Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow አብዛኞቹ ዛፎች ሕልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል
አብዛኞቹ ዛፎች ሕልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል E-mail
Sunday, 03 February 2008
ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ከ800 ያላነሱ የዛፍ ዝርያዎችና ዛፍ ያልሆኑ ተክሎች አሏት፡፡ እነዚህ የዛፍ ዝርያዎች ሰፊ ጠቀሜታ ያላቸው የእንጨት ውጤቶችንና የአካባቢ ጥበቃ አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡ አብዛኞቹ ዛፎች ጥቅማቸውና የአጠቃቀም ዘዴያቸው ሳይታወቅ እንዲሁም ተመዝግበው ሳይቀመጡ ሕልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ አንዳንዶቹ ጨርሰው ከምድረ ገጽም የጠፉበት ሁኔታ እየተከሰተ መሆኑን ዶክተር ዓለሙ ገዛኸኝ በግብርና ምርምር ድርጅት የደን ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
ለዚህ ጥፋት ምክንያት አንዱ ኅብረተሰቡ እንጨቶችን የሚያውቃቸው በልምድ በመሆኑ እንጨቶቹ ማገዶ ከመሆን ሌላ ጥራት ያለው የጣውላና ቪኒየር ምንጭ መሆናቸውን አለመገንዘብ ነው፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ጥቁር እንጨት፣ ዋንዛ፣ ኮሶ፣ ቀረሮ፣ ጽድና ዝግባ ያሉ ዛፎች እየተቆረጡ በመመናመን ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ምክንያት እነዚህን ዛፎች የሚተኩ በአብዛኛው ወይም ጨርሰው የማይታወቁ ሌሎች ዛፎችን ባህሪያቸውንና ጥቅማቸውን በደን ባለሙያዎች እና ተጠቃሚዎች ዘንድ የበለጠ እንዲታወቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ዓለሙ አመልክተው ምንም እንኳ በአገር ዛፎች ላይ ባህሪያቸውን ለማወቅ በተደረገው ጥናት የተገኙ መረጃዎች በሥርዓቱ ተጠናቅረው በሕትመት የበቁ ባይሆንም ጥናቱ ግን እስካሁን መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በ35 የዛፍ ዝርያዎች ላይ አስፈላጊው ጥናት ተካሂዶ አጥጋቢ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ከእነዚህም ዛፎች ውስጥ ስምንቱ ለቪኒየር ምርት የሚመቹ መሆናቸው በጥናት ተለይቶ ታውቋል፡፡ ቪኒየር ስስ የሆነ ከግንድ ላይ እየተላጠ የሚወጣ የምርት ውጤት ነው፡፡

አገልግሎቱም ለኮምፔንሳቶ ሥራ እንደ ሬዲዮና ጠረጴዛ የመሳሰሉትን ውጫዊ አካላቸውን ለማስዋብ እንዲሁም ገበያ ላይ ቀርቦ ገቢ ማስገኘት የሚችል እንጨት ነው፡፡
ከቋር፣ ከመሰንጠቅና ከመበስበስ የፀዱና ጠንካራ ዝርያዎችን ያካተቱ እነዚህ ስምንት የዛፍ ዝርያዎች የሚገኙትም በጅማ - ምበቃ፣ በበቾ ጢሮ - ቦተረ፣ ሲዳማ - ጀምጀም፣ አርሲ - ደጋጋ፣ ሸዋ - ጅባት፣ ጊምቢ - ምበቃና በሚባሉት ሥፍራዎች ነው፡፡

ዶክተር ዓለሙ እንዳብራሩት ዛፎች በተፈጥሮ ይዘውት የመጡት ሁለት ዓይነት ባህሪያት አሏቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው አርቶደክስ ዘሮች (ሲድሶ) ሲሆን እነዚህም ዘራቸው በቀላሉ የማይሰበር፣ የመብቀል ኃይላቸውን ሳያጡ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩና ፍሬ ያላቸው የዛፍ አይነቶች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ሪኮንልትራንት ዘሮች (ሲድስ) ሲሆኑ የመብቀል ኃይላቸውን በአጭር ጊዜ የሚያጡ ናቸው፡፡

የግራር ዛፍ ዘር ሽፋኑ በጣም ጠንካራ ስለሆነ ቶሎ አይበቅልም፡፡ ስለሆነም ዘሩ በፈላ ውሃ ተዘፍዝፎ ለ24 ሰዓት ከተቀመጠ በኋላ ከተዘራ 90 በመቶ ያህሉ ይበቅላል ወይም ይፀድቃል፡፡ የሀበሻ ጽድና ወይራ ለተከላ እስከሚደርስ ድረስ በችግኝ ጣቢያ ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት ይኖርበታል፡፡ ቁመቱ ለተከላ ሳይደርስ ከወዲሁ ቢተከል ውጭ ያለውን ሁኔታ ሊቋቋም ባለመቻሉ ይሞታል፡፡

እንጨት ያልሆኑ የደን ውጤቶች በሚባል ከሚታወቁትም ምርቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ እጣን፣ የተፈጥሮ ሙጫ፣ ከርቤ እና አበከድ መሆናቸውንና እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው በአገሪቱ ደረቅና ቆላማ አካባቢዎች ከሚበቅሉ የተለያዩ የዛፍ አይነቶች ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

እጣንና ሙጫን ማምረትና መጠቀም በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የሚታወቅ ሲሆን ምርቶቹም ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ አገራችን ከዕጣን፣ ከተፈጥሮ ሙጫና ከመሳሰሉት ምርቶች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ገበያ በአማካይ በዓመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ታገኛለች፡፡

በአገሪቱ ሰባት አይነት የዕጣን ዛፎች አሉ፡፡ እስካሁን ግን ከፍተኛ ምርት እየሰጠ ያለው “በሶሊያፓንሪፈራ” የተባለው አንድ ዛፍ ብቻ ነው፡፡ በአብዛኛው የሚገኘውም በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ነው፡፡ በሶማሊያ ክልል ዕጣን መስጠት የሚችል የዛፍ አይነት አለ፡፡ ኅብረተሰቡ ሥራዬ ብሎ ዕጣኑን የሚሰበስበው ከዛፍ ላይ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያት መሬት ላይ የወደቀውን በመልቀም ነው፡፡

የዕጣን ዛፍ ብዙ ራሱን እየተካ አይደለም፡፡ እስካሁን እየተጠቀምን ያለነው በተፈጥሮ ከለማው ዛፍ ነው፡፡ የዕጣን ዛፍ የሚበቅልበት አካባቢ በጣም አስቸጋሪና ድንጋይ በበዛበት ሥፍራ ላይ ነው፡፡

ዶክተር ዓለሙ እንደገለፁት በመላ አገሪቱ ባሉ አንዳንድ ሥፍራዎች ውስጥ የሚገኘውን የፈረንጅ ጥድ የሚያጠቃ በሽታ ለመከላከል የሚያስችል ተባይ ተባዝቶ በ6ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ለሙከራ ተለቅቋል፡፡ ከኬንያ የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የተገኘውና ሳይፕረስ አፒድ (Cypress Aphid) ተብሎ የሚጠራው ይኸው ተባይ ተባዝቶ የተሰራጨው ሙኒስ ሻሸመኔ የደን ልማትና አጠቃቀም ኢንተር ፕራይዝ የፈረንጅ ጥድ በተተከለበት ቦታ ላይ ነው፡፡

ይህ አይነቱ የተፈጥሮ መቆጣጠሪያ ዘዴ ጥሩ ውጤት ካሳየ የፈረንጅ ጥድ ዛፍ በተተከሉባቸው ልዩ ልዩ ቦታዎች ሁሉ ተባዩን ለመልቀቅ መታቀዱን ዶክተር ዓለሙ ጠቁመው ለዚህም እውን መሆን ካለፉት ሦስት ሳምንታት ጀምሮ ተባዩን የማባዛት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ዘዴ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ማላዊ ላይ እ.ኤ.አ በ1980 ተካሂዶ አጥጋቢ ውጤት መገኘቱን፤ በደን ውስጥ የሚከሰተውን በሽታ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ ለማጥፋት ሲባል ኬሚካል መርጨት በጣም ውድና ሥራውም አስቸጋሪ መሆኑን ከዶክተር ዓለሙ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በታደሰ ገብረማርያም
 
< Prev   Next >