| “በግብር ከፋይና በግብር ሰብሳቢው... |
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
|
“በግብር ከፋይና በግብር ሰብሳቢው መካከል ትልቅ የአመለካከት ችግር አለ”
ፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር በግብር ሰብሳቢውና በግብር ከፋዩ መካከል ከፍተኛ የሆነ የአመለካከት ችግር መኖሩ የተረጋገጠ መሆኑን የፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ጥር 23 ቀን 2000 ዓ.ም በሚሌኒየም ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናገሩ፡፡ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ ፈንታ ይህንን የተናገሩት “የግብርና ቀረጥ ሳምንት” በሚል ከነገ ጥር 26 እስከ የካቲት 1 ቀን 2000 ዓ.ም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ የሚያካሂደውን የሚሌኒየም ኤግዚቢሽን (ዝግጅት) አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ለተነሱላችው ጥያቄዎች በሰጡት መልስ ነው፡፡ “ግብር ሰብሳቢው ግብር ከፋዩን ዘርፎ እንዳገኘው በማሰብ ጠማማ አመለካከት ያለው አለ፡፡ መታረም አለበት፡ ግብር ከፋዩም ሰርቶ ካገኘው ላይ ለመንግስት መክፈል ያለበትን በማጭበርበር ለማለፍ የሚያደርገው ሙከራ አለ፡፡ በሁለቱም በኩል መስተካከልና ስርዓት መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ ግብር ሰብሳቢው አንድ ባለሃብት (ነጋዴ) መኪና ይዞ ሲያየው፣ ዘርፎ ነው ብሎ ማሰብ የለበትም፣ ያሉት ሚኒስትሩ፣ በሚሌኒየሙ ይህንን አስተሳሰብ በመስበርና ወደ ጎን በመተው ግንዛቤ በማስጨበጥ ስርዓት ያለው ግብር ከፋይና ሰብሳቢ ዜጋ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሚኒስትሩ ሌላው እንደ ሁለተኛ ችግር ያነሱት፣ ከአሰራር ስርዓት ውጭ የሚመጣ ነው፡፡ የአሰራር ስርዓቱ ግልጽ ካልሆነ ለድርድር በር በመክፈቱ ሥራዎች በፍጥነትና በቅልጥፍና እንዳይሰሩ ይደረጋል፡፡ በቅርቡ የንግድ ፈቃድን ለማሳደስ ክሊራንስ ለመውሰድ በሚመጡ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ በቅርቡ የተፈጠረው ችግር የመንግስትን የታክስ አሰባሰብ ስርዓት ኮምፒዩተራይዝድ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጽዕኖም እንደነበረበት የተናገሩት አቶ መላኩ፣ ቀደም ብሎ ቫት ብቻ በኮምፒዩተር ማሽን ይሰራ የነበረው አሰራር በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም የታክስ አስተዳደር ስርዓት በማሽን ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡ በውጭ አማካሪዎች የሚሰራው የማሽን ተከላው ሥራ ሞዴሉ የካናዳ መሆኑን፣ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ ተሰርቶ ማለቁን፣ መሠረታዊ የዳታ ማስገባቱ ሥራ በመጠናቀቁ በዚህ ወር መጨረሻ አዲስ አበባ ላይ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆንና በክልል ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችም ላይ በሂደት ላይ መሆኑን አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡ “ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው በሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ መንግሥት ወይም የሚመለከተው አካል ያወጣውን መመሪያ በመተላለፍ፣ ያለአግባብ ተሽከርካሪዎች እየተያዙ ባለንብረቶች እንደሚጉላሉና ንብረታቸው የት እንደታሰረ እንኳን ሳያውቁ ብዙ ጊዜ ማስቆጠራቸውን፣ አንዳንዶቹ ተሽከርካሪዎችም ከፍርድ ቤት ትዕዛዝና አሰራር ውጭ የመንግስት ሰሌዳ (ታርጋ) ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምን አስተያየት አለው?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ይህ ተደርጎ ከሆነ ስህተት መሆኑን፣ ህግን በሚጥስ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ (ማስረጃው ሲደርሳቸው..፣ ነገር ግን ተሽከርካሪዎቹ በጠቋሚዎች ተይዘው (ጉምሩክ በኮሚሽን ያሰማራቸው ጠቋሚዎች) በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ጨረታ ወጥቶባቸው፣ ክርክር ተደርጎባቸው ለመንግስት ከተወሰነ፣ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደሚታደሉ አቶ መላኩ በሰጡት መልስ ገልፀዋል፡፡ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው የተያዙ ተሽከርካሪዎችን መንግስት ከባለንብረቶቹ ጋር ባደረገው ድርድር (ንግግር)ና ስምምነት ሊያጣው የነበረውን 200 ሚሊዮን ብር (ግማሽ ክፍያ) ማግኘቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ያለ አግባብ ጠቋሚዎች ያስያዟቸው ከ200 በላይ ተሽከርካሪዎች ለባለንብረቶቹ መመለሳቸውን፣ ነገር ግን በዚህ መሃል ተጎጂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚሌኒየሙ በርካታ ዕቅዶችን ይዞ በመስራት ላይ እንደሚገኝና ከጅምሩ ስድስት ሺ ችግኞችን ተክሎ 90 በመቶ የፀደቀለት መሆኑን የተናገሩት አቶ መላኩ፣ በሚሌኒየሙ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተባባሪዎቹ ሊሰሩ ከታቀዱት ውስጥ የወጣቶችን ተቋም በ20 ሚሊዮን ብር ወጭ ለማስገንባት ከአዲስ አበባ አስተዳደር ነፃ ቦታ የተፈቀደላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |