| የትምህርት ጥራት ጉድለት መንስዔው ምንድነው? |
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
![]() አቶ ሀጎስ ኃይሌ የባዮ ሜዲካል ቴክኖሎጂ ትምህርት የተጀመረው በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ወደ 58 የሚጠጉ ተማሪዎች ትምህርቱን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡ የራዲዮ ግራፊና አንቴሲንዚያ ትምህርቶች በዲፕሎማ ደረጃ ለመስጠት የታሰበው በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በሚገኘው የነርሲንግ ኮሌጅ ውስጥ መሆኑን ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አሁን በመሰጠት ላይ ያለውና በቅርቡም የሚሰጡት ትምህርቶች የሦስት ዓመት ፕሮግራም መሆናቸውን አቶ ሀጎስ አመልክተው፣ ለመማር ማስተማሩ ሥራ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ አይነት የሕክምና መሳሪያዎች ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር እየተገዙ በመቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እነዚህን የትምህርት መስኮች በመተባበር የከፈቱት የትምህርትና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ትምህርትና ጤና ቢሮዎችም ተሳትፈውበታል፡፡ አቶ ሀጎስ እንዳብራሩት አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከ110 በላይ የሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጆች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ከ80 በላይ የሚሆኑት በግሉ ዘርፍ የታቀፉ ናቸው፡፡ ኮሌጆቹ የሚያስመርቋቸውን ተማሪዎች ዲፕሎማ ከሰጡ በኋላ ብቁ (ስኪልድ) መሆን አለመሆናቸው ይፈተናሉ፡፡ ፈተናውን ለጊዜው የሚሰጠው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሲሆን ወደፊት ግን የሚፈትነው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ይሆናል፡፡ በዚህም የተነሳ ቢሮው በቅርቡ በአካውንቲንግ፣ በኢንሹራንስ፣ በሴክሬታሪያልና በባንኪንግ ትምህርቶች ላይ በግንቦት ወር ደግሞ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ”፣ ከዚያም በኋላ በቢዝነስ ትምህርቶች ላይ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ይሰጣል፡፡ ፈታኞቹም አሁን በማስተማር ላይ የሚገኙት መምህራን ሳይሆኑ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ተቋማት ውስጥ ችሎታና ብቃት ያላቸው ሙያተኞች ይሆናሉ፡፡ ፈተናውም በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ይሆናል፡፡ ፈተናውንም ካለፈ ብቃት ችሎታ ያለው ያላት አካውንታት የሚል ማዕረግ ይሰጣል፡፡ ኮሌጆች ለተማሪዎቻቸው የሚሰጡት ዲፕሎማ ትምህርቱን ተከታትሎ ማጠናቀቁን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ፈተና ተማሪው ከያዘው ዲፕሎማ ሌላ የሙያ ብቃትና ችሎታ አለው የሚል ማረጋገጫ የሚያሰጥ ነው፡፡ ይህ አይነቱንም አካሄድ በእንግሊዝ፣ በጀርመን ወዘተ የሚጠቀሙበትና በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ነው፡፡ ይህንንም በኃላፊነትና በቋሚነት ተረክቦ የሚያንቀሳቅስ “ሴንተር ኦፍ ኮምፒታንስ” የሚባል ድርጅት በመቋቋም ላይ ነው፡፡ ድርጅቱም ዳይሬክተር ተመድቦለታል፣ በጀትም ተይዞለታል፡፡ ለሥራ የሚገለገልበትም ሕንፃ በጂ.ቲ.ዜድ አማካይነት እየተገነባለት ነው”. ነገር ግን ግንባታው ተጓቷል፡፡ እስከዚያው ድረስ የትምህርት ቢሮው የተወሰነ ክፍል በውሰት መልክ በመስጠት ድርጅቱ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የማድረግ ሀሳብ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላዩ ትምህርት ላይ የጥራት ጉድለት ሊከሰት የቻለው ከአለምአቀፍ የትምህርት አሰጣጥ ጋር የሚስተካከል የመማር ማስተማር ሥራ እስካሁን ድረስ ባለመከናወኑ ነው ያሉት አቶ ሀጎስ ከዚህም ችግር ለመላቀቅ የሚያስችልና በአብዛኞቹ አገሮች እየተሰራበት ያለው የትምህርት ፓኬጅ ተጀምሮ ሥራ ላይ መዋሉን አስረድተዋል፡፡ ፓኬጁም በጥራት ላይ ትኩረት ያደረጉ ስድስት ነጥቦችን አካትቷል፡፡ እነሱም የትምህርት መሻሻል፣ የመምህራን ልማት፣ ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ሲ.ቲ”፣ ሲቪክ ኤንድ ኤቲካል ኤጂዩኬሽን፣ ካሪኩለምና የትምህርት ቤት አመራር ናቸው፡፡ በእነዚህ ላይ እንደ ፓኬጅ ተወስዶ ለውጥ ከመጣ የትምህርት ጥራት ይኖራል፡፡ በዝርዝር ከተቀመጡት ስድስት ነጥቦች መካከል ትምህርት ቤት ማሻሻልን በተመለከተ እቅድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላት አሉ፡፡ እነርሱም ተማሪው፣ መምህሩ፣ የትምህርት ቤቱ አመራር፣ ወላጅና መንግሥት ናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ርዕሰ መምህሩና ዩኒቲ መሪው ብቻ ነበሩ ዕቅድ የማውጣትና ያወጡትንም እቅድ ለመምህራኑ በማሳወቅ ሥራ ላይ እንዲውል የማድረግ ሥልጣን የነበራቸው፡፡ አሁን ግን ይህ አይነቱ አካሄድ ቀርቶ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል፡፡ ይህም ማለት ተማሪዎች ከመማክርቶቻቸው ጋር ተሰብስበው በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ለይተው ያወጣሉ፡፡ መምህራኑ፣ የትምህርት ቤት አመራሩና ወላጅም በየፊናቸው ችግሮቹን ለይተው ይይዛሉ፡፡ ከዚያ የሁሉም ችግሮች በአንድነት ተሰብስበው ይጨመቁና ቁልፍ የሆኑት ችግሮች ተለይተው ይወጣሉ፡፡ ለእነዚህ ቁልፍ ችግሮች አስፈላጊው መፍትሄ ለመሻት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራና በተናጠል ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከዚህም ሌላ እያንዳንዱ ክፍል ደረጃውን የጠበቀ መስፈርት (ስታንዳርድ ሪኳይርመንት) ይወጣለታል፡፡ አንድ ተማሪ ዓመቱን ሙሉ አንድ ክፍል ቁጭ ብሎ የሚፈለገውን መስፈርት ካላሟላ ትምህርት ቤቱና ርዕሰ መምህሩ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ርዕሰ መምህሩ የእያንዳንዱን ተማሪ ፋይል ይይዛል፡፡ ወላጅም ትምህርት ቤት ድረስ እየመጣ የልጁን የትምህርት አቀባበል የሚያይበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይህ ሁሉ ተከናውኖ ልጁ በትምህርቱ ለውጥ ካላመጣ ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ ችግሩም የአእምሮ ዘገምተኛነት ሊሆን ይችላል ወይም የወላጅ እንክብካቤ ጉድለት ሊሆን ይችላል፡፡ የወላጅ ችግር ሆኖ ከተገኘ “አንተ ችግር አለብህ፡፡ የልጅህን ትምህርት አቀባበል በደንብ አትከታተልም፡፡ ክፍል እንዳይደግም በሚቀጥለው ሲሚስተር እንዲያሻሽል እርዳው” ተብሎ ለወላጅ እንደሚነገረው አቶ ሀጎስ አውስተዋል፡፡ የመምህራን ልማትን በተመለከተም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ከዘጠነኛ እስከ 12 ክፍል ድረስ የሚያስተምሩ መምህራንና ርዕሰ መምህራን በሙሉ ማስትሬት (ሁለተኛ) ዲግሪ ያላቸው መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ርዕሰነ መምህራን የሦስት ሳምንት ስልጠና የተቀበሉ መሆን አለባቸው፡፡ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምሩ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ዲፕሎማ ያላቸው መምህራን ብቻ ናቸው የሚያስተምሩት፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን መምህራን በሙሉ የክረምት ኮርስ በነፃ እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው፡፡ በተለያዩ አውደ ጥናቶችና ሴሚናሮች በመሳተፍም የሙያ ማሻሻያ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ይህ እስኪሟላ ድረስ ግን ባለው የሰው ኃይል የመማር ማስተማሩ ሥራ ይቀጥላል፡፡ አይ.ሲ.ቲ በአሁኑ ጊዜ በመሰናዶ ትምህርት ደረጃ እየተሰጠ ነው፡፡ በቅርቡ ግን ለዘጠነኛና ለአሥረኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሰጥበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱና የመማሪያ መጽሀፍት እየተከለሱ ነው፡፡ መጽህፍት በሙሉ ካልተከለሱ እድገት አይኖርም፡፡ ከዚህ አኳያ ከአንድኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት መጽሀፍት በቅርቡ ይለወጣሉ፡፡ የሲቪክና ኤቲኪስ ትምህርት በመስጠት ተማሪው ስለአገሩ ሁኔታ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ ይህንን የሚያስተምሩ መምህራን ራሳቸው ኤቲካል መሆን ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎች የእነሱን ፈለግ እየተከተሉ ስለሚሄዱ ነው፡፡ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫና የፈተናዎች ኤጄንሲ የሚያወጣው የአሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ አይሰጥም እየተባለ የሚወራው ፈጽሞ ሀሰትና ከእውነት የራቀ መሆኑን አቶ ሀጎስ ገልጸው የትምህርት ፖሊሲው እስካለ ድረስ ፈተናው እንደሚኖር፣ ፖሊሲው የሚለወጠውም ሕዝቡ ተወያይቶበትና መክሮበት፣ መምህራን ተነጋግረውበት እንጂ የአንድ ትምህርት ቢሮ ወይም አንድ ከተማ ብቻውን የሚፈጽመው አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የትምህርት ፖሊሲው ያስቀመጠው ከአንድ እስከ ስምንት የመጀመሪያ ደረጃ፣ ከዘጠኝ እስከ 12 የሁለተኛ ደረጃ፡፡ ከዛ በኋላ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሚል ነው፡፡ ከአንድ እስከ ስምንት ደግሞ በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪ ሳይክል ከአንድ እስከ አራት፣ ሁለተኛ ሳይክል አንደኛ ደረጃ አምስት እስከ ስምንት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል ጠቅላላ ትምህርት ነው፡፡ እንዲሁም 11 እና 12 ለዩኒቨርሲቲ መሰናዶ ትምህርት ሲሆን ከዚህ በኋላ ደግሞ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ትምህርት ኮሌጅ ነው፡፡ በታደሰ ገብረማርያም |
|
| Last Updated ( Sunday, 03 February 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |