Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow ፖለቲካ ፓርቲዎችና ውሳኔ አሰጣጣቸው
ፖለቲካ ፓርቲዎችና ውሳኔ አሰጣጣቸው Print E-mail
Sunday, 03 February 2008
የጥንታዊ ግሪክ ዲሞክራሲያዊ ፅንስ ሀሳብ “አንድ ድምፅ አንድ ሰው” የሚለውን መርህ ከመከተሉና ወደ ተወካይ ዲሞክራሲ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ሰው በሀገሪቱ ዲሞክራሲ እኩል መብትና ግዴታ ነበረው፡፡ በተወካይ ዲሞክራሲ ጥቂቶች በውክልና የብዙሀኑን ድምፅ ይወክላሉ፡፡ ብዙሀኑ የሀገሪቱ ዜጐች ሲሆኑ ተወካዮች ግን የተለያየ አጀንዳ፣ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ድርጅታዊ መዋቅር አሊያም ግለሰባዊ ስብዕና የሚይዙ ተፎካካሪ አካሎች ናቸው፡፡
ተፎካካሪ አካሎች ወይም ግለሰቦች ለሀገሪቱ በሚያመጡት ውጤትና የሥራ ብቃት፣ በድርጅቶች ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ተባብሮና ተከባብሮ የመስራት ባህል፣ በውስጠ ፓርቲ የመረጋጋት ሁኔታና በተለይም ውሳኔ የማሳለፍ ስርዓቱን በማየት ይመረጣሉ አልያም አይመረጡም፡፡

ተወካዮች ሊያስተጋቡ የሚችሉት ሀሳብም ሆነ ሀሳብ የሚያዝበት ስርዓት የወከለውን የብዙሀኑን ህዝብ ስሜትና ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓቱ ሲቀረፅ ጀምሮ የተወሰነውን አካል ተጠቃሚ እንዲያደርግ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ በተለይ በህገ ደንብ የፀና የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ግልፅና የተለያዩ አተረጓጎምን የሚጋብዝ መሆን አይኖርበትም፡፡ የሚያምታታና ግልፅ ያልሆነ ቃላት፣ ሀረግ፣ አረፍተ ነገር በህገ ደንብ ሲታቀፍ በተለመደው የብዙሀን ድምፅ ውሳኔ መስጠቱ ከተገማችነትና ከተደራሽነት አንፃር ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ሀሳብን በክርክርና በውይይት ማስቀየር ወይም መቀየር የሚቻል ሲሆን የውሳኔ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ግን አንዴ ካልተደገፈ ሌላ ጊዜ የሚደገፍበት እድል ብዙም አይኖርም፡፡

ከላይ የተገለፁት የዲሞክራሲ ችግሮች ምላሽ የሚያገኙት በተቋሞች አወቃቀር ነው፡፡ በሌላም በኩል የዲሞክራሲ ተዋናዮች እንዴት ስርዓቱን እንደሚያደራጁ ያለው እውነት ተጨማሪ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእነዚህ ተዋናዮች ስርዓቱን በመርዳትም ሆነ በመጉዳት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም ህገ ደንብ ቀላልና ግልፅ ሲሆን ዜጎችን በቀላሉ መምረጥ ስለሚችሉ በተወሳሰበው የመንግሥት ስርዓት ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ፓርቲዎች የሚመለምሏቸውና የሚያሰለጥኑአቸው ልሂቃን በብዛት በአንድ የተለየ ነገር ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸውና የአባላቱን ንቃተ ህሊና የማቅናት አሊያም የማጥመም ክህሎት አላቸው፡፡ ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ ግለሰቦች እንደ አመጣጣቸው የሚሄዱ በመሆናቸው የፓርቲውን ህልውና ዘላቂ የሚያደርግ ስርዓት መገንባት ወሳኝ ነው፤ በተለይም ውሳኔ አሰጣጥን፡፡

ዲሞክራሲ የህዝብ ውሳኔ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደድርጅት አሊያም የፓርቲው መሪዎች እንደግለሰብ የፓርቲውን ዝርዝር አላማዎች ለሕዝቡ ያስረዳሉ፡፡ በአንድ ወቅት የአሜሪካን ኘሬዚዳንት የነበሩ አብርሀም ሊንከን “ዲሞክራሲ ማለት የሕዝብ የበላይነት የሚረጋገጥበት፤ በሕዝብ የሚመራና ለህዝብ መገልገያ የሚሆን ነው” ብለው ነበር፡፡ ዲሞክራሲ ያለምንም ጫና በነፃነት የሚተገበር  ነው፡፡ ዋነኛ ተዋናዩም ሕዝቡ ነው፡፡

ለዚህ ሂደት መጎልበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔ አሰጣጥን በዋነኛነት መስመር ከሚያስይዙ መርሆዎች ዋነኛዎቹ የብዙሀን የበላይነት የአነስተኞች መብት መከበር፤ ዲሞክራሲያዊ የሆነ የሕብረተሰብ ክፍል መገንባት (በፖለቲካ የተደራጀ፣ በሙያ ማህበራት የታቀፈና ተቻችሎ የሚኖር) እና የመናገርና የመሰብሰብ ነፃነት (መረጃ ማግኘት፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ) መረጋገጥ እና የሕግ የበላይነት መከበር ናቸው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው የውስጥ ጉዳይም ይሁን በብሔራዊና ክልላዊ ምርጫዎች ወቅት ይህን መርህ ከተከተሉ የሚፈጠሩ የሀሳብ ልዩነቶችና የአተረጓጐም አለመግባባቶች በቀላሉ መፍትሄ ያገኛሉ፡፡ ከምዕራባዊያንና ከአሜሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደምንረዳው ለውሳኔ አሰጣጥ እነዚህን መርሆች በአግባቡ ይጠቀሙባቸዋል፡፡

በጀርመን፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስቸጋሪ የተባሉ ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ የህዝቡን ስሜትና ፍላጎት የፓርቲውን ኘሮግራም፣ የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ፣ በተለይም የፓርቲውን ህገ ደንብ ግምት ውስጥ ያስገባሉ፡፡

በ1980 እ.ኤ.አ በጀርመን በተደረገው የፓርላማ ምርጫ የሶሻል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን ሲይዝ የጣምራ ፖለቲካ ለማካሄድ የሊበራሎችን ፓርቲ መጠየቅ ነበረበት፡፡ ይህ ካልሆነ ከተቀናቃኙ ፓርቲ ከክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት ጋር በጣምራ ለመሥራት ስለሚስማማ በምርጫው አሸናፊ የሆነው ፓርቲ በፓርላማው ውስጥ ያለው ድምፅ አነስተኛ ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ ከሊበራል ፓርቲ ጋር ተስማምተው በጋራ የመንግሥትን ስልጣን ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በጋራ የምናራምደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አልተስማማኝም በማለት የሊበራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲው ሶሻል ዲሞክራቶችን በመክዳት ጭምር ፖለቲካውን አልፈልግም በማለቱና ከክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት ጋር በማበሩ ምክንያት የምርጫው ጊዜ ሳይደርስ በ1981 የመንግሥት ሥልጣን ከሶሻል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ወደ ክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት እንዲሸጋገር ግዴታ ሆነ፡፡

በእንግሊዝም በ1929 እ.ኤ.አ የእንግሊዝ ሠራተኞች ፓርቲ በምርጫ የተረከበውን የመንግሥት ሥልጣን እስከሚቀጥለው የምርጫ ዘመን በእጁ ሳያቆየው በ1931 ለወግ አጥባቂዎች ፓርቲ ለማስረከብ ተገዷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በፓርቲው ውስጥ የሃሳብ ልዩነቶች በመከሰታቸው ነው፡፡ በ1981ም የፓርቲው የቀኝ ክንፍ አክራሪ ወገኖች የሆኑት የሀሳብ ልዩነቶች አለን በማለት ከፓርቲው ከወጡ በኋላ የራሳችን ሶሻል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ መስርተናል ቢሉም ያራምዱት የነበረው አላማ የሶሻል ዲሞክራቶች ሳይሆን ከወግ አጥባቂው ፓርቲ ጋር የሚቀራረብ ስለነበር የእንግሊዝን ህብረተሰብ ድጋፍ አግኝተው በፓርላማ ውስጥ ለመግባት አልቻሉም፡፡

በአሜሪካም ቢሆን ከታሪካዊዎቹ ሪፐብሊካንና ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች በመገንጠል እንቅስቃሴ ያደረጉ በርካታ ፓርቲዎች ሲኖሩ ሁለቱ ዋነኛ ፓርቲዎች ግን እየተፈራረቁ በገዟት አሜሪካ ከ1854 እ.ኤ.አ ጀምሮ የፓርቲዎቹን ውሳኔ የሚፈታተኑ ነገሮች የገጠሟቸው ሲሆን በዲሞክራሲ መርህ በመመራት አንዱ የአንዱ ጠባቂ በመሆኑ እራሳቸውንም ሀገራቸውንም ጠብቀው አሁንም አሉ፡፡

በፈረንሳይ በ1995 እ.ኤ.አ በተደረገው የኘሬዚዳንትና የፓርላማ ምርጫዎች ሶሻሊስቶች በወግ አጥባቂዎች ተሸነፉ፡፡ የወግ አጥባቂዎቹ ኘሬዚዳንት ዣክ ሺራክን ፈተና ውስጥ የጣላቸው በ1997 እ.ኤ.አ በተደረገው የፓርላማ ምርጫ የሶሻሊስት ፓርቲው በማሸነፉና የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሰይም ብሎም የሀገሪቱን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስተዳደር እንዲመራ በመደረጉ ነው፡፡ ለኘሬዚዳንት ዣክ ሺራክ ምቹ ሁኔታን የማይፈጥር ቢሆንም ለሀገሪቱ አስተዳደር ግን በጣም ውጤታማ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በተለያዩ የመንግሥት ስልጣን መዋቅሮች ላይ ስለወጡ አንዱ ወገን ሌላውን ጥፋት እንዳይፈፅም በዓይነ ቁራኛ ስለሚመለከትና ስለሚቆጣጠር ነው፡፡

ከላይ የአደጉትን አገሮች የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኔ ስንመለከተው የዲሞክራሲን የብልፅግና ደረጃ እናያለን፡፡ ለሀገራቸው ህግ፣ ለሚወክሉት ህዝብ ስሜትና ፍላጎት፣ ለራሳቸው ህገ ደንብ በሚገባ ክብር የሚሰጡ ከመሆናቸውም ባሻገር ልዩነትን ለማጥበብ፣ ለማስወገድ ሞክረው ካልተሳካላቸው በሰላም ተለያይተው ይፎካከራሉ፡፡ ወሳኔአቸው ደረጃ ያለው ሲሆን ሥራ አስፈፃሚ፣ የተለያዩ ኮሚቴዎች፣ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የህዝብ አስተያየት በየደረጃው ይገመገማሉ፡፡ የዲሞክራሲ ተቋሞች ማለትም እንደ ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤቶች የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡

በሀገራችን ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቋቋሙ የራሳቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም ህገ-ደንብ ቢያንስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ፖሊሲ ስትራቴጂና ህገ ደንብ የሚተረጉሙበት የራሳቸው ነፃነት አላቸው፡፡ በአተረጓጎም ላይ አለመግባባት ቢፈፀም እንኳን ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ መፍትሄ ማግኘት ይችላሉ እንጂ የምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ የመግባት ስልጣን የለውም፡፡

ምርጫ ቦርድ ለምሳሌ የቀድሞ ቅንጅቶች በቀድሞው ሊቀመንበር ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል ምትክ የመወከል ስልጣንና አምስት የሥራ አስፈፃሚ አባላትን ያባረሩበትን ስልጣን በህገ ደንቡ መሰረት ነው ወይም አይደለም የማለት ስልጣን የለውም፡፡ በሌላ በኩል ሌላውን የቀድሞውን ቅንጅት ያላግባባው የመለያ ምልክት ጉዳይ የምርጫ ቦርድ የመወሰን ስልጣን የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. አንቀፅ 52 ላይ ተሰጥቶታል፡፡ በአንቀፅ 52(5) መሠረት በምርጫ መለያ ምልክት ላይ ለሚነሱ አለመግባባቶች ቦርዱ አስፈላጊውን ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ስላለው የጣት ምልክቱን በቅርቡ ለኢዴአፓ መድህን በመስጠት ለአለመግባባቱ መቋጫ ሰጥቷል፡፡ ይሁንና በህገ ደንቡ አተረጓጎም ላይ የተነሳው አለመግባባት ወደ ፍርድ ቤት ባለማምራቱ ሁሉም ወገን በመሰለው እየተረጎመው ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ አንቀፅ 7 ላይ ስልጣንና ተግባሩ የተዘረዘረ ሲሆን በአንቀፅ 7(6) ላይ የፖለቲካ ድርጅቶችን የመመዝገብ፣ ፈቃድ የመስጠት፤ በህጉ መሰረት የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣን ሲሰጠው በአንቀፅ 7(9) መሠረት ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን የጋራ መድረክ የማደራጀትና የማስተባበር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህም ማለት ምርጫ ቦርድ የአንድን ፓርቲ የግል ችግር በተናጠል የማዬት ሳይሆን የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ችግር ለመፍታት ነው የሚሞክረው፡፡ በዚህም ህገ ደንብን አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ የሚገባው የወጣው ወይም ሊቀየር ያለው ህገ ደንብ በሀገሪቱ ህግ መሠረት ያልተከናወነ ከሆነ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ እነዚህ ተግባሮቹን ያለቀስቃሽ በራሱ ጊዜ ይፈፅማቸዋል፡፡

ነገር ግን ፍርድ ቤቶች በህግ አተረጓጎም ላይ የሚነሳ አለመግባባትን ለመፍታት የሀሳብ ልዩነት ወይም ምክንያት ያለው አካል ወደ ፍርድ ቤት በመቅረብ የትርጉም ልዩነትን ሲጠይቅ መፍታት ይችላሉ፡፡ ህገ መንግሥቱ በአንቀፅ 37(1) ላይ “ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው” የሚል በመሆኑ እንዲሁም ከላይ እንዳየነው ምርጫ ቦርድም ሆነ ሌላ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው የዳኝነት አካል ባለመኖሩ ያልተግባቡበትን ጉዳይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ አለባቸው፡፡

ይሁንና ፍርድ ቤቶች በህገ ደንቡ በግልፅ የተመለከቱና የማያከራክሩ ጉዳዮችን አጥፊ ካለ በደንቡ መሠረት ይቀጣሉ እንጂ ህገ ደንቡ ያለውን አጠቃላይ መንፈስና አላማ በሚቃረን መልኩ ውሳኔ አይሰጡም፡፡ ለዚህም ነው ህጉ በነፃነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዩ ላይ እንዲደራደሩና በተግባቡበት ጉዳይ ላይ ህገ ደንብ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲያወጡ ያለጣልቃ ገብነት የለቀቃቸው፡፡ ህገ ደንብ ለምሳሌ ከያዛቸው ወሳኝ ነገሮች አንዱ  ጉባኤን ይመለከታል፡፡ ነገር ግን የቅንጅት ጉዳይ ያሳየው የተለየ ነገር ምልዐተ ጉባኤ በተለያየ ጉዳይ ለመሙላት ባልቻለበት ሁኔታና ወደ ፊትም የማይለወጥ ከሆነ የሚወሰዱ ጉዳዮች እንዴት እንደሚታዩ፣ የሥራ አስፈፃሚ፣ ላዕላይ ምክር ቤትና ጠቅላላ ጉባኤ ልዩነት ፈጥረው ተከፋፍለው በመሰብሰብ የአንድ ድርጅት አባላት የሚያሳተላልፉት ውሳኔ ህገ ደንቡን መሠረት በማድረግ ለሚፈጠረው ችግር መፍትሔ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ነገሮች የሚስተናገዱበት የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡

ዶክተር ዘውዱ ውብእንግዳ “የፌዴራላዊ መንግሥት ታሪካዊ አመጣጥ፤ የመንግሥት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ” በተባለው መፅሀፋቸው “ለሀገር ግንባታ መፋጠን፤ ለዴሞክራሲ እድገት እውን መሆን፤ ለሰው ልጆች መብቶች መከበርና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ዋስትና ሊሰጥ የሚችለው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያራምዷቸው የፖለቲካ መስመሮች ዙሪያ ሕዝብን አሰባስበው እያሳመኑና እያስተማሩ በማዘጋጀት ሕጋዊ በሆነ መልኩ ለሥልጣን ትግል ብቁ ሆነው ሲገኙ ነው፡፡ ለዚህ ሀሳብ ተግባራዊነት ደግሞ ሶስት መሠረታዊ የፖለቲካ ትግል ዘዴዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው፣ 1ኛ/ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያራምደውን የፖለቲካ መስመር በሕዝብ ፊት ይፋ ማድረግና ለተግባራዊነቱም ጠንክሮ መሥራት፣ 2ኛ/ እያንዳንድ ፓርቲ ከራሱ ከአባላቱ በመጀመር ዴሞክራሲያዊ አሰራርን ማለትም ሂስ ማቅረብንና መቀበልን ውሳኔዎችን በዴሞከራሲያዊ መንገድ ማስተላለፍንና ተግባራዊነታቸውንም መከተልን፤ በአባላት ፊት የሥራ ሪፖርት አቅርቦ በማወያየት ማፅደቅን፤ በአባላት ሙሉ ፍላጎትና እምነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ የፓርቲ አመራር ምርጫ ማድረግን፤ 3ኛ/ ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ላይ እየተጣመሩ ወይንም እየተዋሃዱ መሥራት” ብለዋል፡፡

ዶክተር ዘውዱ “ዲሞክራሲ” የሚለው ቃል መደጋገማቸው ወደው አይደለም፡፡ ልሂቃን የምንላቸው አካሎች የበለጠ የቃሉን ተግባራዊነት ሲያጣምሙት ሲታይ እውነትም ደጋግሞ መከለስ አስፈላጊ ነው፡፡ ፓርቲዎች ዴሞክራሲን መሠረት አድርገው ሕዝብን የስልጣን ባለቤት የማድረግ አካሄዳቸውን ለማሳመር የትብብርና የመረዳዳት ባህልን ለማዳበር ሙሉ ነፃነት ቢያንስ በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁንና ገዥውም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬም “እናውቅልሀለን” የሚሉትን ሰፊውን ሕዝብ የውሳኔ ሰጭነቱ አካል አላደረጉትም፡፡ በተጨማሪም ሕዝቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ በህይወቱና በጊዜው ፈርዶ ያቋቋማቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ ሲፈርሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች መስዋዕት የሆኑባቸው ፓርቲዎች ሲባክኑ አቤት የሚባልበት ተቋም ጠፍቶ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ፈላጭ ቆራጭ ሲሆኑ በጣም ያሳዝናል፡፡ ምርጫ ቦርድም የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደ አንድ የንግድ ተቋም ከአንዱ ቀምቶ ለአንዱ ሲሰጥ የሚጠቀምበት ህግና ደንብ የቱ እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡ በነጋ በጠባ “መድብለ ፓርቲ ሥርዓት” እያልን ብንወተውትም የሚያጎለብተው ሳይሆን እያሳሳ ሊያጠፋው የተቃረበው ሁሉም አካል ነው፡፡ ተጠያቂነትንና ግልፅነትን ያላረጋገጠው የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ውሳኔ አሰጣጥ እስካልተለወጠ ድረስ ሕዝቡ ለምን የፖለቲካ ሥርዓቱን ተጠራጣሪ ሆነ ማለት አግባብ አይሆንም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝባዊ መሠረት ላይ እንደቆሙ፣ ውሳኔ አሰጣጣቸው ግልፅ እንዲሆን፣ አባላቱና መሪዎቹ ግዴታና መብታቸው እንዲከተል፣ ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ውሳኔ እንዲወስኑ፣ በድፍረት ወደ እነዚህ አካላት ወስዶ በትክክል ለሕዝቡ የሚታገል ታማኝ ዜጋ እስካላፈራን ድረስ ሁሉንም የሚያግባባ የውሳኔ አሰጣጥ ባህል ብሎም የዴሞክራሲ መርህ መፍጠር አንችልም፡፡

በሠለሞን ጐሹ
 
< Prev   Next >