Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow “. . . ትልቁ ነገር በአስተሳሰብ መለወጥ ነው”
“. . . ትልቁ ነገር በአስተሳሰብ መለወጥ ነው” Print E-mail
Sunday, 03 February 2008
Imageአቶ ሳሙኤል ታፈሰ
የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር

“በሥራ የሚያምን፣ የሰራና የሠራውን በአግባቡ የሚይዝ ካሰበበት ይደርሳል”  በማለት የሚናገሩት በመደጋገም ነው፡፡ የደረሱበት የሀብት ደረጃም ለሚናገሩት ማረጋገጫ ነው፡፡
የድርጅታቸው ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ ያላቸው ቢሮና ቢሮውን ውበት የሰጡት የቢሮ ቁሳቁሶች ባለሀብቱ ጥሩ ነገር ማየት እንደሚወዱ ይመሰክራል፡፡ በዘመናዊ ዲዛይን በልዩ ትዕዛዝ በተሰሩ እቃዎች የተዋበው የመኖረያ ቤታቸውም (ቪላ) የጐበኙትና በአጠገቡ ያለፉ በሙሉ አድንቀውላቸዋል፡፡

ሲጃራና ማስቲካ ቸርችረዋል፡፡ የተቀደደ ጣሪያ በማደስና ቀለም በመቀባት የኮንስትራክሽን ሥራን የተቀላቀሉት ባለሀብት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ጨርቆስ (ቂርቆስ) ነው፡፡

በቅርቡ ካሰሩት ቪላ ቤት ምረቃ ጋር 50ኛ የልደት በዓላቸውን አክብረዋል፡፡ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ አሰግድ ተፈራ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኮንስትራክሽን ሥራ ሲገቡ ካፒታል ነበረዎት?

አቶ ሳሙኤል፡-
አንድ ከስቴዲየም ዙሪያ የገዛኋት ጥሩ የቆዳ ጃኬትና 500 ብር ብቻ ነበረኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ እንዴት ፈቃድ አገኙ?

አቶ ሳሙኤል፡-
አባቴ በፍልውሀዎች ድርጅት ተቀጥሮ በቀለም ቀቢነት፣ በግንበኛነትና በፎርማንነት ይሠራ ነበር፡፡ ይከፈለው የነበረው በወር 2ዐዐ ብር ብቻ ስለነበር የቤተሰባችንን ኑሮ ለማገዝ በየመንደሩ ቱታ ለብሼ ከትምህርቴ ጐን ለጐን የቀለም መቀባት ሥራ ጀመርኩ፡፡ በ1976 ዓ.ም በወቅቱ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር የሚደርስ የኮንስትራክሽን ፈቃድ ለመስጠት የ10 ሺህ ብር የባንክ አካውንት ይጠይቅ ነበር፡፡ አንድ ወዳጄን አሳዝኜ ገንዘቡን ባንክ በስሜ እንዲያስገባልኝ ለመንኩት፡፡ የራሴን 5ዐዐ ብር ጨምሬ 10”500 ብር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስገብቼ ለኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ካሳየሁ በኋላ በዕለቱ ገንዘቡን አውጥቼ መለስኩ፡፡ በወቅቱ መተማመን አለ፡፡ ክህደት ብሎ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ፈቃድ ካወጡ በኋላ መጀመሪያ የተረከቡት ሥራ ምን ነበር?

አቶ ሳሙኤል፡-
ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራሁት የዋቢ ሸበሌን የጣራ እድሳት ነው፡፡ አንድ መቶ ሺህ ብር ነበር ዋጋው፡፡ በወቅቱ ገንዘብ ወስዶ የሚከዳ ስለሌለ ነው መሰለኝ ያለምንም መያዣ ሃያ ሺህ ብር ቅድሚያ ተሰጠኝ፡፡ ባገኘሁት ገንዘብ እቃ ገዛዝቼ ሥራውን ጀመርኩ፡፡ 25 ሺህ ብር አተረፍኩ፡፡ ከትርፉ ታሪካዊዋን ቶዮታ ቀስት መኪና ገዛሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣይ ሥራዎ ምን ሆነ?

አቶ ሳሙኤል፡-
የሚያፈስ ጣሪያ መፈለግና ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ጓደኞችዎ “ሳሙኤል ጣሪያ” ያሉዎት ለዚህ ነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
የዘውዲቱ፣ የጥቁር አንበሳ፣ የጳውሎስ ሆስፒታል፣ የስታዲየምን፣  የትምባሆ ሞኖፖል፣ አባቴ ይሰራበት የነበረውን የፍልውሃዎች ድርጅት ጣራ ሳድስ በዛው ጓደኞቼ ሳሙኤል ጣሪያ አሉኝ፡፡  ያደስኩት የሚያፈስ ጣራ ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ የሚያፈስ ጣሪያ በመሥራት ተካንኩ፡፡ የወተር ፕሩፍን ሥራ ባለሙያ ለመሆን ቻልኩ፡፡ እግረ መንገዴንም ደረጃዬን እያሳደግኩ 2.5 ሚሊዮን የሚያወጣ ሥራ መሥራት የምችልበት ደረጃ ላይ ደረስኩ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮንስትራክሽን ሥራ ከትምባሆ ሞኖፖል ወስጄ ሠራሁ፡፡ ከ1976 እስከ 1980 ጣራ ሳድስ ቆየሁ፡፡ በ1983 ትልቅ የምለውን ሥራ ስሠራ ኮሌኔል መንግሥቱ አገር ለቅቀው የወጡበት ጊዜም የማልረሳው የመደናገጥ ግጥምጥም ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በሚያስገርም ፍጥነት የባለሀብቶችን ጐራ ተቀላቅለዋል፡፡ ምስጢሩ ምንድነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
ምንም ምስጢር የለውም፡፡ በደርግ ጊዜ እድሳትና አነስተኛ ሥራዎች እንጂ ከፍተኛ የኮንትራት ሥራ የለም፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ የኮንስትራክሽ ሥራ ፀሐይ ወጣለት፡፡ ለዘርፉ በተከፈተው የሥራ መስክ ተጠቃሚ ለመሆን ቻልኩ፡፡ በዝርዝር ልገልፃቸው የማልችላቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች መሥራት ጀመርኩ፡፡ ቀደም ሲል በአንድ ፒክአፕ መኪና ሾፌር፣ መሀንዲስ፣ ገንዘብ ከፋይ፣ አስተዳደሪ ወዘተ. ሆኜ ስሠራ የነበረበት ታሪክ ተለወጠ፡፡ ቃሊቲ ቢሮ ከፈትኩ፡፡ በየዘርፉ ባለሙያዎች ተቀጠሩ፡፡ ዛሬ ከስድስት ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት ድርጅት ለመፍጠር በቃሁ፡፡ ምንም ምስጢር የለም የምለው ይህንን ነው፡፡ ምስጢሩ መሥራት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው መሥራት ከቻለና ያገኘውን ከሳንቲም ቤት ጀምሮ ሳይንቅ በአግባቡ ከተጠቀመ ያድጋል፡፡ ልዩ እርዳታም አያስፈልገውም፡፡ በየደረጃው በእጃችን ያለውን እየበተንን ለማደግ የምናስብ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ እኔ ሲጋራም እሸጥ ነበር፡፡ የአበባ ቀለም ለዘመን መለወጪያ እሸጥ ነበር፡፡ አበባ እየሰራሁ እሸጥ ነበር፡፡ ከሁሉም የማገኘውን ቤተሰብ በመርዳት፣ ወንድምና እህቶቼን እያስተማርኩ የሚተርፈኝን አስቀምጥ ነበር፡፡ ከዜሮ ተነስቼ ያደግኩት ምስጢር ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መኖሪያ ቤትዎ ቆንጆ ነው፤

አቶ ሳሙኤል፡-
መኖሪያ ቤቴ ብቻ ሳይሆን ቢሮዬም ቆንጆ ነው፡፡ ይህንን ያደረግኩት ሆን ብዬ ነው፡፡ በውጪ አገር ለአገራችን ያለው አመለካከት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከከፍተኛ የቢዝነስ ድርጅቶች ጋር ስንገናኝ ለእኛ ያላቸው ትኩረት ብዙም ደስ የሚል አይደለም፡፡ በዚህ በጣም እናደዳለሁ፡፡ እልህም ይይዘኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ከእነሱ የተሻለ ነገር ሰርቼ ማሳየት አለብኝ በሚል ዘመናዊ ቢሮ አሰራሁ፡፡ የተለያዩ ኩባንያዎች ከውጪ አገር ሲመጡ ቢሯችንን ተመልክተው ይደነቃሉ፡፡ ለካ ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲህ ዓይነት ድርጅት አለ ይላሉ፡፡ የመኖሪያ ቤቴም ከዚህ የሚለይ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የሰሩት ቤት ተጋኗል የሚሉ አሉ፤

አቶ ሳሙኤል፡-
በጣም የሚያምር ነገር ሳይ እረካለሁ፡፡ ውብ ነገር ስመለከት እደሰታለሁ፡፡ እየሰራን ባለው ሪል ስቴት ውስጥ ከገባሁ ውጣ ውጣ አይለኝም፡፡ የሌሎች አገሮች ባለሀብቶች የሚያሰሯቸው ቪላዎችና ልዩ መኖሪያዎች ለምን እኛ አገር አይኖሩም?

ሪፖርተር፡- ድሆችን መርዳት ቢቀድምስ የሚሉ አሉ፤

አቶ ሳሙኤል፡-
ስለድህነትና ድህነት እንዴት እንደሚያደርግ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በመረዳዳትም አምናለሁ፡፡ መተዛዘን እንደሚገባንም እረዳለሁ፡፡ አብዛኞች አዲሱን መኖሪያ ቤቴን ተመልክተው አብዛኛው ሕዝብ ደሀ በሆነባት አገር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ቤት መሥራት አግባብ እንዳልሆነ ይነግሩኛል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በፊልም የምናየውን ቤት ይመስላል፡፡ በውጪ አገር ቢሊየነሮች የሚያሰሩት ቤት ይመስላል የሚሉና ደስታቸውን የሚገልፁ አሉ፡፡ ሁልጊዜ ሁለት ዓይነት አስተያየት የሚጠበቅ ነው፡፡ ሼክ መሀመድ አላሙዲ ሸራተንን ፈር ቀዳጅ በአገራችን በመስህብነት ጉልበት ፈጥሯል፡፡ በዚህ ሁላችንም በማሠራታቸው ደስ ሊለን ይገባል፡፡ እንግዶቻችንን ወስደን እንጋብዛለን፡፡ እንዝናናለን፡፡ የሚዝናናበት ሕዝብ ነው፡፡ የአገርንም አቅም ከፍ ያደርጋል፡፡ ገና ለገና ድህነት ውስጥ ነን በማለት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ከማካሄድ ወደ ኋላ ማለት አይቻልም፡፡ ከፍተኛ ግንባታ መሥራትን በማቆም ድህነትን መቀነስ አይቻልም፡፡ አገራችንን ሁላችንም ባልችን ሀብትና ጉልበት ተባብረን ካልለወጥናት፣ ካልሰራንባት መቼ ትለወጣለች? መጪው ትውልድ መቀየር አለበት፡፡ ዛሬ ከሩስያና ከሕንድ ከፍተኛ የዓለማችን ቱጃሮች እየወጡ ነው፡፡ ብልጫውን እየያዙ ነው፡፡ እኛም መንግሥት ብቻውን አገር መለወጥ እንደማይችል ተገንዝበን አገራችንን ለመቀየር መጣር አለብን፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ደግሞ አገራችን ላይ ሰርተን ከአገራችን ያገኘነውን ሀብት አገራችን ውስጥ ማፍሰስ አለብን፡፡ ድህነትን መቀነስ፣ ማጥፋትና መርሳት የሚቻለው በዚህ መልኩ ብቻ ነው፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር በአስተሳሰብ መለወጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገራችን ባለሀብቶች ብራቸውን አገር ቤት ካላስቀመጡና አገራቸው ላይ ካላለሙ ችግር ነው እያሉ ነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
ዱባይ ያደገችው ዜጐቿ ያላቸውን ሀብት መሉ በሙሉ አገራቸው ላይ በማስቀመጣቸው ነው፡፡ እኛም ሀብታችንን እዚሁ በማስቀመጥ አገራችንን መቀየር አለብን፡፡ ይህንን ካላደረግንና አገራችን የሰጠችንን ሀብት ወደ ውጭ ይዘን የምንሄድ ከሆነ የትም አንደርስም፡፡ ፍርሀት አለ፡፡ ልንፈራ ግን አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- የምን ፍርሀት?

አቶ ሳሙኤል፡-
በደርግ ጊዜ የነበረው ሁኔታ የፈጠረው ፍርሀት፡፡ በደርግ ጊዜ ንብረቱን ሲነጠቅ፣ ሚስቱን ሲቀማ ፈሪ ሆኖ ቀረ፡፡ ያ ችግር ዛሬም ሙሉ በሙሉ የዳነ አይመስለኝም፡፡ ጠባሳው ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ቆንጆ መኪና፣ ቆንጆ ቤት፣ ቆንጆ ነገር ሲያዝ “አይን ውስጥ ትገባለህ” የሚባል ምክር ከየአቅጣጫው ይመጣል፡፡ እንዲህ ያለው ምክር ቀደም ብዬ የገለፅኩት ፍርሃት የፈጠረው ስሜት ነው፡፡ በግሌ አልቀበለውም፡፡ አየር ላይ የሚንጠለጠል ቤት መሥራት ከተቻለ እሰራለሁ፡፡ የምሠራው ግን አገሬ ላይ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አለ የሚሉት ፍርሃት እንዴት ማስወገድ ይቻላል?

አቶ ሳሙኤል፡-
አሁንም ፍርሃትን የሚፈጥሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ ግብር፣ ቀረጥ፣ ታክስ በአግባቡ አለመክፈል፡፡ በአቋራጭ ለመክበር ሕጋዊ መንገድን አለመጣስ፡፡ ሕግንና ሕግን ብቻ ተከትሎ አለመሥራት ካለ ያስፈራል፡፡ ሕግን ጠብቄ ከሠራሁ ምን ያስፈራኛል፡፡ ሕግን ጠብቆና አክብሮ በመሥራት ያገኙትን አገር ውስጥ ማስቀመጥ ከሀብት በላይ ልዩ ኩራት ይሰጣል፡፡ ጥለነውም ብንሄድ ለአገር ነው፡፡ አገር ውስጥ ሰርቶ በማግኘት አገር ውስጥ ማልማት ያኮራል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በውጪ አገር የመኖሪያ ቤት የለዎትም?    

አቶ ሳሙኤል፡-
የልጆቼ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ለምን አይሰሩትም?

አቶ ሳሙኤል፡-
በሚኖሩበት አገር ለራሳቸው መኖሪያ ሰርተዋል፡፡ እኔም ስሄድ አርፍበታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በውጪ አገር ባንኮች ገንዘብ አለዎት?

አቶ ሳሙኤል፡-
የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ የእርስዎ መኖሪያ ልዩ የሚያደርገው ምንድነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
ከሁሉም በላይ አጨራረሱና የማስዋቢያ እቃዎቹ ቤቱን ልዩ ያደረጉት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ለቤትዎ ማስዋቢያ የተጠቀሙበት የእቃ ዓይነት ልዩ እንደሆነ ይነገራል፤

አቶ ሳሙኤል፡-
እያንዳንዱ ክፍል ሰፊ ነው፡፡ ማስተር ቤድ ሩሙ 400 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ማስተር ቤድ ሩሙ ሳሎን፣ መኝታ፣ መታጠቢያ፣ መልበሻ ወዘተ. አለው፡፡ ሌላው ቤቱን ውድ የሚያደርገው የቪላው በር በቫቲካን አገር የቫቲካን ቤተክርስቲያን ላይ የተገጠመው የእንጨት በር በመገጠሙ ነው፡፡ እምነበረዱ የስፔን ነው፡፡ የመታጠቢያና የመፀዳጃ እቃዎቹ ከእምነበረድ የተሰሩ ናቸው፡፡ ፓርኬ (Parquet) የመሬት ጣውላው የመጣው ከአውስትራሊያ ነው፡፡ ዋጋው ውድ ነው፡፡ መብራቶቹ የመጡት ከቻይና በትዕዛዝ ነው፡፡ የራሱ መዋኛ አለው፡፡ የዋናውን ባሕር ተጠግቶ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ ቀለል ያለ ቪላ አለ፡፡ ይህንን ስል አስቀድሞ እንደተባለው ተጋኗል ሊባል ይችላል፡፡ ቤቱ ግን ለአገር ቅርስ ነው፡፡ ሌሎች ባለሀብቶችንም ይቀሰቅሳል፡፡ ሼክ መሀመድ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማካሄዳቸው ሌሎችን ያደፋፍራል፡፡ ኢንቨስትመንት ይስፋፋል፣ ሥራ ይፈጠራል፣ ሀገር ይለማል፡፡ ከዚህ አንፃር ቢታይ ጥሩ ነው፡፡ በተለይ በተለይ በተፈጠረው ሰላምና የመሥራት መብት ተጠቅመን እያሳየን ያለውን ለውጥ ለውጪው አገር ሕዝቦች ማሳየት ይገባናል፡፡ የቤቱን ዲዛይን ወስደው ሌሎችም ቢሰሩት ደስ ይለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ለህብረተሰቡ ሰራሁ የሚሉት የተለየ ነገር ምንድነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
ሆስፒታሎች፣ የጉድጓድ ውሀ ሰርተናል፡፡ አሁን ግን የተለየ ሥራ መሥራት ጀምረናል፡፡ አንድ ሰው ወይም ቤተሰቡ ተለይተው ወጥተው ሀብታም ቢሆኑና የራሳቸውን ኑሮ ብቻ ቢኖሩ ዋጋ የለውም፡፡ የሌላውን ሕዝብ ኑሮም መኖር ያስፈልጋል፡፡ አስቀድሜ መተዛዘን አለብን ያልኩት ለዚሁ ነው፡፡ በአንድ አገር ሁሉም ሰው ሀብታም ሊሆን አይችልም፡፡ ቢቻል ግን 80 - 90 በመቶ የሚሆነው መካከለኛ ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል መረባረብ አለበት፡፡ ከግል ስኬት በላይ አገራዊ ስኬት ከፍተኛ ኩራት ይሰጣል፡፡ አገር ተሳክቶላት ከማየት በላይ የሚያስደስት ምን አለ?

ሪፖርተር፡- የተለየ የጀመራችሁት ሥራ ምንድነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
ሰንሻይን ሕንፃ ከዛሬ 1ዐ ዓመት በፊት ተሰራ፡፡ እዳውን ከፍሎ ጨርሷል፡፡ በዓመት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኛል፡፡ ይህንን ብር ዝም ብለን ከምንሰበስብ ለምን አሳሳቢ በሆኑ ችግሮች ላይ አትኩረን አንሰራም በማለት ጠየቅን፡፡ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እናትና አባት የሞቱባቸው ህፃናት አሉ፡፡ እነዚህን ልጆች ማን ያሳድጋቸው? የሚለው የጊዜው አሳሳሰቢ ችግር በመሆኑ የበኩላችንን ለማድረግ ወሰንን፡፡ በአምስት ክፍሎች ለእያንዳዳቸው 5 ሚሊዮን ብር በማውጣት በየዓመቱ 400 ተማሪዎች የሚይዝ ትምህርት ቤት የመሥራት እቅዳችንን ባለፈው ዓመት የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት በተገኙበት በነቀምት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠን አሁን ግንባታውን ጀመርን፡፡ ለተማሪዎቹ በወር 150 ብር የኪስ ገንዘብ፣ ዩኒፎርም፣ የመማሪያ መሳሪያዎች የመምህራን ደመወዝና የሥራ ማስኬጃ እንመድባለን፡፡ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ጐበዝ ተማሪዎችን መርጠን ኮሌጅ እንዲማሩ የማድረግ፣ ከዚያም አልፎ የስኮላርሺፕ እድል የሚገኝበት መንገድ እንፈልጋለን፡፡ በቀጣዩ ዓመት አዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ክልል እንሰራለን፡፡ ወደፊትም ያሰብናቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳችን መረዳዳት አለብን፡፡ የውጪ አገር ዜጐችን እጅ መጠበቅ የለብንም፡፡ በራችንን ዘግተን ሌላውን አያሳየኝ ማለት ኑሮን መኖር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ካፒታልዎ ምን ያህል ነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
አንድ ቢሊዮን ይደርሳል፡፡ ይህ እንግዲህ ቋሚ ካፒታል መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የባንክ ብድር አለብዎ?

አቶ ሳሙኤል፡- አለብኝ፡፡ ከባንክ የማይበደር ኢንቨስተር የለም፡፡ ካለም ኢንቨስተር አይባልም፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛውን ጊዜ ባለሀብቶች ከባንክ የተበደሩትን የገንዘብ መጠን መግለፅ አይፈልጉም፡፡ ወይም ይፈራሉ፡፡ እርስዎስ?

አቶ ሳሙኤል፡-
ትክክለኛውን አሃዝ ከፋይናንስ ክፍል ጋር ተነጋግሬ መግለፅ እችላለሁ፡፡ ተበድሬያለሁ፡፡ በተበደርኩት ገንዘብ ሰርቻለሁ፡፡ በወቅቱ መክፈል የሚገባኝን እዳ እከፍላለሁ፡፡ እኔ ስከፍል ሌሎች ይበደራሉ፡፡ ተበድሮ አለመክፈል እንጂ የተበደሩትን መጠን መናገር አያስፈራም፡፡ በዓለም ላይ ያሉ የመጨረሻ ሀብታሞች ይበደራሉ፡፡ ሰሞኑን የቡታጅራ አገና የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በ637 ሚሊዮን ብር ወሰድን፡፡ ለ637 ሚሊዮን መንገድ ፕሮጀክት የ100 ሚሊዮን ብር ማሽኖች ያስፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ግዢ ከህብረት ባንክ ጋር ባደረግነው ስምምነት 60 ከመቶ ተከፈለልን፡፡ 40 ከመቶ ከድርጅታችን ወጪ ተደረገ፡፡ እኛ የምንበደረው በፕሮጀክት ነው፡፡ ብድሩም ተከፍሎ የሚያልቀው ፕሮጀክቱ ሲያልቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያለብዎትን የብድር መጠን አልነገሩኝም?

አቶ ሳሙኤል፡-
ትክክለኛ ቁጥሩን ለጊዜው ለመናገር ስለምቸገር እንጂ ለመደበቅ አይደለም፡፡ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ይሆናል፡፡ የአንድ ቢሊዮን ብር ቋሚ ካፒታል ያለው ድርጅት ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ብር ቢወስድ አነሰ እንጂ በዛ የሚል አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- ሊገነቡ ላሰቡትና እየገነቡ ላሉት ሆቴል የተለየ ስምምነት አለዎት?

አቶ ሳሙኤል፡-
ይህ ሆቴል ኢንዱስትሪ አይር (AYR) ከሚባል የአሜሪካ ኩባንያ ጋር የጋራ ኢንቨስትመንት (Joint Venture) ስምምነት በቅርቡ ተፈራርመናል፡፡ የሆቴሉ ተጨማሪ የህንፃ ግንባታ ሥራ በቀጣዮቹ ወራት ተጀምሮ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ ሆቴሉ ይፈጃል የተባለውን 850 ሚሊዮን ብር ከአይር ኩባንያ ጋር በመደራደር ብድር ለመውሰድ ተስማምተናል፡፡ እስከ 500 ሚሊዮን ብር ሊሰጡን ይችላሉ፡፡ ማደግና መሥራት የሚቻለው በባንክ ብድር ነው፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ግን ከባንክ የተወሰደውን ገንዘብ በሚያተርፍ ነገር ላይ አውሎ በአግባቡ መመለሱ ላይ ነው፡፡ ይህንን ያደረገ ሰው ማደግ ይችላል፡፡ ከቢሊኒየር አባት የተወለደ ከአባቱ ሀብት ተነስቶ ሀብታም ሊሆን ይችላል፡፡ እንደኔ ከምንም ነገር የተነሳ ደግሞ ከባንክ ብቻ ይበደራል፡፡ በባንክ ሰርቶ ይሻሻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በባንክ እዳ ከስረው የሚዘጉና ንብረታቸው የሚሸጥ በርካታ ድርጅቶች አሉ፡፡ የሰንሻይን የተለየ ተሞክሮ ምንድነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
የምንበደረው በፕሮጀክቶች ነው፡፡ የተበደርነውን ለተበደርንበት አገልግሎት ብቻ እናውላለን፡፡ ኩባንያዎች እቃ እንዲሰጡን ስንጠይቅ እንጠነቀቃለን፡፡ የምንወስደውን ብድር ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ፋይሉን ከእዳ ነፃ ብለን እንዘጋለን፡፡ የተለየ ተአምር አንሰራም፡፡ ማንም የተበደረውን በጊዜው ከከፈለ አበዳሪ አያጣም፡፡ ብድር የጀመርኩት በአስር ሺህ ብር ነበር፡፡ ጠዋት ተበደርኩ ከሰዓት በኋላ መለስኩ፡፡ የመክፈል ልምድ አለኝ፡፡ አንዳንዴ የሚገርሙ ቀልዶችን እሰማለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከባንክ ይበደሩና በዚያ ባንክ በኩል ማለፍ ያቆማሉ፡፡ የባንክ ስም ሲነሳ ይደነግጣሉ፡፡ ባንኩን ከመሸሽ ይልቅ ገንዘቡ ሳያልቅ የምክር አገልግሎት መጠየቅ ይጠቅማል፡፡ ሙሉ በሙሉ እዳ ውስጥ ከመነከር በፊት ምክር ቢጠየቅ ባንኮች ተጨማሪ ገንዘብ ሰጥተው ከውድቀትም ያነሳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰንሻይን ሕንፃ አጠገብ የተሰቀለው ትልቅ ፖስተር ላይ ያሉት ሕንፃዎች፣ መኖሪያ ቤቶችና ሆቴሎች በእርግጥም እንደማስታወቂያው እውን ይሆናሉ?

አቶ ሳሙኤል፡-
በእርግጠኛነት እውን ይሆናሉ፡፡ እኛ የማስታወቂያ ድርጅት አይደለንም፡፡ በተግባር ለማዋል ግን የመንግሥት እገዛ ያስፈልገናል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ አስተዳደር በየዕለቱ ሊረዳን ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በፕሮጀክቱ ተደስቶ ተግባር ላይ ግን ሊያግዘን አልቻለም፡፡ ከዋናው ቢሯችን በስተጀርባ ልንሠራ ላቀድናቸው ሕንፃዎች ከአካባቢው የሚነሱ ነዋሪዎች አሉ፡፡ ለእነሱ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አድርገን”.

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ የበኩሉን ያልተወጣው ለምንድነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
ከሰንሻይን ጀርባ እስከ ኖክ ቤንዚን ማደያ ለሚነሱት ነዋሪዎች ምትክ ቤት ለመሥራት 100 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ወስደናል፡፡ የመሬት ዝግጅቱን አጠናቅቀን የግንባታውን ሥራ እየጀመርን ነው፡፡ በቀበሌ ቤት ለሚኖሩ የጋራ መኖሪያ አፓርታማ፣ የራሳቸው ቤት ላላቸው የግል የመኖሪያ ቤት እንሰራለን፡፡ እስከ 300 ሚሊዮን ብር ወጪ እናወጣለን፡፡ ነዋሪዎቹ የሚነሱት ምትክ ቤቱን ካገኙ በኋላ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ ከተነሱ በኋላ ዘመናዊ ሕንፃዎችን መሥራት እንፈልጋለን፡፡ 3.5 ቢሊዮን የሚፈጅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በውጪ አገር እንዳሉት ዓይነት ዴሉክስ አፓርትመንቶች ናቸው፡፡ ቦታው ከተማ መሀል በመሆኑ የሚሰሩት ሕንፃዎች ለከተማ ውበት ይሆናሉ፡፡ ለአገራችን፣ ለከተማዋ እንዲሁም ለድርጅታችን የሚያስገኙት ጥቅምና ገቢም ቀላል አይደለም፡፡ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት ሰርተን ቦታውን እንድንረከብ ያቀረብነው ጥያቄ ግን ከአስተዳደሩ መልስ አላገኘም፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢሲኤ በስተጀርባ ገደሉ ውስጥና ገደሉ ጠርዝ ላይ ያለውን ቦታም የመውሰድ እቅድ አላችሁ ይባላል፤

አቶ ሳሙኤል፡-
በኢሲኤ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የተቀመጡ ወደታች ሲመለከቱ የሚያዩት ያረጀ ቆርቆሮ ነው፡፡ እነዚያን ቤቶች መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ካዛንቺስ ኢሲኤ ፊት ለፊት የተሰሩት ሕንፃዎች እየፈጠሩ ያለው ውበት ልዩ ነው፡፡ በዚህም በኩል ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ እስከ ድልድዩ ድረስ ህንፃዎች ብናቆም እኛም እንጠቀማለን፡፡ እዚያ ላይ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለመሥራት አስበናል፡፡ ኮርድ ሆርድ የሚባል ማሪዮት ሆቴል ለመሥራት አስበናል፡፡ ዲዛይኑን ሰርተን አቅርበናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለተሻለ ልማት የሚጠየቁ ቦታዎች ላይ የሚነሱ ነዋሪዎች ማኅበራዊ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ይናገራሉ፡፡ በዚህ በኩል ምን አስባችኋል?

አቶ ሳሙኤል፡-
ችግር አለ ተብሎ ከተማ እንዳረጃ ይኑር አይባልም፡፡ ለተነሺዎች የሚሰሩት ቤቶች በአንድ መንደር ላይ ናቸው፡፡ እድሩም፣ እቁቡም አብሮ ነው የሚሄደው፡፡ እኔ ጨርቆስ ነበርኩ፡፡ ዛሬ ቦሌ ገብቻለሁ፡፡ እስጢፋኖስ አካባቢ ያሉ ሰዎች ወደ ሲኤምሲ ቢሄዱ ምን ችግር አለው? በአሜሪካ አሮጌ ሕንፃ እየፈረሰ ወደ አዲስ ይቀየራል፡፡ የነዋሪዎችም የኑሮ ደረጃ የሚሻሻል ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የሠራተኛ ቁጥር ለማሳደግ የያዛችሁት እቅድ አለ፡፡ ባልተጋነነ መልኩ ተግባር ላይ የሚውልበትን ጊዜ ገልፀው ሊነግሩኝ ይችላሉ?

አቶ ሳሙኤል፡-
በያዝነው ዓመት የሠራተኞች ቁጥር ከ6 ሺህ ወደ 11 ሺህ ይደርሳል የሚል እቅድ አለን፡፡ ትልልቅ የምንላቸውን ግንባታዎች ስንጀምር በቀጣዩ ሦስት ዓመት ውስጥ እስከ 50 ሺህ ሠራተኞች ይኖሩናል ብለን አቅደናል፡፡ ይህ እቅድ በተግባር የሚቀየር ይሆናል፡፡ በአገሪቱ እየታየ ያለው የኮንስትራክሽን አካሄድ ሠራተኛ  ከውጪ አገር አስመጥቶ እስከመቅጠር የሚያደርስ ይመስለኛል፡፡ የቀን ሠራተኛ እያጣን ነው፡፡ ወደፊት ይበልጥ የሥራ እድል ይፈጠራል፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ እያጓጓዝን የምናሰራበት ሁኔታ አለ፡፡ የባለሙያ ችግርም ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞ ሰፈርዎ ጨርቆስ ይሄዳሉ?

አቶ ሳሙኤል፡-
መሠረቱን የሚረሳ አለ? የተወለድኩበትን፣ ያደግኩበትን፣ የጨርቅ ኳስ የተጫወትኩበትን ክፉና በጐውን ያየሁበትን ሰፈር እንዴት እረሳዋለሁ፡፡ ሄጄ አየዋለሁ፡፡ የቂርቆስ ገበያ ከመቃጠሉ በፊት ትዝታ አለኝ፡፡ አንድ መቶ ብር አበድሮኝ ሲጃራና ማስቲካ ያስነግደኝ የነበረ ሰው አለ፡፡ ሱቁ ተቃጠለ፡፡ አንድ የሚያረካኝ ነገር ቢኖር ሱቁ አዲስ የገበያ ማዕከል ሆኖ ሲሰራ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ አድርጌ፣ ሰርቼ አስረክባለሁ ብዬ ቃል ገባሁ፡፡ ዛሬ እዚህ ደረጃ ደረሰ፤ ሳየው ደስ ይለኛል፡፡

    ከዚህ ውጪ ግን ኑሮዬ ቢቀየርም በየትኛውም ተራ ሻይ ቤት ገብቼ የምጋበዝ፣ ፊልድ ስወጣ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ የምተኛና ያገኘሁትን የምመገብ ነኝ፡፡ የስኬት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በሳሙኤልነቴ ለውጥ የለኝም፡፡ ድሮም አሁንም ሳሙኤል ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የመኖሪያ ቤትዎን ሲያስመርቁ የተኮሱት ርችት አስደንግጦ ነበር . . .

አቶ ሳሙኤል፡-
ርችት ሲተኮስ የአገሪቱን ሕግና ደንብ መከበር አለበት፡፡ ቤቴን ሳስመርቅ አንድ ወዳጄ መጋዘኑ ውስጥ ስለነበረው፣ ለደስታው ስጦታ አቀረበ፡፡ ለደህንነት የፈንጂና የርችት ዲፓርትመንት ርችቱን መርምሮ የትክክለኛነት ማረጋገጫ ሰጠን፡፡ ለአዲስ አበባ ፖሊስ የምንተኩስበትን ሰዓት ገልፀን ጥበቃ እንዲደረግልን ላቀረብነው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ አግኝተናል፡፡ እኔ ራሴ በአካል ተገኝቼ ነው ያስፈቀድኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ነዋሪዎች ማወቅ የለባቸውም?

አቶ ሳሙኤል፡-
እኛ ስለህጋዊነት መጨነቁን እንጂ ሌላውን አላሰብንም፡፡ የደስታ ጊዜዬ ነው፡፡ ልጄን ድሬያለሁ፡፡ አዲስ ቤት አስመርቄያለሁ፡፡ የርችት ስጦታ መጣልኝ፡፡ አስፈቀድኩ፡፡ በሰብአዊ ጉዳዮች ገብቼ እርዳታ እንደማደርግ ሁሉ ብዝናና ምን ነውር አለው ብዬ ነው፡፡ ሕዝቡ አስቀድሞ ቢያውቅ ጥሩ ነበር፡፡ ይህ የፈቃጁ ክፍል ሥራ እንጂ እኛን የሚመለከት አይደለም፡፡ በሌላ ጊዜ ርችት ሲተኮስ የሚከታተሉት አሠራር እንዳላቸው ነው የምናስበው፡፡ ችግሩ የታየው ርችቱ ከተተኮሰ በኋላ ነው፡፡ በእለቱ ከመደሰቴ የተነሳ ያዘዝኩት ሄሊኮኘተር ገብታ ቢሆን ኖሮ ሙሽሮቹን በገመድ ከአየር ላይ አወርዳቸው ነበር፡፡ ርችት ሲተኮስ ስመለከት ደስ ይለኛል፡፡ ለበዓልና ለአዲስ ዓመት ርችት ሲተኮስ ሰዓቱን ነው የምጠብቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ከድርጊቱ የተማሩት ትምህርት የለም?

አቶ ሳሙኤል፡-
ነገ ሌላውም ቤት በሰራ ቁጥር ርችት ሊተኩስ ይችላል፡፡ ግን ነዋሪዎች አስቀድመው የሚያውቁበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ሄሊኮኘተሯ ትመጣለች እየተባለ ግን ቀረች፤

አቶ ሳሙኤል፡-
ፈቃድ ጠይቀን እየጨርስን ነው፡፡ አልቀረችም ትመጣለች፡፡

ሪፖርተር፡- ዋጋዋ ስንት ነው? በተለይ ለምን ጉዳይ ነው የታሰበችው?

አቶ ሳሙኤል፡-
ለመንገድ ሥራ ኘሮጀክት፣ ለሆቴል ሥራና ለንግድ ነው የታሰበችው፡፡ ተጨማሪም የመግዛት እቅድ አለን፡፡ ዋጋዋ 2.5 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጀመራችኋቸው የሪል ስቴት ኘሮጀክቶች ውል የተዋዋላችሁት ቀደም ብላችሁ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታ ውል የማቋረጥ፣ ገንዘብ የመጨመር፣ የመሳሰሉ ችግሮች አሉ፡፡ እናንተ ገንዘብ ትጨምራላችሁ ወይም ውል ታቋርጣላችሁ? ወጪያችሁ በጨመረ ቁጥር ከዓመት ወይም ከዚያ በፊት የነበረው ውላችሁን እንዴት ነው የምትተገብሩት?

አቶ ሳሙኤል፡-
ነገሩ እንደ ቢዝነስ ጥሩ ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን እዚህ አገር ላይ የሪል ስቴት ግንባታዎች በሰፊው ተጀምረዋል፡፡ መንግሥት በሪል ስቴት ግንባታ ላይ ብዙ ኢንቨስተሮች እንዲገቡ ሲፈቅድ ይህን ያህል ገበያ ይኖራል ብለን አልገመትንም፡፡ ይህን ያህል ገበያ አልጠበቅንም፡፡ ይህንን ሰው ወደ ገበያ ለመሳብ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን አሰብን፡፡ ዋጋ ቢጨምር አንጨምርም ብለን ቃል እንግባና ግንባታውን እንጀምር አልን፡፡ የድርጅታችንን ስም ብዙ ሰው ይወደው ስለነበር ግንባታውን ስንጀምር ገዢው በአንድ ጊዜ ተጥለቅልቆ ውሉን ፈርመን ጨረስን፡፡ እኛም እስከአሁን የጀመርናቸው ቤቶች ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ አላደረግንም፡፡ አንድም የውል ማቋረጥ አላደረግንም፡፡ ለምሳሌ ያህል የመጨረሻውን የመጀመሪያዎቹ ተብለው ከ1-9 ብሎኮች የምንላቸውን ወደ 160 ቪላዎች፣ 16 አፓርታማዎች ሚያዚያ 23 አጠናቀን ለሕዝቡ እንሰጣለን ብለን በእቅድም መቶ በመቶ እንደሚሳካ በኘሮግራም ይዘናል፡፡ በፋሲካ ማግስት በዳግማዊ ትንሳኤ እናስረክባለን ብለን ኘሮግራም ይዘናል፡፡ በዚያ ጊዜ የጀመርናቸው ቤቶች ላይ ቋምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪም ሆነ የውል ማቋረጥ አላደረግንም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለሰራናቸው ቤቶች የዋጋ ለውጥ ቢመጣ ትጨምራላችሁ ብለን በውሉ ውስጥ አካትተናል፡፡ የመጀመሪያዎቹን ግን ገበያው እንዲህ ይለዋወጣል ብለን አልገመትንም፡፡ ሁለት ሺህ ተመዝጋቢ በተጠባባቂነት አለን፡፡ ያወጣናቸው ቤቶች ላይ አንድ ቤት አለ ከተባለ ወዲያው ሸጠን እንጨርሳለን፡፡

ሪፖርተር፡- የለገጣፎ ኘሮጀክትስ እንዴት ነው?

አቶ ሳሙኤል፡-
የለገጣፎ ኘሮጀክት ገና በሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ በኘሮጀክቱ ለየት ያለ ኢንቨስትመንት ነው መሥራት የምንፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ካሬ ሜትር ነው የጠየቃችሁት?

አቶ ሳሙኤል፡-
አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ካሬ ሜትር በላይ ነው፡፡ ግን ትክክለኛው መጠን ገና እየተለካ ነው እንጂ አልተረከብንም፡፡ እዚያ ላይ ትልቅ የቢአይፒ መንደር የሚባል የሪል ስቴት ግንባታ ወደ 550 ሺህ ካሬ ሜትር የሚገመት ቦታ ላይ የጐልፍ መጫወቻ፣ ይህን ጐልፍ መጫወቻ ያስፈለገው እዚህ አገር ያሉ የውጭ ሰዎች የሚዝናኑበት ቦታ የለም፡፡ ይህችን አገር እንዲወዱ ደግሞ ብዙ የመዝናኛ ቦታ ማዘጋጀት ከባለሀብቱ ይጠበቃል እና እዚያ ላይ ትልቅ የጐልፍ መንደርና አንድ ዘመናዊ ሆቴል የመስራት እቅድ ይዘናል፡፡ ለመንግሥት አመልክተናል፡፡ ለውጭ ሀገር ዜጐች ብቻ የሚሆን ልዩ መንደር ለመሥራት ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ በዕቅድም ይዘናል፡፡ ከመንግሥት ግን ፈቃድ አላገኘንም፡፡ ጥያቄው በመንግሥት ደረጃ ውሳኔ አላገኘም፡፡ መንግሥት ፈቃድ ባይሰጥ እንኳ እኛ ኢንቨስተሮች የመንግሥትን ሃሳብ ማስለወጥ አለብን፡፡ ለዚህም ማመልከቻ አስገብተናል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማግኘት እየሞከርን ነው፡፡ በግብፅ ለውጭ ሀገር ዜጐች ብቻ የሚሆን የመዝናኛ ቦታ አለ፡፡ እኛ ሀገር ያሉ የውጭ ዜጐች ሀገራችንን ይወዳሉ፣ ሕዝቡን ይወዳሉ፣ በሁሉም ነገር ደስተኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ቅር የሚላቸው ነገር ብዙ መዝናኛ አለመኖሩ ነው፡፡ ይህንንም ችግር መቅረፍ ያለበት መንግሥት ብቻ አይደለም፣ አገር ውስጥ ያለው ባለሀብትም ይመለከተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የጐልፍ መጫወቻ፣ የተለየ ሆቴል እና ተጨማሪ መዝናኛ ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይህንንም ሆነ ሌሎች ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሥራት 10.4 ቢሊዮን ገደማ በጀት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይህም አጠቃላይ በሆነ ስሌት ነው፡፡
 
< Prev   Next >