| መዋጮ ያልከፈሉ የአፍሪካ ኅብረት... |
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
|
መዋጮ ያልከፈሉ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት በማዕቀብ ስር እንዲውሉ ተጠየቀ
መዋጮ በማይከፍሉ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት በማዕቀብ ሥር እንዲውሉ የኅብረቱ ቋሚ ተወካዩች ኮሚቴ በ15ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ባቀረበው ሪፖርት ጠየቀ፡፡ እስከ አሁን ድርስ 111,797,082.86 ዶላር ውዝፍ እዳ አልተሰበሰበም የመዋጮ ውዝፍ እዳን በተመለከተ ከመዋጮ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ዝርዝር ሪፖርት የቀረበለት የህብረቱ ቋሚ ኮሚቴ መዋጮ ያልከፈሉ አገሮች በማዕቀብ ስር እንዲውሉ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቆ የውሳኔ ሪፖርቱን ለበላይ አካል አቅርቧል፡፡ የመዋጮ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ለቋሚ ኮሚቴው ካቀረበው ሪፖርት ለመረዳት እንደተቻለው የአፍሪካ ኅብረት አባላት ከሆኑት 53 አገራት መካከል 28ቱ ከአንድ አመትና ከዚያ በላይ ውዝፍ እዳ አለባቸው፡፡ ቀሪዎቹ 25 አገራት ክፍያቸውን በወቅቱ ያጠናቀቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ የወደፊት ክፍያን ጭማሪ አከናውነዋል፡፡ የመዋጮ ውዝፍ እዳ ባለመክፈላቸው ምክንያት በማዕቀብ ስር እንዲውሉ በቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ የቀረበባቸው አገሮች ኬፕቬርዴ፣ ማዕከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኤርትራ፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ ሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ፣ ሲሸልስና ሱዳን ናቸው፡፡ መዋጮ ባለመክፈላቸው ምክንያት ማዕቀብ እንዲደረግባቸው የውሳኔ ሃሳብ የቀረበባቸው እነዚህ አገራት ለኅብረቱ ጽ/ቤት አካላት በሚደረገው የሰው ኃይል ምልመላ የነሱ ድርሻ ክፍት ሆኖ ሊጠብቃቸው እንደማይገባ ተገልጿል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት አገራት መካከል ዴሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎና ብሩንዲ በግጭት ውስጥ በነበሩበት ወቅት የተከማቸባቸው ውዝፍ የመዋጮ እዳ እንዲሰረዝላቸው ማመልከታቸውንና ቱኒዝያም የ2004 እና 2005 የመዋጮ ሂሳብ እንደገና እንዲታይላት ጥያቄ ማቅረቧን ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡ ከቀውስና ግጭት እየወጡ ያሉት አባል አገሮች የመዋጮ ክፍያን በሚመለከት ረገድ ቋሚ ኮሚተው ባቀረበው ሃሳብ ከዚያ ቀደም ጊዜያዊና የተለየ አስተያየት በተደረገላቸው አገሮች አይን እንዲታዩ ጠይቋል፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |