Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የቤተሰብ ህጉና ያልተመለሱ ጥያቄዎች
የቤተሰብ ህጉና ያልተመለሱ ጥያቄዎች Print E-mail
Sunday, 03 February 2008
Image“ከባለቤቴ ጋር በቤተክርስቲያን ህግና ሥርዓት ከተጋባን አሥር ዓመት ሆኖናል፡፡ በነዚህ ዓመታት የተጣላንበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ እንዋደዳለን፤ እንከባበራለን፡፡ እንከባከበዋለሁ፤ እርሱም እንዲሁ፡፡ ባለቤቴ የከባድ መኪና ሾፌር ሲሆን እኔ የቤት እመቤት ነኝ፡፡ ሁልጊዜ ለሥራ በሄደ ቁጥር ሀዘን ይሰማኛል፡፡ ባለቤቴ ሲበዛ ያሳዝነኛል እጨነቅለታለሁ፡፡
እሱም ቢሆን በሥራ ምክንያት እቤት ባይኖርም አንድም ቀን ሳይደውልልኝ አድሮ አያውቅም፡፡ በጣም ከመተሳሰባችን የተነሳ ደህና ምግብ የምመገበው እርሱ ሲኖር ነው፡፡ በሌለበት የማደርገው ሁሉ አያስደስተኝም፡፡ ይህንን ፍቅራችንን የሚያዩ “ትዳርስ እንደ ሕይወትና ሰሎሞን” ብለውልን ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ባለቤቴ ስራ ፈቶ የሰርጋችንን የስጦታ ሳህን ሳይቀር ሸጠን ክፉውን ቀን አሳልፈናል፡፡

አንድ ቀን የባለቤቴ ጓደኛ ሊያገባ አጃቢ እንድንሆነው ሰርግ ጠርቶን ወደ ሰርጉ ቦታ ለመሄድ እየለባበስን እያለ ድንገት የቅርብ ዘመዴ ትመጣለች፡፡ ሁለታችንም ከምንቀር እርሱ ወደ ሰርጉ እንዲሄድ አግባብቼው ቀረሁ፡፡ በግምት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ባለቤቴ ሞባይሉን እቤት ረስቶት ኖሮ ጮኸና ሳነሳው ጆሮዬ ላይ ተዘጋ፡፡ በተከታታይ ለአምስት ጊዜ ያህል ተደውሎ ሳነሳው ድምፄን ከሰሙ በኋላ ተዘጋብኝ፡፡ ለካ ደዋዮቹ የእኔንም የሞባይል ቁጥር ስለሚያውቁ የእርሱን እቤት ከተወው የእርሷን ይዞ ይሆናል በማለት በተደጋጋሚ ደውለው ሳነሳው ዘጉት፡፡ ቁጥሩን ሳየው የክፍለ ሀገር ስልክ በመሆኑ መልሼ ብደውል ሊያነሱት አልፈለጉም፡፡ ለሥራ የሚፈልጉት ደንበኞች ስለሚደውሉ ምናልባት የኔት ወርክ ችግር ይሆን? ብዬም ስላሰብኩ ከቤት ወጥቼ በህዝብ ስልክ ደወልኩላቸው፡፡ በተከታታይ መደወላቸውንና ባለቤቱ መሆኔን በመግለጽ መልዕክት ካላቸው ማቆየት እንደምችል ነገርኳቸው፡፡ በስልክ ውስጥ የሰማኋት ሴት እንደ መደንገጥ ብላ ስልኩን ጆሮዬ ላይ ዘጋችው፡፡

አመሻሹ ላይ በሞባይሌ ላይ ተደወለልኝ፡፡ በተመሳሳይ የክፍለ ሀገር ስልክ ሲሆን የደወልኩ ጊዜ ያነጋገረችኝ ሴት አልነበረችም፡፡ “ደግና ቆንጆ ሴት ባለቤቱም መሆንሽን እናውቃለን፡፡ ስላሳዘንሽን ሀቁን እንንገርሽ ብለን ነው፡፡ ባለቤትሽ በአንቺ ላይ ሌላ ትዳር ከመሰረተ ሰባት ዓመት አልፎታል፡፡ በነዚህ ዓመታት ሁለት ልጆች ወልዷል” በማለት አረዳችኝ፡፡ ላምናት አልቻልኩም፡፡ አንዳንድ ሰዎች መሃል ገብተው ዋሽተው እንደሚያጣሉ ስለምሰማ በፍፁም እኛ አንጣላም፡፡ አንቺ ልታጣይን ነው? አላምንሽም ብዬ በስልክ እየተከራከርኩ እያለ ባለቤቴ ስለመጣ ስልኩን ዘጋሁት፡፡

ባለቤቴም ምን ሆንሽ? ምን አገኘሽ? ብሎ ሲጠይቀኝ ሁሉንም ነገርኩት፡፡ ሐሰት ነው ብሎ ድርቅ አለብኝ፡፡ ያደርገዋል ብዬ ባላምንም ጠበቅ አድርጌ ልጠይቀው ፈለግኩ፡፡ ፣እባክህን እውነቱን ንገረኝ፡፡ እንዳትዋሸኝ” በእግዜአብሔር ስም እማፀንሃለው ብዬ ስጠይቀው፣ የሰማሽው ሁሉ እውነት ነው፣ አለኝ፡፡ ወዲያው ህሊናዬን ስቼ መሬት ተዘረርኩ፤ ለብዙ ቀናትም ታመምኩ፡፡ ኑሮዬ፣ ትዳሬ ብዬ ለፍቼ የሰራሁት ቤት ለሌላ ሰው ነበር ለካ? ሀዘኔን የምገልፅበት ምንም ቃላት የለኝም፡፡ የጠለቀ ሀዘን፣ ተስፋ መቁረጥ፣ መጨነቅ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ከደረሰብኝ ክህደት የተነሳ የመጣብኝ ችግር ነው፡፡

ባለቤቴ ልቤን አድምቶታል፡፡ በጣም የረገመኝ ማስመሰሉን ከየት አመጣው? በእኔ ላይ ድራማ ነው የሰራው፡፡ እንዴት አድርጌ ልጠርጥረው? አንድ ቀን እንኳን የተለየ ፊት አሳይቶኝ አያውቅም፡፡ አሁን አሁን ሳስበው ከባድ እንቅልፍ ውስጥ ነበርኩ? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡

ይህን ጉድ እንደሰማሁ ቤተዛታ ሆስፒታል ሄጄ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አደረግኩና ከቫይረሱ ነፃ መሆኔን አረጋገጥኩ፡፡ በኤች.አይ.ቪ ብትያዝስ ብሎ አልተጠነቀቀልኝም፡፡ ለምንድነው ከሌላ ሴት ጋር አብረህ እየሄድክ ለኤች.አይ.ቪ ብትጋለጥስ ብለህ ያልተጠነቀቅክልኝ? ብዬ ጠየቅኩት፡፡ የእርሱ ምላሽ ግን “እርሷ እንደዚህ ዓይነት ሴት አይደለችም” የሚል ነበር፡፡ ይህ አባባሉ ደግሞ ይበልጥ ውስጤን አሳመመኝ፡፡

አሁን ጤንነት እየተሰማኝ ነው፡፡ ወደ ተጠቂ ሴቶችና ህፃናት አገልግሎት ማዕከል ሄጄ ምክር በማግኘቴ ከእኔ ርቋል፡፡ በተሰጠኝ የምክር አገልግሎት ተጠቅሜያለሁ፡፡ ከንዴት የተነሳ ቤቱን ጥዬ ለመጥፋት ሀሉ አስቤ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ቆም ብዬ ማሰብ ጀምሬያለሁ፡፡ አስር ዓመት የደከምኩበት ንብረቴ የሌላ መሆን ስለሌለበት ባለቤቴ ቢበድለኝም ከቤት አልወጣሁም፡፡ ከቤት ብወጣ የቤቱን ንብረት በሙሉ ያሸሻል፡፡ በእኔ ላይ ያገባትን ሚስቱን ሊያስገባት ይችላል፡፡ በጥረቴ ባለንብረት አድርጌዋለሁ፡፡ ምን ዋጋ አለው ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንደሚባለው ሆነብኝ እንጂ፡፡ አሁን ለሁሉም አውቄያለሁ በህጋዊ መንገድ መብቴን አስከብራለሁ”

ይህ ታሪክ ፣ዜማ ሴቶች ለፍትህ፣ የተሰኘው ተቋም ባቋቋመው ፣የተጠቂ ሴቶችና ህፃናት፣ ማዕከል እርዳታ ፍለጋ ከሚመጡ ባለጉዳዮች የተመረጡ ታሪኮችን ካሳተመበት ቡክሌት የተገኘ ነበር፡፡ ታሪኩ እንደመነሻ ከመሆን በዘለለ ተሻሽሎ የወጣው የቤተሰብ ህግ የመሰል ታሪኮች መፍትሄ ሊሆን ይችላልን የሚለውን ጥያቄም እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

ቤተሰብ ሰላማዊ ቦታ ከመሆን አልፎ በተጓዳኞች መካከል አለመስማማት ሲፈጠር ሰላም የምታጣበት ቦታም ይሆናል፡፡ በህግ የተመሠረተ ጋብቻና በህግ ዕውቅና የሚሰጠው አብሮ መኖር መቀጠል ሳይችል በህግ ይፈርሳል፡፡

በ1992 ዓ.ም. የቤተሰብ ህጉ ቀደም ሲል ከነበረው የፍትሀ ብሄር ህግ ተገንጥሎ፣ ካለፈው ሲነፃፀር በተሻለ የሴቶችን መብቶች ያስከብራል ተብሎ ፀድቆ ወጥቷል፡፡ ሆኖም ህጉ በአፈፃፀም በኩል ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ይህንኑ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ የአፈፃፀም ችግሮችን አስመልክቶ ያስጠናውና በቅርቡ አሳትሞ ያወጣው ጥናት እንደሚለው የህጉ አፈፃፀም ችግሮች በተለይ በስድስት አካባቢዎች ላይ ጐልተው የሚንፀባረቁ ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ነጥብ ጋብቻንና ከጋብቻ ውጪ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አብሮ መኖርን ማረጋገጥ የሚለው ሲሆን በአንዲት ሴትና ወንድ መሀል ያለውን ግንኙነት በማረጋገጥ ረገድ የተጠቀሰውን ፣ሁኔታን ማረጋገጥ፣ የሚለው ሀረግ ዳኞች በተለያየ መልኩ የሚረዱት በመሆኑ አንድ ግንኙነት ጋብቻ ነው ወይስ ከጋብቻ ውጪ በግብረ ሥጋ ግንኙነት መኖር የሚለውን መወሰኑ እንደዳኞቹ ግንዛቤ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ወጥ አሠራር እንዳይኖር ማድረጉ በጥናቱ ተቀምጧል፡፡

ሁለተኛው ነጥብ አባትነት ማረጋገጥን የሚመለከት ሲሆን አንዲት እናት አንድን ሰው አባትነት ሲክድ/ማረጋገጥ ስትፈልግ በሚቀርብ ክስ መሠረት በፍርድ ቤት የአባትነት ጉዳይ ሲታይ በዳኞች በኩል ተቀባይነት የሚኖራቸው አካሄዶች የተለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በጥናቱ እንደተጠቆመው አባትየው ለህፃኑ ትምህርትና እንክብካቤ የሚውል ወጪ ማውጣቱን የሚመለከተውን ነጥብ የተለያዩ ዳኞች በተለያየ መልኩ ተመልክተውታል፡፡

የልጆች ቀለብ አወሳሰን ሌላው በጥናቱ የተጠቆመ ሌላው የቤተሰብ ህጉ የአፈፃፀም ችግር ሲሆን በዚህ ረገድ የተገለፀው አብረው በሚኖሩ ጥንዶች መካከል አባት ለልጆቹ ቀለብ የሚውል ገንዘብ የሚጠየቅበት ክስ ሲመሰረት ፍርድ ቤቶች (ከፍቺ በመለስ ባለ ጉዳይ) ለማስተናገድ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ የቀለብ ጥያቄ የሚስተናገደው ጥንዶቹ ከተለያዩ በኋላ የሚቀርብ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

የልጆች ሞግዚትነት ጥያቄ ሌላው በህጉ የአፈፃፀም ችግር ተከስቶበታል ተብሎ የቀረበ ነጥብ ሲሆን በህጉ በፍቺ ወቅት ልጆች የትኛው ወላጅ ጋር ይደጉ? የሚለውን ለመወሰን ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸውን ነጥቦች በግልፅ ቢዘረዝርም ዳኞች ውሳኔ በሚሰጡባቸው ጊዜያት በምን መመዘኛ ውሳኔውን እንደሰጡ አያስቀምጡም፡፡ ምክንያታቸውን ቢያስቀምጡ ውሳኔው የተሰጠበትን ሁኔታ ለማብራራት ይረዳል፡፡

ጋብቻ ወይም ከጋብቻ ውጪ በግብረ ሥጋ ግንኙነት መኖር ሲፈርስ የሚሰጥ ካሳን በተመለከተ ሌላው የአፈፃፀም ችግር የተከሰተበት ነጥብ ሲሆን በፍቺ ወቅት የሚሰጥ ካሳን/አንደኛው ወገን በድሎ ፍቺ ሲጠየቅ/ በተመለከተ ወጥ አሰራር የለም፡፡ በተለይ ጉዳት ተከስቶ ከሆነ ጉዳቱ ቁሳዊ/አካላዊ እና የሞራል መሆኑና ለየትኛው ካሳ ሊሰጥ ይገባል የሚለው ላይ ስምምነት የለም፣ የካሳው መጠን ምን ያህል መሆን አለበት በሚለውም እንዲሁም፡፡

የንብረት ክፍፍል ሌላው የአፈፃፀም ችግር የሚታይበት፣ በቶሎ የማያልቅ ይልቁንም በሴቶች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ጉዳይ ነው፡፡ በህጉ መሠረት የንብረት ክፍፍል ፍቺው በተፈፀመ ስድስት ወራት ውስጥ ማለቅ አለበት ቢልም በብዙ የፍቺ ጉዳዮች የንብረተ ክፍፍል ዓመታትን ይፈጃል፡፡

በዚሁ በንብረት ክፍፍል ላይ የተቀመጡት የህጉ አንቀፅች ሙሉ በሙሉ የማይተገበሩባቸው የፍቺ ጉዳዮችም ብዙ ናቸው፡፡ ይኸውም በሴቷና በቀድሞ የትዳር ጓደኛዋ መካከል የሚፈጠረው ውዝግብ እንዳይቆም ያደርጋል፡፡

እንደ የቀበሌ ቤት፣ የጡረታ አበል የመሳሰሉት ደግሞ በፍርድ ቤቶች ግልፅ አቋም ያልተያዙባቸውና የጋራ ሀብት ውስጥ ይካተታሉ/አይካተቱም የሚለውም በግልፅ የማይታወቅባቸው ናቸው፡፡

ፍቺን በቶሎ በመወሰን፣ በአብዛኛው ለሴቶች በጐ ውጤት የማያመጡ የቤተዘመድ ሽማግሌና ጉዳዮችን ማየቱና ሌሎችም በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ መቅረታቸው ለሴቶች እፎይታን ያስገኙ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ሆኖም በአብዛኛው በፍቺ ወቅት /ፍቺ በፍርድ ቤት ከመረጋገጡ/ በፊት ከቤት ለመውጣት የሚገደዱና የፍርድ ቤቱን ሂደት ለማስጨረስ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና የሚከሰትባቸው ሴቶች ሂደቱ በአንፃራዊ መልኩ በቶሎ ቢያልቅም ቀሪ አፈፃፀሙ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ሌላ ራስ ምታት ሆኗል፡፡

በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ ከፍቺ በኋላ በዘገየ የንብረት ክፍፍል ጉዳይ እያለ የቀድሞ ባለቤታቸው ሌላ ትዳር የሚፈፅምና ንብረቱን ለሌላ የሚያጋራ፣ በዚህም ምክንያት ጉዳያቸው ውስብስብ የሚሆን ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ ዋናው ተከሳሽ በሞት በሚለይበትና ሁለተኛ ተጋቢ በሚከራከርበት ዓይነት ጉዳዮች ሁለተኛ ተጋቢ በሚከራከርበት ዓይነት ጉዳዮች ደግሞ ሁኔታው የበለጠ የተወሳሰበ ይሆናል፡፡

በኢኮኖሚ ጥገኝነት ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሴቶች በትዳር አለመስማማት ሲገጥማቸውና ፍቺ ሲጠይቁ ፍቺው ተወስኖ የንብረት ባለቤት  እስኪሆኑና መቆያ እስከያገኙ እንዲሁም የልጆች ቀለብ እስኪቆረጥላቸው ያለው ጊዜ ልጆቻቸውን ይዘው በየቦታው ለመንከራተትና ለበርካታ ችግሮች የሚጋለጡበት ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት ጐዳና የወጡ ሳይቀር መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህም የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ የአፈፃፀም ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው የግድ ነው፡፡

በቤተልሔም ነጋሽ
 
< Prev   Next >