| ተመድ ለኬንያ ውዝግብ መፍትሄ... |
|
| Sunday, 03 February 2008 | |
|
ተመድ ለኬንያ ውዝግብ መፍትሄ እንዲፈልግ ጥሪ ቀረበ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በርናንድ ኩችነር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኬንያን ውዝግብ መፍትሄ እንዲፈልግ ሲሉ ለፀጥታው ምክር ቤት ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በርናንድ ኩችነር የኬንያን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ተከትሎ የተነሳው ውዝግብ ወደ ጎሳ ግጭት ማምራቱን ጠቁመው ተመድ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበዋል፡፡ ሚኒስትሩ ከፓሪስ በላኩት ደብዳቤ “በኬንያ ኢሰብዓዊ ድርጊት እየተፈፀመ ነው፤ ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ ነው፤ ህፃናትና ሴቶች ተደፍረዋል” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልፀዋል፡፡ “ተመድ ኢሰብአዊ ጥቃትን የመከላከል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል፡፡ በኬንያ መንግስትና በተቃዋሚ ፓርቲ መካከል በናይሮቢ ተጀምሮ የነበረው ድርድር ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባላት በፖሊስ ከተገደሉ በኋላ ተቋርጧል፡፡ በተያያዘ ዜና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር አልፋ ኦማር ኮናሬ በኅብረቱ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ መሪዎች ለኬንያ ውዝግብ መፍትሄ እንዲያፈላልጉ አሳስበዋል፡፡ የቻድ አማጽያን ወደ አገሪቱ መዲና የሚያደርጉትን ግስጋሴ አጠናክረዋል የቻድ አማጽያን በአገሪቱ በስተምስራቅ አቅጣጫ ወደ ዋና ከተማዋ የሚያደርጉትን ግስጋሴ አጠናክረው መቀጠላቸውን ቢቢሲ ከስፍራው ያስተላለፈው ዘገባ አመለከተ፡፡ የአገሪቱ አማጽያን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እድሪስ ዲያቢን ከስልጣን በማስወገድ የአገሪቱን መንግስታዊ አወቃቀር ለመቀየር የሚታገሉ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜና ያለፈው ሰኞ የአውሮፓ ኅብረት በአካባቢው የሚሰማራውን የአውሮፓ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ዘመቻ አጽድቋል፡፡ በዚህም መሰረት በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሦስት ሺ ሰባት መቶ የአውሮፓ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ቻድ ይገባሉ፡፡ አማጽያኑ የአውሮፓ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ገለልተኛ እንደማይሆን ከወዲሁ ገልፀዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ 1500 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በጆሀንስበርግ በሚገኝ በሜቶዲስት ቤተክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ አንድ ሺ አምስት መቶ ቤት አልባ ዜጎችንና ዙምባብዌያን ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡ የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ፖል ቨሪን ፖሊስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባት ያደረገው ዘመቻ “የቤተክርስቲያንን ክብር መድፈር ነው” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ የተደበቁ የጦር መሳሪያና አደንዛዥ ዕጽ ፍተሻ ለማድረግ መግባቱን ገልጿል፡፡ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምንም አይነት የጦር መሳሪያም ሆነ አደንዛዥ ዕጽ አለመኖሩን ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ሰዎች ማስጠለላቸውን ገልፀዋል፡፡ ሰሜን ኮርያ የኒውክሊየር ፕሮግራሟን እንደምትዘጋ በድጋሚ አረጋገጠች ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ፕሮግራሟን ለመዝጋት የተደረሰውን ስምምነት እንዳማትለውጥ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኢል አረጋገጡ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ ጉብኝት ላይ ያሉትን የቻይና ዲፕሎማት ባነጋገሩበት ወቅት የኒውክሊየር ማበልፀጊያ ማዕከላትን በማምከን ሂደት ላይ የተፈጠረው ችግር ጊዜያዊ መሆኑንና በቅርቡ በውይይት የሚፈታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ማበልፀጊያ ማዕከላት የሚወገዱበትን ሁኔታ እንዲሁም አገሪቱ እርዳታ የምታገኝበትን መንገድ በተመለከተ የተጀመረው ውይይት ቀጣይ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ መግለፃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |