Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራዮች...
የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራዮች... E-mail
Sunday, 03 February 2008
የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራዮች በውኃ ዋጋ ላይ ቅሬታ አቀረቡ

የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በሚያስተዳድራቸው አፓርታማዎች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ነዋሪዎች ለውሃ ፍጆታ በግለሰብ ደረጃ በየወሩ እስከ 30 ብር ይከፍሉ የነበሩትን የዋጋ ተመን በአሁኑ ወቅት ወደ 875 ብር ከፍ በማለቱ ለችግር መዳረጋቸውን አስታወቁ፡፡ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ በበኩላቸው ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት አስፈላጊው እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ መሆኑን ገለፁ፡፡
ነዋሪዎቹ “የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የሚፈጽመውን በደል መንግስት ያውቅ ይሆን?” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ እንዳመለከቱት እያንዳንዱ ነዋሪ የውሃ ኪራይ የሚከፍለው ከቤቱ ኪራይ ጋር በቋሚነት ነበር፡፡ ይህም እንደ መኝታ ቤቶች ብዛት ወይም እንደ ቤቱ ስፋት ሲሆን ዝቅተኛው አሥር ብር ከፍተኛው ደግሞ 30 ብር ነበር፡፡

በመካከሉ ኤጀንሲው “ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች ከነዋሪው የሚሰበሰበው የውሃ ክፍያ መጠን ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በኪሳራ ስሸፍን ነበር” በሚል ሰበብ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ይህንን ማድረግ ስለማይችል ነዋሪዎች ኮሚቴ አቋቁመው የውሃ ፍጆታ ሂሳባቸውን በጋራ እንዲከፍሉ መመሪያ መሰጠቱን አውስተዋል፡፡

የኮሚቴውን አሠራር ወደ ጎን ትቶ የመጣውን የውሃ ሂሳብ ኤጀንሲው ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግስታዊ አካል፣ ነዋሪው ደግሞ ለኤጀንሲው እንዲከፍል ማድረጉን ጽሁፉ አመልክቶ በዚህ አይነት የክፍያ ዘዴ አንድ ነዋሪ ብቻ ለኤጀንሲው እስከ 875 ብር እንዲከፍል መጠየቁን አስረድተዋል፡፡

ነዋሪዎች የቤቱን ኪራይ ለመክፈል ሲሄዱ የውሃ ካላመጣችሁ የቤቱን ኪራይ አንቀበልም፣ እንዲሁም የቤቱን ኪራይ ሳትከፍሉ እስከ ሦስት ወር ካለፋችሁ ደግሞ ኤጀንሲው ውል ያቋርጣል መባላቸውን አብራርተዋል፡፡

ነዋሪውም ስብሰባ አድርገው በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያዩ በኋላ የውሃ ቆጣሪ ለየብቻ እንዲሆን የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው፣ አሁን የመጣውም ሂሳብ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ቆጣሪው ተመርምሮ ችግር ካለበት እንዲስተካከል መጠየቃቸውን ጽሁፉ ጠቁሞ ይህም ጥያቄያቸው ለኤጀንሲው ቀርቦ “የመጣውን ሂሳብ ባትከፍሉ ውል የምናቋርጥ መሆኑን እንገልፃለን” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

አቶ ካሳሁን ወልደጊዮርጊስ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ ኤጀንሲው በእያንዳንዱ ሕንፃ የውሃ ቆጣሪ ለማስገባት የሚያስችለውን ጥናት ማጠናቀቁንና ምን ያህል ወጪ እንደሚያስፈልግም መታወቁን ይፉ አድርገዋል፡፡

ስለአፈፃፀሙም ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር መመካከሩን ኃላፊው አመልክተው፣ የባለስልጣኑም መሥሪያ ቤት የበኩሉን ሥራ በፍጥነት እንደሚያከናውንና ሥራውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት ላይ እንዲውል ለማድረግ ተገቢውን ክትትል እያካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
< Prev   Next >