| የፀቡ ተራ ለአፍሪካውያን ደርሷል |
|
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
![]() ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ምዕራባውያንን በጉልበት ለመቋቋም አስበዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን መጨረሻቸው ከአጋሮቻቸው ጋር በኩርፊያና አንዳንዴም ጦር በመማዘዝ ሆኖ ይቀራል፡፡ አሁንም ከአፍሪካውያን ጋር ፍቅራቸውን ጨርሰው የጥላቻ ጎራዲያቸውን ለመምዘዝ ማሰባቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ ጋዳፊ የአፍሪካ አንድነት መንግስት እንዲቋቋም የራሳቸው አጀንዳ አድርገው መያዝ ከጀመሩ ዘጠኝ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ፊታቸውን ወደ አፍሪካውያን አዙረው አንድ መንግስት እንሁን ያሉበት ጊዜ፣ ሊቢያ ማዕቀብ ተጥሎባት የአረብ አገሮችና ሌሎች ወዳጆቻቸው ርቀዋቸው፣ የአፍሪካ መንግስታት አጋርነታቸውን ባሳዩዋቸው ጊዜ ነበር፡፡ የቀድሞው የጦር ሰራዊት ሻለቃ መዓመር ጋዳፊ በነዳጅ ኃብት የተትረፈረፈች አገራቸውን ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር አንድ መንግስት የነክዋሜ ኑክሩማህን ዓላማ ተከታይ ሲሆኑ ራዕያቸውን ማስቀመጣቸው አልቀረም፡፡ ግን በአፍሪካ ባለው ምስቅልቅል ሁኔታ እንኳንስ አንድነታቸውን ሊያረጋግጡ ቀርቶ ለጦርነት ከመሰለፍ የታቀቡ መንግስታት ባለመሆናቸው ሕልማቸውን እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ጋዳፊ የተባበሩት የአፍሪካ መንግስታትን ለመፍጠር ቆርጠው የተነሱት እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ ነው፡፡ እንዲያውም መስከረም 9 ሰርት (ሊቢያ) በነበረው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ 9/9/99ን ታሪካዊ ቀን እናድርጋት እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡ በዚያ ስብሰባ ቢያንስ መንግስታቱን የአንድ ቀን የፕሮቶኮል ስምምነት ለማግኘት ጥረው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በሜዲትራንያን ባህር አጠገብ ለመሪዎቹ ባሳዩት ወታደራዊ ሰልፍ ታላቅና ዘመናዊ የሆኑ ሠራዊታቸውን፣ “የአፍሪካ የሰሜን በሩ ጦር” እያሉ እስከማስተዋወቅ ደርሰዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በዚያን ጊዜ ባይተባበሩዋቸው የአፍሪካ ሕብረት ይኸን ሕልማቸውን ይዞ እንዲጓዝ በእጅጉ ተመኝተው ነበር፡፡ ጥናቶች አስጠንተዋል፡፡ በራሳቸው ወጭ ሊቢያ ድረስ የመሪዎች ስብሰባ አዘጋጅተዋል፡፡ የሲቪል ሶሳይቲውንና የፕሬስ ሰዎችንም ትሪፖሊ ድረስ ጠርተው አነጋግረዋል፡፡ በምዕራብ አፍሪካ ባሉ አገሮች በመኪና ተዘዋውረው ሕዝቡን አነጋግሬያለሁ ይላሉ፡፡ ጋዳፊ በመጨረሻ የደረሱበት ድምዳሜ አንድነቱን የአፍሪካ ሕዝቦች ሲፈልጉ መንግስታቱ ግን እንቅፋት ሆነዋል፤ የሚል ነበር፡፡ ጋዳፊ የአፍሪካ አንድነት መንግስታት ለመመሥረት ሲያስቡ ሰፊ ራዕይ እንዳላቸው ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ “በፌደራል መንግሥት ሥር የተዋቀረች አፍሪካ ብትኖር በአገራቱ መካከል የሚታየው የወሰን ግጭት ይጠፋል፡፡ ድህነት ይጠፋል፤ እንደ አሜሪካ ጠንካራ አገር እንሆናለን” አፍሪካ የነዳጅ፣ የማዕድን፣ የእርሻና የቱሪስት መስህብነት አሟልቶ የሰጣት በመሆኑ በርካታ ችግሮች እንደሚቀረፉ ሲሰብኩ ኖረዋል፡፡ ይኽ ካልሆነ የአፍሪካ ኅብረት መኖሩ ምንም ችግር ሊያቃልል የሚችል አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ “በእኛ በአፍሪካውያኖችም ዘንድ የኅብረቱን የመከላከያ ኮሚሽነር ማን ያውቀዋል? የአሜሪካን የመከላከያ ራምስፊልድ ግን የማያውቀው የለም” ሲሉ የኅብረቱን አቅም ማነስ በንፅፅር በማሳየት የአፍሪካ ሕብረትን “ጥርስ አልባነት” በማሳየት ላይ ናቸው፡፡ በርሳቸው እምነት አአድ ለአፍሪካውያን ነፃ መውጣት እንደሰራ ሁሉ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ አንድነቱን ማምጣት መሆን እንዳለበት ይገልፃል፡፡ በአሜሪካም አንድነትን ተቃውመው እንደነበርና በኃይልም ቢሆን አንድ ከሆኑ በኋላ እንዴት የሚገልፁት ጋዳፊ፣ ባለፈው ሰኔ ወር አክራ ላይ በተደረገው ስብሰባ የአንድነቱ መንግሥት ምስረታ ውሳኔ እንዲያገኝ ብዙ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ይሁንና የጋዳፊን የአንድነት ተነሳሽነት ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጥያቄ ውስጥ ያስገቡታል፡፡ ከቶውንም የፖለቲካ ሞኛሞኝነት አድርገው የሚቆጥሩባቸው አልጠፉም፡፡ በእነዚህኞቹ ወገኖች እምነት፣ አፍሪካውያን ፖለቲካዊ ውህደት ለመፈጸም ከተበተቡት የርስ በርስ ትንቅንቅ መላቀቅ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ከዚያ ይልቅ አሁን በየቀጠናው እንደተጀመረው የኢኮኖሚ በመፍጠር ቀስ በቀስ ወደ ፖለቲካ አንድነቱም መዝለቅ እንደሚቻል ያምኑበታል፡፡ የእነዚህኞቹ ቡድኖች የደረጃ በደረጃ መቀራረብ ለጋዳፊ አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህ ከአፍሪካውያን ጋር ያላቸው ፍቅር ሊበጥሱት መድረሳቸውን ባለፈው ማክሰኞ ለ10ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ መናገራቸውን ሮይተር ዘግቦታል፡፡ መሐመድ አል ጋዳፊ በአፍሪካውያኑ መንግስታት ለአንድነት ውሳኔ ባለመሰለፋቸው አናደዋቸዋል፡፡ ቀድሞ አፍሪካውያን አንድ ነን የሚሉትን ንግግራቸውን ለውጠው በአረቦችና በጥቁሮች የተከፈለች አፍሪካ እንደምትሆን ፊት ለፊት እስከመናገር ደርሰዋል፡፡ እስካሁን በአፍሪካ ውስጥ ያላቸውን የ5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አንስተው ወደ ሜዲትራንያን አገሮች እንደሚያዞሩት ዝተዋል፡፡ “አፍሪካ ዘረኝነትን የምትመርቅ ከሆነችና ራሷን መስዋዕት ለማድረግ ከፈለገች ሊቢያ በአፍሪካ ያላትን ኢንቨስትመንት ወደ ሜዲትራንያን አገሮች ታዞረዋለች” ማለታቸውን የሊቢያ የዜና ወኪል ጃን ገልጿል፡፡ ጋዳፊ ዘረኝነትን መጥቀሳቸው፣ በአፍሪካ ኅብረት ሊቢያ ወይም አረቦች ከፍተኛውን የሥልጣን እርከን አለመጨበጣቸው የሌሎቹ የዘረኝነት ስሜት ውጤት አድርገው በመውሰዳቸው ሊሆን እንደሚችል ሮይተር ግምታቸውን የሰጡ ተመልካቾችን አስተያየት ዘግቧል፡፡ የሊቢያ ዲፕሎማሲ የሚከታተሉትን ባለሙያዎች ጠቅሶ ሮይተር እንደዘገበው ከሆነ ጋዳፊ የጋራ መንግስት ከሌለ በቀር አፍሪካ በሰሜን በሚገኙት ከሰሃራ በታች በሚገኙት አፍሪካውያን መሐከል መገንጠሏ አይቀርም ብለው ያምናሉ፡፡ “በአዲስ አበባ በሚደረገው ስብሰባ የእስካሁኑ ስህተቶች ከተደገሙ ይላሉ፡- ጋዳፊ፣ (10ኛውን የመሪዎች ሰብሰባ) “ስህተቶች ከተደገሙ . . .ሰሃራ የአህጉሪቱ የነጭና የጥቁር አፍሪካውያን የመለያያ ወሰን መሆኑ አይቀርም፡፡” ጋዳፊ በአፍሪካ ውስጥ ያላቸው ተሰሚነት እንደፈለጉት አልሆነላቸውም፡፡ በርግጥ ጋዳፊ በተለይ በቅኝ ግዛት ሥር ላሉ የአፍሪካ የነፃነት ተጋዳዮች ሰፊ እጃቸውን ሲዘረጉ ኖረዋል፡ ይኸንኑም የደቡብ አፍሪካው ኒልሰን ማንዴላ መስክረውላቸዋል፡፡ ሊቢያ የአየር በረራ እንዳይደረግባት በተመድ ማዕቀብ በተጣለባት ወቅት ማንዴላ በቱንዚያ በኩል በመኪና ገብተው ጋዳፊን አሞግሰዋል፡፡ “የክፉ ቀን ደራሻችን ስለሆኑ አጋርነታችንን ለመግለጽ ነው” ሲሉ በዓለም ሕዝብ ፊት አክብረዋቸዋል፡፡ ጋዳፊን ያሞገሰ ሁሉ ከሰፊው ልግስና ችሮታቸው ያላገኙ ቢኖሩ ጥቂቶች ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ይሁንና ጋዳፊ በገንዘባቸው ክብራቸውን ለማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ እንዲደመጥላቸው የሚፈልጉት ሀሳብ ተቃውሞ ከገጠመው ይቆጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚያሳዩት እንቅስቃሴ የበለጠ ጥላቻ ይፈጥርባቸዋል፡፡ በሉከርቢ ሰማይ ላይ ለፈነዳው የአሜሪካ የመጓጓዣ አውሮፕላን ፍንዳታ እጃቸው እንዳለበት መነገሩ፣ በፈረንሰይ አይሮፕላን ለሌሎች የሽብር ሥራዎች ከኋላ የሚደግፉ መሆናቸው ሲገለፅ መቆየት እንዳይታመኑ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህም የአፍሪካ አንድነት መንግሥትን የመመስረት ታላቅ ተግባር የአፍሪካ መሪዎች ጋዳፊን አምኖ መጀመር ቢፈሩ የሚያስወቅሳቸው ላይሆን ይችላል፡፡ የዜና ወኪል ጃን በዘገበው የጋዳፊ ንግግር ጋዳፊ የተደማጭነትን ጉዳይ ማንሳታቸውን ጠቁሟል፡፡ “ይኸን ገንዘብ /5 ቢሊየን/ ኢንቨስት ስናደርግ ለአፍሪካውያን በነፃ የተሰጣቸው ሳይሆን ሊቢያ ምላሹን የምትጠብቅበት ነው፡፡ 5 እና 10 ቢሊዮን ዶላር በሜዲትራንያን አካባቢ ኢንቨስት ብናደርግ በሜዲትራንያን ወይም በአረብ ወይም በአውሮፓ አገሮች የምንደመጥ ልንሆን እንችላለን”፡፡ ጋዳፊ በአረብ በሜዲትራንያን በአውሮፓ ተደማጭነት ሊኖራቸው እንደሚችል ያመኑ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን በአብዛኞቹ አረቦች በኩል ጋዳፊ ተወዳጅ መሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ምልክት የለም፡፡ በቦንቡ በቀጠቀጠቻቸውና ማዕቀብ ባደረገባቸው ጊዜ አንድም የአረብ አገር አብሩዋቸው አልቆመም፡፡ ጥፋተኛ የተባሉትን ሊቢያውያን አሳልፈው ከሰጡና የማዕቀቡም ሰበብ ከተፈታ በኋላ እንኳ የአረብ ሊግ አባላት ወደ ትሪፖሊ ለመሄድ አልደፈሩም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ቀዳሚውን ርምጃ እስኪወስዱ ድረስ፡፡ በፍልስጢኤማውያን ከእስራኤል ጋር ስምምነት መፈረም ጀምሮ በአረብ አገሮች አቋም ተቀይመዋል፡፡ እንደነ ሶሪያና ኢራቅ ካሉ አገሮች ጋር ፀበኛ ናቸው፡፡ ሥልጣን እንደያዙ ከሶሪያና ከግብጽ ጋር የአንድነት መንግሥት ለማቋቋም ተስማምተው ነበር፡፡ ወዲያው ስለተጣሉ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ተሰልፈዋል፡፡ እንዲያውም ከግብጽ ጦርነት ገጥመው ሊቢያ ተሸናፊ ሆነች፡፡ አውሮፓን መጥቀሳቸው እንደ ቀድሞው ሁሉ አዲሱ ሽርክናቸው ስላስመረቀናቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ከሳዳም ሁሴን መመታት በኋላ ጋዳፊ በስልጣን ለመቆየት ብቸኛው መንገድ “እጃቸውን በመስጠት” መሆኑን ለመረዳት ብልህ መሪ ሆነዋል፡፡ የገነቡዋቸውን የኒውክሊየር መሳሪያዎችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አወደሙ፡፡ በአውሮፕላኑ ፍንዳታ ለሞት ካሳ ከፈሉ፤ ተጠርጣሪውን አስረከቡ፡፡ ስለዚህ አሜሪካ ፀቧን አርግባ ኤምባሲ ለመክፈት ስትጠይቅ የቀድሞውን ንጉሥ መኖሪያ ሰጥተው ከ30 ዓመት በላይ የተቋረጠውን ግንኙነታቸውን አደሱ፡፡ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩን ብሌር ትሪፖሊ ድረስ ሄደው ጎበኟቸው፡፡ ፈረንሳይ ለተገደሉ ዜጎቿ እሷ በጠየቀችው ልክ ካሳ ከከፈሉ በኋላ ወዳጅነት ፀንቶ የመከላከያ ትብብር እስከመነጋገር ደርሰዋል፡፡ ወደ አውሮፓ አገሮችም ጉብኝት ጀምረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ጊዜው የአዲሶቹ ወዳጆች የአውሮፓና የሜዲትራንያን ሊሆን ግድ ነው፡፡ በዚያው ልክ ፀቡም ለእስካሁኑ ወዳጆቻቸው አፍሪካውያን መሆኑ አይቀርም፡፡ ቀድመው ወደ ሌላው ሲሄዱ የበፊቱን ተጣልተው ስለሚሆን አፍሪካ ከዚህ በኋላ ከአጀንዳቸው ትፋቃለች፡፡ አፍሪካን በሚመለከት በትሪፖሊ የሚደረጉ የማያቋርጡ ስብሰባዎች ይቀራሉ፡፡ በሊቢያ የሚኖሩ የሰሃራ በታች አፍሪካውያን ይባረራሉ፡፡ 40ኛውን የሥልጣን ከአውሮፓውያን ጋር ማክበር ተረኛው ጊዜ ይሆናል፡፡ አፈወርቅ አባ መርሳ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |