልትቆጣጠር የቻለችውና የሰውን መንፈስ የማረከችው በመሳሪያ እና በሀብቷ ብቻ ሳይሆን፣ ቀሪውን ዓለም የባህል ቅኝ ተገዢ ያደረገችው፣ በሚማርኩ ሙዚቃና ፊልሞቿ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ የሲኒማ ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በርቱ ተበራቱ፡፡
 
< Prev   Next >