| አርሶ አደሮች ተጨማሪ እሴት ወደጨመሩ... |
|
| Sunday, 06 January 2008 | |
|
አርሶ አደሮች ተጨማሪ እሴት ወደጨመሩ የልማት ሥራዎች እንዲሸጋገሩ የተሻለ አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች ተጨማሪ እሴት ወደሚጨምሩ የልማት ሥራዎች እንዲሸጋገሩ ለማስቻል በመሰረተ ልማት ግንባታ የመንግሥትና የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረውን የአርሶ አደሮች ፌስቲቫል በማስመልከት በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴርየማስታወቂያና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ታረቀኝ ጠጄ ትናንት ማክሰኞ ታህሳስ 22 ቀን 2000 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የተሻለ ካፒታል እያስመዘገቡ ያሉ አርሶ አደሮች ለላቀ ልማትና ተጨማሪ እሴት ወደሚጨምሩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲሸጋገሩ ለማስቻል የመንግሥትና የሕብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረው አርሶ አደሮች ፌስቲቫል በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ክልል ዋና ከተማ በሆነችው በሐዋሳ ከጥር 3 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በተለያዩ ፕሮግራሞች የሚከበር መሆኑም ተገል..ል፡፡ በበዓሉ አርሶ አደሮች፣ ባለሙያዎች፣ የአስተዳደር አካላት፣ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተሸላሚ ሲሆኑ በዚህ ዓመት በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች ያሉ ከፊል አርሶ አደሮች፣ ሞዴል ቀበሌዎች ተሸላሚ እንደሚሆኑ አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል፡፡ አርሶ አደሩ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሮ ወጥቶ ወደ ገበያ ተኮር ዘመናዊ ግብርና እንዲሸጋገር ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ታረቀኝ፣ በአገራችን ያለውን የዋጋ ንረት በተለይ በምግብ እህሎች እየጨመረ ባለበት ወደ ገበያ ምርቶች ማተኮሩ ችግሩን አያባብሰውም ወይ ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ፣ የምርት እጥረት አለ ተብሎ ለወደፊት ውጤት የሚሰጡን የገበያ ምርቶች መቀነስ አግባብ አለመሆኑን አርሶ አደሩ ከሰብል ምርት ጎን ለጎን ትኩረት ሰጥቶ የገበያ ምርቶችን ማምረቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በሚደረገው ሂደት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎች በገበያ እየተመራ ማምረቱ በሰብል ምርቶች ላይ ያለውን ትኩረት እንደማይቀንስ፣ አሁን ያለው ምርታማነት በሰብል እህሎች ላይ በመጨመሩ በዋጋው ላይ መሻሻል እንደሚኖር አመልክተዋል፡፡ ሽልማቱ የተሻለ ሥራ እየሰሩ ያሉ አርሶ አደሮችን ለማበረታታት ሲረዳ ተሸላሚዎች ለሌሎች አርአያ በመሆን የውድድር መንፈስ ለመፍጠር እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ እንደ አቶ ታረቀኝ ገለፃ፣ በበዓሉ ሁሉም ክልሎች ተሳታፊ የሚሆኑበት ኤግዚቢሽን ይኖረዋል፡፡ በግብርና ልማት የተገኙ መልካም ልምዶች ወደ ሌሎች አካባቢዎችና አርሶ አደሮች ለማስፋፋት በሚያስችሉ ሂደቶች ላይ በተመረጡ ርዕሶች በምርትና ምርታማነት፣ በጥቁር አፈር፣ በምግብ ዋስትና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በተጨማሪ እሴት ዙሪያ የፓናል ውይይት ይካሄዳል፡፡ እስከ 4 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 525 አርሶ አደሮች፣ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጡ 90 የግብርና ባለሙያዎች፣ በድርቅ አካባቢ የሚገኙ ሆነው ሰባ በመቶ የሚሆነው አካባቢ በምግብ እህል ራሳቸውን እንዲችሉ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡና በትርፍ አምራች አካባቢዎች በሀገር ውስጥና በዓለም ገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ምርቶች በማምረት 50 በመቶ የሚሆነውን ምርቶቻቸውን ለገበያ ያቀረቡ 20 ሞዴል ቀበሌዎች ይሸለማሉ፡፡ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡ 15 ባለሀብቶች 30 የወረዳና የቀበሌ አመራሮች፣ 10 የብዙሃን ማህበራት፣ 20 ግብዓቶችንና ሸቀጣ ሸቀጦች በማቅረብ ገበያ በማፈላለግ የተሰማሩ የሕብረት ሥራ ማህበራት፣ 2 የብድርና ቁጠባ ተቋማት በጠቅላላ 670 ሽልማቶች ይሰጣሉ፡፡ ከተሸላሚዎቹ 30 የሚሆኑ ሴት አርሶ አደሮች ሲሆኑ ከትግራይ ከተላኩት 35 አርሶ አደሮች 612 ሺህ ብር ያስመዘገበችው ሴት አርሶ አደር መሆኗም ተመልክቷል፡፡ አርሶ አደሮችን ለመምረጥ ሁለት ወራት የፈጀ ሲሆን አርሶ አደሮቹ ባስመዘገቡት ካፒታል ብቻ ሳይሆን ያላቸው የተሻለ ተሞክሮና ውጤታማነት የታየ ሲሆን ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታልና 2 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ያላቸው አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ፡፡ የተገኘውን ውጤት ቀጣይ እንዲሆን አርሶ አደሩ ጉልበቱን፣ መሬቱንና መስኖን በስፋት መጠቀም፣ የሚቀርበውን ምርጥ ዘር ማዳበሪያና ቴክኖሎጂ በባለሙያዎች እገዛ መሥራት እንዳለበት፣ የግብርናና የእርሻ ምርምር ባለሙያዎች፣ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራት፣ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አቶ ታረቀኝ አመልክተዋል፡፡ በቤዛዊት ሥዩም
|
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |