| ሰንሻይን የ10.45 ቢሊዮን ብር የግንባታ እቅድ ያዘ |
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
![]() አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ከማሪዮት ዓለም አቀፍ ሆቴልና አይር /ኤ.ዋይ.አር/ ከሚባል የአሜሪካን አገር ኩባንያ ጋር ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት የተለያዩ ስምምነቶች ማድረጉ ተገለፀ፡፡ ኮንስትራክሽን ድርጅቱ 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የግንባታ እቅድ አቀረበ፡፡ አይር ከሚባል የአሜሪካ ኩባንያ በጋራ ኢንቨስትመንት (ጆይንት ቬንቸር) ለመስራት ስምምነት የተፈረመው (ጂ+ 12) የሆኑ ሦስት ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎችን ለመገንባት መሆኑን የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለንብረትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡ አቶ ሳሙኤል እንዳሉት ሆቴሎቹ እጅግ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ 252 ክፍሎች፣ 7 ሬስቶራንትና ባር፣ 4 የስብሰባ አዳራሾች እያንዳንዳቸው 1500 ሰዎች የሚይዙ፣ ጂም፣ ማሳጅና መዋኛ ያላቸው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል፡፡ ግንባታውም በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ሲሉ ባለሃብቱ ተናግረዋል፡፡ የሆቴሉ የማኔጅመንት ሥራ ለማሪዮት ዓለም አቀፍ ሆቴል ለመስጠት የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት መደረሱን አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል፡፡ የግንባታው አጠቃላይ ወጪ 850 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስም አስታውቀዋል፡፡ በመስቀል አደባባይ ጫፍ የተገነባው ባለ አስር ፎቅ ሆቴል 94 ክፍሎች ያሉት ሲሆን ጥር 2001 ሥራ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ ከሰንሻይን ኮንስትራክሽን ቢሮ በስተጀርባ ባለው ቦታ ላይ ባለ አስር ፎቅ 20 ዴሉክስ አፓርታማዎችና ባለ አምስት ፎቅ 5 ህንፃዎች ለመኪና ማቆሚያ ይገነባሉ፡፡ ግንባታዎቹ 3.5 ቢሊዮን ብር ይፈጃሉ፡፡ ከሰንሻይን የሆቴል አፓርትመንት ፊት ለፊት ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ወረድ ብሎና ከኢሲኤ በስተጀርባ በኩል ባለው ሸለቋማ ቦታ ላይ ባለ አስር ፎቅ 2 ህንፃዎች ለመገንባት መታሰቡን የኮንስትራክሽን ድርጅቱ ያወጣው እቅድ ያስረዳል፡፡ እንደ እቅዱ ግንባታው ግማሽ ቢሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ ከሁለቱም አካባቢዎች ለሚነሱ ዜጎች ምትክ የግል ቤትና የጋራ መኖሪያ ለማስገንባት 50ሺ ካሬ ሜትር ቦታ መዘጋጀቱን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ለግንባታው 300 ሚሊዮን ብር መያዙንና ግንባታው መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል አያት አካካቢ በሚገኘው ቦታ ሊሰራ ለታሰበው የሪል ስቴት ግንባታ ቦታ ጥያቄ ከኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቢሮ ቀና ምላሽ በማግኘት የኢንቨስትመንት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በእቅዱ እንደተመለከተው ባለ ስድስት ፎቅ ሶስት ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች፣ ለውጪ አገር ዜጎች ብቻ የሚሆን ልዩ መዝናኛ፣ በ550..000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የጎልፍ መጫወቻ ወደ ፊት በአካባቢው ለሚኖሩና ለውጭ አገር ዜጎች ይዘጋጃል፡፡ በዚሁ ቦታ በ800..000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በሪል ስቴት 640 ዘመናዊ የመኖሪያ ቪላ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል፡፡ ለሁሉም የተጠቀሱት ግንባታዎች 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል፡፡ ሲ ኤም ሲ አካባቢና በአያት አካባቢ ለወሰዱት የሪል-ስቴት ግንባታ ከከተማ ክልል በመራቁ በመካከለኛ ገቢ ላይ ያለው የአፓርትማ ነዋሪ ብዙ ርቆ በመሄድ የአፓርታማ ቤት በመፈለጉና መግዛቱ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ በነፃ የወሰዱትን ቦታ የሊዝ ሂሳብ በመክፈል ወደ ቪላ ቤት ግንባታ እንዲለወጥላቸው ለክልል 14 በተደጋጋሚ አመልክተው እንዳልተፈፀመላቸው አቶ ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡ በዚሁ ቦታ ላይ 189 ቪላዎች የሚሰሩ ሲሆን የዚህም የግንባታ ጠቅላላ ወጪው 3.5 ቢሊዮን እንደሚሆን በእቅዱ ተመልክቷል፡፡ በመጪው አምስት ዓመታት ውስጥ በጠቅላላው ብር 10.45 ቢሊዮን በሚገመት ወጪ የተጠቀሱት አምስት ዋና ዋና የልማት ሥራዎች ለማካሄድ መታቀዱን ከዝርዝር እቅዱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በህንፃ ግንባታ፣ በመንገድ ሥራ፣ በሪል ስቴት ልማትና በተያያዥ የንግድ ሥራዎች የተሰማራው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ድርጅት ግምታቸው 488 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ 41 ህንፃዎችን ሰርቶ አጠናቋል፡፡ ግምታቸው 207..166..815 የሚገመት 7 የመንገድ ሥራዎችን አጠናቆ አስረክቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት 1.2 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የመንገድ ሥራዎችን በመገንባት ላይ ሲሆን በህንፃ ግንባታና ሪል ስቴት ልማት በአራት ፕሮጀክቱ 897 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የግንባታ ሥራዎች እየሰራ ነው፡፡ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ የግንባታ ሥራ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ካፒታል፣ 448.9 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ቋሚና ተሽከርካሪ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች፣ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች ያሉት ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ከአስር ዓመት በፊት ካስገነባው ህንፃ በዓመት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት 6 ሺ የሚደርሱ ሠራተኞችን የያዘው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን በቅርቡ የሠራተኞቹን ቁጥር 11ሺ እንደሚያደርሰ ባለንብረቱ ገልፀዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ድርጅቱ በዱከም ተርሚናል መጋዘኖች፣ የጥገና ክፍል፣ የአጠቃላይ ፕሮጀክቶች የሎጅስቲክ ድጋፍ መስጫ ዲፓርትመንት ሲኖረው ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች አስተማማኝ የመለዋወጫ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ተሟልቶ እንደሚገኝ የተለያዩ ክፍል ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ከ100ሺ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ያለው የኮንስትራክሽን እቃዎች ማምረቻ ማዕከል ድንጋይ ይፈጫል፣ ብሎኬትና ጡብ ያመርታል፡፡ እንደ ኃላፊዎቹ ገለፃ ለኮንስትራክሽን ድርጅቱ የግንባታ እቃ በማቅረብ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል፡፡ በሲ ኤም ሲ ቁጥር 2 መሪ ሎቄ ሰፈር 11 አፓርታማዎች በ5 ዓይነት ዲዛይን እየተገነቡ ነው፡፡ ወጪውም 10 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ እጅግ ውብ የሆነውና ከገቡበት ለመውጣት የሚያስቸግረው ..ቦሌ ድሮ ቀረ.. የሚያሰኘው የሲኤምሲ ቁጥር 1 መሪለሮቄ መንደር የ211 ባለ አንድ ፎቅ ቪላዎች ግንባታ ተጠናቆ በፋሲካ በዓል ለባለንብረቶች ይሰጣል፡፡ እንደ አቶ ሳሙኤል ገለፃ መንደሩ በእቅዱ መሰረት ተጠናቋል፡፡ አንድም ሰው ውል አልፈረሰበትም፡፡ የግንባታ ወጪ ንሯል በሚል የዋጋ ጭማሪ አልተደረገበትም፡፡ ወደፊትም አይደረግም፡፡ መንደሩ የገበያ ማዕከል፣ የእድር (የማህበራዊ ግንኙነት ማመቻቺያ ቢሮ)ና ለነዋሪዎች ልጆችና ቤተሰቦች የስፖርት መስሪያ ቦታ አለው፡፡ ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ቤቶቹ በተለያዩ ዲዛይኖች የተሰሩ ሲሆን ዲዛይናቸው የሰጣቸው ውበት ልዩ ነው፡፡ በመደዳ በኮሪደር ተለያይተው የተቀመጡት የመኖሪያ ቪላዎች ውስጣቸው በኢትዮጵያ በመኖሪያ ቤት እየታየ ያለውን ለውጥ ያረጋግጣሉ፡፡ ዋጋቸውም ከ1 እስከ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ በሰንሻይን ገርጂ ቁ 1 ከ660 በላይ አባወራዎችን የሚይዙ አፓርትመንቶች በ897 ሚሊዮን ብር በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ ባለሃብቱ አስታውቀዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
|
| Last Updated ( Sunday, 03 February 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |