| ዩኒየኑ የቤቶች ፈንድ ሊያቋቁም ነው |
|
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
|
ባንክ ለመመስረት የሚያስችለውን ጥያቄ ሊያቀርብ ነው
የአዲስ አበባ ገንዘብና ቁጠባ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን የቤቶች ፈንድ ሊያቋቁም ነው፡፡ የራሱን ኮኦፕሬቲቭ ባንክ መመስረት ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ሊያቀርብ ነው፡፡ የዩኒየኑ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ እስራኤል ካሳ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ሀሙስ ጥር 22 ቀን 2000 ዓ.ም ሣምንት ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባው ላይ የከተማዋን የቤት ችግር ለመቅረፍ ይችላል ተብሎ የታመነበትን የቤቶች ፈንድ ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ አንድ መቶ ሃምሳ የሚሆኑ በተለያዩ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ባቋቋሟቸው የብድርና ቁጠባ ማህበራት ጥምረት ዩኒየኑ የተቋቋመው ዩኒየን አራት ዓመታትን አስቆጥሯል ነው፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት በሌሎች አገሮች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲሰጡና በትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ በመሳተፍ አባላትን በተለያዩ መንገድ እንደሚጠቅሙ አቶ እስራኤል አስታውቀዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በአገሪቱ መስረፅ እንዳለበት በመታመኑ በየመስሪያ ቤቱ የተቋቋሙ የብድርና ቁጠባ ማህበራትን አንድ ላይ በማጣመር የካፒታል አቅምንና የአባላትን ቁጥር በማሳደግ ወደ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ በተደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይም በዋናነት ድህነትን ለመቅረፍና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ በማተኮር አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ሥራ ላይ እንዲውሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በተለይ የመኖሪያ ቤት በዋናነት የተነሳ ችግር በመሆኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዩኒየኑ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውና የገንዘብ አቅሙም ስለሚኖር የራሱ የሆነ የቤቶች ፈንድ በማቋቋም አባላቱን መጥቀም ይችላል፡፡ የሚቋቋመው ፈንድ በዋናነት ቤቶችን በመገንባት በዩኒየኑ ስር ላሉ አባላት በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በዩኒየኑ ለረዥም ጊዜ የቆጠቡ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው እንደሚያደርግም ተጠቁሟል፡፡ ዩኒየኑ ከተመሰረተ ወዲህ የዩኒየኑ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ብድርና ቁጠባ ማህበር በገርጂ የሚገኘውን የኮንዶሚኒየም ቤት በመግዛት ማስረከቡ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡ እንደ ዩኒየኑ እምነት ቦታ ተረክቦ ግንባታ ማካሄድ ከሚፈጀው ጊዜ አንፃር ቤት ገዝቶ ለቆጣቢዎች ማስተላለፉ ተመራጭ ሆኖ መገኘቱንም አቶ እስራኤል አስረድተዋል፡፡ ዩኒየኑ የራሱ የሆነ የኮፕሬቲቭ ባንክ ለማቋቋም ያቀደው እቅድ ተግባራዊ እንዲደረግ ጠቅላላ ጉባኤው በመወሰኑ ባንኩን ለመመስረት የሚያስችለውን ጥያቄ ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያቀርብም ታውቋል፡፡ ባንኩ እንደ ሌሎች የንግድ ባንኮች ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም አነስተኛ ብድሮችን በመስጠት በበለጠ ለአባላቱ የሚያገለግል ነው፡፡ ከ150 በላይ ከሚሆኑት መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢትየጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሠራተኞች የብድርና ቁጠባ ማህበራት ይገኙበታል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |