| ባላደራ ጮኸ ከተራራ!... |
|
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
|
ባላደራ ጮኸ ከተራራ! እስከማዕዜኑ ተሐነክሱ!
(እስከመቼ ታነክሳላችሁ) ከዮሐንስ አርአያ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ምስል ከፍ ባለ ደረጃ በቢልቦርድ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዐውደ ምሕረት የመሰቀል አዝማሚያ ተገቢነት እንደሌለው ከትውፊትና ከሥርዓት አኳያ በዚሁ ጋዜጣ በዘርዓ ብሩክ ሰላማ መጻፉ ይታወሳል፡፡ ዘርዓ ብሩክ ያቀረበበት መንገድ በአስተዋይ ኅሊና፣ በትሁት ሰብእና ለቤተክርስቲያን አበው ተገቢውን ክብር ሰጥቶ መሆኑን አይተናል፡፡ ለዚህ ምዕዳንና ተግሳጽ ለያዘ ጽሑፍ መልስ ይሆን ዘንድ በድፍረት የታጀበው የወልደ ሥላሴ ዘብሔረ ካኑ ጽሑፍ ቀዳሚውን ጽሑፍ ያልተገነዘበ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ “የአመፅ አባት የወለደው የጥፋት ብዕር” ምን ማለት ነው? “ወልደሥላሴ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን በቅጡ የሚያውቅ እንዳልሆነ ከጽሑፉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሥርዓቷን ትውፊቷን መሠረቷን ላለማወቁ ጽሑፉ በግልጽ ያሳያል፡፡ የዘርዓ ብሩክ ፅሑፍ የተነሳው ፎቶ ግራፍ መስቀል የክብር መግለጫ አለመሆኑና በቤተክርስቲያኗ ትውፊትም የተለመደ አለመሆኑን ነበር፡፡ በየጽሕፈት ቤት በመጠነኛ መልኩ ሊደረግ ይችላል፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔር በሚፈጸምበት፣ ምእመናን ለፈጣሪ ለልዑል እግዚአብሔር የአምልኮት ሰጊድ በሚያደርጉበት ስፍራ ላይ ቤተክርስቲያኑን በሚከልል ደረጃ ቢልቦርድ መትከል ተገቢ አለመሆኑን ማሳየት ነው፡፡ ወልደሥላሴ ግን በሚወርፉ ቃላት ፀሐፊውን አንጓጠው ፓትርያርኩ ..ፍፁማዊ.. በመሆናቸው ለቅዱሳኑ የተደረገው ሁሉ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያስባሉ፡፡ መነጋገራችን ለቤተክርስቲያናችን የሚበጅ ነውና እውነቱን ሳንደብቅ፣ በውዳሴ ከንቱ ሳንንበረከክ መናገር እንጀምራለን፡፡ አንዳንዶቹን ልጥቀስ በአዲስ አበባ ያሉ አድባራት በሕዝብ መሰራታቸውን ከፓትርያርኩ አመራር ተለይቶ አይታይም ይሉናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ቤተክርስቲያን ሲገነቡ ግለሰብ “አባቶች” ከሚያዙበትና ከሚናዘዙበት አንዲት ቤሳ ረድተዋል ማለታቸው ይሆን? እንኳንስ ሊለግሱ ለምርቃትም ሲመጡ በጭንቅ ነው፡፡ አበባዎቹ ቤተክርስቲያኖችስ ዕድሜ ለለጋሱና ለሃይማኖቱ ቀናዒ ለሆነው ሕዝብ በአስደናቂ ሁኔታ ተሰርተዋል፡፡ ግን በአቡነ ጳውሎስ ዘመን የገጠር ቤተክርስቲያናት በስፋት እየተዘጉ ነው፤ እየፈረሱ ነው፤ ፓትርያርኩ ከሚያዙበት ከቁልቢ ገብርኤልና ከሌሎች የሚሰበሰበው ገንዘብ ግን ለግለሰቦች ይቸራል፡፡ በችጋር አለንጋ እየተገረፉ ገዳማቶቻችንን እየጠበቁ ያሉት አባቶች በችግር ላይ ናቸው፡፡ ተርፎ ለግብዣና ለስጦታ ከሚውለው ገንዘብ እንካችሁ ብሎ የሚጥልላቸው የለም፡፡ አንድ የሃይማኖት አባት ቤተክርስቲያን ሲመርቅ በ60ና 70 ሺህ ብር ከጊዮንና ከዋቢ ሸበሌ ካልተደገሰ አልመጣም? ሲል በየገጠሩ እየፈረሱና እየተበተኑ ያሉትን ቤተክርስቲያናትና ምዕመን አስተውሏል ማለት ይቻላል? እነዚያንስ ካልጠበቀ ኃይማኖት ጠብቋል ማለት ይቻላል? እንኳንስ በሩቅ ርቀት ያሉት አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ በርካታ አድባራት በችግር ምክንያት መዘጋታቸውን መካድ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በዓይን የሚታይ ነውና፡፡ ቤተክርስቲያናችን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውድድር ውስጥ ያለች እንደመሆኗ ራሷን መርምራ ማስተካከል አለባት፡፡ ጉድፏን መጥረግ፣ ሊተበትቧት የሚፈልጉትን ማጽዳት አለባት፣ አደግዳጊዎችና ለዕለት እንጀራቸው በትህትና ስም የሚያደዘድዙ አገልጋዮች ይገሏታል እንጂ አያድኗትም፡፡ ዝናብ እንደመታው ውሻ እጅን ሸግቦ ፍጡሩን ..አንተ መለኮት ነህ.. ማለት ትህትና ተብሎ ሊፈረጅ አይችልም፡፡ ፀሐፊው የፓትርያርካችንን “ቅድስና” ሊነግሩን ሞክረዋል፡፡ እንደዚያ ቢሆንማ እድላችን? ነገር ግን የአንድ መንፈሳዊ አባት ቅድስና በሁሉም፣ ካልሆነም በብዙው የመንፈስ ልጆቹ የሚታወቅ ሲሆን እንጂ በዙሪያ የከበቡት ጋሻጃግሬዎች ምስክርነት ያለው አይደለም፡፡ እንኳንስ መንፈሳዊ አባቶች የፖለቲካ መሪዎች በጊዜያቸው አሽቃባጭና አደዝዳዥ አላቸው፡፡ ነገር ግን ስማቸውን ታሪካቸው ከሥልጣን የወረዱ እለት እንደ ጉም በኖ ይጠፋል፡፡ በሕዝብ ልብ ያሉት ግን ዝንተ ዓለም ስማቸው ሲነሳ ይኖራል፡፡ ፓርትርያርክ አባ ጳውሎስ በሕዝባቸው የመታመን ደረጃ የበቁ የምናውቃቸውን ሁሉ መዘርዘር ደስ የማያሰኝ ስለሚሆን ትተነው ፀሐፊው ባሉት ላይ ብቻ እንጠያየቅ፡፡ በገጠር ያሉ ገዳማትና አድባራት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተዘጉ ባሉበት ወቅት የሕዝብ ገንዘብ ግን ለግለሰቦች ይረጫል፤ ለቀረቡ ሰዎች መሸለሚያ ይሆናል፡፡ ዛሬ ደግሞ እንሸልምዎት በሚሉ “ወዳጆች” አቅራቢነት ልሸለምበት ሲባል ለእምነታችን አያስፈራምን፡፡ ማስረጃ ላቅርብ፡፡ በፓትርያርክ ልዩ ፅህፈት ቤት ፓትርያርኩ ብቻ የሚያዙበት ሂሳብ አለ፡፡ ያ ሂሳብ ከቁልቢ ገብርኤል፣ ከአዲስ አበባ አድባራት፣ ከልማት ኮሚሽንና፣ በእርዳታ ስም ከውጭ ከሚመጣ ገንዘብ እየተቀነሰ የሚከማች ነው፡፡ ፓትርያርኩ ይኸን ገንዘብ ለተቸገሩ ቤተክርስቲያናት ማዋል ሲገባቸው፣ የት እንደሚገባ የሚያውቅ የለም ኦዲት መደረጉንም ይነግሩን እንደሆን እናያለን፡፡ በአንድ ወቅት የሰሌዳ ቁጥሩ አ/አ321894 የሆነ ቶዮታ ላንድ ክሩዘር ባለቤት የሆነ ሰው በሌላ ሰው ላይ አደጋ ያደርሳል፡፡ ለካስ የምከፍለው ይሰጠኝ ስላሉ (ቅርበታቸውን ተማምነው ነው) 5,000 ብር እንዲከፈል ያዙላቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ ለምን እንደምትከፍልላቸው አልተገለፀም፡፡ ሰውዬው ቀርበው ለመውሰድ ስላልፈለጉም በሌላ ሰው ስም ቼክ እንዲሰራላቸው ፓትርያርኩ አዘው በቁጥር 260/11/89 ተፅፎ ይወስዳሉ፡፡ ልብ በሉት፡፡ የሚዘጉ ቤተክርስቲያን፣ የተራቡ ካህናት፣ ሞልተው ለባለ ክሩዘር “ሃብታም” ክፍያ እርዳታ ማድረግ ምን መስሎ ይታያል? የዚህ ዓይነት ደብዳቤ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ለአንዲት ወይዘሮ በቁጥር 120/423 በተፃፈ ደብዳቤ የተሰጠው ዓይነት ማለቴ ነው፡፡ ወልደሥላሴ ምንም የማናውቅ አድርገው ስለነካኩን እንጂ ይኸን ሁሉ መጥቀስ አስፈላጊ ባልሆነ ነበር፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ገንዘብ በእርዳታ ስም ለማንም ግለሰብ መስጠት ቅድስናን ያመለክታል ወይ? የአክሱም ተወላጆች ጋር የተጣሉበት ጊዜ በዝርዝር እንደቀረቡት ከሆነ ፓትርያርካችን ከ30 በላይ ዘመዶቻቸውን ወደውጭ ልከዋል፡፡ ማስተባቢያ እስካልተፃፈ ድረስ ይኸንኑ ማመን ነውር አይመስለኝም፡፡ ይኸ ቅድስናን ያሳያል? ፎቶግራፍ ለመስቀል የሚያበቃ ቱርፋት መኖሩን ያመለክታል? ገንዘብ ካላቸው ሰዎች ጋር ሆኖ ወይም በራስ ገንዘብ ሺ ጊዜ መሸለም ሺ ጊዜ መወደስ ቀላል ነው፡፡ ግን ከሕዝብ ያርቃል እንጂ አያቀርብም፡፡ አሁን ደግሞ የመኳንንት ልጆች የሆኑት ወይዘሮና አቶ፣ ካልሸለምናቸው ብለው ያዙን ልቀቁን ሲሉ ሰምተናል፡፡ ማ ማን ሆኖ ነው በታላቋ ቤተክርስቲያናችን ስም ሸላሚ የሚሆነው፡፡ እኛ ማን ነን ብለው ሲጠይቁ ከእምነታቸው ጭምር የሚያውቃቸው መኖሩ መጠርጠር ጥሩ ነበር፡፡ አንድም የሚያሳዝነው ታላቁን የእኔነት ሹመት የያዘ አባት በእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ለመሸለም ሲፈልግ ነው፡፡ የብዙሃን መንፈሳዊ አባት ብቻ ውዳሴ ሲታለል ያሳዝናል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክነቱን ሲይዙ ዘርፈ ብዙ የወንጌል ስርጭትን ሁሉም ጠብቆ ነበር፡፡ ሕንፃ ቤተክርስቲያን በምእመናን ከፍተኛ ጥረት የመገንባቱን ያህል ለትምህርተ ወንጌል የተደረገው ጥረት የጎላ አይደለም፡፡ ከወንጌል ይልቅ ወንጀል ይጎላ ነበር፡፡ መንፈሳዊ ማኅበራት በአጓጉል ቅጥያ፣ መሠረተ ቢስ ምክንያት እንዲበተኑ ምእምናን ለተኩላዎች ሲሳይ እንዲሆኑ የተደረገበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ለትምህርተ ወንጌል ድጋፍ ከሚሰጠው አንዱና ዋነኛው የካሴት አገልግሎት ነው፡፡ በንጉሡ ዘመንና በኋላም በደርግ ጊዜ በቤተክህነት ተጠናክሮ የነበረው በስብከተ ወንጌል ሐዋሪያ ተልዕኮ መምሪያ ስር የነበረው የካሴት ሐዋርያ አገልግሎት እንዲጠፋ የተደረገው በዘመነ ቴክኖሎጂ፣ በዲጂታል ዘመን ተጠናክሮ መታየት በሚገባበት በአሁኑ በአባ ጳውሎስ ዘመን ነው፡፡ ለመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ ከምእመናን ጋር የምትገናኝበት ጋዜጣና መጽሔት አላት? ጋዜጣ ማለት በዕለት ወይም በሳምንት የሚወጣውን እንጂ በየሁለት ወሩ የሚወጣውን፣ ሲያሰኘውም የሚከርመውን “ጋዜጣ” ማለት ያስቸግራል፡፡ በአቀራረባቸውና በአዘገጃጀታቸው በምእመናን ዘንድ ተወዳጅ የነበሩት “ድምፀ ተዋሕዶ” ጋዜጣ፣ “ትንሣኤ”ና “ማዕዶት“ መጽሔቶች፣ የት ደረሱ? በዘመነ ደርግ ያልጠፉት እነዚህ የኅትመት ውጤቶች አሁን እንዲኖሩ ያልተፈለገው ለምንድን ነው? የማን አመራር ውጤትስ ነው? ይኸ እምነቱን የማስፋፋት ብቃትን ሊያሳይ ይችላልን? መንግሥት ለሃይማኖት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አልፈቅድም፤ ቢልም ሌሎች የክርስትና ሃይማኖት ተቋማት ግን በእጅ አዙር ከውጭ አገር እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ የቤት ሥራቸውን በአግባቡ ይወጣሉ፡፡ የኛ ቤተክርስቲያን ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከተለያዩ አካባቢዎች ለማሰራጨት ምን ያቅታታል? ራእይ ያለው መሪ ባለማግኘቷ ለራስ ክብርና ልዕል የሚተጋ መሪ በማግኘቷ ነው ትኩረት ያጣችው፡፡ የየአብያተ ክርስቲያናቱ አለቅነት አሿሿም በእውቀት ሳይሆን በጅረት መሆኑ ያስተዛዘበ ጉዳይ ነው፡፡ የአንድ አካባቢ ሰዎች የአዲስ አበባን አብዛኛውን አድባራትና ገዳማት የተቆጣጠሩበት ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ ይኸ መንፈሳዊ ብቃትን ያሳያልን? በንጉሡም ሆነ በኋላ በደርግ ኃላፊዎች የነበሩ አባቶች ካህናት ሲመድቡ (ሲቀጥሩ) ጥያቄያቸው ምንድን ነበር፡፡ አሁን ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው፡፡ ወልደሥላሴ በክታባቸው ስለ ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ አንስተዋል፡፡ በፓትርያርኩ ጥረት ኮሌጁ መመለሱ በአሁኑ ጊዜ በዲግሪና በዲፕሎማ ደቀመዛሙርት እንደሚያስመርቅ ገልፀዋል፡፡ የኮሌጁ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑ የትምህርት ሥርዓቱና አሰጣጡ ውዝግብ አስከትሎ በሁከት እስከመዘጋት መድረሱ የማን አመራር ውጤት ነው? የኮሌጁ ዲን የነበሩት የግብፅ ኦርቶዶክስ ምሁሩ ሲለቁ፣ የቤተክርስቲያኒቱና የኮሌጁን አካሄድ አይተው በዚህ አካሄድ ቤተክርስቲያኒቱ ከ1ዐ ዓመት በኋላ ምን ሊያጋጥማት እንደሚችል የተናገሩት እየተፈጸመ መሆኑ እያየን ነው፡፡ የቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነትም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑ አይሳትም፡፡ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በሚደረጉ ጉባኤዎች የኢትዮጵያ ተሳትፎ እስከዝምታ የደረሰ ነው፡፡ የኦሬንታል፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክሶችና ካቶሊኮች በጳጳሳት ደረጃ ሲወያዩ ብዙውን ጊዜ የኢትዮጵያ ውክልና ከማኅበረ ካህናት የዘለለ አይደለም፡፡ ለምን? ሲኖዶሱ ያቀፋቸው አብዛኞቹ ጳጳሳት የዕውቀት ደረጃ እምን ድረስ ቢሆን ነው? የቅዱሳት መጻሕፍት ኅትመትና ስርጭት ለሊቃውንት ያደላ እንጂ ምእመናን ተኮር አለመሆኑ አንዱ አሳሳቢ ችግር ነው፡፡ በዘመኑ አጻጻፍና አቀራረብ መጻሕፍትን ለማዘጋጀት የተደራጀ የሥነ ጽሑፍ ክፍል አለመኖሩ ገሀድ ነው፡፡ በአልጋወራሽ ተፈሪ መኰንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) አማካይነት የታተሙት መጻሕፍትን እንደ ጥንቱ አሳትሞ ማሰራጨት ተጠቃሚው ማን ነው? የዘመኑ ትውልድ በሚረዳው አማርኛ በተለይም ሁለተኛና ሦስተኛው ቋንቋው ለሆነው የተለያየ ብሔረሰብ ምእመን በሚገባው ቋንቋ መጻሕፍት ማዘጋጀት ይገባ ነበር፤ ፈጽሞ አልሆነም፡፡ የሌላውን አገርና ሃይማኖት ትጋት ትተን የቅርባችን የግብፅ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ እንደጻፏቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት፣ ሌሎች ጳጳሳትም እንደተጉበት ሁሉ እነ አባ ጳውሎስ እስካሁን አለመትጋታቸው ለመንፈሳዊ ድህነታችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ካሉት ጳጳሳት ይልቅ ባሕር ማዶ ያሉትና በሕይወት የሌሉት አበው ጳጳሳት ያበረከቷቸው መጻሕፍት ዐቢይ አገልግሎት መስጠታቸው ግልጽ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤተክህነት ከማኅበረ ምእመናን ወገን የሆኑ ዘመናዊውን ከጥንታዊው ጋር አቆራኝተው የያዙ ምሁራንን ታስጠጋለች? አታደርገውም፤ ታርቃለች እንጂ፡፡ በዘመነ ቴዎፍሎስ እስከ ዱክተርና የደረሱ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች የሆኑትን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቤተክህነት ታቀርባቸው ነበር፡፡ ዓለማቀፍ ጉባኤ ሲኖር በማደራጀት የሕትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት ይሳተፉ ነበር፡፡ እነዚያ ፕሮፌሰሮች እስከ ክህነት ድረስ የተሰጣቸውም ነበሩ፡፡ በዘመነ ጳውሎስ በቅርቡ የደመራ ዕለት በተካሄደው የሰላም ዓለማቀፍ ጉባኤ አጋፋሪ የነበሩት የቤተክርስቲያን ሰዎች በአፍሪካ ያሉ የዘመኑ የፖለቲካ ፊታውራሪዎች መሆናቸው በመድረኩም በቴሌቪዥንም ነው፡፡ ግሪክ ካይሮ ላይ የአፍሪካ ፓትርያርክ ስታስቀምጥ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ የአክሱም ጳጳስ ብላ ያስቀመጠችው መዋቅር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ግን እስከ አሁን በአቴንስ መንበረ ጵጵስና ማስቀመጥ የግሪክ ፍላጎት ምን ይሆን? የግሪክና ምሥራቅ ኦርቶዶክስ አስተምሕሮ የሚከተሉ ኢትዮጵያውያን ኅብረት ፈጥረው መንበረ ጵጵስና እናቋቁም ቢሉ ተባባሪያቸው ግሪክ ልትሆን እንደምትችል እነ አቡነ ጳውሎስ ተረድተውታል ወይ? ድሮ በነበረው በአስተምህሮ የመከራከር ሁኔታ ዳግም ቢያንሰራራ የየራሱን ተቋም ሊመሠርት ቢነሳ አሁን ባለው የዴሞክራሲ መብት አንፃር ሊከላከለው የሚችል የለም፡፡ ከለላ የነበሩት ንጉሣዊውና ደርጋዊው ሥርዓቶች ቤተ ክህነት ራእይ ኖሯት ሊፈጠር የሚችለውን ክስተት እንዳይከሰት ሰላማዊ ጥንቃቄ መፍጠር ይገባታል፡፡ ብልህ አመራር የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የኢትዮጵያን ሚሌኒየም አስመልክቶ የተለያዩ የዓለም ሃይማኖት መሪዎችን ጋብዞ ውይይት ማካሄዱ ጥሩ ቢሆንም፣ በመስከረም 2000 ዓም የተካሄደው ጉባኤ ወደ ዓለማዊነት ያደላ በቤተክርስቲያን፣ በክርስትናና በምእመኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ዓለማቀፍ ችግር ላይ ያላተኮረ በመሆኑ ቅሬታን ያስከተለ ነበር፡፡ ከመስኮብና ከአንዳንድ አገራት የመጡት የኦርቶዶክስ ልዑካን በነገረ መለኮት ዙሪያ፣ በአክራሪዎች ሳቢያ በክርስትና ላይ እየደረሰ ባለው ችግር ዙሪያ እንወያይ የሚል አጀንዳ እንዲቀርብ ቢጠይቁ በጎ ምላሽ ባለማግኘታቸው ቅሬታ ማሰማታቸውን አንዳንዶችም ከውይይቱ ማቋረጣቸው ያየነው፣ የሰማነው ጉዳይ ነው፡፡ አቶ ወልደሥላሴ በክታባቸው የፓትርያርክ ጳውሎስን ዓለማቀፍ ሊቅነት ከጥቂት የዓለም ምሁራን ግንባር ቀደም መሆናቸውን ይነግሩናል፡፡ መጠየቂያቸው ብሎም ማስረጃቸው ምንድን ነው? የንግግርና የምርምር ቋንቋ ዕውቀቶች ሁለት ነገሮች መሆናቸውን አልተረዱትም፡፡ ዝነኛ የሃይማኖት ምሁራን ተርታ የሚያሰልፋቸው የጻፉት መጽሐፍ አለን? እስካሁን በሚያውቋቸው የውጭ ቋንቋዎች ቀርቶ በአማርኛና በትግርኛ ለምእመናንም ሆነ ለደቀመዛሙርት ያተረፏቸው አንድም የታተመ መጽሐፍ አላየንም፡፡ ከንቱ ውዳሴ ምን ይጠቅማል? ወልደሥላሴ ፓትርያርኩ ከበቂ በላይ ቅድስና እንዳላቸው ነግረውናል፤ በድንግልና መኖራቸውንም ጭምር፡፡ ቀደም ያለው ጽሑፍ በዚህ ጥርጣሬ ስላላሳደረ ለምን እንዳነሱት አልገባንም፡፡ ግን ባለፈው ለጳጳስ የማይፈቀደውን ቆባቸውን አውልቀው ፎቶ ታትሞ አይተናል፡፡ ይኸ ቅድስናን ያሳይ ይሆን፡፡ ቤተክህነት መታደስ ያስፈልገዋል፣ የአማካሪዎች ምክር ቤትም ያስፈልገዋል፡፡ ከምእመናንና ከካህናት ዘመናዊ ትምህርት እስከ ፕሮፌሰርነት የደረሱ ምእመናን ቢኖራትም ልትጠቀምባቸው አትፈልግም፡፡ ለምን? መንግሥት መሪ ፓርቲ እያለው የአማካሪ ምክር ቤት አለው፡፡ ከዓለማውያንም መማር ያስፈልጋል፡፡ በ1985 ዓ.ም ከዘመነ ቴዎፍሎስ ዠምረው የነበሩ ምርጥ የቤተክርስቲያን ዘመናዊ ምሁራን ምክር ቤት አቋቁመው ቤተክርስቲያኒቱን እንርዳ ባሉ በአባ ጳውሎስ እንቢተኛነት ጅምሩ እውን ሳይሆን ቀርተዋል፡፡ በፓትርያርክ ጳውሎስ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከምን ጊዜውም የከፋ ችግር አጋጥሟታል፡፡ ፓትርያርኩ 1984 ዓ.ም ላይ ከመንበሩ ሲቀመጡ ያስቀረጹት “ነዋ ወንጌለ መንግሥት” (እነሆ የመንግሥት ወንጌል) ዓርማ ከተግባር ይልቅ መፈክር ሆኖ ለመቅረቱ ብዙ ማስረጃ መደርደር አያስፈልግም፡፡ በቤተክህነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተደጋጋሚ በመፈጸሙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰጠው ማሳሰቢያ ባለመፈጸሙ ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ማስጠንቀቁ ለጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ታላቅ ሀፍረት ነው፡፡ ፓትርያርኩ ኅዳር ጽዮንና ሚሌኒየምን በአክሱም፣ ጥምቀትና ሚሌኒየሙን በጎንደር ተገኝተው ሲያከብሩ፣ ሲያስከብሩ በልደትና ሚሌኒየም የላሊበላ ክብረ በዓል ወቅት ያለመገኘታቸው ምስጢር ምን ይሆን? ቤተክህነት እስከ መቼ ነው የምታነክሰው? እንደ ወልደ ሥላሴ ያሉ ጨዋ ጸሐፍት የሚቀልዱባትስ እስከ መቼ ነው? ሳይመረምሩ ከሚጽፉ፣ ብዕር ከሚጨብጡ እግዜር ይጠብቅ፡፡ ወልደ ሥላሴ “ኢትሒስ ዘእንበለ ትሕትት” (ሳትመረምር አትንቀፍ) የሚለውን የታላቁን መጽሐፍ አነጋገር ያውቁታል? በመጨረሻ አንድ አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ የሚሌኒየሙ ተሸላሚ እንዲሆኑ ተወስኗል ይባላል፡፡ ሸላሚዎቹና አጋፍሬዎቹ ደግሞ የግል ወዳጆች ናቸው፡፡ ከተፈቀደልን ሁሉንም እንዘረዝረዋለን፡፡ ግን በእምነቱ ተከታይነቴ አንድ ምክር ላቅርብ ሽልማቱ ይቅርብዎት፡፡ አንዳችም ነገር አይጨምርልዎትም፡፡ ግን ብዙ ነገር ይቀሰቅስብዎታል ጥላቻን ያተርፉበታል ከመለስ ዜናዊ ተማሩ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |