| ቅንጅት ስንት ካሬ ሜትር ነው? |
|
| Sunday, 06 January 2008 | |
|
በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ ሰው የሚነጋገርበት ችግር ለአንድ ቦታ በርካታ ካርታዎች በብዙ ሰዎች መገኘታቸው ነው፡፡
ይህ በኢኮኖሚው መስክ ያለው የሕዝብ መወያያ አጀንዳ ሲሆን ተመሳሳይነት ያለው የሕዝብ መወያያ የሆነ ሌላ አጀንዳም አለ፡፡ እሱም የፖለቲካ አጀንዳ ነው፡፡ አጀንዳውም ለአንድና አንድ ለሆነ ቅንጅት ለተባለ ስም በርካታ ሰዎች የእኔ ነው፤ የእኔ ነው፤ የሚሉበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው፡፡ ችግሩ የእኔ ነው፤ የእኔ ነው፤ እያሉ በቅንጅት ባለቤትነት ላይ እየተጣሉ ያሉት ሰዎች ባለቤትነት የሚያዩት ቅንጅት አንድ ዓይነት ቅንጅት ነው ወይስ የተለያየ ነው የሚለው ነው፡፡ ቅንጅት ስንት ካሬ ሜትር ነው? የሚል ጥያቄ ከማንሳት ይልቅ የቅንጅት አባላት እነ ማን ናቸው? ወይም ቅንጅቶች እነማን ናቸው? የሚል ጥያቄ መጠየቁ ይመረጥ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የቅንጅት ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀመንበሯ የቅንጅት አባል አይደለችም በሚሉበት ጊዜ፣ የቅንጅት ምክትል ሊቀ መንበር ዋናው ሊቀ መንበር የድርጅቱ አባል አይደሉም በሚሉበት ጊዜ የቅንጅት ፀሃፊው የቅንጅት አባል አይደሉም፣ ተብለው በዋናው ሊቀመንበር በተፈረጁበት ጊዜ ስለ አባልነት ማውራት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ እንኳን ታች ያለው የቅንጅት አባል የቅንጅት አመራር አባልም የድርጅቱ አባል አይደለም እየተባለ ነው፡፡ ይህ ስለሆነም ነው እያንዳንዳቸው ቅንጅት የእኛ ነው የንብረትነት ማረጋገጫ ካርታ አለን እያሉ የሚጠይቁት፡፡ ስለዚህም ነው ለመሆኑ ካርታ አለን ማለት የቅንጅት ንብረትነት ማረጋገጫ ስንት ካሬ ሜትር ሆኖ ነው? ብለን የምንጠይቀው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ ሊቀመንበር በመሆናቸው የሚታወቁት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል፣ ቅንጅት የምባለው እኔ ነኝ ቢሉ የእሳቸው ቅንጅት ስንት ካሬ ሜትር ነው? የአቶ አየለ ጫሚሶንና የአቶ ተመስገን ቅንጅት ይጨምራል? ወ/ት ብርቱካን፣ ሊቀመንበሩ የለበትም የሚሉለት ቅንጅት ስንት ካሬ ሜትር ነው? የኢንጂነር ቅንጅትን ይጨምራል? የአቶ አየለ ጫሚሶን ይጨምራል? የአቶ ተመስገንን ይጨምራል? የዶክተር ብርሃኑ ነጋን ይጨምራል? ስንት ካሬ ሜትር ነው? አቶ አየለ ጫሚሶ፣ የእኔ ቅንጅት፣ ህጋዊ ቅንጅትና ህጋዊ ካርታ ያለው ነው ይላሉ፡፡ የአቶ ተመስገን ቅንጅትን ይጨምራል? የወ/ሮ ብርቱካንን ይጨምራል? የኢንጂነርን ይጨምራል? ወይስ ከዛ ውጭ የሆነ ካርታና ንብረት ነው? ስፋቱ ምን ያህል ነው? የት ጀምሮ የት ያበቃል? የአቶ ተመስገን ዘውዴ ቅንጅትስ ለየት ያለ ካርታ አለው? ወይስ ሌሎች የያዙትን የቅንጅት ካርታም ያጠቃልላል? ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ቅንጅት የሚሉትስ ሌሎች የያዙትን ያጠቃልላል? ወይስ ገንዘብ የሚያዋጣውን ብቻ የሚያጠቃልልና ኦዲት ይደረግ የሚለውን ከካርታ ውጭ የሚያደርግ ነው? የእሳቸው የቅንጅት ካርታ፣ ኢትዮጵያ ያለውን ቅንጅት ያጠቃልላል ወይስ በአሜሪካ ጭምር እስከ ፖርቹጋልና ብራስልስ ድረስ የተዘረጋው ነው? የፕሮፌሰር ታየ ቅንጅትስ? የአቶ ብርሃነ መዋ ቅንጅትስ? የአቶ ሰለሞን በቀለ ቅንጅትስ? የአቶ ታማኝ ቅንጅትስ? ወዘተ. ስንት ካሬ ሜትር ነው? የት ጀምሮ የት በምን ይወሰናል? ለየት ያለ ካርታ ነው ወይስ ሌሎች የያዙት የቅንጅት ካርታን ይወክላል? በቅንጅት ባለቤትነትና ካርታ ዙሪያ እየተጣሉ ያሉት እነዚህ የጠቀስናቸው ቡድኖች ብቻ አይደሉም፡፡ ካርታና ባለቤትነት አለ ሳይሉ እዚያና እዚህ የጨረቃ ቤት ሰርተው የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ ከዚህ መንግሥት ካርታና የባለቤትነት ማረጋገጫ ባናገኝም ከአስመራና ከሞቃዲሾ ማግኘት እንችላለን ብለው የሚያምኑም አሉ፡፡ ፊት ለፊታችን እነሱ እየመሩን እኛ እየታረምን ብሎ ተስፋ በማድረግ የነበረ የቅንጅት አባልና ደጋፊ የባለቤትነትና የካርታ ሽኩቻው እጅግ አሳዝኖታል፣ አሳፍሮታል፡፡ በጋራ ሆነው እኛን ጨምረው አንድ ባለቤትና አንድ ካርታ ለምን አይዙም እያለ እስከ አሁን ድረስ መጥቷል፡፡ አሁን ከህሊናውና ከልቦናው ውጭ ስለሆነበት ወደ ሌላ ቁም ነገር ለመግባት መገደዱ አይቀርም፡፡ እንዲህ መሆኑም ብቻቸውን ሊያስቀራቸው ይችላል፡፡ እና ምን ይሻላል? መፍትሄው ግልፅና ግልፅ ነው፡፡ አገርንና ሕዝብን ከግል ጥቅምና ስልጣን በፊት በማስቀደም፣ ከኢትዮጵያ ጥቅም ውጭ የሆነውን ሁሉ እርግፍ አድርጐ በመተው ለምን ወደዚህ ሽኩቻ ገባን ብሎ ወደ ውስጥ ማየትና መገምገም፣ የአባል ወሳኝነት መቀበልና ማረጋገጥ፣ የውስጥ ዲሲፕሊን ማስፈን፣ ፕሮግራም መንደፍና በዚህ ዙሪያ በጥቅም ሳይሆን በዓላማ መደራጀት፡፡ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻን መከተል፡፡ የሚሻለውና የሚበጀው ይህና ይህ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ድጋፍ ማጣት ብቻ ሳይሆን የውሸት የባለቤትነት ማረጋገጫ በመያዝ ፎርጂድ ካርታ በማሰራት መጠየቅን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የሚያሳዝነው፣ እነዚህ ቡድኖች በቅንጅት ባለቤትነትና ካርታ ዙሪያ ይህን ያህል ፀብ፣ ሽኩቻና መጠላለፍ ሲያካሂዱ፣ ስለህጋዊነቱ አያስቡም፣ አያዩም፡፡ የሚያሳዝነው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ራሳቸውም በየፊናቸው የባለቤትነት ማረጋገጫና ካርታ አለን፤ አለን ቢሉም አንዳቸውም ቢሆኑ ፈፅሞ ..የግንባታ.. ሥራ አለመጀመራቸውም ጭምር ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |