Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow “የምርጫውን ጨዋታ ኢህአዴግ...
“የምርጫውን ጨዋታ ኢህአዴግ... Print E-mail
Sunday, 03 February 2008
“የምርጫውን ጨዋታ ኢህአዴግ ጨርሶ አበላሽቶታል”
ኦፍዴንና ኅብረት

የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት ኢህአዴግ የምርጫውን ጨዋታ ጨርሶ አበላሽቶታል ሲሉ አማረሩ፡፡
ያለፈው ረቡዕ ሁለቱ ፓርቲዎች በሰጡት የጋራ መግለጫ ገዢው ፓርቲ በሚያዚያ ወር የሚያካሄደውን የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ሆን ብሎ እያበላሸ ነው ሲሉ አሳውቀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የምርጫው አካሄድ ከወዲሁ ተጭበርብሯል ብለዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ገዢው ፓርቲ ምርጫውን በብቸኝነት ለመወዳደር ዘርፈ ብዙ መሰናክሎችን እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ላይ እስራትና ወከባ፣ ጽ/ቤቶቻቸው እየተዘጉ መሆኑን፣ ደጋፊዎቻቸው እንደሆኑ የሚጠረጠሩ ገበሬዎችና ነጋዴዎች ላይ ግብር እስከ 300ኀ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑን፣ የምርጫ ምዝገባ ያለ ታዛቢ አካል እየተከናወነ መሆኑን፣ የምርጫ ጣቢያዎች በፖሊስ ጣቢያና በገዢው ፓርቲ አባላት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ መሆናቸውንና መሰል ሁኔታዎችን በመጥቀስ የምርጫው ሂደት ከወዲሁ እየተጭበረበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ “የገዢው ፓርቲ ከምርጫ 97 ወዲህ ብዙ ነውረኛ የሆኑ ድርጊቶችን እየፈፀመ ነው” ሲሉ በመግለጫው ወቅት አማርረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የምርጫውን ሂደት እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ሂደት በተመለከተ ገዢው ፓርቲ ዘላቂ መፍትሄ እንዳይገኝ ሁኔታው እያሳሰበ መሆኑን ገልፀው ፓርቲዎች ባላጠፉት ጥፋት ይቅርታ ጠይቁ መባላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የገዢው ፓርቲ ትምክህተኛ መሆኑንና የውይይት መድረክ መጥፋቱን ገልፀዋል፡፡

 አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው የምርጫው ሂደት እጅግ የሚያስፈራና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀው፤ “ኢህአዴግ ሁሉን ነገር የመጣው ይምጣ በሚል አሰራር እየሰራ ነው” ሲሉ አማርረዋል፡፡ አቶ ቡልቻ የምርጫው አካሄድ ኢፍትሃዊ መሆኑን ጠቁመው “ጭቆናው በዚሁ ከቀጠለ የምርጫውን ውድድር ለማቆም እንገደዳለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ዶ/ር መራራ ጉዲና በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ነገር ግን ውሳኔው የኢህአዴግ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን እያሰረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር መራራ ከግንቦቱ ምርጫ ወዲህ ከ300 በላይ አባሎቻቸው መታሰራቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 130ዎቹ በቅርቡ የታሰሩ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ዶ/ር መራራ የእጩዎች ምዝገባ በቀበሌ ውስጥ 300 እጩ እንዲሆን መደረጉ በኦሮሚያ ውስጥ ለመወዳደር 1.5 ሚሊዮን ተወዳዳሪ ለማቅረብ የሚገደዱ መሆኑን ገልፀው በምርጫው የሚወዳደሩ ሌሎች ፓርቲዎች ከሚያቀርቡት እጩ ተወዳዳሪ ጋር በአንድ ቀበሌ ከ25ኀ በላይ ተወዳዳሪ እንደሚኖርና ተግባራዊ ለማድረግ የማይመች መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በአጠቃላይ “የምርጫውን ጨዋታ ኢህአዴግ ጨርሶ አበላሽቶታል” ሲሉ አማርረዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ አንድ ቀበሌ ውስጥ 300 እጩ መባሉ ገዢው ፓርቲ የተቃዋሚዎች እጩ ምልመላ ምንጮችን ለማድረቅ የቀየሰው ስልት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህም “91 ፓርቲዎች አሉ በሚባልበት አገር ውስጥ የምርጫው ሁኔታ ተግባራዊ የማይሆን ነው” ሲሉ አማርረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ገዢው ፓርቲ የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሂደት እያጨለመ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ የገዢው ፓርቲ መጠነ ሰፊ እንቅፋቶች እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀው የምርጫው ሂደት በአሳሳቢና ከባድ አደጋ ውስጥ መውደቁን ገልፀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በምርጫው ሂደት ውስጥ እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች የምርጫ ቦርድና የመንግስት አካላት አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስዱና በምርጫው ሂደት ውስጥ የምንቀጥልበት ሁኔታ እንዲመቻችልን በአንክሮ ጠይቀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናትና ካድሬዎች እያደረሱት ያለውን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር ከቀጠሉ ምርጫው ኢፍትሃዊና የተጭበረበረ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡  

በተሾመ ንቁ
 
< Prev   Next >